የአፈጻጸም ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት ለአፈጻጸሙ ተስማሚ በሆነ መንገድ ፍርድ እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሚሰጠው የፍርድ ባለዕዳውን ጠርቶ ከመረመረው በኃላ እንደፍርዱ የማይፈጸምበት ምክንያት አለመኖሩን ካረጋገጠ በኃላ ስለመሆኑ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 207 እና 320(2) መሰረት በተሰጠው ትእዛዝ ላይ ቅሬታ አቅርቦ ነገር ግን ቅሬታው ተቀባይነት ቢያጣ የይግባኝ መብቱን (የይግባኝ ጊዜ ላሰላበት) ስለሚችልበት አግባብ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 392 (1)
No summary available.
ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ ለላሴ ደሳለኝ አመልካች፡- ክራውን ቴክስታይል ዊቪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠበቃ ቸርነት ወርደፍ ቀረቡ ተጠሪዎች፡-
ጉዳዩ የፍርድ አፈጻጸም ክርክርን የሚመለከት ሲሆን በዚህ መዝገብ ለቀረበው የሰበር ክርክር መነሻ የሆኑትም የፍርድ ባለመብት በነበረው የአሁነ 2ኛ ተጠሪ፣የፍርድ ባለዕዳ በነበረው የአሁነ አመልካች እና በአፈጻጸም መዝገቡ ላይ “ተጠሪ” ተብሎ በተሰየመው የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ መካከል የነበረውን የፍርድ አፈጻጸም ክርክር የተመለከተው የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ በ10/09/2003 ዓ.ም.እና በ29/11/2003 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጣቸው ትዕዛዞች፣እንዲሁም በትዕዛዞቹ ቅር በመሰኘት የስር የፍርድ ባለዕዳ ያቀረበው ይግባኝ ጊዜው ያለፈበት በመሆኑ ላስተናገድ አይገባውም በማለት የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የአሁኖቹን ተጠሪዎች ተቃውሞ በመቀበል በመዝገብ በ30/03/2006 ዓ.ም.
በዋለው ችሎት የሰጠው ብይን ናቸው።
በ10/09/2003ዓ.ም. የተሰጠው የአፈጻጸም ትዕዛዝ፡-
የፍርድ ባለዕዳ ለተጠሪ አክሲዮን ድርሻውን /ለሚድሮክ / በውልና ማስረጃ አቅርበው በስምምነቱ መሰረት ፈጽመው እንዲቀርቡ ታዟል።
የፍርድ ባለዕዳ መጋቢት 20/2002 በተደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት የአክሲዮን ማህበሩን እንዲያሰረክቡ ታዟል።
የአክሲዮን እና የኩባንያው ርክክብ እንደተፈጸመ ተጠሪ በስምምነቱ የተገለጸውን 12 ሚላዮን ብር ለፍርድ ባለመብቱ እንዲከፍሉ ታዟል።ቀጠሮ ውጤት ለመጠባበቅ ቀጠሮ 29/09/2003 በ3፡00 ሰዓት ተቀጠረ።
ዳኛ እንዲነሳ በ10/09/2003 በአቶ ምኒልክ ሙሉዓለም በቀረበው አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ 12/09/2003 በ8፡00 ሰዓት ተቀጠረ።
የሚል ሲሆን በ29/11/2003 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የተሰጠው ትዕዛዝ ይዘት ደግሞ ጉዳዩ በዚህ ቀን ለተሰየመው ችሎት የተመራው ቀደም ሲል በ10/09/2003 ዓ.ም. የአፈጻጸም ትዕዛዝ የሰጡት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ በመደረጉ መሆኑን፣ቀደም ሲል በ10/09/2003 ዓ.ም. በተሰጠው የአፈጻጸም ትዕዛዝ ላይ የፍርድ ባለዕዳው ቅሬታ ካለው ለበላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ ማሳረም የነበረበት ከመሆኑ በቀር ጉዳዩ የተመራለት በተመሳሳይ ደረጃ የሚገኝ ችሎት የቀድሞውን የአፈጻጸም ትዕዛዝ ለመቀየር የሚያስችል ስልጣን የልለው መሆኑን የሚገልጽ እና ቀደም ሲል በ10/09/2003 ዓ.ም. በተሰጠው የአፈጻጸም ትዕዛዝ መሰረት እንዲፈጸም ጉዳዩ ለፍድራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት እንዲተላለፍ መደረጉን የሚያመለክት ነው።
የስር የፍርድ ባለዕዳ ያቀረበው ይግባኝ ጊዜው ያለፈበት በመሆኑ ላስተናገድ አይገባውም በማለት የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የአሁኖቹን ተጠሪዎች ተቃውሞ በመቀበል በመዝገብ በ30/03/2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በሰጠው ብይን መዝገቡን የዘጋው ይግባኙ ያስቀርባል ተብሎ የነበረው በ10/09/2003 ዓ.ም. የተሰጠውን የአፈጻጸም ትዕዛዝ ተገቢነት ለማጣራት ተብሎ መሆኑን፣የፍርድ ባለዕዳው በ10/09/2003 ዓ.ም. በተሰጠበት የአፈጻጸም ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ የጠየቀው በ29/11/2003 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የተሰጠበትን የአፈጻጸም ትዕዛዝ በማስታከክ መሆኑን፣ይሁን እና በ29/11/2003 ዓ.ም. የተሰጠው የአፈጻጸም ትዕዛዝ ቀደም ሲል በ10/09/2003 ዓ.ም. በተሰጠው የአፈጻጸም ትዕዛዝ መሰረት እንዲፈጸም የሚል እንጂ ከቀድሞው ትዕዛዝ የተለየ ባለመሆኑ ምክንያት በ29/11/2003 ዓ.ም. የተሰጠው ትዕዛዝ ራሱን ችሎ የይግባኝ ምክንያት ላሆን የማይችል መሆኑን፣ይግባኝ ባዩ ያቀረበው የይግባኝ ማስፈቀጃ አቤቱታ አለመኖሩን እና የይግባኝ ጊዜው ያለፈበት ይግባኝ ላስተናገድ የሚችልበት የሕግ አግበብ አለመኖሩን በምክንያትነት በመጥቀስ ነው።
የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ10/09/2003 ዓ.ም.
በዋለው ችሎት ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ዳኝነት ከመስጠቱ በፊት ዳኛው ከችሎት ይነሱልኝ የሚል አቤቱታ የአሁን አመልካች አቅርቦ እንደነበረ በ10/09/2003 ዓ.ም. የተሰጠው ትዕዛዝ የሚያስገነዝብ ሆኖ እያለ ዳኛው ከችሎት ላነሱ ይገባል ወይስ አይገባም? በሚለው ጉዳይ ላይ ትእዛዝ ከመሰጠቱ በፊት ዳኛው በዋናው ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ መስጠታቸው እስከታወቀ ድረስ ለይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው መነሻ ተደርጎ መያዝ የሚገባው ጉዳዩን ቀደም ሲል ባዩት ዳኛ በ10/09/2003 ዓ.ም. የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመለወጥ የሚያስችል ስልጣን የለኝም በማለት በኃላ ላይ ጉዳዩ የቀረበለት ችሎት በ29/11/2003 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ትዕዛዝ የሰጠበት ቀን ሳይሆን የመጀመሪያው የአፈጻጸም ትዕዛዝ የተሰጠበት ግንቦት 10 ቀን 2003 ዓ.ም. ነው በማለት በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በ30/03/2006 ዓ.ም. የተሰጠውን ዳኝነት አግባብነት ከፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 207 እና ተከታይ ድንጋጌዎች አንጻር ተጠሪዎቹ ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር የተለዋወጡ ከመሆኑም በላይ በ02/10/2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የቃል ክርክር አድርገዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ይግባኙ የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው ካለፈ በኃላ የቀረበ በመሆኑ ላስተናገድ አይገባውም በማለት በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን ሕጋዊ መሰረት ያለው መሆን አለመሆኑን እንደሚከተለው መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልች አጥብቆ የሚከራከረው በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ10/09/2003 ዓ.ም. የአፈጻጸም ትዕዛዝ የተሰጠው ትዕዛዙን የሰጡት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ ጥያቄ ካቀረብን በኃላ አመልካች የትዕዛዙን መሰጠት ማወቅ በማይችልበት ሁኔታ በመሆኑ የትዕዛዙን መሰጠት ያወቅነው በ10/09/2003 ዓ.ም. በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ፈጽመን እንድንቀርብ በ14/11/2003 ዓ.ም. የተሰጠው ትዕዛዝ ከደረሰን በኃላ ነው፣በ10/09/2003 ዓ.ም. ትዕዛዝ የተሰጠው የፍርድ ባለዕዳው እንደፍርዱ የማይፈጽምበትን ምክንያት በወከላቸው የሕግ ባለሙያዎች አማካይነት ቀርቦ ተገቢውን መከራከሪያ እንዲያቀርብ ሳይደረግ ከስረ ነገሩ ስምምነት ይዘት ውጪ በመሆኑ ይኸው የአፈጻጸም ትዕዛዝ እንዲታረምልን በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 207 ድንጋጌ መሰረት ያቀረብነው ጥያቄ በ29/11/2003 ዓ.ም. ተቀባይነት ያጣውም አላግባብ ነው፣ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የይግባኝ ጊዜው አልፎበታል በማለት የያዘው አቋምም የፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 207 እና 320 (2) ድንጋጌዎችን ያላገናዘበ ነው በማለት ሲሆን ተጠሪዎቹ በበኩላቸው በ10/09/2003 ዓ.ም. የአፈጻጸም ትዕዛዙ የተሰጠው የፍርድ ባለዕዳው ተወካዮች ጭምር ባሉበት እና ክርክራቸውንም ካሰሙ በኃላ ነው፣ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ የፍርድ ባለዕዳው በ10/09/2003 ዓ.ም. ጥያቄ ያቀረበውም በዕለቱ የተሰጠበትን የአፈጻጸም ትዕዛዝ ዳኛው በችሎት ከገለጹ በኃላ ነው፣ትዕዛዙም ላለወጥ ወይም ላታረም የሚገባው በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንጂ በዚያው ትዕዛዙን በሰጠው ፍርድ ቤት ባለመሆኑ የይግባኝ ማቅረቢያው ጊዜ አልፎአል በሚል በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን ላነቀፍ አይገባውም በማለት መሆኑን ተገንዝበናል።
ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ በ10/09/2003 ዓ.ም. አቤቱታ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ እስከ 14/11/2003 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ በመዝገቡ ላይ የተለያዩ ትዕዛዞች ሲሰጡ የቆዩት ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ ከቀረበው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ጉዳይ መሆኑን የከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ ያመለክታል።አመልካች በ10/09/2003 ዓ.ም. የአፈጻጸም ትዕዛዝ የተሰጠብኝ መሆኑን ያወቅሁት በ10/09/2003 ዓ.ም. በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ፈጽሜ እንድንቀርብ በ14/11/2003 ዓ.ም.
የተሰጠው ትዕዛዝ ከደረሰኝ በኃላ ነው በማለት የተከራከረ ቢሆንም አመልካቹ ጉዳዩን በማየት ላይ የነበሩት ዳኛ ከችሎት እንዲነሱ በ10/09/2003 ዓ.ም. ጥያቄ ያቀረበው ዳኛው የአፈጻጸም ትዕዛዙን ከሰጡ በኃላ እና የትዕዛዙን መሰጠትም እያወቀ ስለመሆኑ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ በ10/09/2003 ዓ.ም. አዘጋጅቶ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ የፍትሐብሕር ቀጥታ ክስ ችሎት ያቀረበው አቤቱታ በግልጽ እና በማያሻማ ሁኔታ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ ጥያቄ ያቀረብኩት የአፈጻጸም ትዕዛዙ ከመሰጠቱ በፊት እና የትዕዛዙን መሰጠት ሳላውቅ ነው በማለት አመልካቹ ያቀረበው የክርክር ነጥብ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የተደረገውን የክርክር ሂደት መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
በልላ በኩል የፍርድ ባለዕዳው እንደ ዕርቅ ስምምነቱ የማይፈጽምበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ተጠርቶ በቀረበበት ቀን የፍርድ ባለዕዳውን ወክለው የቀረቡት ስራ አስኪያጅ ናቸው የተባሉት አቶ ምኒልክ ሙሉዓለም እና ሁለት ጠበቆች መሆናቸው አላከራከረም።በዚህ ሰበር ችሎት በተደረገው የቃል ክርክር እንደ ስምምነቱ የማይፈጽምበትን ምክንያት እንዲያስረዳ የፍርድ ባለዕዳው በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠርቶ ምክንያቱን በጠበቆቹ አማካይነት እያስረዳ በነበረበት ሂደት ከፍርድ ባለዕዳው ጠበቆች አንዱ ከችሎት እንዲወጡ በችሎቱ ታዘው መውጣታቸውን እና ልላኛው ጠበቃም እንዲቀመጡ ታዘው መቀመጣቸውን በመግለጽ የአመልካቹ ጠበቆች እና ተወካዮች የተከራከሩ ሲሆን ተጠሪዎቹ በበኩላቸው አንዱ ጠበቃ ከችሎት የወጡት በራሳቸው አነሳሽነት እንጂ በችሎቱ ትዕዛዝ እንዳልሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል።የፍርድ ባለዕዳው ሁለቱ ጠበቆች ረዥም ንግግር በማድረግ ንግግር ላያቆሙ ባለመቻላቸው እንዲቀመጡ እና ስራ አስኪያጁ አቶ ምኒልክ ሙሉዓለም ባለዕዳው እንደፍርዱ የማይፈጽምበትን ምክንያት እንዲያስረዱ የተደረገ ስለመሆኑ ዳኛው ከችሎት የሚያስነሳቸው በቂ ምክንያት አለመኖሩን ገልጸው በ12/09/2002 ዓ.ም. በሰጡት ትዕዛዝ ላይ ገልጸዋል።
በመሰረቱ የአፈጻጸም ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት ለአፈጻጸሙ ተስማሚ በሆነ መንገድ ፍርድ እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሚሰጠው የፍርድ ባለዕዳውን ጠርቶ ከመረመረው በኃላ እንደፍርዱ የማይፈጸምበት ምክንያት አለመኖሩን ካረጋገጠ በኃላ ስለመሆኑ በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 392 (1) ላይ ተመልክቶአል።በዚህ ድንጋጌ መሰረት ለሚደረግ ምርመራ የሚሰጠው ምላሽ ደግሞ የፍሬ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕግ ጭምር ላሆን እንደሚችል የሚታወቅ ነው። በመሆኑም እነዚህ ሁኔታዎች ተገናዝበው ሲታዩ በሕግ ጠበቆቼ ሳልወከል በቁጥር 392 (1) የተደረገው ምርመራ መሰረት ተደርጎ አፈጻጸሙ እንዲቀጥል በ10/09/2003 ዓ.ም. የተሰጠብኝ ትዕዛዝ ከስነ ስርዓት ውጪ በመሆኑ በቁጥር 320 (2) ድንጋጌዎች 207 ድንጋጌ መሰረት ይግባኝ ከመቅረቡ በፊት በዚያው ፍርድ ቤት ላታረም የሚገባው ነው የሚል በፍርድ ባለዕዳው ላይ እምነት ላያሳድሩቡት የሚችሉ አይደሉም ከሚል የተረጋገጠ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ሆነው አልተገኙም።ጉዳዩም የስረ ነገር ሳይሆን የአፈጻጸም ክርክር ነው።አመልካቹ በ10/09/2003 ዓ.ም.
የተሰጠው ትዕዛዝ እንዲታረምለት የፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 207 ድንጋጌን ጠቅሶ በጽሁፍ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ ስለመኖሩ የመዝገቡ ግልባጭ የሚያመለክተው ነገር ባይኖርም በ28/11/2003 ዓ.ም. ግራ ቀኙ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ያስመዘገቡት ክርክር ይዘት ሲታይ አመልካች በዚህ ረገድ በቃል ክርክሩም ቢሆን ጥያቄ አቅርቦ የነበረ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል ነው።ፍርድ ቤቱ በ29/11/2003 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ ላይ በ10/09/2003 ዓ.ም.
የተሰጠው ትዕዛዝ ላታረም የሚችለው በበላይ ፍርድ ቤት እንጂ በራሱ በዚህ ፍርድ ቤት አይደለም የሚል ይዘት ያለው ትችት ማስፈሩም አመልካቹ የእርማት ጥያቄ ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ ተገንዝቦ የነበረ መሆኑን የሚያመለክት ነው።እንዲህ ከሆነ ደግሞ በ10/09/2003 ዓ.ም.
በተሰጠው ትዕዛዝ ላይ የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው መቆጠር መጀመር የሚገባው ትዕዛዙ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ሳይሆን ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በዚያው ፍርድ ቤት ላታረም የማይችል መሆኑን ገልጾ በቀድሞው ትዕዛዝ መሰረት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ከሰጠበት ከ29/11/2003 ዓ.ም.
ነው።ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሲቆጠር ደግሞ ይግባኙ የቀረበው በሕግ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ነው።
ሲጠቃለል ይግባኙ የቀረበው የይገባኝ ማቅረቢያው የጊዜ ገደብ ካለፈ በኃላ በመሆኑ ላስተናገድ አይገባውም በማለት በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት እና ላታረም የሚገባው ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
ይግባኙ የቀረበው የይግባኝ ማቅረቢያው የጊዜ ገደብ ካለፈ በኃላ በመሆኑ ላስተናገድ አይገባውም በማለት የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ በ30/03/2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠው ብይን በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348 (1) መሰረት ተሽሯል።
ከላይ በውሳኔው ዝርዝር ውስጥ በተገለጸው መሰረት የይግባኝ ጊዜው ያላለፈ መሆኑን በመገንዘብ የግራ ቀኙን የይግባኝ ክርክር መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 341 (1) መሰረት ጉዳዩ ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እንዲመለስ ወስነናል።
ተገቢውን መፈጸም ያስችለው ዘንድ የውሳኔው ግልባጭ ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይላክ።
የስር ፍርድ ቤት መዝገብ ይመለስ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.