አንድ ፍርድ የማይፈፀምበት ምክንያት ያለመኖሩ ሲረጋገጥ ለአፈፃፀም ተስማሚ በሆነ መንገድ ፍርድ እንዲፈፀም ትእዛዝ መስጠት የሚቻል ስለመሆኑ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 392(1)
No summary available.
ጥቅምት 2 ቀን 2008ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ ብርሃኑ አመነው ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ አመልካች፡- የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት - አልቀረቡም ተጠሪ፡- አቶ በየነ አሸናፊ - አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል።
ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው የአማራ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ያሳለፈው የአፈጻጸም ትእዛዝ ነው። የአሁኑ አመልካች በስር የአፈጻጸም ተከሳሽ እንዲሁም የአሁኑ ተጠሪ የአፈጻጸም ከሳሽ ነበሩ።
ግራ ቀኙ በአፈጻጸም ያደረጉት ክርከር ታይቶ በመጨረሻ በተሰጠው ትእዛዝ ለአፈጻጸም የቀረበው ውሳኔ በሐምል 2002 ዓ.ም በወጣው በኃላፊነት የሚነሱ የመንግስት ተሿሚዎች ምደባ አሰጣጥ እና ክፍያ አፈጻጸም መመሪያ መሰረት ምደባ እንዲደረግ እና በመመሪያው ቁጥር 2.1 አግባብ እንዲፈጸም የተወሰነ በመሆኑ፤ በዚህ መመሪያ መሰረትም ከ3 ዓመት በላይ በሹመት አገልግሎት ከኃላፊነት የተነሳ ከሆነ ይዞት የነበረው ደመወዝ ይዞ ላቀጥል እንደሚገባ የተደነገገ መሆኑን ከድንጋጌው ይዘት መገንዘብ ይቻላል፤ በመሆኑም የአፈ/ከሳሽ ይዞት የነበረውን 3348.00 ውሳኔ ከተሰጠበት የካቲት 26/2005 ዓ.ም ጀምሮ ላከፈለው ይገባል በማለት የአፈጻጸም ተከሳሽ እንዲከፍል ታዟል።
በዚህ ትእዛዝ ላይ አቤቱታ የቀረበበት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር አፈፃፀም ችሎት የተፈጸመ የህግ ስህተት የለም በማለት አቤቱታውን ሰርዟል።
አመልካች ለዚህ ፍ/ቤት ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ በዋናው ፍርድ እና በመመሪያው መሰረት የተፈጸመ በመሆኑ፤ የስር ፍ/ቤት ያሳለፈው የአፈጻጸም ትእዛዝ ዋናውን ውሳኔ መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ እና ትእዛዙ የመመሪያውን አንቀጽ 2.1 እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 375(1) ሥር የተደነገገውን የስልጣን ወሰን የተላለፈ በመሆኑ እንዲሻር ጠይቀዋል።
ተጠሪ መልስ እንዲሰጡ ተደርጎ በሰጡት መልስ በአፈጻጸም የተላለፈው ትእዛዝ ውሳኔውን እና መመሪያውን መሰረት ያደረገና ተገቢነት ያለው በመሆኑ ቅሬታው ውድቅ ተደርጎ የሥር ፍ/ቤት ትእዛዝ እንዲጸና ጠይቀዋል። አመልካቹም ክርክራቸውን በማጠናከር የመ/መልስ ሰጥተዋል።
በበኩላችን እንደፍርዱ አልተፈጸመም ተብሎ አመልካች እንዲፈጽም በተሰጠው ትእዛዝ ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክር ከህጉ ጋር በማያያዝ መርምረናል።
እንደመረመርነው ለአፈጻጸሙ ምክንያት በሆነው ፍርድ እና ውሳኔ የክልሉ የአቅም ግንባታ እና ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ በሐምል 2002 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ ክፍል ሁለት በቁጥር 2.1 በተመለከተው መሰረት ለአሁን ተጠሪ ባላቸው የትምህርት ዝግጅት እና የስራ ልምድ በሚመጥናቸው መደብ ላመደቡ እንደሚገባ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ላያገኙ የሚገባው ጥቅማ ጥቅም ላያገኙ እንደሚገባ ተወስኗል።
የአሁን አመልካች መ/ቤት የሰው ሀይል ስራ አመራር ደጋፊ የስራ ሂደት የምደባ እና መረጣ ክፍል የፍርድ ውሳኔውን በተመለከተ መጋቢት 18/2005ዓ.ም በተያዘ ቃለ ጉባኤ ተጠሪን በጽ/ቤቱም ሆነ በወረዳው በሚገኙ ጽ/ቤቶች ለመመደብ በትምህርት ዝግጅታቸው የስራ መደብ የጠፋ መሆኑን፤ የሚያሟሉት የስራ ደረጃ በማይገኝበት ጊዜ በመመሪያው ቁጥር 2-2-1 መሰረት ከሚያሟሉት የስራ ደረጃ አንድ ደረጃ ያነሰውን ደመወዝ እየተከፈላቸው በተገኘው ክፍት የስራ ደረጃ እንዲመደቡ እንደሚደረግ፤ በዚህም መሰረት ለተጠሪ የምደባ ቦታ ባለመኖሩ መመደብ እና ጥቅማ ጥቅም ለመስጠት አስቸጋሪ በመሆኑ ከዚህ በፊት በተመደቡበት የስራ መደብ ተመድበው እንዲሰሩ ብሐል።
ይህን ተከትሎ ተጠሪ እንደፍርዱ አልተፈጸመም በማለት አመልካች ደግሞ ተፈጽሟል በማለት ተከራክረው ከላይ የተገለጸው ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነው የአፈጻጸም ትእዛዝ ተሰጥቷል።
በመሰረቱ አፈጻጸምን ከሚመሩት የስነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች መረዳት እንደሚቻለው በውሳኔ ባለመብት የሆነ ሰው ፍርዱ ባስገኘለት መብት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ስለሚገባ ላፈጸም የሚችል ውሳኔ እስከቀረበ ድረስ በውሳኔው መሰረት እንዲፈጸም ተገቢው ትእዛዝ መሰጠት ይኖርበታል። በተለይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 392(1) እንደተደነገገው ፍርዱ የማይፈጸምበት ምክንያት ያለመኖሩ ሲረጋገጥ ለአፈጻጸሙ ተስማሚ በሆነ መንገድ ፍርዱ እንዲፈጸም ትእዛዝ ይሰጣል። አፈጻጸሙ መመራት ያለበት በዚህ ስርዓት ነው።
በተያዘው ጉዳይ ለስር ፍርዱ መሰረት የሆነው የመመሪያው ቁጥር 2.1 በተከታታይ ሶስት ዓመት እና በላይ በሹመት ላይ ቆይተው በተለያየ ምክንያት ከኃላፊነት የሚነሱ ተሿሚዎች ምደባ የሚደረግላቸው ያላቸው የት/ዝግጅት እና የስራ ልምድ ከግምት ውስጥ ገብቶ በሚያሟሉበት የስራ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ ይደነግጋል። ፍርዱም የተሰጠ በዚህ መሰረት ነው። ከዚህ በቀር ቅሬታ ባስነሳው የስር ፍ/ቤት ባሳለፈው ትእዛዝ እንደተገለጸው ከ 3 ዓመት በላይ በሹመት አገልግሎት ከኃላፊነት የተነሳ ከሆነ ይዞት የነበረውን ደመወዝ ይዞ ላቀጥል እንደሚገባ በመመሪያው አልተደነገገም። ስሆነም በአፈጻጸም የተሰጠው ትእዛዝ የሥር ፍርዱንም ሆነ ፍርዱ የተመሰረተበትን የመመሪያውን ድንጋጌ የተከተለ ሆኖ አላገኘነውም። ትእዛዙ ከላይ የተመለከተውን አፈጻጸምን የሚመሩትን የስነ-ሥርዓት ህጉን ድንጋጌዎች የተከተለ ባለመሆኑም የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ብለናል።
1ኛ. የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት በፍ/ብ/ይ/መ/ቁ. 35184 ሚያዚያ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ያሳለፈው ትእዛዝ፤ እንዲሁም የክልሉ ሰበር ችሎት በሰ/አ/መ/ቁ. 39465 ግንቦት 4/2006 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሯል።
2ኛ. የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የተዘጋውን መዝገብ በማንቀሳቀስ የፍርዱን አፈጻጸም በተመለከተ ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክር ከስር ፍርዱ፤ ለፍርዱ መሰረት ከሆነው መመሪያ፤ አፈጻጸሙ ከሚመራበት ስነ-ሥርዓት እና ተገቢነት ካላቸው ህጎች ጋር በመመርመር ተገቢውን ይወስን ብለናል። የውሳኔው ግልባጭ ይተላለፍ።
3ኛ. ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ። መዝገቡ ወደ መ/ቤት ይመለስ የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት ።
No topics extracted.