በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በምትክ ቦታ ይሰጠኝ ጥያቄ ላይ የሚሰጠው የመጨረሻ ፍርድ የሰበር አቤቱታ ለከተማው ፍ/ቤት ሳይቀርብ ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ የሚቀርብበት የህግ አግባብ የልለ ስለመሆኑ የከተማው ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 43(5)፣ አንቀጽ 42(2) አንቀጽ አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 29(6)
No summary available.
ታህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ አመልካች፡- አቶ ታደሰ ካሣ - ጠበቃ እንዳልካቸው ይሳቅ - ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1ኛ. ቦል ክ/ከተማ ወረዳ 12 አስተዳደር 2ኛ. ቦል ክ/ከተማ የመሬት አስተዳደር አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል።
የሰበር አቤቱታው የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት ከከተማ ቦታ ማስለቀቅ እና የካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ምትክ ቦታን በተመለከተ በተሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚቀርብ አቤቱታን ተቀብሎ ለመወሰን የዳኝነት ሥልጣን የለኝም በማለት ያሳለፈውን ትዕዛዝ በመቃወም ነው።
አመልካች ነሀሴ 27/2006 ዓ.ም ያቀረቡት የሰበር ማመልከቻ ተመርምሮ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ትዕዛዝ ከአዋጅ ቁጥር 721/2003 አንቀጽ 29 እና 30 ድንጋጌዎች አንፃር ተገቢ መሆኑን ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል። ተጠሪዎች መጥሪያ ደርሷቸውና መልስ ለመስጠትም ቀጠሮ እንዲለወጥላቸው ጠይቀው ነገር ግን መልስ ስላላቀረቡ በፅሑፍ መልስ የማቅረብ መብታቸው ታልፎ መዝገቡ ለምርምራ ተቀጥሯል። በበኩላችን የከተማው ሰበር ችሎት ያሳለፈውን ትዕዛዝ አመልካች ካቀረቡት ቅሬታ እና ተገቢነት ካላቸው ህጎች ጋር በማያያዝ መርምረናል።
ከመዝገቡ መረዳት እንደሚቻለው አመልካች በቦል ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 አስተዳደር ውስጥ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በ200 ካ.ሜ ቦታ ላይ ቤት ገንብተው እየኖሩ ከተጠሪዎች ቦታው ለልማት ይፈለጋል በሚል እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ በፅሑፍ ስለተሰጣቸው የቤት ካሣ እና ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀው አስተዳደሩ በህግ ተቀባይነት በልለው ምክንያት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎብኛል በሚል ይግባኙን ለመስማት ለተቋቋመው ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የተጠሪዎችን መልስ ተቀብሎ ጉዳዩን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ለንብረት ካሣ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን ከወጣው አዋጅ ቁጥር 455/1997፤ ስለ ካሣው አወሳሰን ከወጣው የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 135/1999 እንዲሁም አዋጅና ደንቡን ለማስፈፀም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከወጣው መመሪያ ቁጥር 3/2002 አንፃር በመመርመር በህጎቹ እንዲቀርብ የሚጠበቀው የንብረት ካሣ እና ምትክ ቦታ ለማግኘት የሚያበቁ ማስረጃዎ አልቀረቡም ስለሆነም ይግባኙ ተቀባይነት የለውም በማለት ወስኗል።
አመልካች የምትክ ቦታ ጥያቄውን በተመለከተ የጉባኤው ውሳኔ የመጨረሻ ነው በማለት የሰበር አቤቱታ ለከተማው ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የሚኖረው የአ/አበባ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ነው፤ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም ሥልጣን ያለው የፍ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ነው በመሆኑም ጉዳዩ በከተማው ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ቀርቦ ላታይ የማይችል ነው በማለት መዝገቡን ዘግቷል።
እንደመረመርነው የከተማው ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ምትክ ቦታን በሚመለከት በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ በሰበር አይቶ ለመወሰን የዳኝነት ሥልጣን አለው ወይስ የለውም? የሚለው የህግ ጭብጥ ውሳኔ የሚሻ ነው።
የከተማ ቦታን በላዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 29(3) መሰረት በካሣ ክርክር ላይ ካልሆነ በቀር ምትክ ቦታን ጨምሮ በልሎች በህግም ሆነ በፍሬ ነገር ላይ የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው። በልላ በኩል በካሳው ላይ የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ይግባኝ ላቀርብ እንደሚችል በአንቀጽ 29 (4) ሥር ተመልክቷል። የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ደግሞ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ በከተማው ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 43(5) እና አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 29(6) ድንጋጌዎች መሰረት የመጨረሻ በመሆኑ በዚህ ውሳኔ ላይ አቤቱታ ላቀርብ የሚችለው በሰበር ስርዓት ለከተማው ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ስለመሆኑ በቻርተሩ አንቀጽ 42(2) ተመልክቷል።
የከተማ ቦታ ማስለቀቅ እና የካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤም በቻርተሩ አንቀጽ 40 ከተዘረዘሩ በህግ የመዳኘት ሥልጣን ከተሰጣቸው አካላት የሚመደብ ነው።
በመሆኑም ጉባኤው ምትክ ቦታን በተመለከተ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑና ጉባኤውም በህግ የመዳኘት ስልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመ የአስተዳደሩ አካል መሆኑ እየታወቀ በዚህ ውሳኔ ላይ የቀረበውን የሰበር አቤቱታ የከተማው ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የመመለስ ሥልጣን የለውም ተብሎ የተሰጠው ትዕዛዝ ህጉን የተከተለ ሆኖ አላገኘነውም። በተመሳሳይ ጉዳይ የፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በ
ህዳር 24/2008 ዓ.ም በዋለ ችሎት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በምትክ ቦታ ይሰጠኝ ጥያቄ ላይ የሚሰጠው የመጨረሻ ፍርድ የሰበር አቤቱታ ለከተማው ፍ/ቤት ሳይቀርብ ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ የሚቀርብበት የህግ አግባብ እንደልለም ተወስኗል። ይኸው ውሳኔም በተያዘው ጉዳይ በተመሳሳይ ተፈፃሚ ነው።
በመሆኑም የከተማው ሰበር ችሎት ያሳለፈው ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ተከታዩ ተወስኗል።
1ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 22374 ነሀሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ያሳለፈው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሯል።
2ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት የቀረበውን የሰበር አቤቱታ ተቀብሎ ለመወሰን ሥልጣን ያለው በመሆኑ ጉዳዩን ተመልክቶ ተገቢውን እንዲወሰን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.
341(1) መሰረት መልሰናል ይፃፍ።
3ኛ. ወጪና ኪሣራ ይቻቻሉ መዝገቡ ወደ መ/ቤት ይመለስ።
No topics extracted.