በቅጂና ተዛማጅ መብቶች መጣስ /ለሚደርስ ለጉዳት ካሳ/ ወይም የሞራል ካሳ ዋጋው በተዋዋዮች ወገን ካልተቆረጠ የወቅቱን ዋጋ አጣርቶ መወሰን የሚገባ ስለመሆኑ፣ የሞራል ካሳ አከፋፈል ከፍ/ብ/ሕ/ቁ ውጪ መወሰን የልለበት ስለመሆኑ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ቁ 410/96 አንቀጽ 7፣8፣37 የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2102 የዳኝነት ሥልጣን
No summary available.
ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ተኽላት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ አመልካች፡- ወ/ሮ ፍሬ ህይወት ደመቀ (የመካኒኩ ፊልም ኘሬዲውሰር)- ጠበቃ ሙሉጌታ ዘመነ ቀረቡ።
ተጠሪ፡- ወ/ት ቤሩት ዳዊት - ጠበቃ መንግስቴ ቀረቡ።
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቶአል።
ጉዳዩ የቅጅና ተዛማጅ መብት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኗ አመልካች ላይ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።
የተጠሪ የክስ ይዘትም፡- ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን በመሰዋት በነጠላ ዜማ የለቀቁትን “በትዝታ አቅርቤ” የተሰኘውን የዘፈን ሥራቸውን ያለፈቃዳቸውና ያለ ስምምነታቸው የአሁኗ አመልካች ኘሮዲውስ ላደረጉት "መካኒኩ" ለተባለው ፊልም በማጀቢያነት (ሳውንድትራክ) በመጠቀም ያለአግባብ ቁሳዊ ጥቅም ያገኙበት መሆኑን፣በአመልካች አድራጎትም 164,000.00 የሚገመት የኢኮኖሚ ጥቅም ማጣታቸውንና የብር 100,000.00 የሞራል ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሰው በድምሩ ብር 264,000.00 (ሁለት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ብር) ከነወለድ ወጪና ኪሣራ ጨምረው እንዲከፍሐቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሁኗ አመልካች ለተጠሪ ክስ በሰጡት መልስም፡- የተጠሪ የሙዚቃ ሥራ ለመካኒኩ ፊልም ማጀቢያነት የተጠቀሙት መሆኑን ሳይክዱ የሙዚቃው ሥራ ለፊልሙ መጠቀም ይችሉ እንደሆነ በአቶ ዮናስ ብርሃነ መዋ በኩል ተጠሪን ጠይቀውና ተገናኝተንው የተጠሪን ስራ እንዲያስተዋውቁላቸው ተነጋግረው ሰኔ 8 ቀን 2003 ዓ.ም በአቀነባባሪያቸው የእጅ ጽሑፍ የተፃፈ ሲዲ ተጠሪ አምጥተው የሰጧቸው መሆኑን፣ በዚህም ተጠሪ ወደውና ፈቅደው በማጀብያነት አመልካች እንዲጠቀሙበት ሰጥተዋቸው እያለ ያለፍቃድ ነው ማለታቸው ሐሰት መሆኑን ጠቅሰው ተጠሪ ክስ ለመመስረት የሚያስችላቸው ምክንያት የለም በማለት ክሱ ውድቅ እንዲደረግላቸው በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያቀረቡ ሲሆን በአማራጭም እንደተጠሪ ያለ ጀማሪ ዘፋኝ የዘፈነው ዘፈን ከብር 3000.00(ሶስት ሺህ) ባለይ እንደማይሸጥ እየታወቀ ተጠሪ ብር 164,000.00 የኢኮኖሚ ጉዳት ደርሶብኛል በማለት ዳኝነት መጠየቃቸው ያላግባብ መሆኑንና በዚህ ረገድ የቀረበውን የተጠሪን ግምት እንደሚቃወሙ፣አዲስ ዘፈን እንደመሆኑ መጠን ለዘፈኑ ገንዘብ ከሚከፈላቸው ክላፕ እንዲሰራላትና ዘፈኑ የፊልም ማጀቢያ እንዲሆን የምረቃ ቀን ቀርበው ምስጋናና ሰርቲፊኬት እንዲሰጣት፣ዘፈኑ በተለያዩ ሚዲያዎች ተሰራጭቶ እንዲተዋወቅላት በዝርዝር ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ሰኔ 08 ቀን 2003 ዓ/ም ተፈራርመው ከስምምነቱ በኋላ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ/ም በአቀናባሪያቸው የእጅ ፅሑፍ የተፃፈ ሲዲ እራሷ አምጥታ የሰጠቻቸው መሆኑን፣በዚህም መሰረት የሙዚቃ ሲዲዋን በላይ ላይ ድምፃዊት እራሷ መሆኗን አቀናባሪያቸው ሮቤል ዳኜ መሆኑን፣ ስራቸው በቅርብ ቀን በአልበም እንደሚወጣ፣ሲዲውም ላይ በመግለፅ የተለያዩ ሚዲያዎች በፕሮግራማቸው በማስተላለፍ እንዲያስተዋወቁላቸው ያደረጉ መሆኑን፣ፊልሙ በሚመረቅበት ጊዜም ለፊልሙ ማጀቢያነት የተጠቀሙት ሙዚቃ የተጠሪ መሆኑን በማስተዋወቅ በመድረክ ላይ ተጠርተው ሰርቲፊኬት እንዲሰጣቸው ማድረጋቸውንና በስምምነቱ መሰረት በአመልካች በኩል ሳይፈፀም የቀረው የዘፈኑን ክላፕ ማዘጋጀት ብቻ ሲሆን ይህን በተመለከተም ስራው ያልተሰራው ተጠሪ የዘፈኑን ታሪክ አዘጋጅተው ባለማቅረብና ለክላፑ የሚሆነውን አልባሳትና ቦታ አዘጋጅተው ባለመቅረባቸው ጥፋት መሆኑን፣ ክላፑ የሚሰራበት ዋጋ ከብር 4000.00 እንደማይበልጥና ተጠሪ ዜማቸውን በመሸጥ ላያገኙ ይችሉ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አመልካች ያለማስቀረታቸውንና በፈቃዳቸው መሰረት ለተከናወነ ተግባርም የሞራል ካሳ የሚከፈልበት አግባብ የልለ መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙ ክርክር እና የአመልካችን የሰው ምስክሮችን ከሰማ በኋዋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ከተጠሪ ዕውቅና ውጭ ማጀቢያ ዘፈኑን ለፊልሙ ያለመጠቀማቸውን ያስረዱ ስለሆነ ከሳሽ የደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊም ሆነ የሞራል ጉዳት የለም በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የአሁኗ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልሙ ማጀቢያነት የተጠቀሙት በተጠሪ ሙሉ ፍቃድ ስለመሆኑ ተረጋግጦአል ተብሎ በስር ፍርድ ቤት መወሰኑ ባግባቡ ነው በማለት የተቀበለው ሲሆን ተጠሪ ዘፈናቸውን ለአመልካች ፊልም ማጀቢያ በፍቃዳቸው ሲሰጡ ተጠሪ በአመልካች በኩል የማስተዋወቅ ስራ እንዲሰራላቸው፣በገንዘብ መልክ ከሚሰጣቸው ይልቅ የዘፈኑ ክላፕ እንዲሰራላቸው አመልካች መዋዋላቸውን አልካዱም፣አመልካች እንደውሉ ያልፈጸምኩት ተጠሪ የዘፈኑ ታሪክ፣ አልባሳት እና ክላፑ የሚሰራበት ቦታ ባለመምረጣቸው ነው ቢሉም አመልካች ክላፑን ለመስራት የጠቀሷቸው ነገሮች ተጠሪ ሟሟላት እንደሚገባቸው የሚያመላክት ስምምነት ስለመኖሩ አላስረዱም በሚል ድምዳሜ ተጠሪ እነዚህ ነገሮች ባይሟሉኳ በክላፑ ፈንታ ገንዘብ ላከፈላቸው ይችል እንደነበረ፣ አመልካች በክላፑ ፋንታ ለተጠሪ ክፍያ ላፈጽሙ እንደሚገባ ፍርድ ቤቱ አምኖበታል በማለት የካሳውን መጠንም በርትዕ ብር 100,000.00(አንድ መቶ ሺህ) አድርጎ ይህንኑ ገንዘብ አመልካች ለተጠሪ ላከፍሉ ይገባል ሲል ወስኗል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘትም፡- ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልሙ ማጀቢያነት የተጠቀሙት በተጠሪ እውቅና እና ፈቃድ ስለመሆኑ ከአረጋገጠ በኋላ በክላፑ ፋንታ ተጠሪ ገንዘብ ላከፈላቸው ይገባል በማለት የሰጠው ውሳኔ ተጠሪ በውሉ መሰረት ግድታቸውን ባልተወጡበት አግባብ ከመሆኑም በላይ የካሳው መጠንም ማስረጃ ቀርቦ እያለ በርትዕ መወሰኑ ከሕጉ ይዘትና መንፈስ ውጪ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመርነውም
አመልካች ለተጠሪ በክላፑ ፈንታ ገንዘብ እንዲከፍሉ መወሰኑ የግራ ቀኙን ተነፃፃሪ ግድታ ያገናዘበ ነው? ወይስ አይደለም?
የካሳው መጠን በርትዕ መወሰኑን ሕጋዊ ነው? ወይስ አይደለም? የሚሉት ነጥቦች በጭብጥነት ላታይ የሚገባ ሁነው አግኝተናል።
የመጀመሪያውን ጭብጥ በተመለከተ፡- የበታች ፍርድ ቤቶች በአመልካችና በተጠሪ ውል መኖሩን በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጡት ጉዳይ ሲሆን ተጠሪ አመልካች በጽሑፍ የተደረገው ውል ጠፍቶአል በማለት በሰው ምስክሮች ማረጋገጥ እንደሚችሉ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መወሰኑ ተገቢነት የልለውና የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2003 ድንጋጌን የሚቃረን ነው በማለት የሚከራከሩ መሆኑን ለዚህ ችሎት በጽሑፍ ከአቀረቡት መልሳቸው የተገነዘብን ቢሆንም ይህ የተጠሪ ክርክር በዚህ አመልካች ባስከፈቱት የሰበር መዝገብ ላስተናገድ የሚችልበት አግባብ የልለ በመሆኑ ተቀባይነት የልለው ነው። ተጠሪ በዚህ ረገድ ራሱን የቻለ የሰበር አቤቱታ ያቀረቡ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን በዚህ ረገድ አለ የተባለውን የሰ/መ/ አስቀርበውን ስንመለከተውም መዝገቡ በሰበር አጣሪ ችሎት በ03/10/2006 ዓ/ም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አልተፈፀመበትም ተብሎ መዘጋቱን መረዳትን ችለናል። በመሆኑም ተጠሪ በግራ ቀኙ መካከል በፅሑፍ የተደረገ ውል የለም በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት ላሰጠው የሚገባ ሁኖ አልተኘም። በግራ ቀኙ መካከል ሕጋዊ ውል መኖሩ ከተረጋገጠ ደግሞ የግራ ቀኙ ተነፃፃሪ ግድታ የሚለየው በዚሁ ውል በመሆኑ እያንዳንዱ ተዋዋይ ወገን የሚቀርበው ክርክር በዚሁ የውል ሰነድ ይዘት መደገፍ ያለበት መሆኑን ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2001 እና 2005 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ነው።
በመሰረቱ ውል ሕጋዊ ውጤት ያለው ተግባር እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ተዋዋይ ወገን በውሉ የተጣለበትን ግድታ መፈጸም ይኖርበታል። ተዋዋዮች በውሉ በተገለጸው ስምምነት መሰረት ግድታቸውን ከተወጡ ውለታው በታሰበው ዓላማ መሰረት ተፈፅሟል ለማለት የሚቻል ሲሆን ይህም ማለት የውሉ ግድታ ያለበት ሰው በውሉ ላይ የተገለጸውን የመስጠት፣ የማድረግ ወይም ያለማድረግ ተግባር በተገቢው መንገድና በብቃት ማከናወኑን ማረጋገጥ መሆኑ ይታመናል። ተዋዋይ ወገኖች በምን አይነት አኳኋን፣ ጊዜና ቦታ የውል ግድታቸውን መፈጸም እንዳለባቸው በፍትሓ ብሕር ሕጉ ከቁጥር 1740 እስከ 1762 ድረስ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ያሳያሉ። አንድ ተዋዋይ ወገን በውሉ የገባውን ግድታ በውላቸውና በሕጉ ውስጥ በተደነገገው አኳኋን ያልፈፀመ እንደሆነ የውል ግድታውን እንደጣሰ የሚቆጥር ሲሆን የውሉ ተጠቃሚ የሆነ ተዋዋይ ወገን ደግሞ እንደውሉ እንዲፈጸምለት ወይም ውሉ እንዲፈርስለት የመጠየቅ መብት ያለው ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1771(1) ስር ተመልክቷል። ይሁን እንጂ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1757 ድንጋጌ እንደሚየሳየው ውሉ እንዲፈፀምለት የሚጠይቀው ወገን ጥያቄውን ማቅረብ ያለበትና ተቀባይነት ላኖረው የሚችለው በውሉ መሰረት አስቀድሞ ላወጣው የሚገባ ግድታ የተወጣ ስለመሆኑ ሲረጋገጥ ነው። በተያዘው ጉዳይ አመልካች ክላፕ ለማሰራት ግድታ መግባቸውን ሳይክዱ የክላፑ ስራ እንደውሉ ያልተፈፀመው በተጠሪ ጥፋት ነው፣ተጠሪ የዘፈኑን ታሪክ፣አልባሳት ባላማቅረባቸውና ክላፑ የሚሰራበትን ቦታ ባለመምረጣቸው ነው በማለት የሚያቀርቡት ክርክር በማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን በዚህ ረገድ ስልጣን ያለው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጠው ጉዳይ ነው። በመሆኑም አመልካች ውሉ መኖሩን አምነው የተጠሪ ግድታ ነው እስካአሉ ድረስ ይህንኑ የማስረዳት ግድታ መወጣት የነበረባቸው መሆኑን ከክርክራቸው አቀራረብ መረዳት ችለናል። ስለሆነም ተጠሪ በውሉ የገቡትን ግድታ ያልተወጡበት መንገድ ስለመኖሩ ያልተረጋገጠ በመሆኑ አመልካች በዚህ ረገድ የሚያቀርቡት ክርክር ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 258 እና 259፣ እንዲሁም ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1757፣ 2001 እና 2005 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንፃር ተቀባይነት ላሰጠው የሚገባው ሁኖ አልተገኘም።
ሁለተኛውን ጭብጥ በተመለከተ፡- ከክርከሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ዘፈኑ ለፊልም ማጀብያ እንዲውል ፈቅደው ከሰጡ የሞራል ጉዳት ደርሶብኛል፣ የሞራል ጉዳት ካሣ ይከፈል ላሉ አይችሉም በማለት መወሰናቸውን፣ግራ ቀኙን እስከዚህ ችሎት የሚያከራክራቸው ነጥብ ግን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በክላፑ ፈንታ አመልካች ለተጠሪ ገንዘብ ላከፍሉ የሚገባ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አምኖአል በማለት አመልካችን ኃላፊ አድርጎ የኃላፊነቱን መጠንም በርትዕ ብር 100,000.00 ነው በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል መሆኑን ነው።
የተጠሪ ስራ በአዋጅ ቁጥር 410/96 አግባብ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑና አመልካች ለፊልማቸው ማጀቢያነት የተጠቀሙበት መሆኑ ግራ ቀኙን ያከራከረ ጉዳይ አይደለም። አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊማቸው ማጀቢያነት ሲጠቀሙ ግን ለተጠሪ የከፈሉት ገንዘብ ስለመኖሩ በፍሬ ነገር ደረጃ አልተረጋገጠም። ይልቁንም ለተጠሪ ገንዘብ ከሚከፈላቸው የክላፑን ወጪ አመልካች ሸፍነው ክላፑን ላሰሩላቸው መስማማቸውን፣ ሆኖም ይህ ስምምነት ተፈፃሚነት ሳያገኝ የቀረው ተጠሪ በራሳቸው በኩል የሚጠበቅባቸውን ግድታ ባለመወጣታቸው ነው በማለት አመልካች ተከራክረው ይህ የአመልካች ክርክር በማስረጃ ያለመደገፉን ይግባኝ ሰሚው ችሎት ማረጋገጡን ይህ ችሎት ተገንዘቦአል።
በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 410/96 ጥበቃ ያገኘውን የተጠሪን ዘፈን አመልካች መጠቀማቸው እስከተረጋገጠ ድረስ አንድ ዘፈን ለፊልም ማጀቢያነት ሲውል ለዘፈኑ ባለቤት ላከፈል የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያህል ተጠሪ የማያገኙበት አግባብ የለም። ስለሆነም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ አመልካችን ኃላፊ ማድረጉ ከአዋጅ ቁጥር 410/96 አንቀጽ 7፣ 8 እና 34 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንጻር የሚነቀፍ ሁኖ ስላልተገኘ በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን ክርክር የምንቀበለው ሁኖ አልተገኘም።
በዚህ ረገድ የዚህን ችሎት ምላሽ የሚሻው አቢይ ነጥብ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ካሳውን የወሰነበት አግባብ ሕጋዊ መሆን ያለመሆኑ ነው። በቅጅ ወይም በተዛማጅ መብቶች መጣስ ምክንያት ለፍ/ቤት የቀረቡ የፍትሐብሕር ጉዳዮች የካሣ አከፋፈል ባለመብቱ የደረሰበት የገንዘብ ጉዳት እና በመብቱ መጣስ ምክንያት የተገኘ ትርፍን መሰረት ያደረገ መሆን እንደአለበት የሕጉ ይዘትና መንፈስ ያስገነዝባል። የካሳ አከፋፈሉ ባለመብቱ መብቱ ለተጣሰበት ሥራ ያወጣውን ወጪና ተከሣሹ ያገኘው ትርፍን ኢኮኖሚያዊ መብቱን ለማስከበርና የሞራል ካሣ የመክፈል ኃላፊነትን የሚያጠቃልል መሆኑ ይታወቃል። አዋጁ ለሞራል ጉዳት የሚከፈል ካሣ በጣም አነሰ ቢባል ከ100,000 /አንድ መቶ ሺህ ብር/ የማያንስ ሆኖ እንደ ጉዳቱ መጠን ከ100 ሺህ ብር በላይ ላወሰን እንደሚችል የአንቀፅ 34(4) ድንጋጌ በግልፅ ያስቀመጠ ሲሆን የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን በመጣስ የሚኖር የፍትሐብሕር ኃላፊነት የጉዳት ካሣና የሞራል ካሣ ከመክፈል በተጨማሪ ለካሣ አከፋፈሉ ምክንያት የሆነው ሥራ በባለመብቱ ላይ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ ከንግዱ እንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆኑ ወይም እንዲወገዱ ወይም በልላ ተገቢ አኳኋን እንዲጣሉ ለማዘዝ እንደሚቻልም ሕጉ ይደነግጋል። ፍርድ ቤት በዚህ አግባብ ውሳኔ ሲሰጥ የተከራካሪ ወገኖችን የማስረዳት ግድታ ግንዛቤ ባስገባ መልኩ ማስረጃን መሰረት ማድረግ እንዳለበት የሚታወቅ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ማስረጃ ቀርቦ በማስረጃው መወሰን አስቸጋሪ ሁኔታ ካለም በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 በተመለከተው አግባብ ካሳውን መወሰን እንደሚቻል የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1790(2) ድንጋጌን በምንመለከትበት ጊዜ የምንረዳው ጉዳይ ነው። ካሳ በርትዕ ከሚወሰንባቸው ምክንያቶች ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 ስር የተመለከቱት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የነገሮች ተራ ሁኔታዎች የሚለው ሐረግ ይገኝበታል። ይህ የድንጋጌው ይዘት ነባራዊ አለምን መሰረት በማድረግ የነገሮች ተራ ሁኔታዎች ተመዛዝነው የካሳ መጠኑ ላወሰን እንደሚችል የሚያስገነዝብ ነው።
በተያዘው ጉዳይ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልሙ ማጀቢያ በመጠቀማቸው ምክንያት በተጠሪ የደረሰ የኢኮኖሚ ጉዳት አልያም አመልች የተጠሪን ዘፈን በፊልም ማጅብያ ሲጠቀሙበት በገንዘብ ምን ያህል ይከፈላቸዋል ለሚለው ጥያቄ ተጠሪ 164,000.00 (አንድ መቶ ስድሳ አራት ሺህ ብር) የኢኮኖሚ ጉዳት ደርሶብኛል ከማለታቸው በቀር ይህንኑ የኢኮኖሚ ጉዳት የደረሰባቸው ለመሆኑ የሚያስረዳ ማስረጃ እንዳላቀረቡ፣ አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልም ማጀብያ ሲያውሉ ላከፍላቸው ያሰቡት አልያም ለዘፈኑ ክላኘ ምን ያህል እንደሚያወጡ ተዋውለናል ከማለታቸው ውጪ በጽሑፍ ውስጥ አስፍረው የነበረ ስለመሆኑ ያስረዱት ነገር የለም የሚሉትን ምክንያቶችን ጠቅሶ በተጠሪ ላይ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ወይም የቀረ ጥቅም ለመገመት አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱን መደምደሙን በዚህም ምክንያት አመልካች በርትዕ ብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) ለተጠሪ ላከፍሉ ይገባል በማለት መወሰኑን የውሳኔው ግልባጭ ያሳያል። ይሁን እንጂ አመልካች በውል ሰነዱ ላይ የሰፈረውን ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ባያስረዱም ለአንድ ፊልም ማጀቢያነት የሚውል ዘፈን ላከፈልበት የሚገባው ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ገበያውን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ዘፋኞች ለተያዩ ፊልሞች የተከፈላቸውን ዋጋ ለይተው በመግለፅ፣ በዚህ ረገድም የሰነድ ማስረጃ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው የተከራከሩ መሆኑን የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ ሲሆን ተጠሪም አመልካች የጠቀሷቸው ዘፈኖችና ዋጋቸው በስር ፍርድ ቤት በክርክር ደረጃ አልተነሱም ሳይሉ አመልካች ላከፈል ይገባል የሚሉት ዋጋ የወቅቱን የፊልም ማጀቢያ ዘፈን ዋጋ ያላገናዘበ ነው በማለት የሚከራከሩ መሆኑን ለዚህ ችሎት ከሰጡት የፅሑፍ መልስ ተመልክተናል። ስለሆነም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች በዚህ ረገድ ማስረጃ ቆጥረው እያሉና ማስረጃዎቹ ለጉዳዩ ያላቸውን አግባብነት ሳይመረምር በውል ሰነዱ ላይ ሰፍሮ የተገኘ ዋጋ አልተገኘም በሚል ምክንያት ብቻ ወደ ርትዕ መሄዱ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 ድንጋጌን ይዘትና መንፈስ እንዲሁም የተከራካሪ ወገኖችን ማስረጃ የመስማት መብት እና ፍርድ ቤቱ እውነትን መሰረት ያደረገ ዳኝነት ለመስጠት ይቻለው ዘንድ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 ድንጋጌን ተግባራዊ ላያደርግ የሚገባበትን አግባብ ያላገናዘበ ሁኖ ተገኝቷል።
አንድ ዘፈን ለአንድ ፊልም ማጀቢያ ሲውል ዋጋው በተዋዋይ ወገኖች ላቆረጥለት የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም ዋጋው በውሉ መታወቅ ካልተቻለ ግን ተከራካሪ ወገኞች በሚያቀርቧቸው አግባብነት ባላቸው ልሎች ማስረጃዎች ወይም ፍርድ ቤቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 መሰረት መድቦ በሚያጣራው ባለሙያ ላታወቅ የሚችል መሆኑን የነገሮች ተራ ሁኔታዎች የሚያስረዱ መሆኑን ነባራዊው አለም ያስገነዝባል። ስለሆነም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተጠሪ ዘፈን ለፊልም ማጀቢያነት ሲውል ላከፈል ይችል የነበረውን ዋጋ አመልካች በዚህ ረገድ ማስረጃዎቼ ናቸው በማለት ከአቀረቧቸው የሰነድ ማስረጃዎች ወይም ከሚመለከተው የሙያ ማህበር አግባብነት ያለውን ባለሙያ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 መሰረት እንዲመደብ አድርጎ ትክክለኛውን የወቅቱን ዋጋ አጣርቶ መወሰን ሲገባ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ውጪ በርትዕ መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ሁኖ አግኝተናል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ ሐምል 16 ቀን 2005 ዓ.ም ተሰጥቶ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ/ም በከፊል የተሻረው ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1 መሰረት ተሻሽሐል።
አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልሙ ማጀቢያ በመጠቀማቸው ዋጋውን ላከፍሉ ይገባል ተብሎ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል።
ሆኖም አመልካች ብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) ክሱ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ከሚታሰብ ህጋዊ ወለድ 9% (ዘጠኝ በመቶ) ጋር ለተጠሪ እንዲከፍሉ በርትዕ መወሰኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 ትክክለኛ አፈፃጸም ያላገናዘበ በመሆኑ ተሸሯል።በመሆኑም የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ኃላፊ የተባሉ መሆኑን በመገንዘብ የኃላፊነት መጠኑን ግን በፍርድ ሀተታው ላይ በተገለጸው አግባብ አግባብነት ባላቸው የአመልካች ማስረጃዎች እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 መሰረት ከሚመለከተው የሙያ ማህበር ተጣርቶ በሚቀርበው ማስረጃ መሰረት በመመርመር ላወሰን ይገባል በማለት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል። ይጻፍ።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራቸውን ይቻቻሉ ብለናል።
አለበት።
No topics extracted.