አንድን ንብረት የሸጠ ሰው የሸጠውን ንብረት ባለሃብትነት ለገዥው የማዛወር ግድታ ያለበትና ይህንን ለመፈፀም አስፈላጊ የሆኑ ተግባራቶችን የማከናወን ግድታ ያለበት ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ.2273፣2281፣1771(1)፣1757
No summary available.
የሰ/መ/ የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ/ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ተኽላት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ አመለካች፡- ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይ - ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን - ነ/ፈጅ ግርማ ዘለቀ - ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ኤፍሬም አሸቱ - የቀረበ የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የመኪና ሽያጭ ውልን መሰረት ያደረገ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- አመልካች መጋቢት 10 ቀን 2003 ዓ/ም ባወጣው የመኪና ሽያጭ ጨረታ ላይ ተሳትፈው የታርጋ ቁጥር 3-18353 ኢት የሆነውን መኪና በብር 127,915.55 (አንድ መቶ ሃያ ሰባት ሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ አምስት ብር ከሃምሳ አምስት ሳንቲም) የገዙ ቢሆንም ለስም ዝውውሩ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተሸከርካሪውን ማጣሪያ ክላራንስ እንዲመጣ መጠየቃቸውንና ተጠሪ አመልካችን በዚህ አግባብ እንዲፈፀም ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም አመልካች ለማስጠንቀቂያው በሰጠው ምላሽ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስም ዝውውሩ እንዲፈጸም ቃል የገባ ቢሆንም አለመፈጸሙን፣ በዚህ መሰረት አመልካች መኪናውን ለገዛው ተጠሪ ስም ለማዛወር የሚረዱ ሰነዶችን ለተጠሪ የማስረከብ ግድታውን ያልፈፀመ እና የመኪናው የኪራይ ገቢ ዋጋ በቀን ገቢ ተሰልቶ ብር 205,000.00(ሁለት መቶ አምስት ሺህ) ጥቅም የቀረባቸው መሆኑን ዘርዝረው አመልካች ለተጠሪ መኪናው ከግብርና ታክስ እዳ ነፃ የሆነበትን የክላራንስ ሰነዶች እንዲያስረክብ፣ በቀን የታጣ ገቢ ብር 205,000.00 እንዲከፍል፣ ሰነዶቹን እስከሚያስረክብ ድረስ ያለውን ኪሳራ የመጠየቅ መብት እንዲጠበቅላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም፡- ተጠሪ አከራካሪውን መኪና ከአመልካች በጨረታ መግዛታቸውን ሳይክድ በመኪናው ላይ ምንም አይነት እዳና እገዳ የልለበት መሆኑን፣ መኪናው ሲሸጥም የመኪናውን የባለቤትነት ደብተር/ላብሬ/፣ ልሎች ማስረጃዎችን በሙሉ ከነመለያው ለተጠሪ ማስረከቡን፣ ለሚመለከተው አካልም ስመ ሃብቱ እንዲዞርላቸው ነሀሴ 03 ቀን 2003 ዓ/ም ደብዳቤ የፃፈላቸውና ተጠሪም ግልባጩን ተረክበው የወሰዱና ለፕሮክጀት ስራ ተቋራጭ ነፃ በገቡ ማስረጃዎች ጋር በተያያዘ ከኢትዩጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ጋር በተፈጠረ ችግር ኃላፊነትት የለብንም በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው። የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ አመልካችን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ አመልካች ለተጠሪ መኪናው ከግብርና ታክስ እዳ ነፃ የሆነበትን የክላራንስ ሰነዶች እንዲያስረክብ፣ በቀን የታጣ ገቢ ብር 205,000.00 እንዲከፍል፣ ሰነዶቹ እስከሚያስረክብ ድረስ ያለውን ኪሳራ ደግሞ ተጠሪ የመጠየቅ መብት የተጠበቀ መሆኑን ገልፆ ወስኖአል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አጽንቶታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘት፡- ለክሱ መነሸ የሆነውን መኪና አመልካች በግልጽ ጨረታ ሽጦ የስም ዝውውር በተመለከተም በጨረታው መመሪያው መሰረት በሕግ የሚፈለገውን ተግባር ሁሉ አመልካች ድርጅት ፈጽሞ እያለ ንብረቱ ለስም ዝውውር ምንም አይነት እዳና እገዳ ሳይኖርበት የሕግና የፍሬ ነገር መሰረት በልለበት አግባብ አመልካች ለክሱ ኃላፊ ተደርጎ የቀን ገቢ ብር 205,000.00 እና የጠበቃ አበል እንዲከፍል መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው። አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች አከራካሪውን መኪና ስም ለማዛወር የሚያስፈልጉትን ሰነዶች ለተጠሪው አስረክቢያለሁ ብሎ ተከራክሮ ባለበት ሁኔታ የስር ፍርድ ቤት ስም ለማዛወር የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ያላስረከበ መሆኑን አመልካች አልካደም በሚል ምክንያት አመልካች ግድታውን አልፈፀመም በማለት የተሰጠውን ውሳኔ አግባብነት ለመመርመር ተብሎ ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል።
የክርክሩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ባወጣው የመኪና ሽያጭ ጨረታ ላይ ተጠሪ ተወዳድረው ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ተሸከርካሪ መግዛታቸው ግራ ቀኙን ያላከራከረ ነጥብ መሆኑን፣ አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩት ለስም ዝውውሩ አስፈላጊ ከሆኑት ሰነዶች መካከል መኪናው እዳና አገዳ የልለበት መሆኑን የሚገለፅ የክላራስን ሰነድ ለተጠሪ የመስጠት ግድታ አመልካች ያለው መሆን ያለመሆኑን ላይ ስለመሆኑ ነው።
ከላይ እንደተገለጽው የተጠሪ ዋነኛ የዳኝነት ጥያቄ በውል ገዝቼዋለሁ የሚሉትን መኪና ስመሃብት በስማቸው እንዲመዘገብ መኪናው እዳና እገዳ የልለበት ስለመሆኑ የሚያሳይ ሰነድ በአመልካች ይሰጠኝ ሲሆን በስሜ እንዲመዘገብ ለማድረግ አስፈላጊ ሰነዶች ከአመልካች አልተሰጠኝም የሚሉት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ስለ መኪናው ከእዳና እገዳ ነፃ መሆን የሚያሳይ የክላራንስ ሰነድን ነው። አመልካች የመኪናውን የባለቤትነት ደብተር/ላበሬ/ እና ልሎች ማስረጃዎችን በሙሉ ከእነመለያው ለተጠሪ ማስረከቡን ገልፆ ለአቀረበው ክርክር ተጠሪ ማስተባበያ ክርክርና ማስረጃ ያቀረበ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ አሳያስም።
አንድን ንብረት የሸጠ ሰው በፍትብሐር ሕግ ቁጥር 2273 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የሸጠውን ንብረት ባለሀብትነት ለገዥው የማዛወር ግድታ ያለበት ሲሆን ይኸም የሻጭ የንብረቱን ባቤትነት ለገዥ የማዛወር ግድታ በምን መልኩ መፈፀም እንደሚገባው ህግ አውጭው ‹‹ሻጩ የሸጠውን ነገር የማያስነካ መብት ለገዥው ለማስተላለፍ አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮችን ለመፈፀም ግድታ አለበት›› በማለት በፍትብሕር ህግ ቁጥር 2281 በግልጽ ከደነገገው የምንረዳው ጉዳይ ነው።
ስለሆነም አመልካች ተጠሪ የመኪናን ሽያጭ በውሉ መሰረት እንዲፈጽሙና ስመንብረቱን ለተጠሪ ለማዛወር አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን መፈጸን የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም የስም ሃብት ዝውውሩን ለማድረግ አስፈላጊ ተግባራት አልተከናወኑም የሚለው ገዥ እነዚህን በሻጭ ያልተከናወኑትንና የስመ ሃብት ዝውውሩን የሚያከናውን አካል ኃላፊነቱንና ተግባር ለመፈፀም የማያስችለው አስፈላጊ ተግባር ምን እንደሆነ እና አስፈላጊነቱን ማስረዳት መቻል አለበት።
ከዚህ ውጪ ተገቢው ሰነድና ለሽያጩ መሰረት የሆነው ንብረት ርክክብ ተፈጽሞ እያለ ስመ ሃብቱ አልተዛወረልኝም በሚል ምክንያት ብቻ በሻጩ ላይ ክስ ማቅረብ እና ተቀባይነት የሚያገኝበት አግባብ የለም።
ከተዋዋዮቹ አንዱ ወገን የውል ግድታውን ያልፈጸመ እንደሆነ ልላው ወገን እንደነገሩ አጋጣሚ ሁኔታ ውሉ እንዲፈጸምለት የመጠየቅ መብት እንዳለው፣ ካልሆነም ውሉ እንዲፈርስ መጠየቅ እንደሚችል ወይም ውሉ መፍረሱን ለልላው ወገን ላገልጽ የሚችል መሆኑን የፍ/ህ/ቁ/1771(1) የሚደነግግ ሲሆን በውሉ አለመፈጸም የተነሳ ጉዳት የደረሰበት ከሆነም ኪሳራ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት ያለው መሆኑን የድንጋጌው ንዑስ ቁጥር 2 ያመለክታል። ውሉ ተዋዋዮቹ በአንድነት የሚፈጽሙትን ግድታ (simultaneous performance) የሚጥል ሆኖ ከተገኘም ተዋዋዩ የተዋዋለበትን ግድታ በውሉ እንደተመለከተው እንዲፈጸምለት የሚጠይቀው ወገን ከውሉ ስምምነት የተነሳ እሱም በበኩሉ ያለውን ግድታ ወዲያውኑ መፈጸም ወይም ለመፈጸም የተዘጋጀ መሆኑን ማረጋገጥ የሚገባው መሆኑን የፍ/ህ/ቁ/1757 ያስገነዝባል።
በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ አመልካችን ላከሱ የቻሉት የስመ ሃብቱን ዝውውር በሚያደርጉት እለት በመኪናው ላይ የእዳና እገዳ ነፃ መሆኑን የሚያሳይ የክላራንስ ሰነድ ከገቢዎችና ጉምሩክ ተጠይቀው ይኼው ሰነድ በአመልካች ላቀርብላቸው ባለመቻሉ ነው። ይሁን እንጂ ይህን የክላራንስ ሰነድ ማቅረብ የአመልካች ግድታ ስለመሆኑ የሚያሳይ የውል ግድታ የልለ ከመሆኑም በላይ ተጠሪ ሰነዱን ራሳቸው ለመውሰድ ያላስቻላቸው ምክንያት ስለመኖሩ ወይም የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ክላራንስ የከለከላቸው መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ተጠሪ አላቀረቡም።
ተጠሪ ስመ ሃብቱን ለማዛወር የሚያስችለው አስፈላጊ ተግባር በአመልካች መከናወን ያለበት ስለመሆኑ ባላስረዱበት ሁኔታና አመልካች ደግሞ መኪናውንና አስፈላጊ ሰነዶችን ለተጠሪ ማስረከቡን ገልፆ በተከራከረበት አግባብ የስር ፍርድ ቤት አመልካች አስፈላጊ ሰነዶችን ያላስረከበ መሆኑን አልካደም በማለት የደረሰበት ድምዳሜ ለጉዳዩ የቀረበውን የግራ ቀኙን ክርክር ይዘት ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 235 እና 83 ድንጋጌዎች ይዘት ያላገናዘበ ሁኖ አግኝተናል። እንዲሁም ተጠሪ አመልካች ነሐሴ 03 ቀን 2003 ዓ/ም በፃፈለት ደብዳቤ መነሻ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሂደው መኪናው ከእዳና እገዳ ነጻ ስለመሆኑ የሚያሳይ የክላራንስ ሰነድ ማግኘት ያልቻሉ መሆኑን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2001፣ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 258 እና 259 ድንጋጌዎች ይዘት መሰረት ባላስረዱበት ሁኔታ አመልካች ለክሱ ኃላፊ መደረጉ ከማስረዳት ሽክም አንፃር ተቀባይነት ያለው አይደለም። ስለሆነም አመልካች የሸጠውን መኪና ስመንብረት (ባለሀብትነት) ለተጠሪ ለማዛወር አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን የመፈፀም ግድታና ሀላፊነት ስላለመወጣቱ ተጠሪ ባለስረዱበት ሁኔታ አመልካች ስም ለማዛወር የሚያስፈልጉ ሰነዶች ያላስረከበ መሆኑን አልካደም ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘውን ተከታዩን ወስነናል።
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ በ19/09/2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ በ06/08/2007 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
ተጠሪ ከአመልካች ለገዛው ተሸከርካሪ ስመ ሃብት ዝውውር ያልፈፀመው አስፈላጊ ተግባር ስለመኖሩ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2273 እና 2281 ድንጋጌዎች አግባብ ተጠሪ ስላላስረዱ አመልካች ለክሱ ኃላፊ የሚሆንበት የሕግ አግባብ የለም ብለናል።
ለክርክሩ ምክንያት የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.