አንድ የዋስትና ውል ዋሱ ግድታ የገባበትን ኃላፊነት መጠን ወይም ልኩ ምንያህል እንደሆነ በዋስትና ውሉ ላይ በገንዘብ ካልተገለፀ በስተቀር ዋስትናው ፈራሽ ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ህ/ቁ-1922(3)
No summary available.
መስከረም 25ቀን 2008ዓ᎐ም ዳኞች:- አልማዉ ወል ረታ ቶሎሣ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ ልላሴ ደሣለኝ አመልካቾች፦ አቶ ፍቅሬ ግርማ ቀረቡ ተጠሪ፦ አቶ ደስታ ጫምሶ አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ ከዋስትና ውል ጋር ተያይዞ የቀረበ ክርክርን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩም የጀመረው ያአሁኑ አመልካች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ነገል ወረዳ ፍ/ቤት የሰበር ክርክሩ ተከፋይ ያልሆነው አቶ አበበ ኤርጊቾ እና ሰበር ተጠሪ ላይ በመሰረተው ክስ መነሻነት ነው።የክሱ ፍሬ ነገርም ባጭሩ፦ግምቱ 20,000 ብር የሆነውን የኢጣላያን ስሪት እህል ሚዛን 1ኛተከሳሽ በ 24/2/2001 ዓም በተደረገ ኪራይ ውል ወስዶ በኋላ ላይ እንዲመልስ ሲጠየቅ ለመመለስ ፊቃደኛ አልሆነም፣2ኛ ተከሳሽም በበኩሉ ሚዛኑን ለመመለስ ወይም መተካት የዋስትና ግድታ ገብቷል፣ስለዚህ ተከሳሾቹ ተጠይቀው ሚዛኑን የማይመልሱ ከሆነ በገቡት ግድታ መሰረት ግምቱን ይክፈሉኝ በሚል ዳኝነት የተጠየቀበት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽን በተመለከተ ክሱ ስነ-ስርዓቱን ጠብቆና ተሟልቶ አልቀረበም በሚል ምክንያት ተከሳሹ በወረዳ ፍ/ቤቱ ከክሱ ወጭ መደረጉን ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ ግን ቀርቦ ለክሱ በሰጠው መልስ የገባው የዋስትና ግድታ የልለ መሆኑን፣የዋስትና ውል ነውተብሎ በቀረበው ሰነድ ላይ ያለውም ፊርማ የራሱ ያለመሆኑንና የዋስትና ውሉም ራሱ ለምን ያህል ገንዘብ ግድታ እንደተገባ ስለማያሳይ በፍ/ብ/ህ/ቁ-1922(3) መሰረት ውሉ ፎርማላቲን አያሟላም ተብሎ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ በማለት ተከራክሯል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ወረዳ ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና በዋስትና ውሉ ላይ የተጠቀሱትን ምስክሮች ቃል ሰምቶ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ተጠሪ የዋስትና ዉሉን መፈረሙ በምስክሮች ቃል መረጋገጡን መገንዘቡን ካሰፈረ በኋላ ተጠሪ በዉሉ የተጠቀሰውን ሚዛን አይነት አዲስ ለአመልካች ይተካ ሲል ወስኗል። ባአሁኑ ተጠሪ የይግባኝ ቅሬታ መነሻነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ ቤት በበኩሉ ግራ ቀኙን አስቀርቦ ካከራከረ በኋላ በዋስትና ውሉ ላይ ያለው ፊርማ የተጠሪ መሆን ያለመሆኑን ለማጣራት ሲባል ፊርማው በፎረንሲክ ተመርምሮ ውጤቱ እንዲቀርብ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የዋስትና ውሉ ፎቶ ኮፒ በመሆኑ ምርመራውን በዚህ ምክንያት ማካሄድ አልተቻለም የሚል ምላሽ ከተሰጠው በኋላ ጉዳዩን ባለበት ሁኔታ መርምሮ የስር ፍ/ቤቱን ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ- 348(1) መሰረት መልሶ አፅንቶታል። ተጠሪ አሁንም በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ችሎት አቅርቦና ችሎቱም በበኩሉ ግራ ቀኙ ቀርበው እንዲከራከሩ ካደረገ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የዋስትና ውሉ ዋሱ (ተጠሪ) ለምን ያህል ገንዘብ ግድታ እንደገባ የማይገልፅ መሆኑን ጠቅሶና እንዲህ ከሆነ ደግሞ ውሉ በፍ/ብ/ህ/ቁ-1922(3) ስር የተመለከተውን የህግ መስፈርት ስለማያሟላ በዋሱ ላይ ግድታ ላጥል አይችልም በማለት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሽሯል።
አመልካችም ይሄንኑ በክልሉ ስበር ሰሚ ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም የሰበር አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን መሰረታዊ ይዘቱም ባጭሩ፣ለዋስትና ውሉ መነሻ የሆነው ግድታ ዓይነትም የእቃ ኪራይ እንጅ ብድር ውልን የሚመለከት ካለመሆኑ በላይ ተጠሪም እራሱ በዋስትና ውሉ መሰረት የገባው ግድታ በፍ/ብ/ህ/ቁ-2727 እና 2738 ስር እንደተመለከተው ሚዛኑን እራሱን በአይነት ለመተካት ወይም ለመመለስ ከመሆኑ አንፃር በውሉ ላይ የገንዘብ መጠን መጥቀስ የግድ አይደለም የሚል ይዘት ያለው ሲሆን አቤቱታውም ተመርምሮ ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት በመመራቱ ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን እኛም በበኩላችን በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን ያለመሆኑን በጭብጥነት ይዘን ጉዳዩን መርምረናል። መዝገቡን እንደመረመርነውም ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ሚዛን ከአመልካች የተከራየሁ ግለሰብ (ዋና ባለእዳ) በውሉ መሰረት መልሶ ለአመልካች አለማስረከቡ ክርክር የቀረበበት ጉዳይ አይደለም።ተጠሪም በበኩሉ በዋስትና ውሉ ላይ ተመሳሳዩን ሚዛን በዓይነት ለመተካት በሚል የዋስትና ግድታ እንደገባ ተደርጎ በውሉ ላይ መስፈሩን የክርክሩ ሂደት ያሳያል።ሆኖም ግን የዋስትና ውሉ አፃፃፍ ወይም ይዘት ምንም ይሁን ምን ዋሱ ግድታ የገባበትን የኅላፊነት መጠን ወይም ልኩ ምን ያህል እንደሆነ በዋስትና ውሉ ላይ በገንዘብ ካልተገለፀ በስተቀር ዋስትናው ፈራሽ እንደሚሆን ከፍ/ብ/ህ/ቁ-1922(3) ድንጋጌ ይዘት መገንዘብ ይቻላል።
በተያዘው ጉዳይም ተጠሪ ተመሳሳዩን ሚዛን በዓይነት ለመተካት በሚል የዋስትና ውሉን የፈረመ ቢሆንም የግድታው መጠን ግን እስከ ምን ያህል እንደሆነ በገንዘብ ተገልፆ በውሉ ላይ አልተመለከተም። ይህ የዋስትና ግድታ አድማስ ደግሞ ለምን ያህል እንደሆነ በውሉ ላይ በገንዘብ ካልተገለፀ የዋስትና ውሉ ዋጋ ስለማይኖረው ወይም ፈራሽ ስለሚሆን አመልካች የገንዘቡ መጠን መገለፅ የግድ አይደለም በማለት ያቀረበው ክርክር የህግ መሰረት ስለልለው አልተቀበልነውም።
በልላ በኩል ለዋስትና ግድታው መሰረት የሆነው ጉዳይ የእቃ ኪራይን የሚመለከት ግድታ ይሁን ወይም ልላ ዋናው ቁም ነገር በዚህ ጉዳይ ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለው የዋናው ግድታ ውል (የእቃ ኪራይ ውል) እራሱ ሳይሆን የእሱ ተቀፅላ (accessory) የሆነው የዋስትና ውል ነው።አከራካሪ ሆኖ የቀረበው ጉዳይ የዋስትና ውሉ ከሆነ ደግሞ በተለይ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የህጉ ክፍል የፍ/ብ/ህ/ቁ- 1920ና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ናቸዉ እንጂ አመልካች በሰበር አቤቱታዉ የጠቀሳቸዉ የፍ/ብ/ህ/ቁ᎐2727 እና 2738 ለጉዳዩ አግባብነት የላቸውም። ሲጠቃለል የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በግራ ቀኙ መካከል የተፈፀመው የዋስትና ውል ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን የፍ/ብ/ህ/ቁ-1922(3) ድንጋጌን መስፈርት ስለማያሟላና ፈራሽ ስለሆነ ተጠሪ ላይ ግድታ ላጥል አይችልም በማለት ከኃላፊነት ነፃ በማድረግ መወሰኑ ህጉን በትክክል መሰረት ያደረገነው ከሚባል በስተቀር ልላ ላባል የሚቻል ባለመሆኑ ተከታዩን ወስነናል።
የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመቁ-175321 በ 23/10/2006 ዓ᎐ም የሰጠዉ ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ-348(1) መሰረት ፀንቷል።
የአመልካች ሰበር አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ብለናል።
የሰበር ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.