እብደቱ በግልጽ ያልታወቀ ሰው ወራሾች ወይም ባለገንዘቦች ይህ ሰው የፈጸመው ውል ጉድለት የልለበት ፈቃድ አልሰጠበትምና ውሉ ላፈርስ ይገባል ሲሉ እብደቱን ምክንያት በማድረግ የውሉን መፍረስ መጠየቅ የማይችሉ ስለመሆኑ፡የማይንቀሳቅስ ንብረት ሽያጭ ውልን ዋጋ ተጎዳሁ በሚል ምክንያት ላፈርስ የማይችል ስለመሆኑ፡የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ ሕ/ቁ. 348፣347/1//2/፣349፣350፣341፣342 የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2887
No summary available.
ታህሳስ 18 ቀን 2008ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ተኽላት ይመስል እንደሻው አዳነ ቀንዓ ቂጣታ አመልካች፡- አቶ ጥላሁን ዓለሙ ጠበቃ አቶ ተስፋሁን ጸጋዬ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ደረጀ ማሞ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ሟች እናቴ በአእምሮ ህመም ሲሰቃዩ ቆይተው ከዚህ ዓለም በ2003 ዓ.ም በሞት ተለይተዋል። ስለዚህ እናቴ የአእምሮ ህመምተኛ በሆኑበትና ፈቃዳቸውን ለመስጠት በማይችሉበት ሁኔታ በእርካሽ ዋጋ ቤታቸውን ለተከሳሽ (ተጠሪ) ለመሸጥ የተዋዋሉት ውል እንዲፈርስ ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት ክስ አቅርበዋል።
ተጠሪ በስር ፍ/ቤት በተከሳሽነት ቀርቦ የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያና የመከላከያ መልስ አቅርቧል። ተከሳሽ የከሳሽ እናት የአእምሮ ህመም በግልጽ የታወቀ የአእምሮ ህመም አይደለም። ተከሳሽ ቤቱን ከከሳሽ እናት የገዛሁት እናቱ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ቀርበው ጤናማ አእምሮ እንዳላቸውና ቤታቸውን ለመሸጥ ፈቃደኛ መሆናቸው ተረጋግጦ ነው። የከሳሽ እናት የሽያጭ ውሉን ከተከሳሽ ጋር በተዋዋሉበት ጥር 18 ቀን 2001 ዓ.ም ድብርት ውስጥ አልነበሩም። ተከሳሽ ቤቱን የገዛሁበት ትክክለኛ ዋጋ ብር 1,350,000 /አንድ ሚላዮን ሶስት መቶ ሃምሳ ሺ ብር/ ሲሆን የከሳሽ እናት ይህንን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ተቀብለዋል። ተከሳሽ ቤቱን ከገዛሁ በኋላ ከፍተኛ ወጭ በማውጣት የተለያዩ የእድሳት ስራዎችን የሰራሁ በመሆኑ ውሉ ፈርሶ ተዋዋዮች ወደ ነበርንበት ለመመለስ የማይቻል በመሆኑ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም የሚል መከራከሪያ አቅርቧል።
የስር ፍ/ቤት የከሳሽ /የአመልካች/ እናት ወ/ሮ ዘውድ በየነ የቤት ሽያጭ ውል ከተጠሪ /ከተከሳሽ/ ጋር ሲዋዋሉ የታወቁ የአእምሮ ህመምተኛ ነበሩ? ወይስ አልነበሩም? የቤት ሽያጭ ውሉ ላፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? ውሉ ላፈርስ ይገባል ከተባለ ተዋዋዮች ወደነበሩበት መመለስ አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚሉትን ጭብጦች መስርቶ፣ የከሳሽ እናት በድብርት ምክንያት በአማኑኤል ሆስፒታል በየቀጠሮ እየተመላለሱ የህክምና አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ መሆናቸው የህክምና ማስረጃው ያሳያል። የከሳሽ እናት ተመላላሽ ታካሚ በመሆናቸው በግልጽ የታወቀ የአእምሮ ህመም የነበረባቸው ሴት ነበሩ ብሎ ለመደምደም በህጉ የተቀመጠውን መስፈርት አያሟሉም፤ ተከሳሽ የከሳሽ እናት የአእምሮ ህመም /ችግር/ ያለባቸው መሆኑን እያወቀ ውሉን የተዋዋለ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም። ከዚህ በተጨማሪ የከሳሽ እናት በመጨረሻ ጊዜ በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው የሕክምና አገልግሎት ያገኙት ጥር 21 ቀን 2001 መሆኑን የቀረበው የሕክምና ማስረጃ ያሳያል። ይህም ውሉ በተደረገበት ሰኔ 18 ቀን 2001 ህክምናቸውን ጨርሰው በጤናማ የአእምሮ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ያሳያል።
ከዚህ በተጨማሪ ተከሳሽ የከሳሽ እናት በጤናም አእምሮ የቤት ሽያጭ ውል የተዋዋሉ ስለመሆኑ የመከላከያ ማስረጃ በማቅረብ አስረድቷል። ስለዚህ የቤት ሽያጭ ውሉ የሚፈርስበት ህጋዊ ምክንያት የለም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪ መስቀለኛ ይግባኝ ማመልከቻ አቅርበዋል። ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል። ተጠሪ የስር ፍ/ቤት ክሱ በይርጋ ይታገዳል፤ አመልካች የመክሰስ መብት የለውም በማለት ያቀረብኩትን የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ አላግባብ ውድቅ አድርጎብኛል በማለት ያቀረበውን መስቀለኛ ይግባኝ ሳይቀበለው ቀርቷል።
እናቴ ቤት ተዘግቶባት የምትኖር ነበረች። ቤቱንም የሸጠችው በእርካሽ ዋጋ ነው።
እንደዚሁም ውሉ የሟች ጣት አሻራ የልለው መሆኑ ዋናውን ቅጅ ለማረጋገጥ ፈልጎ ላያገኘው እንዳልቻለ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ገልጾ እያለ፤ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
በሆስፒታሉ ህክምና ቦርድ በኩል ተረጋግጦ የቀረበ ማስረጃ አይደለም። አመልካች እናታቸው የአእምሮ ህመምተኛ መሆናቸውን ካወቁ በህግ በተደነገገው መሰረት እናታቸው ውል እንዳይዋዋሉ በፍርድ ማስከልከል ሲገባቸው ይህንን ሳያደርጉ ውሉ ይፍረስ በማለት ያቀረቡት ክርክር የህግ መሰረት የለውም። የአመልካች እናት፤ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም በተደረገው ውል ከተገለጸው በላይ የሆነ ገንዘብ ከተጠሪ መቀበላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ቀርቧል። በአጠቃላይ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ውድቅ ተደርጎ እንዲሰናበት በማለት መልስ ሰጥቷል። አመልካች ጥቅምት 19 ቀን 2007ዓ.ም የተጻፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በዚህ ሰበር ችሎት ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የበታች ፍ/ቤቶች አመልካች ተጠሪ ከሟች ወ/ሮ ዘውድ በየነ ጋር አድርጎት የነበረው የቤት ሽያጭ ውል ፈራሽ ይሁንልኝ በማለት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ያደረጉት በህግ አግባብ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
መዝገቡን እንደመረመርነው የአመልካች እናት ወ/ሮ ዘውድ በየነ የፍተሐ ብሕር ህግ ቁ.
341 እና የፍተሐ ብሕር ህግ ቁ. 342 በሚደነግገው መሰረት የነበረባቸው የአአምሮ ጉድለት፤ በግልጽ የሚታወቅ የአእምሮ ጉድለት ስለመሆኑ አመልካች የማስረዳት ግድታውን /Burdon or proof/ ያልተወጣ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባላቸው የበታች ፍ/ቤቶች ተረጋግጧል። ከዚህ አንጻር ሲታይ አመልካች በወላጅ እናቱ ላይ ነበረ የሚለው የአእምሮ ጉድለት በፍተሐ ብሕር ህጉ በግልጽ ያልታወቀ የአእምሮ ጉድለት በሚል መንገድ የሚገልጸው የአእምሮ ጉድለት መሆኑ ተረጋግጧል።
የእብደቱ ሁኔታ በግልጽ ያልታወቀ ሰው የፈጸማቸው የህግ ስራዎች በዚሁ ሰው የአእምሮ ጉድለት ምክንያት ላሻሩ የማይችሉ ስለመሆኑ በመርህ ደረጃ የፍተሐ ብሕር ህግ ቁ. 347 ንዑስ አንቀጽ 1 ደንግጓል። ከዚህ ጠቅላላ መርህ በልዩ ሁኔታ የተፈቀደው በፍትሐብሕር ሕግ ቁ. 347 ንዑስ አንቀጽ 2 እብደቱ በግልጽ ያልታወቀ ሰው ውሉ እንዲፈርስለት የሚጠይቅበት ሁኔታና በፍተሐብሕር ህግ ቁ. 349 እና በፍተሐብሕር ህግ ቁ. 350 የተደነገጉት ልዩ ሁኔታዎች ናቸው። ሟች ወ/ሮ ዘውድ በየነ ቤታቸውን ለተጠሪ የሸጡት በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት በተደረገ ውል ሲሆን፤ አመልካች የሚከራከረው የቤቱ ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑ ሟች እናቴ የአእምሮ ህመም ምክንያት ንብረቱን በበቂ ዋጋ ያልሸጠች እና የአእምሮ ህመም ምክንያት ውል የተዋዋለች መሆኑን ያሳያል በማለት ነው።
ተጠሪ አከራካሪውን ቤት በምን ያህል ገንዘብ ነው የገዛው የሚለው ነጥብ፤ በመጀመሪያ ሟች ወ/ሮ ዘውድ በየነ ከተጠሪ ጋር በውሉና በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ያደረጉት ውል ፈራሽ ላሆን ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ጭብጥ ምላሽ ካገኘ በኋላ የሚታይ በመሆኑ አመልካችና ተጠሪ ስለቤቱ ዋጋ ያደረጉትን ክርክርና ክርክሩን ለማስረዳት ለበታች ፍ/ቤቶች ያቀረቧቸውን የተለያዩ ማስረጃዎች ይዘት መመልከቱ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘነውም። በዚህ ደረጃ አመልካች የቤቱ ዋጋ ማነሱን ለውል ማፍረሻነት ምክንያት አድርገው ያቀረቡት ክርክር የህግ ድጋፍ አለው ወይስ የለውም የሚለውን ነጥብ መመልከቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል። ይህ አመልካች ያነሳው መከራከሪያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል ለማፍረስ በቂ ምክንያትና መከራከሪያ ሆኖ ላቀርብ የማይችል መሆኑ በፍተሐብሕር ህግ ቁ. 2887 የተደነገገ በመሆኑ፤
አመልካች ቤቱ በዝቅተኛ ዋጋ የተሸጠ መሆኑ፤ ሻጭ የአእምሮ ጉድለት ያለባቸው መሆኑን ስለሚያሳይ ውሉ ይፍረስልኝ በማለት ያቀረበው ክርክር የህግ መሰረት ያለው ባለመሆኑ አልተቀበልነውም።
በአጠቃላይ ሲታይ የፍተሐ ብሕር ህጉ እብደቱ በግልጽ ያልተወቀ ሰው ወራሾች ወይም ባለገንዘቦች ይህ ሰው የፈጸመው ውል ጉድለት የልለበት ፈቃድ አልሰጠበትምና ውሉ ላፈርስ ይገባል ሲሉ እብደቱን ምክንያት በማድረግ የውሉን መፍረስ መጠየቅ እንደማይችሉ በፍተሐብሕር ህግ ቁ. 348 ተደንግጓል። ህጉ ይህንን የደነገገው ያለ ምክንያት አይደለም። ባለቤቱ በግልጽ ያልታወቀ የአእምሮ ህመም ምክንያት የእለት በእለት እንቅስቃሴው በራሱ መብትና ጥቅም ላይ ጉዳት የሚያደርስ የህግ ተግባር ላፈጽም የሚችል መሆኑን በቅርበት የሚያውቁት ይህ እብደቱ በግልጽ ያልታወቀው ሰው ወራሾች፣ ወይም አበዳሪዎች፣ እብደቱ በግልጽ ያልታወቀ ሰው /ሴት/ ህጋዊ ተግባራትን የመፈጸም ችሎታው በፍርድ ክልከላ እንዲደረግበት ስልጣን ላለው ፍ/ቤት በማመልከትና በፍርድ በማስከልከል መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚችሉበት እድል በትጋት በመጠቀም፣ እብደቱ በግልጽ ያልታወቀውን ሰው፣ የራሳቸው እና በሶስተኛ ወገኖች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚከላከል ግድታ ጥሎባቸዋል። አመልካች የሟች እናቱ የአእምሮ ህመም በስር ፍ/ቤትና ለዚህ ሰበር ችሎት ባቀረበው ደረጃ የሚያውቅበት ጊዜ፣ የእናቱ ችሎታ በፍርድ ክልከላ እንዲደረግበት መጠየቅና ማስወሰን ሲገባው ይህንን ግድታውን በአግባቡ አልተወጣም።
ተጠሪ ከወ/ሮ ዘውድ በየነ ጋር ቤት ገዥ ውል ሲዋዋል፣ ወ/ሮ ዘውድ በየነ የአእምሮ ህመም ያለባቸው መሆኑን የማያውቅና በቅን ልቦና የሽያጭ ውሉን የተዋዋለ መሆኑን የበታች ፍ/ቤት አረጋግጠዋል። ይህ ከሆነ አመልካች የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስለት ያቀረበው ጥያቄ ከላይ በዝርዝር የገለጽናቸውን የህግ ድንጋጌዎች መሰረት ያላደረገና የህግ ድጋፍ የልለው በመሆኑ፣ የበታች ፍ/ቤቶች አመልካች ያቀረበውን የውል ይፍረስልኝ ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው፣ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት፣ ወስነናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 75175 ህዳር 2 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔና የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ. 142657 ሚያዚያ 9 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ፀንቷል።
በዚህ ፍ/ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2006ዓ.ም የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል። የእግድ ትእዛዙ የተነሳ መሆኑ ለሚመለከተው ክፍል ይጻፍ።
በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ። የማይበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት።
No topics extracted.