አንድ ሰው በወላጅ አባቴ ስም መጠራቴ ቀርቶ በአሳዳጊዬ ስም እንድጠራ ብሎ የሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ በሕጉ ስለስም ለውጥ የተጠቀሱትን ድንጋጌዎች የማያሟላ በመሆኑ ተቀባይነት የልለው ጉዳይ ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ.32(1)፣36(1)
No summary available.
የሰ/መ/ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ/ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ተኽላት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ አመልካች፡- ወ/ሪት ሃና ታምራት ጠበቃ አሰፋ ካሳ ቀረቡ ተጠሪ፡- የለም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ አመልካች ያቀረቡትን አቤቱታ ጉዳዩ በመጀመሪያ ደረጃ የቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍርድ ቤት ውድቅ በማድረጉና በየደረጃው ያሉ የከተማው አስተዳደር የበላይ ፍርድ ቤቶችም የመ/ደ/ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማጽናታቸው ነው።
አመልካች ሐምል 08 ቀን 2007 ዓ/ም ያቀረቡት አቤቱታ ፍሬ ቃሉ፡- ቀድም ሲል ጸሐይ ብርሃኔ እና ሀና ታምራት እየተባልኩ በሁለት ስም ስለምጠራ ጸሐይ ብርሃኔ መባል ቀርቶ ሃና ታምራት ብቻ እየተባልኩ እንድጠራ ውሳኔ ይሰጠኝ በማለት ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ሲሆን የስር ፍርድ ቤትም አመልካች የአቶ ታምራት አመድ ልጅ ለመሆናቸው ከሚመለከተው ፍርድ ቤት የልጅነት ውሳኔ ይዘው ሲቀርቡ መዝገቡ ይቅረብ በማለት መዝገቡን የዘጋው ሲሆን በዚህ ትዕዛዝ አመልካች ይግባኛቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ የሰበር አቤቱታቸው ለከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።
የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም በዚሁ ምክንያት ነው። የአመልካቸ የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ሁለት ስም የነበረኝ በመሆኑ የግል ስሜና የወላጅ አባቴ ስም ተቀይሮ በአንዱ የግል ስም እና በአሳዳጊዬ የቤተዘመድ ስም እንድጠራ ያቀረብኩት አቤቱታ ውድቅ መደረጉ ከሕግ ውጪ ነው የሚል ነው።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን አመልካች በወላጅ አባቴ ስም እንዲጠራ ይወሰንልኝ ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ የሥር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ያደረጉት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
በመርህ ደረጃ አንድ ሰው የቤተዘመድ ስም( family name)፣አንድ ወይም ከዚያ በላይ የግል ስሞች( first names) እና የአባት ስም( patronymic ) እንደሚኖረው በፍ/ህ/ቁ/32(1) የተደነገገ ሲሆን ለልጁ የአባት ስም የሚሆነው ደግሞ የአባቱ የግል ስም እንደሆነ በቁጥር 36 ተመልክቷል።
በመሰረቱ እያንዳንዱ ሰው አንድ የቤተዘመድ ስምና አንድ ወይም ብዙ የግል ስሞች እና የአባት ስም እንደሚኖረው፣እንዲሁም ለልጁ የአባት ስም የሚሆነው የአባቱ የግል ስም እንደሆነ በፍ.ሕ.ቁ.32(1) እና 36(1) ድንጋጌዎች ተመልክቶአል።አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች በአባቱ ብቻ ሳይሆን በአሳዳጊው ስም ጭምር ላጠራ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ሰው ተገቢ ሆኖ ባገኘው ጊዜ በአሳዳጊው ስም ጭምር መጠራቱ ቀሪ ሆኖ ከላይ በተጠቀሰው የፍትሐብሕር ሕጉ ድንጋጌ መሰረት በአባቱ ስም ብቻ እንዲጠራ የመወሰን መብት ያለው በመሆኑ ይህንኑ መብቱን በፍርድ ለማረጋገጥ የሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም የሚባልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም። አመልካች ክሱን ያቀረቡት ከሚጠሩበት ሁለት የግልና የቤተዘመድ ስሞች መካከል ባንዱ እንዲጠሩ ሲጠሩበት ከነበረው የቤተዘበመድ ስሞች መካከል ደግሞ አሁን ለመጠራት የፈለጉት ወላጅ አባቴ በሚሉት ሰው ስም ሳይሆን የአሳዳጊያቸው ስም በመምረጥ መሆኑን ከዳኝነት ጥያቄአቸው ይዘት ለመንገዘብ ችለናል።
ይሁን እንጂ አመልካች በአሳዳጊያቸው ስም እንዲጠሩ በፍርድ ቤት ዳኝነት የሚያገኙበት የሕግ መሰረት የለም። ከግል ሰሞቻቸው መካከል ደግሞ ሃና ተብዬ ልጠራ፣ ፀሐይ መባል ይቅርልኝ ብለው በአማራጭ የጠየቁት የሰበር የዳኝነት ጥያቄ የልለ መሆኑን ተገንዝበናል። በመሆኑም አመልካች ወላጅ አባቴ ናቸው በማይሐቸው ሰው የቤተዘመድ ስም ልጠራ ይገባል በማለት ያቀረቡት ጥያቄ በሕጉ ስለስም ለውጥ ጥያቄ ማቅረብ ስለሚቻልባቸውና የዳኝነት አካሉም ለመቀበል መሟላት ከሚገባቸው ሕጋዊ መስፈርቶች ይዘትና ሕጋዊ ውጤት ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ተቀባይነት ላያገኝ የሚችልበትን አግባብ አላገኘንም። በሰ/መ/ የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የቤተዘመድ ስሙ አሳዳጊ በሆኑ ሰው ሲጠሩ የነበሩት አመልካች በትክክለኛ ስጋ ወላጆቻቸው ስም ለመጠራት ባቀረቡት ጥያቄ የተሰጠ ሲሆን በሰ/መ/ የቀረበው ጉዳይም አመልካች ክሱን ያቀረቡት በሚጠሩበት የአሳዳጊያቸው ስም የተሰጡ ሰነዶችን ወደሚጠሩበት አባታቸው ስም በሕግ አግባብ ለማስቀየር እና እነዚሁ ሰነዶች በሚሰጡት መብት ለመገልገል ጭምር ስለመሆኑ ታይቶ ዳኝነት የተሰጠበት በመሆኑ ከአሁኑ ጉዳይ ጋር በመሰረታዊ የፍሬ ነገርና የሕግ ጥያቄዎች ጋር ተመሳሳይነተ የልለው በመሆኑ ይህ ችሎት በእነዚህ መዛግብት የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) መሰረት ለዚህ ጉዳይ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚችልበት አግባብ የለም።
በመሆኑም በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረቡት ክርክርና የሰበር አጣሪ ችሎት የያዘው ጭብጥ ተቀባይነት የልለው በመሆኑ አልፈነዋል። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/ 117/08 በቀን 13/11/2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ፣ የከተማው ይግባኘ ሰሚ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/23938 በቀን 17/11/2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ እና የከተማው አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/24066 በቀን 6/12/2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ጸንቷል።
አመልካች ወላጅ አባታቸው ባልሁኑት አቶ ታምራት አመድ ስም እንዲጠሩ የጠየቁት የዳኝነት ጥያቄ ስለልጅነታቸው ከሚመለከተው አካል ማስረጃ ሲያቀርቡ የሚታይ ነው ተብሎ ውድቅ በመደረጉ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
መዝገቡን ዘግተን ወደ መዝገብ ቤት መልሰናል።
No topics extracted.