በክስ ማሻሻል ሥርዓትና ዓላማ ቀድሞ ዳኝነት ከተጠየቀበት ጉዳይ ፈጽሞ የተለየ ጥያቄ ለማቅረብ የማይቻል ስለመሆኑ፣ ፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 91 IV ፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 342
No summary available.
ታህሳስ 20 ቀን 2008 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ተኽላት ይመስል እንደሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ አመልካች፡- አቶ ሳምሶን አበራ ጠበቃ ክፍል አማረ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ፀሐይ አበራ ጠበቃ አሸናፊ ወጂ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የተጀመረው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን እንደቅደም ተከተላቸው አመልካች እና ተጠሪ በመሆን ተከራክረዋል። ጉዳዩም ፍቺን ተከትሎ የተነሳ የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ነው። ግራ ቀኙ እያከራከረ ያለው መሰረታዊ ጭብጥም የአሁኑ አመልካች የንብረት ክፍፍል በጠየቀበት ጊዜ ለአሁን ክርክር መነሻ የሆነችውን የሰልዳ ቁጥር 3-15556 መኪና በተመለከተ መኪናው የተፈራችው በጋብቻ ውስጥ ሳይሆን እንደባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ የተፈራች ስለመሆኑ ለማሳየት አመልካች የክስ ማሻሻያ ጥያቄ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ፈቅዶ ክሱ ከተሻሻለ በኃላ ጋብቻ ከመመሰረቱ በፊት ከጥቅምት 1998 እስከ ህዳር 2001 ዓ.ም አብሮው ይኖሩ እንደነበር ግምት ተወስዶ መኪናው የጋራ ንብረት ነች ተብሎ ተወስኗል።
የአሁኑ ተጠሪ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 91 አቤቱታ የሚሻሻልበት ሥርዓትና ዓላማው ዳኝነት ከተጠየቀበት ጉዳይ ፈፅሞ የተለየ ጥያቄ ለማቅረብ እንደማይፈቀድ፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደባልና ሚስት አብረን ኖረን ነበር በዚህ ጊዜ የተፈሩ ንብረቶች እንዲከፈል በሚል ማስረጃዎች ጭምር በመጥቀስ የቀረበው ጥያቄ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.256 ድንጋጌን ያላገናዘበ ስለመሆኑ፤ የፍቺ ውጤት በተጠየቀበት መዝገብ እንደባልና ሚስት አብረው ኑረዋል ወይስ አልኖሩም? የሚለው ጥያቄ በክስ ማሻሻል ምክንያት ተቀብሎ መታየቱ የሥነ-ሥርዓት ሕጉን የተከተለ አይደለም። እንደባልና ሚስት አብረው ሳያቋርጡ ኖረዋል ወይስ አልነበረም? የሚለው ነጥብም ማየት ባያስፈልገውም እንደተመለከተው ከጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም እስከ ነሃሴ 19 /1998 ዓ.ም ድረስ አብረው ቆይተው ከዛ በኃላ ግንኝነታቸው እንደተቋረጠ እንደገና አብረው መኖር የጀመሩት ጋብቻ ከተመሰረተበት ህዳር 2001 ዓ.ም ጀምሮ ስለመሆኑ የአሁን ተጠሪ ምስክሮች የአመልካች ምስክሮች ከሰጡት ቃለ ሚዛን በሚደፋ አግባብ አስረድተዋል። በመሆኑም የሰልዳ ቁጥር 3-15556 የሆነውን መኪና የግለ ንብረት ነው በማለት የሥር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሽሯል። ባንክ ላይ ነበር በተባለው ገንዘብ በተመለከተ ግን የስር ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ በማየት እንዲወስን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.343 /1/ መልሶታል።የአሁኑ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ቅሬታ ቢያቀርቡም በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 መሰረት ሰርዞታል። ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንን ውሳኔና ትዕዛዝ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
ጉዳዩ ለሰበር ይቅረብ በመባሉ ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር ተለዋውጠዋል። የአመልካች ቅሬታ መሰረታዊ ይዘትም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደባልና ሚስት አብረው ይኖሩ እንደነበር የፍቺ ጥያቄ የቀረበበት መዝግቦ ለመግለጽ እንደማይገደዱ፤ በአመለካች የቀረቡ ምስክሮችም በተጠሪ ከቀረቡ ምስክሮች በተሻለ አግባብ ያስረዱ በመሆኑ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደባልና ሚስት በመሆን አብረው ይኖሩ እንደነበር የሕግ ግምት እንዲወሰድላቸው ጠይቋል። ተጠሪ በበኩላቸው ከ1998 እስከ ተጋቡበት 2001 ዓ.ም ያልተቋረጠ ግንኙነት መኖሩን አመልካች አላስረዱም። በግል የተፈራ ንብረት የግል ነው መባሉ በአግባቡ ነው በማለት ተከራክረዋል። የመልስ መልስም ቀርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም ግራ ቀኙ በጽሑፍ ያደረጉት ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነውን ውሳኔ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች እና ጉይዩ ለሰበር ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከሥር የክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ቤት የሰልዳ ቁጥሩ 3-15556 የሆነውን መኪና የአመልካች እና ተጠሪ የጋራ ንብረት ነው በማለት የደረሰበት ድምዳሜ በመሻር መኪናው የተጠሪ የግል ሀብት ነው በማለት ወስነዋል። አመልካች ከሥር ፍ/ቤት አንስቶ አጥብቆ የሚከራከረው የፍቺ ጥያቄ በቀረበበት መዝገብ ላይ እንደባልና ሚስት አብረው ይኖሩ ነበር የሚል ክርክር የማቅረብ ግድታ እንደልላቸው ነው። የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ ማሻሻል ጥያቄው የተለየ ውጤት የሚያመጣ መሆን የለበትም እንዲሁም አመልካችና እና ተጠሪ እንደባልና ሚስት አብረው ስለመኖራቸው አላስረዱም በማለት ውሳኔ መስጠቱ መዝገቡ ያሳያል።
በመሰረቱ አቤቱታ የሚሻሻልበት ዓላማና ማሻሻያው የሚቀርብበት ስርዓት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 91 ሥራ ተመልክቷል። የክስ ማሻሻያ ጥያቄ መሰረታዊ ዓላማም ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ የሚረዳ መሆኑ በፍርድ ቤቱ የታመነ ከሆነ ነው። አመልካች የፍቺ ጥያቄ በቀረበበት መዝገብ ላየ እንደባልና ሚስት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ሲኖሩ ቆይተው በ2001 ዓ.ም ስለመጋባታቸው ያቀረቡት ክርክር የነበረ ስለመሆኑ መዝገቡ አያሳይም። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደባልና ሚስት እንኖር ነበር የሚለው አከራካሪ ጥያቄ የተነሳው የጋራና የግል ንብረት ለመለየት የተደረገው ክርክር ስለመሆኑ የሥር ፍ/ቤት መዝገብ ግልባጭ ያመለክታል።
በሥር የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ፍቺን ተከትሎ የቀረበው የንብረት ክፍፍል ጥያቄ የቀረበው በአመልካች ነው። አመልካች የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ሲያነሱ ለክርክሩ መሰረት የሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮች በዝርዝር መገለጽ ያለባቸው ስለመሆኑ ከፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 222/1/ ድንጋጌ መሰረታዊ ይዘት የምንረዳው የጋራ ንብረት የተፈጠረበት /የተገኘበት/ አግባብ እና ሁኔታ በቀረበው ክስ በግልጽ ማመላከት ይጠበቅ ነበር። አመልካች ለክርክሩ መነሻ የሆነው የሰልዳ ቁጥሩ 3-15556 በክስ ማሻሻያ እንደገለጹት እንደባልና ሚስት ሲኖሩ በነበሩበት ጊዜ ከሆነ መጀመሪያ ክስ ሲያቀርቡ ዳኝነት ያልጠየቁበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። አንድ የመብት ጥያቄ የሚያቀርብ ተከራካሪ ወገን ለክርክሩ መነሻ የሆነ መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 222(1)(2) በሚያዘው አግባብ "ምክንያት የሆኑ ነገሮች እና የተፈጠሩበት ሁኔታ" በግልጽ ዳኝነተ መጠየቅ እየተገባው የፍቺ ውጤት ክርክር ሲደረግ ከጋብቻ ውጭ እንደባልና ሚስት አብረን ኖረናል የሚለው አዲስ የተለየ ክርክር ማቅረብ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 91 ያላገናዘበ ነው የሚለው የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድምዳሜ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
የሥር ፍርድ ቤት የአቤቱታ ማሻሻያ ጥያቄ የቀረበበት አግባብ ብቻ ሲሆን በእርግጥም በአመልካች እና ተጠሪ መካከል ከ1998 ዓ.ም እስከ 2001 ዓ.ም ያልተቋረጠ ግንኙነት ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውን ጭብጥ መርምሮ በፍሬ ነገር ደረጃ ግንኙነት አልነበረም ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዎል። አንድ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በመዝገቡ ላይ በሰፈረው ማስረጃ መሰረት ተገቢ ሁኖ ሲያገኘው ጭብጥን በማሻሻል ወይም በመለወጥ ተገቢ የመሰለውን የመጨረሻ ፍርድ መስጠት የሚችል ስለመሆኑ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 342 ሥር ተደንግጓል። የተያዘው ጉዳይ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመረመረው አቤቱታው የተሻሻለበት አግባብ ብቻ ሳይሆን በእርግጥም አመልካች እና ተጠሪ እንደባልና ሚስት አብረው ኖረዋል ወይስ አልኖሩም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ የግራ ቀኙ ማስረጃ መርምሮ ግንኙነት አልነበረም። መኪናው የግል ሀብት ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የፍሬ ነገር እና የማስረጃ ምዘናና ድምዳሜ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት የሚለወጥበት አግባብ የለም። ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሕግ ተለይቶ የተሰጠው ሥልጣን በማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈጸም ያለመፈፀሙን በማረጋገጥ ፍርድ መሰጡት ስለመሆኑ ከኢ.ፍ.ድ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀጽ 80/3/ /ሀ/ እና አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች መሰረታዊ ይዘት የምንገነዘበው ነው። በነዚህ ሁሉ ምክንያት የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሰልዳ ቁጥሩ 3-15556 በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ በመሻር መኪናው የተጠሪ የግል ንብረት ነው ማለቱና በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መጽናቱ በጉዳዩ መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈፀሙን ስለማያሳይ ተከታዩን ወስነናል።
97972 በ30/07/2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል።
የሰልዳ ቁጥር 3-15556 የተጠሪ የግል ሀብት ነው መባሉ በአግባቡ ነው በማለት ወስነናል።
የዚህ ችሎት ክርክር ያስከተለው ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ።
የተሰጠ የዕግድ ትዕዛዝ ካለ ተነስቷል።
መዝገብ ወደ መ/ቤት ይመለስ።
No topics extracted.