አንድ ተከሳሽ በከሳሽ በመጀመሪያ ክስ ሲቀርብበት መጥሪያ ደርሶት በተከራከረበት እና ከሳሽ ክስ ያሻሽል ተብሎ በተዘጋ መዝገብ ላይ ክሱ ተሻሽሎ መዝገቡ ከተከፈተ በኋላ ለተከሳሽ በተገቢው መንገድ መጥሪያ ሳይደርስ የሚሰጥ ውሳኔ ስነ- ስርዓታዊ ስላለመሆኑ፣ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. አንቀጽ 94-110
No summary available.
ቀን 19/4/2008 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ ፈይሳ ወርቁ አመልካች፡-
በዚህ የሰበር አቤቱታ መዝገብ ክርክር አመልካች 1.አቶ ታከለ አረአያ 2.አቶ አብረሃ ተክሉ በቀን 23/3/2007 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 05504 አከራክሮ በቀን 11/2/2007 ዓ.ም የሰጠውን ፍርድ በመቃወም የቀረበ ነው። ቅሬታቸውም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት መጀመሪያ የቀረበው ክስ መጥሪያ ደርሶን ከቀረብን በኃላ በፍ/ቤቱ ክሱ እንዲሻሻል ታዞ መዝገቡን ዘግቶታል።
ክሱ ተሻሽሎ መዝገቡ ሲንቀሳቀስ ግን የአሁን ተጠሪ (ከሳሽ) አድራሻችንን እያወቀ የሁመራ ቤት ሲታገድ መጥሪያ ላሰጠን ሲችል በቤታችን ላይ መለጠፍ ሲቻል ፍ/ቤት ግቢ ውስጥ መጥሪያውን በመለጠፍና በጋዜጣ ጥሪ ማስደረጉ ሆን ብሎና ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ሲቻል የስር ፍ/ቤት በልለንበት የተሰጠው ውሳኔ ይነሳልን ብለን ያቀረብነውን ማመልከቻ ውድቅ ማድረጉ ስህተት በመሆኑ ይታረምል የሚል ነው። መዝገቡ ተመርምሮ አመልካቾች መጀመሪያ ክስ ሲቀርብባቸው ቀርበው መልስ የሰጡ ሲሆን በልሉበት ይታይ የሚል ትዕዛዝ የተሰጠው ተጠሪ ክስ አሻሽሉ ተብለው መዝገቡ ከተዘጋባቸው በኃላ ባቀረቡት የተሻሻለ ክስ ጊዜ አመልካቾች ከአካባቢው አልተገኙም ተብለው በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ እና በጋዜጣ ተጠርተው አልቀረቡም በማለት ክርክሩ በልሉበት ተካሂዶ ውሳኔ የተሰጠውና አመልካቾች ይህንኑ ገልፀው ሲያመለክቱ ማመልከቻቸውን ውድቅ ማድረጉ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አን. 94-110 ጋር ለመመርመር ሲባል ቀርቧል። መልስና የመልስ መልስም ተሰጥቶበታል።
ተጠሪ በቀን 25/7/2007 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካቾች በአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁ.37304 የተወሰነልኝን ውሳኔ በመ.ቁ.08505 የአፈፃፀም መዝገብ ከፍቼ መጥሪያ ላለመቀበል ከተሰወሩ በኃላ ንብረታቸው ከታገደ ከ2 ወር በኃላ ቀርበው ገንዘቡን ገቢ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ በልለንበት የተወሰነ ውሳኔ ነው በማለት በአፈፃፀም መዝገብ ላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አን. 78 መሰረት አመልክተዋል እኔም ይህንኑ አንስቼ ተከራክሬያለሁ። መጀመሪያ መዝገቡ ክስ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ፍ/ቤቱ አዞ መዝገቡን ዘጋው ይበሉ እንጅ የተዘጋ መዝገብ የለም። አመልካቾች በሚኖሩበት ሁሉ ፈልጌ በማጣቴ ለፍ/ቤቱ አመልክቼ መጥሪያው ተለጥፏል በጋዜጣም ጥሪ ተደርጓል። ስለዚህ አቤቱታቸው ውድቅ ይሁንልን ብለው ተከራክረዋል። አመልካችም በቀን 16/8/2007 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል።
በዚሁ መሰረት መዝገቡን እንደመረመርነው ክርክሩ የጀመረው ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት አሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት ሲሆን አመልካች (የከፍ/ፍ/ቤት ተከሣሾች) ለአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ከሳሽ አቶ ደጀን ገ/እግዛብሄር በተከሳሾች (የአሁን አመልካቾች) ላይ በቀን 7/3/2005 ዓ.ም በተፃፈ ክስ አቅርቦብን እኛም ቀርበን ክርክር ከተጀመረ በኃላ ፍ/ቤቱ ከሳሽ ክስህን አሻሽል ተብሎ መዝገቡ ተዘጋ ከዚህ በኃላ መዝገቡ ሲንቀሳቀስ እኛ ያልሰማንና ከሳሽ የኛን አድራሻ እያወቀ ሆን ብሎ ላገኛቸው አልቻልኩም በማለት በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በመለጠፍና በጋዜጣ ጥሪ በማስደረግ ሲሆን ባለመስማታችን በልለንበት ውሳኔ ተሰጥቷል።
በልለንበት መወሰኑን የሰማነው በቀን 6/8/2006 ዓ.ም በመሆኑና እንደሰማንም ቀርበን ያመለከትን ስለሆነ በልለንበት የተሰጠው ውሳኔ እንድነሣልን በማለት አመልክተዋል። የአሁኑ ተጠሪም (የከፍ/ፍ/ቤት ከሳሽ) የሰጠው መልስ የተከሳሾች ማመልከቻ የቀረበው ለፍርድ ቤቱ በመሆኑ እኔ መልስ እንድሰጥ አይጠበቅብኝም። ፍ/ቤቱ ከሳሽ ክሱን ያሻሽል ብሎ መዝገቡን ቢዘጋም በተለዋጭ ቀጠሮ ክሱ ተሻሽሎ የሚቀርብ እንጂ መዝገብ እንድዘጋ የሚያዝ ሥነ ሥርዓትም የለም።
ተከሳሾቹ መጥሪያ እንዳይደርሳቸው ሆን ብለው ከአካባቢው በመሰወራቸው ተፈልገው በአድራሻቸው ስላልተገኙ መጥሪያውን ላያዩት በሚችሉበት ቦታ ተለጥፏል ስለዚህ ማመልከቻቸው ውድቅ ይሁንልኝ ብሐል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት በመ. በቀን 21/9/2006 ዓ.ም በቀረበው ማመልከቻ ላይ የሰጠው ብይን ተከሳሾች ያቀረቡት ማመልከቻ ክርክሩ ተጀምሮ ክሱ እንዲሻሻል ከተደረገ በኃላ ከአካባቢው ቢሰወሩም ይኖራሉ በሚባልበት ቦታና ህዝብ በሚሰበስብበት ቦታ ሁሉ በፍ/ቤት አጥር ግቢ እና በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው አልቀረቡም ተከሣሾች (አመልካቾች) ክሱ እንዲሻሻል የታዘዘ ቢሆንም በቀጣዩ የሚቀጥል ጉዳይ መሆኑን አያውቅም ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ ያቀረቡት ምክንያት በቂ አይደለም በማለት ማመልከታቸውን አልተቀበልነውም ሲል መዝገቡን ዘግቷል። የአሁን አመልካቾች ለቤንሻንጉል ጉሙዝ ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ. በቀን 10/10/2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አን. 337 መሰረት የሚያስቀርብ ሆኖ አልተገኘም ሲል መዝገቡን ዘግቶታል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በመ.ቁ. 05504 አከራክሮ በቀን 11/2/2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ አመልካቾች የተሻሻለው ክስ ከመጥሪያ ጋር እንዲደርሳቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ታዞ ከአካባቢው በመሰወራቸው ልሎች የመጥሪያ አደራረስ ምርጫዎችን በመጠቀም አመልካቾች ላመለከቱት ይችላሉ በተባሉ ግልፅ ቦታዎች እና በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ በመለጠፍና በጋዜጣ ቢጠሩም ስላልቀረቡ በልሉበት መወሰኑ እና የስር ፍ/ቤት ማመልከቻቸውን በዚህ ሁኔታ ውድቅ ማድረጉ ስህተት ያለበት ሆኖ አላገኘነውም በማለት የስር ፍ/ቤትን ትዕዛዝና ብይን በማፅናት ወስኗል።
የአሁኑ አመልካቾች ይህንን ውሳኔ በመቃወም ቀርበዋል።
በዚህ ሰበር ችሎት የተያዘው ጭብጥ አመልካቾች በመጀመሪያ ክስ ሲቀርብባቸው መጥሪያ ደርሷቸው ቀርበው ተከራክረዋል። የአሁን ተጠሪ ክስ ያሻሽል ተብሎ መዝገቡ ተዘግቷል። ክሱ ተሻሽሎ መዝገቡ ከተከፈተ በኃላ አመልካቾች በአካባቢው አልተገኙም በማለት መጥሪያ በፍ/ቤት ግቢ በመለጠፍና በጋዜጣ ጥሪ በማድረግ አልቀረቡም በማለት በልሉበት የተወሰነው ተጠሪና አመልካቾች ጎን ለጎን በእርሻ እንቨስትመንት የተሰማሩ መሆኑ እየታወቀ በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ መለጠፉና በጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው እየታወቀ በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ መለጠፉና በጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው መሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አን 94-110 ካለው የመጥሪያ አሰጣጥ ድንጋጌና ከመጥሪያ አሰጣጥ አላማ ጋር ለመመርመር ነው። በተያዘው ጭብጥ መሰረት አመልካቾች መጀመሪያ በአሁን ተጠሪ ክስ ሲቀርብባቸው መጥሪያ አድርሷቸው ቀርበዋል። የሥር ፍ/ቤት ተጠሪ (የሥር ፍ/ቤት ከሣሽ) ክሱን ያሻሽል ብሎ መዝገቡን ዘግቶታል። ክሱ ተሻሽሎ መዝገቡ ሲከፈት ለአመልካቾች መጥሪያ ላደርሣቸው ይገባል። የስር ፍ/ቤት የአመልካቾች አቤቱታ መጥሪያ ሣይደርሰን በልለንበት የተሰጠው ውሳኔ ይነሣልን ጥያቄ ውድቅ ያደረገበት ምክንያት አመልካቾች መጥሪያ እንዳይደርሳቸው ተሸሽገዋል በሚልና መዝገቡ ተዘግቶ በሚቀጥለው ቀጠሮ ክርክሩ እንዲቀጥል ማወቅ ይችላሉ ሲል ነው። የሥር ፍ/ቤት ተከሣሾች (የአሁን አመልካቾች) በሚቀጥለው ቀጠሮ ክርክሩ ይቀጥላል ለማለት የሚችሉት መዝገቡ ባይዘጋና ቀጠሮ ቢሰጥ እንጂ
አመልካቾች መጀመሪያ መጥሪያ ደርሷቸው ቀርበው እያለ መጥሪያ እንዳይደርሳቸው የተሸሸጉ ወይም መሰናክል ያደረጉ መሆኑን የሥር ፍ/ቤት ተረድቻለሁ የሚለው ተጠሪ ከገለፀላቸው ውጪ በልላ መንገድ የተረጋገጠ ስለመሆኑ የተገለፀው ነገር የለም። አመልካቾች ከተጠሪ ጋር ጎን ለጎን የእርሻ ኢንቨስትመንት ሥራ ይሰራሉ በዚህ የሥራ ቦታቸው መጥሪያ እንዲደርሳቸው የተደረገ መሆኑ ወይም የተለጠፈ መሆኑ የተገለፀ ነገር የለም። የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ.አንቀጽ 100 ይገልፃል።
በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 105 በተደነገገው መሰረት በመኖሪያ ቤታቸው ወይም በመጨረሻ ጊዜ ይኖሩበት በነበረ ሥፍራ መጥሪያ የተለጠፈ መሆኑ የተገለፀ የለም። ይህ በቅድሚያ የሚወሰድ የመጥሪያ አደራረስ ዘድ እያለ የሥር ፍ/ቤት የመጨረሻ አማራጭ በጋዜጣ ጥሪ መጥሪያ ማድረግ ዘድ ተጠቅሞ እና ተከሳሾች (የአሁን አመልካቾች) መጥሪያ ሣይደርሰን ሳንሰማ በልለንበት የተሰጠ ውሳኔ ይነሳልን አቤቱታ ውድቅ ማድረጉ ተገቢ ሆኖ አልታየንም። በመሆኑም አመልካቾች ተዘግቶ የነበረው መዝገብ ተከፍቶ ክርክር የጀመረ መሆኑን ባልሰሙበት የሥር ፍ/ቤት የመጥሪያ አስፈላጊነት ተከራካሪዎች ቀርበው እንዲከራከሩ ያላቸውን ህጋዊ መብት ለማክበር ፍ/ቤቱም እውነቱን እንዲደርስበት ለማስቻል በመሆኑ መጥሪያ ለአመልካቾች ሲያደርሳቸው በቅድሚያ ላጠቀም የሚገባውን የመጥሪያ አደራረስ መንገድ በመተው የመጨረሻ አማራጭ በጋዜጣ ጥሪ በመጠቀሙና አመልካቾች ይህንኑ ገልፀው መጥሪያውን ያልሰሙና በልለንበት የተሰጠው ውሳኔ ይንሣልን ብለው ሲያመለክቱ ውድቅ ማድረጉ መሰረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት ነው ብለናል።
05504 ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አንቀጽ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የአሁን አመልካቾች ክስ እንዲሻሻል ተብሎ የተዘጋ መ. ተከፍቶ ክርክር የጀመሩ መሆኑን ሳያውቁ መጥሪያ በአግባቡ ሳይደርሳቸው የተሰጠ ውሳኔ እንዲነሳላቸው ያቀረቡት ምክንያት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አንቀጽ 78(2) መሰረት ውሳኔውን ለማንሳት በቂ በመሆኑ በመ. የተሰጠው ውሳኔ ተነስቷል የቤ/ጉ/ክ/መ/የአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት የተሻሻለውን ክስ ለአመልካቾች አድርሶ ካከራከረ በኃላ ውሳኔ እንዲሰጥበት መልሰናል።
በዚህ መዝገብ ወጪና ኪሣራ ተቻቻሉ ብለናል።
በ17/6/2007 ዓ.ም የተሰጠ እግድ ተነስቷል። ይፃፍ።
መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መ/ቤት ተመልሷል።የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት።
No topics extracted.