በውጭ ሃገር ስለሚኖር የስራ ውል የግል አገልግሎት(በውጭ ሃገር ለተሰጠው አገልግሎት) ተፈፃሚ ላሆን የሚገባው ህግ ስለስራና ሰራተኛ ማገናኘት አገልግሎት የወጣ አዋጅ 632/2001 ስለመሆኑ በዚህ አይነት የውል ግንኙነት ውስጥ የሚቀርብ የክፍያ ጥያቄ በአስር አመት ይርጋ የሚታገድ ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ. 1677(1) እና 1845
No summary available.
ጥቅምት 24 ቀን 2008 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ተኽላት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ አመልካች፡- ወ/ሮ መስከረም ሞጋ ጠበቃ መስፍን ጌታቸው ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ትዕግስት አረጋ የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩን ፍርድ ተሰጥቷል።
የስራ ውል መነሻ ያደረገ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኗ ተጠሪ በአሁኗ አመልካች በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሰረቱት ክስ መሰረት በማድረግ ነው። አመልካች በየደረጃው ጉዳዩን የተመለከቱት ፍ/ቤቶች መሰረታዊ የሕግ ስህተት የፈፀሙ በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ የሚል አቤቱታ በማቅረባቸው አጣርቶ ለመወሰን የቀረበ ጉዳይ ነው። በአሁኗ ተጠሪ የቀረበው ክስ ይዘት ባጭሩ፡- በፈረንሳይ ሀገር በአመልካች መኖሪያ ቤት ውስጥ በየወሩ 1200 /አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዩሮ/ ደመወዝ እየተከፈላቸው በሞግዚትነት እንዲሰሩ በ19/02/2001 ዓ.ም በተፃፈ ውል በአዲስ አበባ ከተማ ጉለል ክፍለ ከተማ ቀበል 09 በሚገኘው በአመልካች ወላጆች ቤት ውስጥ ተፈራርመው ከመጋቢት 02/2001 ዓ.ም እስከ መጋቢት 08/2002 ዓ.ም ድረስ ለአንድ አመት ሲሰሩ እንደቆዩ፣ የስራ ውሉም አመልካች ፈረንሳይ አገርን ለሁል ጊዜ ሲለቁ የሚቋረጥ ስለመሆኑ፣ አመልካች የተጠሪ ደመወዝ ሳይከፈሉ እንዳሰናበቷቸው የዓመት ረፍት ጊዜም አምስት ሳምንት ላሰጣቸው እንደሚገባ በውሉ የተመለከተ ቢሆንም እንዳልተሰጣቸው፣ አመልካች ደመወዛቸውን እንዲከፍሉዋቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በኩል፣ በሽምግልና ጥረት ቢያደርጉም ላከፈላቸው እንዳልቻለ፣ 1200 ዩሮ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ሲመነዘር 20.80 /ሀያ ሺህ ከሰማንያ ሳንቲም/ በመሆኑ፣ ደመወዝ 299‚520.00 የአምስት ሳምነት የእረፍት ጊዜ 29‚120.00 በድምሩ 328‚640.00 /ሶስት መቶ ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ አርባ ብር/ እና ክስ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ገንዘብ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ 9% ወለድ ጋር እንዲከፈላቸው፣ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
አመልካች የበኩላቸውን መልስ ያቀረቡ ሲሆን ዋና ፍሬ ነገሩ፡- የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና በፍሬ ነገሩ በሰጡት መልስ ክሱ በፍ/መ/ደ/ፍ/ቤት ቀርቦ የተዘጋ ስለመሆኑ፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን እንደልለው፣ የተጠሪ የደመወዝ ጥያቄ በይርጋ የሚታገድ መሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ በፍሬ ጉዳዩም ተጠሪ ያልተከፈላቸው ደመወዝ አለመኖሩን፤ ደመወዝ ካልተከፈላቸው ውሉ ለመዘገበዉ የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀረቡ እንደነበር፣ በመግለፅ መከራከራቸውን የሚያመለክት ነው።
የሥር ፍርድ ቤትም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ በ18/06/2006 ዓ.ም ብይን የሰጠ ሲሆን ጉዳዩን ተመልክቶ የመወሰን የሥረ ነገር ስልጣን እንዳለው በመጥቀስ የአመልካች መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል። የሥር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር እና የቀረቡ ምስክሮች የሰጡት ቃል ከመረመረ በኋላ በግራ ቀኙ የተፈረመው የስራ ቅጥር ውል መኖሩን ተቀብሎ የተጠሪ የወር ደመወዝ 1200 ዩሮ እንደነበር በአመልካች ከቀረበው ማስረጃ ፍ/ቤት የተቀበለው የክፍያ መጠን በድምሩ 6‚408 ብር ብቻ እንደሆነ፤ ተጠሪ የሚገባቸው ቀሪ ክፍያ ብር 293‚112.00 መሆኑን፤ የአምስት ሳምንት የእረፍት ክፍያ በድምር ብር 29‚120.00 እንደሆነ በአጠቃላይ አመልካች ለተጠሪ ብር 322‚232.00 /ሶስት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ ሁለት ብር/ እንዲከፈሉ በማለት ወስኗል። አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ቅሬታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም። ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንን በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ቀርቦ እንዲመረመር በመደረጉ ተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ግራ ቀኙ የፅሁፍ ክርክር አድርጓአል። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የተጠሪ የክፍያ ጥያቄ በፍ/ሕ/ቁ.2601 እና 2023/ሀ/ መሰረት በይርጋ የሚታገድ ነው፤ ጉዳዩ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የሚዳኝ አይደለም፤ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች መቅረብ ከነበረበትም በሥራ ክርክር ችሎት መቅረብ ነበረበት የሚል ይዘት ያለው ነው። ተጠሪ በበኩላቸው ክሱን በወቅቱ ማቅረባቸው እና በይርጋ የሚታገድበት ሕጋዊ ምክንያት የልለ ስለመሆኑ ዝርዝር ክርክር አቅርበዋል። አመልካች ያቀረቡት የመልስ መልስም የሰበር አቤቱታውን የሚደግፍ ነው።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙ የፅሁፍ ክርክር፤ ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ውሳኔ አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመርነውም የዚህ ችሎት ምላሽ የሚያስፈልጋቸው መሰረታዊ ነጥቦች፡-
ግራ ቀኙ በሚከራከሩበት ጉዳይ አግባብነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ የትኛው ነው?
የደመወዝ ክፍያ ግምት በተመለከተ የተነሳው የይርጋ ክርክር ተፈፃሚነት ያለው የይርጋ ድንጋጌ በአጣሪ ችሎቱ የተጠቀሰው የፍ/ሕ/ቁ.2023/ሀ/ ነው ወይስ አይደለም?
አመልካች ለተጠሪ ላከፍሐቸው የሚገባ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? የሚሉት ናቸው።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች እና ተጠሪ የሥራ ውል ግንኙነት እንደነበራቸው፤
ውሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈርሞ በፈረንሳይ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተመዘገበ የተካደ ጉዳይ አይደለም። አመልካች ከተጠሪ ጋር የስራ ውል ግንኙነት እንደነበራቸው ሳይክዱ ሁሉም ክፍያዎች በወቅቱ እንደተከፈሉ፣ አልተከፈለም የሚባል ገንዘብ ካለም በይርጋ እንደሚታገድ ተከራክሯል። ተጠሪ በበኩላቸው በአመልካች ቤት በሞግዚትነት ለአንድ አመት ማገልገላቸው እና የጠየቁት ክፍያ እንዳልተፈፀመላቸው እንዲሁም ክሱን በወቅቱ ስለማቅረባቸው በስር ፍርድ ቤት ካቀረቡት ክርክር መረዳት ይቻላል። ይህ ችሎትም ግራ ቀኙ እያከራከረ ያለው መሰረታዊ ጭብጥ እንደሚከተለው መርመሮታል።
የመጀመሪያው ጭብጥ በተመለከተ፡- አመልካች የተጠሪ የስራ ቅጥር ውል ከፍ/ሕ/ቁ.
2601 አንፃር እንዲታይ በሰበር አቤቱታቸው አመልክቷል። የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ ይዘት በቤተሰብ አስተዳደር ውስጥ ስለሚኖር አሽከር የስራ ውል፤ ሰራተኛውን የሚኖሩት መብትና ግድታዎች የሚመለከት ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል። ይህ ድንጋጌ ያለው የተፈፃሚነት ወሰን ሲታይ በአገር ውስጥ በሚቀጠሩ ሰራተኞች ስለመሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ ነው። በተያዘው ጉዳይ የአመልካች እና ተጠሪ የስራ ውል በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈፅሞ በፈረንሳይ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፀድቆ አመልካች እና ተጠሪም በፈረንሳይ አገር ሲኖሩ እንደነበር ባለተካደበት ሁኔታ ከላይ የተመለከተው ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለው ሁኖ አልተገኘም። በልላ በኩል ስለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ የወጣው አዋጅ ቁጥር 377/96 እና የዚህ አዋጅ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/1998 ዓላማና ግብ በሀገር ውስጥ ስለሚኖረው የስራ ስምሪት የተዋዋይ ወገኖች መብትና ግድታ፤ ላሟሉ የሚገባቸው አነስተኛ መመዘኛዎች ማለትም የስራ ሰዓት፤ የእረፍት ጊዜ፣ የሕመም ፈቃድ ወዘተ ያካተቱ ሕግ እንጂ በውጭ አገር ተቀጠረው ስራ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች የሚያነሱት የመብት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም አመልካች እና ተጠሪ በሚከራከሩበት ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለው ሕግ /Governing Law/ በሀገር ውስጥ ባለው የስራ ስምሪት የግራ ቀኙ አንፃራዊ መብትና ግድታ የሚደነግጉ የፍ/ሕ/ቁ.2601 እና የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ የሚመለከት አዋጅ 377/96 አለመሆኑን ተረድተናል። ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ ስለስራና ሰራተኛ ማገናኘት አገልግሎት የወጣ አዋጅ ቁጥር 632/2001 ነው። የዚህ አዋጅ መግቢያ፤ የተፈፃሚነት ወሰን የሚመለከት አንቀፅ 3/2/ “የግል አገልግሎት ስራ ላይ ለመቀጠር ወደ ውጭ አገር በሚሄዱ ኢትዮጵያ ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል” በማለት ደንግጓአል። በተያዘው ጉዳይ የአመልካች እና ተጠሪ የስራ ውል የግል አገልግሎት /personal service/ ስራ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ በስር ፍርድ ቤት ከተደረገው ክርክር መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ አዋጅ ቁጥር 632/2001 ነው ብለናል።
ሁለተኛ ጭብጥ በተመለከተ፡- ግራ ቀኙ እያከራከረ ያለው መሰረታዊ ነጥብ አንዱ ይርጋን የተመለከተ ነው። አመልካች የተጠሪ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ በ6 ወር የሚታገድ ነው በማለት ተከራክረዋል። በዚህ ችሎት እንዲመረመር የተያዘው ጭብጥም የይርጋ ጥያቄው ከፍ/ሕ/ቁ.2023/ሀ/ አንፃር እንዲታይ ነው። ይህ ድንጋጌ ከፍ/ሕ/ቁ.2601 በማጣመር ስንመለከተው በሀገር ውስጥ በቤት አገልጋይነት የተቀጠሩ አሽከሮች በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ክፍያ ካልተጠየቁ እንደተከፈለ የሕግ ግምት ይወሰዳል የሚል ይዘት ያለው ስለመሆኑ ተመልክተናል። በተያዘው ጉዳይ የፍ/ሕ/ቁ. 2601 ይሁን የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 በሀገር ውስጥ የስራ ስምሪት ላይ በሚነሱ ክርክሮች እንደነገሩ ሁኔታ ተፈፃሚ ከሚሆኑ በስተቀር በውጭ አገር ለተሰጠው አገልግሎት እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የክፍያ ክርክር አግባብነት ያላቸው የሕግ ማዕቀፎች ባለመሆናቸው አመልካች የተጠሪ የመብት ጥያቄ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ የሚታገድ ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሰረት የለውም ብለናል።
አዋጅ ቁጥር 632/2001 አንቀፅ 3/1/ የአዋጁን የተፈፃሚነት ወሰን አንቀፅ 20 ስለ ሰራተኛው መብት፣ አንቀፅ 24 ስለ አነስተኛ ደመወዝ መጠን የሚመለከቱ መሰረታዊ ድንጋጌዎች ያካተተ ቢሆንም በአሰሪና ሰራተኛው የሚነሳው የክፍያ ጥያቄ በተለይም የመብት ጥያቄ ለማቅረብ ተፈፃሚነት ያለው የይርጋ ድንጋጌ በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም። እንዲህ ከሆነ ደግሞ አመልካች እና ተጠሪ እያከራከረ ያለው የይርጋ ጉዳይ መታየት ያለበት ከአጠቃላይ የውል ድንጋጌዎች አንፃር ስለመሆኑ ተቀባይነት ያለው የሕግ አተረጓጎም ስርዓት ነው። የፍ/ሕ/ቁ.
1677/1/ “ግድታዎቹ ከውል የተገኙ ባይሆኑም የዚህ አንቀፅ ደንቦች ይፈፀሙባቸዋል” በማለት የደነገገ ሲሆን የዚህ ድንጋጌ ተዛማጅ የሆነው የእንግላዘኛው ትርጉም” 1677/1/ the relevant provisions of this title shall apply to obligations not withstanding that they do not arise out of a contract” በማለት የተደነገገ መሆኑን ተረድተናል። በተያዘው ጉዳይ አመልካች እና ተጠሪ እያከራከረ ያለው የክፍያ ጥያቄ ክርክር ተፈፃሚነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ ከፍ/ሕ/ቁ.
1677/1/ እና 1845 አንፃር መታየት ያለበት ነው። የአመልካች እና ተጠሪ የስራ ውል ግንኙት መሰረት በማድረግ የሚነሳው ክርክር በ1ዐ ዓመት ይርጋ ቀሪ የሚሆን ነው። ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ በአመልካች እና ተጠሪ መካከል የነበረው የውል ግንኙነት የተቋረጠው መጋቢት 2002 ዓ.ም በመሆኑ ክሱ እስከቀረበበት መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም ያለው ጊዜ ሲታይ በፍ/ሕ/ቁ.
1845 የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ሳይጠናቀቅ ክስ መቅረቡን የሚያሳይ ነው። በመሆኑም አመልካች የማያነሱት የይርጋ ጥያቄ ተፈፃሚነት ካለው የይርጋ ድንጋጌ አንፃር ሲታይ ተቀባይነት ያለው ሁኖ አልተገኘም። ስለሆነም የተጠሪ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ በይርጋ የሚታገድ አይደለም ብለናል።
የመጨረሻው ጭብጥ በተመለከተ፡- የስር ፍርድ ቤት ተጠሪ በወር 1200 ዩሮ እየተከፈላቸው ይሰሩ እንደነበር አረጋግጧል። አመልካች ክፍያ መፈፀማቸው ቢከራከሩም የሥር ፍ/ቤት በማስረጃ የተደገፈ ነው በማለት የተቀበለው ክፍያ 6‚408 ብር ብቻ መሆኑ ከውሳኔው ግልባጭ መረዳት ተችሐል። ተጠሪ ያልተከፈላቸው አጠቃላይ ደመወዝና የዓምስት ሳምንት የእረፍት ጊዜ ክፍያ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ሲመነዘር /6‚408 ተቀንሶ/ 322‚232.00 መሆኑን በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተመልክቷል። የሥር ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ መዝኖ አመልካች ለተጠሪ ብር 322‚232.00 ይክፈሉ በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍልም የሚነቀፍ ሆኖ አልተገኘም። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የስር ከፍተኛ እና የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች በውጤት ፈርጆ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመባቸው መሆኑ የሚያሳይ ነገር ያልተገኘ በመሆኑ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ ግንቦት 6/2006 የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል።
አመልካች እና ተጠሪ የሚከራከሩበት የይርጋ ጊዜ የሚገዛው በፍ/ሕ/ቁ 1677/1/ እና 1845 ነው ብለናል። በዚህ መሰረት የተጠሪ የመብት ጥያቄ በይርጋ ቀሪ አልሆነም በማለት ወስነናል።
አመልካች ለተጠሪ ብር 322‚232.00 /ሶስት መቶ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ ሁለት/ ከ13/07/2003 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ 9% ወለድ እንዲከፍሉ መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል።
በዚህ ፍ/ቤት ክርክር ያወጡት ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ።
ይፃፍ።
No topics extracted.