No summary available.
የሰ/መ/ቁ. 972ዐ6 ሐምል 28 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል አላ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመስል አመልካች፡- አቶ አማረ መልካሙ ራሳቸው ቀረቡ በVC ከመቐለ ተጠሪ፡- አቶ ካልብ ሕሉፍ የቀረበ የለም መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
በዚህ መዝገብ በሰበር ችሎቱ ላወሰን ይገባል ተብሎ የተያዘው ጭብጥ አመልካች የተጠሪ ንብረት የሆነውን በትግራይ ክልል ኮንስትራክሽንና መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ካላቸው ገንዘብ 612,2005.57 ብር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ.ቁ 154/ለ/ መሰረት ማሳገዳቸው ከልሎች የፍርድ ባለገንዘቦች የቀደምትነት መብት ያረጋግጥላቸዋል ወይ የሚለው ነው። አመልካች በተጠሪ ላይ የመሰረቱት ክስ ተከትሎ የፍርድ ባለገንዘብ መሆናቸውን ተረጋግጧል። በአመልካች ጠያቂነት ከላይ በተጠቀሰው ቢሮ የነበረው ገንዘብም አሳግዷል። አመልካች ገንዘቡን ካሳገዱ በኋላ አሥራ ሰባት የፍርድ ባለገንዘቦች ከተወሰነ ቀን በኋላ በተመሳሳይ መንገድ የተጠሪ ገንዘብ ላይ ዕግድ እንዲሰጥ አመልክተው በፍርድ ቤት ተቀባይነት አግኝቷል። አመልካች በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ. ባቀረቡት ክስ ያሳገዱትን ገንዘብ በቅድሚያ ለእሳቸው እንዲከፈል ጠይቋል። የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ለክርክር መነሻ የሆነውን ሀብት ገንዘብ መሆኑን መሰረት በማድረግ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታገደው ገንዘብ ከመሆኑ አኳያ እንደማይንቀሳቀስ ንብረት የማይወሰድ ነው። በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታገደው ገንዘብ ለፍርድ ባለገንዘቦች ባስፈረዱት መጠን በሬሽዎ እንዲከፋፈል በማለት ብይን ሰጥቷል።
አመልካች የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ቢሆንም የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በማጽናት ወስኗል።
አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ተፈጽሟል ያሉትን የሕግ አተረጓጐም ስሕተት በመዘርዘር የሰበር አቤቱታቸውን በ26-05-2006 ዓ.ም አቅርበዋል። የአቤቱታው መሰረታዊ ይዘት የፍርድ ባለዕዳ ገንዘብ ከልሎች የፍርድ ባለገንዘቦች ቀድመው ማሳገዳቸውን መሰረት ተደርጐ የቀደምትነት መብት እንዲከበርላቸው፤ የቀደምትነት መብት በማይንቀሳቀስ ንብረት ብቻ ሳይሆን በሚንቀሳቀስ ንብረትም ማቋቋም እንደሚቻል፤ የሥር ፍርድ ቤቶችም ክፍያ ማስፈጸም ያለባቸው የፍርድ ባለገንዘቦች ገንዘቡን ባስከበሩበት ቅደም ተከተል ላሆን እንደሚገባ በመጥቀስ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲታረም ጠይቋል። ተጠሪ የአመልካች አቤቱታ ከመጥሪያ ጋር የተላከላቸው ቢሆንም በአድራሻቸው ስላልተገኙ በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ በሚለጠፍ መጥሪያ መሰረት እንዲቀርቡ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ባለ መቅረባቸው በጽሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው የጽሑፍ ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ጉዳዩን ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች እና ጉዳዩን ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
ከመዝገቡ እንደሚታየው አመልካች በፍርድ ባለዕዳ ገንዘብ ላይ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማስከበራቸው የቀደምትነት መብት እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም በሥር ፍርድ ቤት ተቀባይነት አላገኘም። ከላይ እንደተገለጸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተከበረው ነገር ገንዘብ ነው። የፍርድ ባለገንዘብ በፍርድ ባለዕዳ ንብረት ላይ የቀደምትነት መብት በሕግ፣ በውል እና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ላያቋቁም ይችላል። ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር በተያያዘ የቀደምትነት መብት በጋራ የንብረት ባለሀብቶች፤ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደውሳኔውን ለማስፈጸም እንዲሁም ግራቀኙ ባደረጉት ስምምነት ላቋቋም እንደሚችል ከፍ.ሕ.ቁ. 3043፣3044 እና 3045 ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በልላ በኩል በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የቀደምትነት መብት ላቋቋም የሚችለው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2825 በሚያዘው አግባብ የፍርድ ባለዕዳው ንብረቱን ለፍርድ ባለገንዘብ ማስረከቡ ሲረጋገጥ መሆኑን ከሕጉ ንባብ የምንገነዘበው ነው። አመልካች የቀደምትነት መብት እንዲሰጣቸው መሰረት ያደረጉት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 154/ለ/ ነው። የዚህ ሕግ አንቀጽ መሰረታዊ ይዘትና ዓላማ ስንመለከተው በክርክር ላይ ባሉ ጉዳዮች የፍርድ ባለገንዘብ በመጨረሻ የረታ ከሆነ ፍርዱን ለማስፈጸም የሚያስችል ንብረት ወይም ገንዘብ እንዳይታጣ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ነው። ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 154 ርዕስ እንደምንረዳው የማገድ ትዕዛዙ የሚሰጠው ለጊዜው ስለመሆኑ፤ በፍርድ ባለዕዳ ሥር ያለው ንብረት በየትኛው መልኩ ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ፤እንዳይበላሽ፤እንዳይጠፋ ፍርድ እስከሚሰጥ ተከብሮ እንዲቆይ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው። አመልካች ከላይ በተገለጸው አግባብ የፍርድ ባለዕዳ ንብረት ማሳገዳቸው በማይንቀሳቀስና በሚንቀሳቀስ ንብረት የቀደምትነት መብት ማቋቋም በሚያስችል አግባብ ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ መብት አግኝቷል ወይ የሚለውን የክርክር ነጥብ በአግባቡ መታየት አለበት። ከሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መረዳት እንደተቻለው አመልካች ከፍርድ በፊት በማይንቀሳቀስ ሆነ በሚንቀሳቀስ ንብረት የቀደምትነት መብት ማቋቋማቸው የሚገልጽ ነገር አላቀረቡም። አመልካች በእጃችን ለተያዘው ጉዳይ አግባብነት ያለው ድንጋጌ ነው በማለት የጠቀሱት የሕግ አንቀጽ 2860 ከላይ በጠቀስነው አግባብ መያዣ/Pledge/ ያቋቋሙ የፍርድ ባለገንዘቦች ያላቸው መብት የሚያመለክት እንጂ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
No topics extracted.
አመልካች የቀደምትነት መብት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማቋቋማቸው የገለጹ ቢሆንም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.154/ለ/ ከልሎች አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች ስንመለከተለው ከዚህ የተለየ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ተገኝቷል። ንብረት ለማስከበር የሚቀርብ ማመልከቻ ላያሟላቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 379 በዝርዝር ደንግጓል። የማይንቀሳቀስ ንብረቱ ዓይነቱን በመለየት ማቅረብ ግድታ መሆኑን፤ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ ደግሞ ንብረቱን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ ምልክቶች መገለጽ እንዳለባቸው ንብረቱ የሚለየው በአካባቢው ውስጥ ወይም ርስተመዝገብ ከሆነ በተራ ቁጥር በሆነ ጊዜ የወሰኑ ምልክት ወይም በመዝገብ ላይ የተሰጠው ቁጥር መግለጽ እንደሚገባ ተመልክቷል። አመልካች በፍርድ ባለዕዳ ንብረት ላይ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማድረጋቸው ከላይ በተገለጸው አግባብ ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ የቀደምትነት መብት አቋቁመዋል ለማለት የሚቻል አይደለም። አንድ የፍርድ ባለገንዘብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 154/ለ/ መሰረት የንብረት ዕግድ ቢያሰጥ የቀደምትነት መብት የሚያቋቁም ስለመሆኑና አለመሆኑ ከአሁን በፊት የሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ የሰጣቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች ተመልክተናል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በማድረግ ብድር በመስጠታቸው ምክንያት የሥር ፍርድ ቤቶች የቀደምትነት መብታቸው የነፈገ ውሳኔ በመስጠታቸው የእነዚህ አበዳሪ ተቋማት መብት የሚያስጠብቅ ውሳኔ መስጠቱ የሚያስረዱ ናቸው።
የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔዎች በተናጠል ሲንመለከታቸው በሰ.መ. የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ግለሰቦች ሲከራከሩ በመያዣ የያዘው ቤት በማሳገዳቸው ዕግዱ እንዲነሳ ሲጠይቅ ጣልቃ ገብተህ አልተከራከርክም ዕግዱ አይነሳም የሚል ውሳኔ በመስጠቱ በቀረበው አቤቱታ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተሽሯል። በልላ በኩል በሰ.መ. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስቀድሞ ንብረት ማስከበሩ ብቻውን የቀደምትነት መብት አያሰጥም ማለታቸው ከሕግ የመነጨ የቀደምትነት መብት የነፈገ ነው ተብሎ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሯል። በእነዚህ ሁለት የሰበር ውሳኔዎች አሁን በእጃችን ካለው ጉዳይ ያላቸው ተመሳሳይነት እንደተመለከትነው ከላይ የተጠቀሱ ተቋማት የቀደምትነት መብታቸው በማይንቀሳቀስ ንብረት ያቋቋሙት የቀደምትነት መብት የነበረ መሆኑ የሚያሳይ ሲሆን የአሁኑ አመልካች ያቀረቡት ጉዳይ ግን በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 154/ለ/ መሰረት በአንድ የመንግሥት ተቋም የተያዘው የሚንቀሳቀስ ገንዘብ የሚመለከት በመሆኑ ለዚህ ጉዳይ ተፈፃሚነት የላቸውም።
የቀደምትነት መብት በሕግ፣ በውል ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ /ውሳኔ/ የሚቋቋም ስለመሆኑ ከላይ በተገለጸው የፍትሐብሄር ሕግ ተመልክቷል። አመልካች በፍርድ ባለዕዳ ላይ አስፈርደው ከልሎች የፍርድ ባለገንዘቦች ቀድመው የፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ ማግኘታቸው ከሕግ፣ ውል ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔ የመነጨ የቀደምትነት መብት አቋቁመዋል ለማለት የሚያስችል የህግ መሰረት የላቸውም።አመልካች በተጠሪ ገንዘብ የሰጡት የዕግድ ትዕዛዝ ከልሎች የፍርድ ባለገንዘቦች የተሻለ መብት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ አይደለም ከተባለ፤ቀጥሎ የሚነሳውን ጥያቄ በተራ የፍርድ ባለመብቶች መካከል ያለው የክፍፍል ሥርዓት ምንመሆን አለበት የሚል ነው።ከሥር ፍርድ ቤት መዝገብ መረዳት እንደተቻለው አመልካችን ጨምሮ በተጠሪ ገንዘብ ላይ 18 ግለሰቦች የዕግድ ትዕዛዝ አሰጥቷል።ከአንድ በላይ የፍርድ ባለመብቶች ባሉበት ጊዜ የሀብትና የንብረት ክፍፍል ሥርዓት ምን መሆን እንዳለበት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.403 ያስቀመጣቸው ሁኔታዎች ማየቱ ተገቢ ይሆናል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት የፍርድ ባለገንዘቦች ተቀማጭ የሆነውን ሀብት በውሳኔው መሰረት እንዲከፋፈሉ እንደሚደረግ ተመልክቷል። አመልካች በተጠሪ ገንዘብ ላይ ቀድመው የዕግድ ትዕዛዝ ማሰጠታቸው ግልጽ ቢሆንም ልሎች የፍርድ ባለገንዘቦችም በተከታታይ ቀናት ይህንን የማሳገድ ተግባር አከናውነዋል።አመልካች ከልሎች የፍርድ ባለገንዘቦች የቀደምትነት መብት ያልተሰጣቸው ከሆነ ሁሉም የፍርድ ባለገንዘቦች እንደተራ ገንዘብ ጠያቂዎች የሁሉም መብት እኩል እንደሆነ የሕግ ግምት ይወሰዳል።
ከላይ እንደተገለጸው አንድ የፍርድ ባለገንዘብ ከልሎች የፍርድ ባለገንዘቦች አስቀድሞ የባለዕዳውን ንብረት በማስከበሩ ምክንያት ብቻ የቀደምትነት መብት አይሰጠውም።በመሆኑም የፍርድ ባለገንዘቦች እንደተራ የፍርድ ባለመብቶች ተወስደው ደረጃቸው(መብታቸው)እኩል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ባስፈረዱት የገንዘብ መጠን መቶኛ ስልት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታገደውን ገንዘብ እንዲከፋፈሉ ማድረጉ የሕግ መሰረት ያለው ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ.403 ይዘት ዓላማና መንፈስ የምንረዳው ነው።ከዚህ አንፃር የሥር ፍርድ ቤቶች የፍርድ ባለገንዘቦች በፍርድ ባለዕዳው ላይ ያላቸው የገንዘብ መጠን በሬሾዎ እንዲከፋፈሉ ትዕዛዝ መስጠታቸው መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ሆኖ ባለመገኘቱ ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል።
ው ሣ ኔ
የመቐለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ.መ.ቁ.14044 በ25/04/2006 የሰጠው ብይን፤የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በኮ.መ.ቁ. 6365 በ12/05/2006 የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል።
አመልካች እና ልሎች የፍርድ ባለገንዘቦች ባስፈረዱት መጠን ገንዘብ መቶኛ ስልት (ሬሾዎ)ድርሻ ድርሻቸውን ይከፋፈሉ ብለናል።
ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ።መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።