No summary available.
የካቲት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም አ.ማ. ዓድዋ ቅርንጫፍ - ነ/ፈጅ ጥላሁን ይህደጐ ቀረቡ ተጠሪዎች፡-
ጉዳዩ ለፍርድ ማስፈጸሚያ የቀረበ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመጀመሪያ የሐራጅ ሽያጭ የሚቀርብበትን የዋጋ ግምት አስመልክቶ የተነሳ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን አፈጻጸሙ በተጀመረበት የዓድዋ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት የአሁኖቹ አመልካች እና ተጠሪዎች እንደቅደም ተከተላቸው የፍ/ባለመብት እና የፍ/ባለዕዳዎች በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩን አመጣጥ እና ሂደት በተመለከተ በግራ ቀኙ መካከል በነበረው የብድር ውል መሰረት አመልካች በተጠሪዎች ላይ ለሰጠው የብር 275165.73 ፍርድ የፍርድ ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ለብድር ውሉ በመያዣነት የያዝኩት ነው ያለውን የተጠሪዎች ንብረት የሆነ ቤት(ሕንፃ) ለአፈጻጸም መምራቱን፣ ቤቱ አመልካች በጠየቀው መሰረት በከተማው ማዘጋጃ ቤት እንዲገመት በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ግምቱ ብር 1525354.85 መሆኑ መገለጹን፣ ግምቱ በቀረበበት በ26/04/2005 ዓ.ም. በነበረው ችሎት የቀረበው ግምት የተጋነነ በመሆኑ በገልተኛ መሐንዲስ እንደገና ተገምቶ እንዲቀርብ እንዲታዘዝለት አመልካች ጥያቄ ማቅረቡን፣ ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙ እስካልተስማሙ ድረስ ግምቱ በልላ መሐንዲስ እንደገና እንዲከናወን ላደረግ የሚችልበት አግባብ አለመኖሩን እና በልላ መሐንዲስ ተገምቶ የሚቀርበው ውጤት የተለየ ከሆነ ተቀባይነት ላያገኝ የሚገባው ግምት የየትኛው መሀንዲስ ወይም ባለሙያ እንደሆነ መወሰኑ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጾ የዳግም ግምት ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ፣ በልላ በኩል ግን ሕንፃው በመንገድ ስራ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት መሆኑ መገለጹን ጠቅሶ የጉዳቱ መጠን በዓድዋ ከተማ ንግድ ኢንዱስትሪና መሬት ልማት ጽ/ቤት ተገምቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱን፣ በትዕዛዙ መሰረትም የጉዳቱ መጠን ብር 54000.35 መሆኑ መገለጹን፣ ይህ ውጤት መቅረቡ በተመዘገበበት በ08/05/2005 ዓ.ም. በነበረው ችሎት ተጠሪዎቹ ገንዘቡን ለመክፈል የሁለት ወር ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ይህ የማይቻል ከሆነ ግን በቀረበው ግምት መሰረት የሀራጅ ሽያጩ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን፣ አመልካች የተጨማሪ ጊዜ ይሰጠን ጥያቄውን በመቃወሙ ፍ/ቤቱ በመንገድ ስራ ምክንያት በሕንጻው ላይ ደርሷል የተባለውን ጉዳት የዋጋ ግምት ቀደም ሲል ከማዘጋጃ ቤት ከተገለጸው የሕንፃው የዋጋ ግምት ቀንሶ በተገኘው ውጤት መሰረት ሕንጻው በብር 1471354.40 የዋጋ ግምት በሐራጅ ሽያጭ እንዲቀርብ በዚያው በ08/05/2005 ዓ.ም. በነበረው ችሎት ትዕዛዝ መስጠቱን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።
አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው ሕንጻው በገለልተኛ መሐንዲስ ወይም ባለሙያ በድጋሚ እንዲገመት አመልካች ያቀረበው ጥያቄ ውቅድ ተደርጎ የሐራጅ ሽያጩ የተጋነነ ነው በተባለው የዋጋ ግምት እንዲቀጥል በተሰጠው ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት አመልካች ለክልሉ የበላይ ፍ/ቤቶች ያቀረበው ይግባኝ እና የሰበር አቤቱታ እንደቅደም ተከተሉ በፍርድ እና በትዕዛዝ ተቀባይነት በማጣቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ አመልካች የንብረቱ የዋጋ ግምት የተጋነነ ነው በማለት ያቀረበው ተቃውሞ ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ተጠሪዎች ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ተደርጎ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል። የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በማዘጋጃ ቤት የቀረበው የሕንፃው ግምት የተጋነነ መሆኑን ገልጾ ግምቱ በድጋሚ በልላ ገለልተኛ መሐንዲስ ወይም ባለሙያ እንዲከናወን እንዲደረግ አመልካች ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የተሰጠው እና በክልሉ የበላይ ፍ/ቤቶች ተቀባይነትን ያገኘው የዓድዋ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት የአፈጻጸም ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
በዚህም መሰረት በአንድ የሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ ላይ በትክክለኛ ሁኔታ መገለጽ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ የሚሸጠው ንብረት ዓይነት እና የግምቱ ልክ መሆኑ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 423(2)(ሀ) ስር የተደነገገ ሲሆን የድንጋጌው ዓላማም የሚሸጠው ንብረት ከትክክለኛ የዋጋ ግምት አላግባብ ከፍ ወይም ዝቅ ተደርጎ እንዳይገመት ለማድረግ እና በዚህ ሳቢያ በፍ/ባለገንዘቡም ሆነ በፍ/ባለዕዳው ላይ ላደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል እንደሆነ ይታመናል። ፍ/ቤቱ በማስታወቂያው ላይ የሚሰፍረውን የንብረቱን የዋጋ ግምት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚችል የሚሸጠውን ዓይነት ንብረት ለመገመት ልዩ ችሎታ ያለውን ኤክስፐርት በማዘዝ ንብረቱ እንዲገመት ለማድረግ እንደሚችል በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 424(2) ላይ የተመለከተው ድንጋጌም ይህንኑ መገንዘብ የሚያስችል ነው።
No topics extracted.
በተያዘው ጉዳይ የሐራጅ ሽያጭ ትዕዛዝ የተሰጠበት የፍ/ባለዕዳዎች ቤት በፍ/ባለመብቱ ጥያቄ በከተማው ማዘጋጃ ቤት መሐንዲሶች በኩል በብር 1525354.85 የተገመተ ሲሆን አመልካች ይህ ግምት የተጋነነ መሆኑን ገልጾ ቤቱ በልላ ገለልተኛ ባለሙያ እንዲገመት ይደረግ ዘንድ ያቀረበውን አቤቱታ የወረዳው ፍ/ቤት ሳይቀበለው የቀረው ከላይ እንደተገለጸው ሁለቱ ወገኖች እስካልተስማሙ ድረስ ቤቱ በድጋሚ ላገመት የሚችልበት አግባብ አለመኖሩን እና ይገመት ቢባል እንኳ የሚቀርበው ግምት ከበፊቱ የተለየ ከሆነ ተቀባይነት የሚኖረው የትኛው ግምት እንደሆነ ለመወሰን አስቸጋሪ ነው በማለት ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱ ወገኖች እስካልተስማሙ ድረስ ቤቱ በድጋሚ ላገመት የሚችልበት አግባብ የለም በማለት በፍ/ቤቱ የተያዘው አቋም ሕጋዊ መሰረት የልለው እና ፍ/ቤቱም የዚህ ዓይነት አቋም ለመያዝ ያስቻለውን ድንጋጌ በትዕዛዙ ላይ ያልጠቀሰ ከመሆኑም በላይ ቤቱ በድጋሚ በልላ አካል ወይም ባለሙያ ተገምቶ የሚቀርበው ግምት ከበፊቱ የተለየ ከሆነ እንደየገማቹ አካል ወይም ባለሙያ ደረጃ እና ማንነት ከሁለቱ ግምቶች ተቀባይነት ላኖረው የሚገባው የትኛው ግምት እንደሆነ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ተገቢውን ትዕዛዝ ይሰጥበት የሚችል በመሆኑ የወረዳው ፍ/ቤት አመልካች ቤቱ በልላ ገለልተኛ ባለሙያ እንዲገመት ይደረግ ዘንድ ያቀረበውን አቤቱታ ላለመቀበል የሰጠው ምክንያት ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም። በማዘጋጃ ቤት በኩል ቤቱ እንዲገመት የጠየቀው የፍ/ባለመብቱ ራሱ በመሆኑ በጥያቄው መሰረት ተሰርቶ የቀረበውን ግምት መልሶ ላቃወም አይችልም በማለት በይ/ሰሚው ፍ/ቤት የተያዘውን አቋም በተመለከተ የቀረበው ግምት የተጋነነ ስለመሆኑ የፍ/ባለመብቱ ያቀረበው መከራከሪያ አሳማኝ ሆኖ አስከተገኘ ድረስ የግምቱ ስራ የተከናወነው የፍ/ባለመብቱ በጠየቀው አካል የመሆኑ ጉዳይ ብቻውን የፍ/ባለመብት ንብረቱ በልላ ባለሙያ በድጋሚ እንዲገመት ጥያቄ ከማቅረብ ላከለክለው የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም።
በልላ በኩል በወረዳው ፍ/ቤት በነበረው የአፈጻጸም ክርክር በ08/05/2005 ዓ.ም. በነበረው ችሎት ተጠሪዎቹ ገንዘቡን ለመክፈል የሁለት ወር ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ይህ የማይቻል ከሆነ ግን በቀረበው ግምት መሰረት የሀራጅ ሽያጩ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን የመዝገቡ ግልባጭ የሚያመለክት ሲሆን ተጠሪዎቹ አሁንም ድረስ የቤቱ ግምት የተጋነነ ስላልሆነ በግምቱ መሰረት የሐራጅ ሽያጩ ላቀጥል ይገባል በሚል ከመከራከር በስተቀር ግምቱ የተጋነነ አይደለም የሚሉ ከሆነ ጠይቀው በነበረው መሰረት ቤቱን በራሳቸው ሽጠው ከቀረበው የቤቱ ግምት አንፃር ሲታይ አነስተኛ የሆነውን ዕዳቸውን ለመክፈል ስላልቻሉበት ምክንያት ያቀረቡት ክርክር የለም። ይህም በማዘጋጃ ቤቱ ተሰርቶ የቀረበው የቤቱ ግምት የተጋነነ በመሆኑ ቤቱ በልላ ገለልተኛ አካል ወይም ባለሙያ ላገመት ይገባል በማለት አመልካች የሚያቀርበው ክርክር ምክንያታዊ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል ነው።
ሲጠቃለል በከተማው ማዘጋጃ ቤት መሐንዲሶች የቀረበው የቤቱ ግምት የተጋነነ መሆኑን ገልጾ ቤቱ በልላ ገለልተኛ ባለሙያ እንዲገመት እንዲደረግ አመልካች ያቀረበውን ጥያቄ ካለበቂ ምክንያት ውድቅ በማድረግ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
በከተማው ማዘጋጃ ቤት መሐንዲሶች የቀረበው የቤቱ ግምት የተጋነነ መሆኑን ገልጾ ቤቱ በልላ ገለልተኛ ባለሙያ እንዲገመት እንዲደረግ አመልካች ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በዓድዋ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ በ08/05/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በዓድዋ ከተማ ከ/ፍ/ቤት እና በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት እንደቅደም ተከተሉ በመ. በ06/07/2005 ዓ.ም. እና በመ. በ13/10/2005 ዓ.ም. በውሳኔ እና በትዕዛዝ የፀናው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
ለአፈጻጸሙ የተመራው የፍ/ባለዕዳዎች ቤት የግምት ስራ የማከናወን ስልጣን እና ሙያ ባለው የክልል ቢሮ ወይም የግምቱን ስራ የማከናወን በሚችል ልላ ባለሙያ ወይም አካል አማካይነት በድጋሚ ተገምቶ እንዲቀርብ በማድረግ፣ የሚቀርብለትን ግምት ከቀዳሚው ግምት ጋር በማገናዘብ እና የግራ ቀኙን አስተያየት ጭምር በመቀበል በሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያው ላይ መገለጽ የሚገባውን የቤቱን የዋጋ ግምት በተመለከተ ተገቢውን ትዕዛዝ በመስጠት የሐራጅ ሽያጩን እንዲያስቀጥል ጉዳዩ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 343(1) መሰረት ለዓድዋ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት እንዲመለስ ወስነናል።
በዚሁ መሰረት መፈጸም ያስችለው ዘንድ የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለወረዳው ፍ/ቤት ይላክ። ለዓደዋ ከተማ ከ/ፍ/ቤት እና ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎትም ይላክ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።