No summary available.
መጋቢት 12 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ አፍሪካ ታደሰተጠሪ፡- 1.ወ/ሮ ያለምወርቅ ታደሰ- ታልፏል 2.የጎባ ከተማ አስተዳደር ፅ/ቤት **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ በሚስትነትና በወራሽነት ድርሻ አለው ተብሎ ውሳኔ ያገኘ ሰው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲሰጠው እንዲታዘዝለት በአፈጻጸም ማመልከቻ ዳኝነት ቢጠይቅ ጥያቄው በፍርድ ቤት ላታይ የሚችል መሆን ያለመሆኑን የሚመለከት ነው።
ክርክሩ የተጀመረው በጎባ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን በዚህ ፍ/ቤት የአሁኗ አመልካች የፍርድ ባለመብት የአሁኑ ተጠሪ ደግሞ የፍርድ ባለእዳ ሁነው ተከራክረው ነበር። አመልካች በአሁኑ ተጠሪና በወ/ሮ ያለምወርቅ ታደሰ ላይ የከፈቱት የአፈጻጸም መዝገብ በወረዳው ፍርድ ቤት በመ/ የተሰጠ ውሳኔ እንዲፈፀምላቸው የሚጠይቅ ሲሆን አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤትም ጉዳዩ እንዲጣራ ትእዛዝ ሰጥቶ የጎባ ከተማ ማዘጋጃ ቤትም በቁጥር 1109/2/4/184 በ14/9/2004 ዓ/ም ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ አመልካች እንዲፈጸምላቸው የሚጠይቁት ቤት ከሟች ባለቤታቸው ኢንስፔክተር ጥላሁን መለሰ ስም ወደ ወ/ሮ ያለምወርቅ ታደሰ (1ኛ ተጠሪ) የተዛወረ ስለሆነ የሚፈፀም ነገር የለም በማለት ገልጿል።ከዚህም በኋላ አፈፃፀሙን የያዘው ፍርድ ቤት ይህንኑ ደብዳቤ መነሻ በማድረግ የአፈጻጸም መዝገቡን ዘግቶታል።በዚህ የአፈፃጸም ትዕዛዝ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለባል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ለተጠሪዎች ጥሪ አድርጎ 1ኛዋ ተጠሪ ባለመቅረባቸው ጉዳዩን በልሉበት እንዲታይ ያደረገ ሲሆን 2ኛው ተጠሪ ግን ቀርቦ ከአመልካች ጋር ከተከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ለአፈጻጸሙ መነሻ የሆነውና በመ/ የተሰጠው ውሳኔ ይዘቱ አመልካችም ሆነ ህፃኑ ድርሻቸውን እንዲያገኙ የሚል እንጂ ስመ ሀብቱ እንዲዛወር የሚል አይደለም፣የአሁኗ 1ኛ ተጠሪ በሐሰተኛ የሚስትነት ማስረጃ ስመ ሃብቱ እንዲዞር ያደረጉ መሆኑ የተረጋገጠ ነው የሚል ክርክር ቢቀርብም ይህ ማስረጃ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 998 መሰረት እንዲሰረዝ አልተደረገም የሚሉትን ምክንያቶችን አስፍሮ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የአፈጻጸም ትእዛዝ አጽንቶታል።በዚህ ውሳኔ የአሁኗ አመልካች ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የበታች ፍርድ ቤቶች በወረዳው ፍርድ ቤት በመ/ የተሰጠውን ውሳኔ የሚፈፀም አይደለም በማለት የአፈጻጸም መዝገብ መዝጋታቸው አንድ ውሳኔ የሚፈጸምበትን ስርዓት ባልተከተለ መንገድ መሆኑን ዘርዝረው አከራካሪው ቤት ስመ ሃብቱ እንዲዞርላቸው አድርገው ዋናውን ውሳኔ ያስፈጽሙ ዘንድ እንዲወሰንላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።አቤቱታቸው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው 1ኛዋ ተጠሪ ላቀርቡ ባለመቻላቸው በፅሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው የታለፈ ሲሆን 2ኛው ተጠሪ ግን በመቅረቡ ከአመልካች ጋር በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ችሎት ሲቀርብ የተያዘው ጭብጥ አመልካች በመ/ በ26/11/2003 በንብረቱ ላይ ድርሻ ያላት መሆኑ በፍርድ ቤት ተረጋግጦ ድርሻዋ እንዲሰጣት ውሳኔ ተሰጥቶ እያለና ውሳኔውም ባልተሻረበት ሁኔታ ባፈፃጸም ችሎቱም ቢሆን 1ኛ ተጠሪ ንብረቱ ላይ አፈጻጸም ላቀጥል አይችልም በሚል ያቀረቡት ተቃውሞ ሳይኖር የበታች ፍርድ ቤቶች ላፈጸም የሚችል ነገር የለም በሚል አቤቱታውን ውድቅ የማድረጋቸውን አግባብነት ለመመርመር ሲባል በመሆኑ ጉዳዩን ከዚሁ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለው ተመልክተናል።ይህንኑ ጭብጥ ለመመለስም በመ/ የተሰጠው ውሳኔ አስቀርበን ይዘቱን ተመልክተናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች በአከራካሪው ቤት ላይ መብት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰውና ይኼው መብታቸው ተረጋግጦ ዳኝነት እንዲሰጥ በአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ላይ ክስ መስርተው የወረዳው ፍርድ ቤት ተገቢ ነው ያለውን ዳኝነት ከሰጠ በኋላ አመልካች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ የአሁኗ 1ኛ ተጠሪ አከራካሪውን ቤት ስመ ሃብቱን በስማቸው ያደረጉት ከቤቱ ባለቤት ውል አድርገው መሆን ያለመሆኑን፣የአሁኑ 2ኛ ተጠሪ የቤቱን ስመ ሃብቱን ከሕግ ውጪ ካዛወረ መከሰስ አለበት? ወይስ የለበትም? የሚሉትን ጭብጦችን ለይቶና የአሁኗን 1ኛ ተጠሪ ወደ ክርክሩ እንድትገባ አድርጎ ጉዳዩን አጣርቶ እንዲወስን ለወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁጥር 343(1) መሰረት መልሶለት ጉዳዩ የተመለሰለት የወረዳው ፍርድ ቤትም ጉዳዩን 1ኛ ተጠሪ በልለችበት አይቶና አመልካችንና 2ኛ ተጠሪን ደግሞ በተገቢው መንገድ አከራክሮና ተገቢ ነው ያለውን ሁሉ ከአጣራ በኋላ የአሁኗ 1ኛ ተጠሪ የሟች ኢንስፔክተር ጥላሁን መለሰ ሚስትነትን በማሳወጅ በያዙት ማስረጃ መሰረት ቤቱን ሙሉ በሙሉ በግላቸው የሚያዛወሩበት ምክንያት እንደልለ፣ተጠሪዋ ድርሻዋን ብቻ የምታገኝ መሆኑን፣የአሁኗ አመልካች ደግሞ የሟቹ ሚስት መሆናቸው መረጋጡንና እርሳቸውም ድርሻቸውን ማግኘት ያለባቸው መሆኑን እንዲሁም አመልካች ከሟቹ የወለዱት ልጅ(ይዲድያ ጥላሁን) ደግሞ የሟቹን ድርሻ ላይ ሙሉ የወራሽነት መብት ያለው መሆኑን ገልፆና ይህንኑ ድርሻውን የማግኘት መብት የተጠበቀ መሆኑን ጠቅሶ በመ/ ሐምል 26 ቀን 2003 ዓ/ም በዋለው ችሎት ዳኝነት መስጠቱን፣ይህ ውሳኔ በየትኛውም እርከን ባለው ፍርድ ቤት ያልተለወጠ መሆኑንና ለአፈጻጸሙ መሰረት የሆነውም ይኼው የአመልካችና የልጃቸው ድርሻ ያለበት መሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተረጋገጠው ውሳኔ መሆኑን ነው።
No topics extracted.
በመሰረቱ በሕግ አግባብ ታይቶ የተሰጠ ፍርድ እንደ ፍርዱ መፈጸም ያለበት ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 378 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ያሳያሉ። በእነዚህ ድንጋጌዎች በተዘረጋው ስርአት አግባብ በመመራት ካልሆነ በስተቀር በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሣኔ ሕጋዊ ባልሆነ እና ውሳኔውን ውጤት አልባ በሚያደርግ መልኩ ውድቅ ላደረግ የሚችልበት አግባብ አይኖርም።ድንጋጌዎች በግልጽ የሚያስገነዝቡት አቢይ ነጥብ የፍርድ አፈጻጸም ስርአት ፍ/ቤት የሰጠውን ፍርድ በእራሱ አማካኝነት ወደ ተግባር ወይም ውጤት የሚለውጥበት ስርአት መሆኑን ነው። በልላ አገላለጽ የድንጋጌዎች አቀራረጽ ይዘትና መንፈስ በጥንቃቄ ሲታይም የፍርድ አፈጻጸም ስለፍርድ አፈጻጸም የተደነገጉትን ድንጋጌዎች በመከተል ፍርድን በተግባር መተርጎም እንደመሆኑ መጠን የአፈጻጸም ስርአቱ ህጉን መሰረት ማድረግ ያለበትና የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህጉን መሰረታዊ ዓላማ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአነስተኛ ወጪ ጊዜና ጉልበት በተፋጠነና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲፈፀም በሚያስችል አግባብ ሕግ አውጪ ያስቀመጣቸው መሆኑን የምንረዳው ጉዳይ ነው።ውሳኔው የማይፈፀምበት ሕጋዊ ምክንያት መኖር ያለመኖሩም በፍርድ ቤቱ ታይቶ ተገቢው እልባት የሚሰጥበት መሆኑን ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 392 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው።ይህ ድንጋጌ አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤት አፈፃፀሙን ምቹ ሁኔታዎች ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በተቻለ መጠን ፍርዱ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ላከተል የሚገባ መሆኑን ያሳያል።ስለሆነም አንድን ፍርድ እንደፍርዱ ይዘትና መንፈስ ውጤት ባለው መልኩ መፈጸም የግድ የሚል ሲሆን ይህ ደግሞ የፍርድ አፈጻጻምን በተመለከተ በስነ ስርዓት ሕጉ የተዘረጉት ስርዓቶች በአግባቡ በማየትና ተፈፃሚ በማድረግ የሚከናወን መሆኑን የድንጋጌዎቹ ይዘት የሚያሳይን ጉዳይ ነው።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ለአፈፃጸም ማመልከቻቸው መሰረት ያደረጉትና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 378 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት አያይዘው ያቀረቡት የወረዳው ፍርድ ቤት በመ/ የሰጠውን ፍርድ ሲሆን ከላይ እንደተገለጸው በአከራካሪው ቤት ላይ መብት ያላቸው መሆኑ ተረጋግጧል።በአፈፃጸም ማመልከቻቸው የጠየቁት ዳኝነትም የቤቱ ስመ ሃብተ በስማቸውና የሟቹ ወራሽ መሆኑ ተረጋግጦ የሟቹን ድርሻ እንዲወርስ ለተወሰነለት አመልካች ሞግዚት ለሆኑት ሕጻን ልጅ ስም ነው፤የበታች ፍርድ ቤቶች ይህንኑ የአመልካችን የአፈጻጸም ዳኝነት ጥያቄ ውድቅ ያደረጉት በመ/ በተሰጠው ውሳኔ ስመ ሀብት እንዲኖር ለፍርድ ባለመብቶች አልተወሰነም በሚል ምክንያት መሆኑን ከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ የምንረዳው ጉዳይ ሲሆን የወረዳው ፍርድ ቤት ግን ቤቱ ወደ አሁኗ 1ኛ ተጠሪ ስም ተዛውሯል ተብሎ በማዘጋጃ ቤት በመገለጹ ብቻ የአፈጻጸም መዝገቡን ዘግቷል።ይሁን እንጂ አመልካችና ሕጻኑ በቤቱ ላይ መብት አላቸው የሚለው የዋናው ክርክር ውሳኔ ይዘትየሚያሳየው አመልካች እና ሕጻኑ በኢ/ፍ/ዲ/ሪፐብላክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 40/1/ እና /2/ ድንጋጌዎች ስር የተከበረውን የንብረት ባለቤትነት ያረጋገጠ መሆኑን፣ በዚሁ ውሳኔ መሰረት የቤቱ ስመ ሃብት በአመልካችና በሕፃኑ ድርሻ መጠን ላይ እንዲመዘገብ የማይደረግበት አግባብ የልለ መሆኑን ነው።በዚህ አግባብ ውሳኔው እንዲፈፀም ካልተደረገ ደግሞ በዋናው ክርክር በሕጉ አግባብ ተጠርተው ያልቀረቡና ድርሻቸውን ብቻ እንዲያገኙ የተወሰነባቸው የአሁኗ 1ኛ ተጠሪ በቤቱ ላይ ተገቢ ያልሆነ ተግባር እንዲፈፅሙ የሚያደርግ ውጤት የሚያስከትል መሆኑ የሚታመን ነው።በመሆኑም አመልካች በቤቱ ላይ መብት እንዳላቸው በዋናው ውሳኔ ተረጋግጦላቸውና በ1ኛ ተጠሪም ስመ ሃብቱ ሙሉ በሙሉ የተመዘገበው ያላግባብ መሆኑን በመ/ የተሰጠው ውሳኔ በግልጽ የሚያሳይ ሁኖ እያለና 1ኛዋ ተጠሪም በፍርድ ባለእዳነታቸው ቀርበው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 386 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ያቀረቡት መቃወሚያ ሳይኖር በፍርድ ኃይል የተረጋገጠውን የአመልካችን የንብረት ባለቤትነት መብት ዋጋ የሚያሳጣ የአፈጻጸም ትእዛዝ መስጠት ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ሁኖ አልተገኘም። 2ኛ ተጠሪም በዋናው ክርክር ተሳታፊ ሁኖ የአመልካችንና የህፃኑን ድርሻ በ1ኛ ተጠሪ ስም እንዲመዘገብ ማድረጉ ተገቢ ያለመሆኑን በሚያስገነዘብ መልኩ በዋናው ጉዳይ ተወስኖበት እያለ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ስመ ሃብቱ በ1ኛ ተጠሪ ተዛውሯል በማለት በአፈጻጸም ጊዜ ለፍርድ ቤቱ በመግለፁ ብቻ የአፈፃፀም መዝገብ የሚዘጋበት ሕጋዊ ምክንያት የለም።ምክንያቱም የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195 እና 1196 ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲነበቡም የአስተዳደር አካል በባለቤትነት ማረጋገጫ ማስረጃ አሰጣጥ ላይ ፍጹም የሆነ አስተዳደራዊ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ አያሳዩም።ይልቁንም ድንጋጌዎች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከፍ/ሕ/ቁጥር 1198 ድንጋጌ ጋር ተዛምደው ሲታዩ የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር የሚሰረዘው በሕጉ በተመለከቱት ምክንያቶች ብቻ መሆኑን ከሕጉ ውጪ ተግባሩ ተከናውኖ ከተገኘም መብቱ የተነካው ሰው በኢ/ፍ/ዲ/ሪፐብላክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37፣78 እና 79 ድንጋጌዎች መሰረት ጉዳዩን ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አቅርቦ አቤቱታው እንዲታይለት የሚያደርግበት ጉዳይ እንጂ አስተዳደር አካሉ የሰጠው ውሣኔ በፍርድ ቤት እንዳይታይ የሚገደብበት ስርአት የልለ መሆኑን የምንገነዘበው ነውና።
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ተጠሪ በሚስትነታቸው ባገኙት ማስረጃ መሰረት የቤቱን ስመ ሃብት እንዲዞር ባደረጉበትና ይኼው ማስረጃ ባልተሰረዘበት ሁኔታ የስመ ሃብት ምዝገባ ጥያቄ በአመልካች መቅረቡ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 998 ድንጋጌ አንፃር ተገቢነት የለውም በማለት በፍርድ ላይ ያሰፈረው ምክንያትም ቢሆን በዋናው ክርክር ጊዜ 1ኛ ተጠሪ ስመ ሃብት እንዲዞር ማድረግ የሚችሉት በሚስትነታቸው ባላቸው ድርሻ ብቻ ነው ተብሎ የተወሰነውን የውሳኔ ክፍል ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ነው።በመሆኑም የ1ኛ ተጠሪ የሚስትነት ማስረጃ ያለመሰረዝ ውጤት ላኖረው የሚችለው በድርሻቸው ብቻ እንጂ በአመልካችና በሟቹ ኢንስፔክተር ድርሻ ጭምር አይደለም።አመልካችም ሆነ 1ኛ ተጠሪ በቤቱ ላይ ድርሻ አላቸው ከተባለም ድርሻቸው ምን ያህል ነው?፤በቤቱ ግማሽ ነው ወይስ ከሟቹ ጋር ሶስቱም እኩል? የሚለው የሟቹን ድርሻ ህፃኑ እንዲወርስ ተብሎ ከተወሰነው የውሳኔ ክፍል እና አግባብነት ካላቸው የህገ መንግስት እና ከክልሉ የቤተሰብ ህግ ድንጋጌዎች ጋር ተገናዝቦ በአፈፃፀሙ ጊዜም ቢሆንም ተገቢው ትዕዛዝ የሚሰጥበት ጉዳይ ነው።ይህም አካሄድ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 392 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ አንጻር የሚነቀፍበት አግባብ የለም።
በአጠቃላይ ተጠሪዎች በዋናው ጉዳይ በፍርድ ቤት በነበረው ክርክሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጎ 2ኛ ተጠሪ ቀርቦ ተገቢ ነው ያለውን ክርክር አቅርቦ አመልካችና ሕጻኑ በቤቱ ላይ መብት ያላቸው መሆኑ ተረጋግጦ በተወሰነበት ሁኔታ በዋናው ጉዳይ ስመ ሃብቱ እንዲዞር አልተወሰነም ተብሎ የአፈጻጸም መዝገቡ መዘጋቱ ከላይ የተመለከቱትን ሕጋዊ ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ባላገናዘበ መንገድ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች አፈፃጸሙ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በጎባ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ ግንቦት 14 ቀን 2004ዓ.ም የተሰጠው ትዕዛዝና ይህንኑ ትዕዛዝ በማጽናት በባል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 06 ቀን 2005 ዓ.ም የተሰጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
አመልካች እና ህፃን ይዲድያ ጥላሁን መለሰ በዋናው ክርክር በቤቱ ላይ መብት ያላቸው መሆኑ እና 1ኛ ተጠሪም በድርሻቸው ብቻ ስመ ሃብቱን ማስመዝገብ ሲገባቸው በቤቱ ላይ ሙሉ መብት እንዳላቸው ተደርጎ ስመ ሃብቱ መዞሩ ተገቢነት የልለው መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ በቤቱ ላይ 1ኛ ተጠሪ ስመ ሃብት ማዞራቸው አፈጻጸሙን ለማስቆም በቂ ምክንያት አይደለም ብለናል።በዚህም ምክንያት አመልካች በራሳቸውና በህፃኑ ድርሻ ስመ ሃብቱ እንዲመዘግብላቸው ያቀረቡት የአፈጻጸም ጥያቄ ተገቢ በመሆኑ የወረዳው ፍርድ ቤት አፈጻጸሙን በመ/ ቀጥሎ በፍርድ ሐተታው ላይ በተመለከተው አግባብ እንዲያስፈፅም ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 343/1/ መሰረት መልሰናል። ይጻፍ።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።