No summary available.
ግንቦት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፉ አህመድ አመልካች፡- ኦዞ ግሎባል ኃ/የተ/የግል ማህበር - ጠበቃ ሙሉጌታ ወንድማገኝ ቀረቡ ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን- ኃ/መለኮት አበበ ቀረበ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበው የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው።ጉዳዩ የጉምሩክ ሥርዓት አልተፈጸመበትም ተብሎ ለተወረሰ ንብረት የተከፈለ ታክስ እንዲመለስ በማለት የቀረበን ክርክር የሚመለከት ነው።በሥር ፍርድ ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ አመልካች ከቻይና አገር ኒግቦ ኦቪል ባትሪ ኮ/ላሚትድ ከሚባል ኩባንያ 100,800 ደርዘን ካርቶኖች የያዘ ባትሪ ወደ አገር ውስጥ አሰገብቻለሁ።ዕቃውን ወደ አገር ውስጥ ሳስገባ በድክላራሲዮን ቁጥር C/D22074 ብር 473,799.65 ቀረጥ ከፍለናል።ነገር ግን ከዚህ በኋላ ህገ ወጥ ተግባር ተፈፅሟል ተብሎ በወንጀል ተከሰን ዕቃው ተወርሶ እኛ በነፃ ወጥተናል።ስለዚህ የከፈልነውን ብር 473,799.65 እንዲመልስ ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት ክስ አቅርቧል።ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ ውርሱ የተከፈለውንም የቀረጥ ገንዘብ የሚያካት ነው።ስለዚህ የምመልስበት ምክንያት የለኝም የሚልና ልሎች ዝርዝር መከራከሪያዎች አቅርቧል።
የሥር ፍርድ ቤት የግራቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካች ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል።አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይግባኝ ማመልከቻ አቅርቧል።ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል።አመልካች ነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ/ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ አመልካች እንዲመልስልኝ የጠየኩት ዕቃዎች የከፈልኩትን መደበኛ የቀረጥ ገንዘብ ነው።የበታች ፍርድ ቤቶች ይህንን በዋስትና እንደተያዘ ገንዘብ በመቁጠር የሰጡት የህግ ትርጉም መሰረታዊ ስህተት ያለበት ሰለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለትአመልክቷል።ተጠሪ በበኩሉ ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ/ም በሰጠው መልስ አመልካች ዕቃው ህገወጥ ተግባር ተፈፅሞበታል ተብሎ ሲወረስ ፤በህጋዊ መንገድ ዕቃው የተከፈለ ቀረጥ ውርሱ መጨመር የለበትም በማለት የሚያቀርበው ክርክር የሕግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክሯል።አመልካቹ የመልስ መልስ አቅርበዋል።
በሥር የክርክሩ አመጣጥና ግራቀኙ በፅሑፍ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች ለተወረሱ ዕቃ የተከፈለው የቀረጥ ገንዘብ እንዲመለስለት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ህጋዊ የጉምሩክ ቀረጥ ከፍየበታለሁ የሚለው ዕቃ የተያዘውና የተወረሰው፤በአመልካች መጋዘን በተደረገ ብርበራ የጉምሩክ ህግን በመተላለፍ ከገቡ ዕቃዎች ጋር ተቀላቅሎ በመገኘቱ እንደሆነ ይኸ ሰበር ችሎት መዝገብ ጥቅምት 8 ቀን 2004ዓ/ም በሰጠው ውሣኔ ለመገንዘብ ይቻላል። ህጋዊ ቀረጥ የተከፈለበት ዕቃ ህጋዊ የጉምሩክ ሥርዓት ካልተፈፀመበት ዕቃ ጋር ተቀላቅሎ በተያዘ ጊዜ፤በህጋዊ መንገድ ለገባው ዕቃ የተከፈለው ታክስ እንዲመለስለት የዕቃው ባለቤት የሚጠይቅበት ህጋዊ ሥርዓት የለም ።የአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 104(3)(ሀ) ድንጋጌም በዚህ መንገድ እንዲተረጎምለት አመልካች ያቀረበው ክርክር አዋጅ ላያስፈፅመው የሚፈልገውን ጠቅላላ አላማና የድንጋጌውን ይዘትና ግብ ያላገናዘበ በመሆኑ አልተቀበልነውም።በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.