No summary available.
የሰ/መ/ ግንቦት 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ሙሉ አሚን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር -ጠበቃ አቶ ገ/መድህን ረዳ ቀረቡ ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን -ዐ/ሕግ አቶ ኃይለመለኮት አበበ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ ለሰበር ክርክር መነሻ የሆነው የአሁን አመልካች ተጠሪው በወሰነበት የገቢ ግብር እና የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን ላይ ቅር በመሰኘት የይግባኝ ቅሬታውን ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ቢያቀርብም ጉባኤው ቅሬታውን ውድቅ በማድረጉና ጉዳዩን በየደረጃው በይግባኝ ያዩት የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፍድራል ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በማጽናታቸው ነው።
አመልካች ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ያቀረቡት የይግባኝ ቅሬታም፡- ይግባኝ ባይ የሚፈለግብኝን ግብር ከከፈልኩ ከ5 ዓመት በኋላ ያለአግባብ የተወሰነብኝ ግብር እና ታክስም በይርጋ የሚታገድ ነው፣የ1997 ዓ/ም የግብር ዘመን በይግባኝ ባይ ድርጅት ስም ገቢና ወጪ፣ትርፍና ኪሳራ በማስላት በሒሳብ መዝገብ መሰረት በማቅረብ ለግብር አስገቢ መስሪያ ቤት ካሳወቅሁ በኋላ ታህሳስ 23 ቀን 1998 ዓ/ም በድርጅቱ ላይ ባጋጠመው የእሳት አደጋ የሂሳብ እና መሰል ሰነዶች ተቃጥለው በመውደማቸው ይግባኝ ባይም ለሚመለከተው የመንግስት አካል አመልክቼ በክፍለ ከተማው ፖላስ መምሪያ በኩል አደጋው ስለመጣራቱ ማስረጃ እያለኝ እና ግብር አስገቢው መ/ቤትም በዚሁ ምክንያት የ1997 ዓ/ም የግብር ዘመን በማገኘው 1.65% ኮሚሽን ላገኝ የሚችለውን ትርፍ ማስላት ሲገባው በእሳት ቃጠሎው ንብረቱ እና ሰነዶቹ መውደማቸውን ቢቀበልም በእሳት አደጋው የወደመውን የሂሳብ መዝገብ ካላመጣህ በስተቀር በ1.65% አይሰላም በማለት ይግባኝ ባዩን በሚጎዳ መልኩ በ7.5% አማካይ የትርፍ መቶኛ በማስላት እጅግ የተጋነነ ግብርና ታክስ መጠየቁ ተገቢነት የለውም፤ በልላ በኩል ይግባኝ ባይ ድርጅት ከኬኬ ኃ/የተ/የግል ማህበር የሚያገኘው የሱፍ ክር ሐምል 15 ቀን 1996 ዓ.ም በተፈራረምነው ውል አንቀጽ 5(5.3) መሰረት ማህበሩ ከሚሰጠው የጅምላ ዋጋ ላይ በፓኬት ከ1ብር እስከ 2 ብር ብቻ በመጨመር እንዲሸጥ የተስማማን ሲሆን ከተስማማነው በላይ የአገልግሎት ዋጋ በመጨመር ልሸጥ እንደማልችል፣ ሽጬ ብገኝም ለውሉ መፍረስ ምክንያት እንደሚሆን በተስማማነው መሰረት ይግባኝ ባይም ይህንኑ የውል ግድታ በማክበር በኮሚሽን የሚሸጠው ክር የትርፍ መቶኛው 1.65 በማይበልጥበት ሁኔታ ግብር አስገቢው መ/ቤት ግብር እና ታክስ በግምት ሲወስን 7.5% የትርፍ ህዳግ መያዙ ተገቢ አይደለም፣እንዲሁም በ1996፣ከ1998 እስከ 2001 ዓ/ም ግብር ዘመን ግብሩ በተሰላበት በ1.65% መሰረት የ1997 ዓ/ም ግብርም መሰላት ሲገባው መስሪያ ቤቱ በተሳሳተ መንገድ ማስላቱ ተገቢ አይደለም፣የግብር አስገቢው መ/ቤት በግብር ማስታወቂያዎቹ ላይ አስመጪ በሚል በመጻፍ በተሳሳተ የስልት መነሻ ወለድ፣ግብር አሳንሶ በመክፈል እና ክፍያ በማዘግየት እንድከፍል የወሰነብኝ መቀጫ ተቀባይነት የለውም ሲል የግብርና ታክስ ውሳኔው ተሰርዞ ኦዲት በተደረጉት የሂሳብ ሰነዶች መሰረት ሂሳብ ተስተካክሎ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
መልስ ሰጪው መ/ቤትም በሰጠው መልስ፡- ይግባኝ ባይ የግብር ውሳኔው መቅረብ ከሚገባው ጊዜ በላይ ቆይቶ የቀረበ በመሆኑ በይርጋ የሚታገድ ነው ቢልም ውሳኔው የደረሰው በ25/02/2003 ዓ/ም በመሆኑ የይርጋው ጊዜ ከማለፉ በፊት የቀረበ ነው፤ጊዜው አልፏል ቢባል እንኳን ግብር ከፋይ የተጭበረበረ ገቢ ያቀረበ እንደሆነም በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 71(3) መሰረት በማናቸውም ጊዜ ግብሩን መወሰን እንደሚቻል በመደንገጉ የይርጋው ክርክር ተቀባይነት የለውም፣ይግባኝ ባይ መስከረም 19 ቀን 2003 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ የሂሳብ መዝገቡን እንዲያቀርብ ተጠይቆ በእሳት አደጋ ምክንያት ንብረቱ የወደመ መሆኑን በመግለጽ ምንም ዓይነት ሰነድ ማቅረብ ባለመቻሉ በአዋጁ መሰረት በይግባኝ ባይ ግብሩ የተወሰነበት ሲሆን ግብሩ በግምት በሚወሰንበት ጊዜም መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት የዘርፉን ዝቅተኛ ትርፍ 7.5% መሰረት በማድረግ ተወስኗል። ግብሩ በመመሪያው መሰረት የተወሰነበት ሆኖ ሳለም ይግባኝ ባዩ ከአምራች ድርጅት ጋር በተዋዋልኩት መሰረት በ1.65% ዝቅ ተደርጎ ላሰላ ይገባል በማለት ያቀረበው ክርክርም የህግ መሰረት የለውም፤የ1996 ዓ/ም የግብር ዘመን ግብር የተሰላው ይግባኝ ባይ አምኖ በገለጸው መሰረት እንጂ በመልስ ሰጪው መ/ቤት ኦዲት ተደርጎ አይደለም፣የ1997 ዓ/ም ግብርም ሲወሰን በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ሲያተርፉ የነበረውን የትርፍ ህዳግ መሰረት አድርጎ በወጣው መመሪያ መሰረት ነው። መቀጫውን እና ወለድን በተመለከተም ማንኛውም ግብር ከፋይ በህጉ የተጣለበትን የግብርና ታክስ የመክፈል ግድታ በአግባቡ ባልተወጣ ጊዜ ወለድም ሆነ መቀጫ በህጉ መሰረት የመክፈል ግድታ ስላለበት መቀጫውንም ሆነ ወለዱን የማይከፍልበት ምክንያት የለም ሲል የግብር ውሳኔው እንዲጸናበት ጠይቋል።
የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤውም ይግባኝ ባይ ያቀረበውን የይርጋ ክርክር በተመለከተ፡- መልስ ሰጪው የግብር ውሳኔውን ያስታወቀው በአዋጁ የተቀመጠው የ5 ዓመት የይርጋ ጊዜ ከማለፉ በፊት በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ያለ ሲሆን በፍሬ ጉዳዩ ላይ በሰጠው ውሳኔ ደግሞ፡-በግብር ከፋዩ የሚቀርቡትን ሰነዶችና መዝገብ ግብር አስገቢው መስሪያ ቤት በማናቸውም ምክንያት ያልተቀበለው እንደሆነ ግብሩን በግምት ላወሰን እንደሚችል በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 69(1) የተደነገገ ሲሆን መልስ ሰጪውም የይግባኝ ባይን የግብይት ሰነድ ውድቅ በማድረግ ግብሩን በግምት የወሰነው ህጉን መሰረት ያደረገ ነው፤ እንዲሁም የግምቱን አወሳሰን በተመለከተም በአዋጁ አንቀጽ 69(2) ስልቱ የመልስ ሰጪው መ/ቤት በሚያወጣው መመሪያ መሰረት እንደሚሆን በመደንገጉና መልስ ሰጪውም ግብሩን በግምት ስለሚወሰንበት ሁኔታ የገቢዎች ሚኒስቴር በ1997 ዓ/ም ባወጣው መመሪያ በተቀመጠው ስልት መሰረት ግብሩን ስለመወሰኑ ስለተረጋገጠ ይግባኝ ባይ ያቀረባቸው የቅሬታ ነጥቦች ተቀባይነት የላቸውም ሲል ይግባኙን ውድቅ አድርጓል። ከዚህ በላይ ከፍ ተብሎ እንደተጠቀሰውም ጉዳዩን በደረጃው ያሉ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ይግባኙን ውድቅ በማድረጋቸው አመልካች የሰበር አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበ ሲሆን የቅሬታ ነጥቦቹም፡- ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በዝርዘር ያቀረባቸው ነጥቦች ሲሆኑ ተጠሪውም ለጉባኤው ያቀረበውን ተመሳሳይ ይዘት ያለውን መልስ ለዚህ ችሎትም አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- አመልካች የ1997 ዓ/ም የግብር ዘመን የሂሳብ መዝገብ እና ተያያዥነት ያላቸው ሰነዶች በድርጅቱ ባጋጠመው የእሳት አደጋ በመውደማቸው ለተጠሪው መ/ቤት ማቅረብ አልችልም ሲል ያቀረበውን ክርክር የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤና የሥር ፍርድ ቤቶች በማለፍ የዘመኑን ግብር ተጠሪው በግምት መወሰኑ አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 69(1) እና በ1997 ዓ/ም የገቢዎች ሚኒስቴር ያወጣውን የግብርና ታክስ ስልት መሰረት ያደረገ ነው ሲሉ በመቀበል ክስ የቀረበበትን ገንዘብ እንዲከፍል የወሰኑት ይህንኑ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ ፍሬ ነገሮች በአግባቡ በተረጋገጡበት ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምረናል።
አመልካች የ1997 ዓ/ም የግብር ዘመን ገቢውን በማስታወቅ ግብሩን ለመክፈሉ በግራ ቀኙ የሚታመን ሲሆን ተጠሪው መስከረም 19 ቀን 2003 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ አመልካች የሂሳብ መዝገቡን እንዲያቀርብ በመጠየቁ አመልካችም መስከረም 25 ቀን 2003 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ በድርጅቱ በደረሰው የእሳት አደጋ ምክንያት ንብረቱና የሂሳብ ሰነዶቹ መውደማቸውን በመጥቀስ ማቅረብ እንደማይችል በማስታወቁ ተጠሪውም የግብሩን መጠን በግምት ስለመወሰኑ የግብር የይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በውሳኔ ላይ ካሰፈረው መገንዘብ ተችሐል። እንዲሁም በእሳት አደጋው ንብረቱ እና የሂሳብ ሰነዶቹ መውደማቸውን ለመንግስት አካል አስታውቆ የአደጋው ሁኔታ በኮልፍ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖላስ መምሪያ እንዲጣራ ስለመደረጉ እና ማስረጃም እንደተሰጠው አመልካች ከሥር ጀምሮ እየተከራከረ ይገኛል። ይሁን እንጂ ይህን አመልካች ያቀረበውን ምክንያት ተጠሪውም ሳይመረምር ግብሩን በግምት የወሰነ ሲሆን የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ እና የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም የፍድራል ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሳይመረምሩ ግብሩ በግምት መወሰኑ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 69(1) መሰረት ተገቢ ነው ሲሉ ተቀብለውታል። በእርግጥ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 69(1) ግብር ከፋዩ ምንም ዓይነት የሂሳብ መዝገብ እና ሰነድ ያልያዘ እንደሆነ ወይም በማናቸውም ምክንያት የሂሳብ መዝገቡን እና ሰነዱን የግብር አስገቢው ባለሥልጣን ያልተቀበለው እንደሆነ ወይም ግብር ከፋዩ በዚህ ህግ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ገቢውን ያላስታወቀ እንደሆነ የግብር አስገቢው ባለሥልጣን የግብሩን ልክ በግምት ለመወሰን እንደሚችል የተደነገገ ቢሆንም ግብር አስገቢው ባለሥልጣን በዚህ ድንጋጌ መሰረት ግብሩን በግምት ከመወሰኑ በፊት ግብር ከፋዩ የሂሳብ ሰነዱን ያልያዘበትን ምክንያት፣ወይም በህጉ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ገቢውን ያላታስወቀበት ምክንያት ከህጉ ጋር አገናዝቦ በመመርመር ምክንያቱ ተቀባይነት ያለው መሆን አለመሆኑን መወሰን ይኖርበታል። እንዲሁም “…በማናቸውም ምክንያት የሂሳብ መዝገቡን እና ሰነዱን የግብር አስገቢው ባለሥልጣን ያልተቀበለው እንደሆነ…” በሚል በድንጋጌው የሰፈረው ሐረግም ግብር ከፋዩ ምንም ዓይነት የሂሳብ መዝገብ እና ሰነድ ባለመያዙ ወይም የሂሳብ መዝገቡንና ተያያዥነት ያላቸውን የሂሳብ ሰነዶች ማቅረብ ባለመቻሉ ብቻ በቀጥታ ግብሩ በግምት እንዲወሰን የሚያደርግ ሳይሆን በቅድሚያ ግብር አስገቢው ባለሥልጣን ግብር ከፋዩ የሚያቀርበው ምክንያት በማስረጃ የተደገፈ መሆን አለመሆኑን፣ ምክንያቱ በማስረጃ የተደገፈ ሆኖ ቢቀርብ እንኳን ግብሩን በግምት ከመወሰን የማይከለክል መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። በዚህ በተያዘውም ጉዳይ አመልካች በድርጅቱ ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ ንብረቱና የሂሳብ ሰነዶቹ መውደማቸውን ገልጾ እስከተከራከረ ድረስም ተጠሪው አመልካች የሂሳብ መዝገብና ተያያዥነት ያላቸውን የሂሳብ ሰነዶቹ እንዲያቀርብ ታዞ አላቀረበም በሚል ግብሩን በግምት በአዋጁ አንቀጽ 69(1)መሰረት ከመወሰኑ አስቀድሞ የአመልካች ደርጅት በእሳት የተቃጠለ ስለመሆኑ፣ የእሳት ቃጠሎ ደርሶ ከሆነም ግብር እንዲከፈል በተጠየቀው ዘመን አመልካች የያዘው የሂሳብ መዝገብ እና የሂሳብ ሰነዶች መቃጠላቸውን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን አመልካች ካሉት ተቀብሎ በመመርመር እንዲሁም ተጠሪውም ከራሱ በኩል በሚኖረው የማጣሪያ መንገድ በማጣራት ማስረጃዎቹን መዝኖ ግብሩ በግምት ላወሰን የሚገባ መሆን አለመሆኑን በመለየት የአመልካችን ክርክር የማይቀበልበት በቂ ምክንያት ካለው ግብሩን በግምት መወሰን ሲገባው ክርክሩንና ማስረጃዎቹን ሳይመረምር በአዋጁ አንቀጽ 69(1)መሰረት ግብሩን በግምት መወሰኑ ተገቢነት የለውም። የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤም አመልካች ድርጅቱ በእሳት መቃጠሉንና የዘመኑ የሂሳብ መዝገቡም ሆነ ተያያዥነት ያላቸው የሂሳብ ሰነዶች በቃጠሎው ምክንያት መውደማቸውን በመግለጽ ግብሩ በግምት ላወሰን አይገባም ሲል ያቀረበውን ቅሬታ በመመርመር አመልካች የጠቀሰው ምክንያት መኖር አለመኖሩን በማስረጃዎች በማጣራት መወሰን ሲገባው ተጠሪው በግምት ግብሩን የወሰነው ህጉን መሰረት ያደረገ ነው ሲል መቀበሉም ሆነ ጉዳዩን በየደረጃ ያዩት የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሆነ የፍድራል ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተጠሪው የሰጠውን የግብር ውሳኔ ተገቢ ነው ሲሉ ማጽናታቸው ውሳኔውን ለመስጠት የሚያስችሉ ፍሬ ነገሮች በአግባቡ ባልተረጋገጡበት ሁኔታ ከመሆኑም ልላ የአመልካችን መሰረታዊ የሆነ የመሰማት መብት ባልተጠበቀበት ሁኔታ ስለሆነ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ስንል ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በመ/ቁ/706 በቀን 21/05/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ፣የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/118346 በቀን 11/04/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ እና የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/86148 በቀን 13/06/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ሽረናል።
የፍድራል የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ እና የሥር ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሰጡት ውሳኔውን ለመስጠት የሚያስችሉ ፍሬ ነገሮች ባልተሟሉበት፣ ባልተረጋገጡበት እና የአመልካች የመሰማት መብት ባልተከበረበት ሁኔታ ነው ብለናል።
በአመልካች ድርጅት ታህሳስ 23 ቀን 1998 ዓ/ም የእሳት አደጋ መድረሱን እና በ1997 ዓ/ም የግብር ዘመን አመልካች የያዘው የሂሳብ መዝገብ እና ተያያዥነት ያላቸው የሂሳብ ሰነዶች በቃጠሎው ምክንያት ስለመውደማቸው የሚያቀርባቸውን ማስረጃዎች እንዲሁም ተጠሪውም በተቃራኒው የሚያቀርባቸው ማስረጃዎች ካሉ የፍድራል የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በመስማት እና በመመዘን ግብሩ ስለሚወሰንበት ሁኔታ በግብር ህግ አዋጅ ቁጥር 286/1994 እና ከልሎች አግባብነት ካላቸው ህጎች አንጻር ጉዳዩን መርምሮ የበኩሉን ውሳኔ እንዲሰጥበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል። ይጻፍ።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሆነው መዝገብ በመጣበት አኳኋን ተመላሽ ይደረግ።
መዝገቡ የተዘጋ ስለሆነ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.