No summary available.
ግንቦት 07 ቀን2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዐቃቤ ህግ - ምህረት ቁምላቸው - ቀረቡ ተጠሪ፡-
ለዚህ ሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሁኑ የሰበር አመልካች ከሳሽነት የተጀመረው በጋምቤላ ከተማ ዙሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪዎች ደግሞ እንደ ቅደምተከተላቸው 1ኛ፣2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ነበሩ። ክሱም፡- ተከሳሾች የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91(1) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ የጉምሩክ ስነ ስርዓት ያልተፈጸመበትን እንዲሁም ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለበትን ብር 250,759.16 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ብር ከአስራ ስድስት ሳንቲም) ለመንግስት መከፈል ሲገባው ይኼው ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለበትን አርባ ስምንት በርሜል ነዳጅ እና አንድ መቶ ኩንታል ሲሚንቶ የታርጋ ኮድ ቁጥር 3-48079 ኢት በሆነ ኤርቴች የጭነት መኪና ላይ በመጫን ባሁኑ 2ኛ ተጠሪ አሽከርካሪነትና በአሁኑ ሶስተኛ ተጠሪ ረዳትነት የኢትዮጵያን መሬት ሙሉ በሙሉ ጨርሰው ሱዳን ላገቡ ሲሉ በኢትዮጵያ ድንበር ላይ በምትገኘው ኩቡሪ ኬላ ላይ በፍድራል ፓላስ አባላትና በጉምሩክ ሰራተኞች ከእነ ሕገ ወጥ እቃዎቹ እጅ ከፍንጅ ሚያዚያ 07 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን መያዛቸውን ዘርዝሮ ተጠሪዎች የኮንትሮባንድ ወንጀል ፈፅመዋል የሚል ነው።
ተከሳሾችም በሕጉ አግባብ ጥሪ ተደርጐላቸው የአሁኑ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ባለመቅረባቸው ጉዳዩ በልሉበት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ግን ቀርቦ በክሱ የተጠቀሰውን ወንጀል ክደው በመከራከራቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የአመልካችን ምስክሮች በመስማት እና ማስረጃዎቹን በመመርመር የአሁኑን 1ኛ ተጠሪ እንዲከላከሉ ትዕዛዝ ሰጥቶ ተጠሪው ከኑዌር ዞን ላሬ ወረዳ የተፃፈ ደብዳቤ እንዲሁም ጥቅምት 06 ቀን 2006 ዓ.ም በቁጥር 5/11/ ጋጉም የተፃፈ ደብዳቤ ሕጋዊ የጉምሩክ ክፍያ ከፍለው ሕጋዊ ደረሰኝ ያላቸው መሆኑና የገቢ ደረሰኝ ቁጥር 764/38 የመቶ ኩንታል ሲሚንቶ ወደ ደቡብ ሱዳን የገባበት የጉምሩክ ገቢ ደረሰኝ ለመከላከያ ማስረጃነት ማቅረባቸውን ጠቅሶ ተጠሪው በእነዚህ የሰነድ ማስረጃዎች የዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን ማስተባበላቸውን ገልፆ ሁሉንም ተከሳሾች ከክሱ በነፃ እንዲሰናበቱ ሲል ወስኗል።
በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙ ለጋምቤላ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦት የአሁኑ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ባለመቅረባቸው ጉዳያቸው በልሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ ከሰጠና አመልካችንና የሁኑን 1ኛ ተጠሪን ግን አከራክሮ ጉዳዩን በመመርመር የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የነፃ መለቀቅ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በድምፅ ብለጫ አፅንቶታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- እቃው ከኢትዮጵያ ግዛት ወደ ልላ አገር ግዛት ሕጋዊ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ሲጓጓዝ የተገኘ መሆኑ ተረጋግጦ ባለበት ሁኔታ በክልሉ በሚገኘው የወረዳው የገቢ ጽ/ቤት የተሰጠው ደረሰኝ ቀረጥና ታክሱ መከፈሉን ያሳያል ተብሎ ተጠሪዎች በነፃ መሰናበታቸው በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ቀረጥና ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን ያለው የፍድራል መንግሰት መሆኑን ባላገናዘበ መልኩ በመሆኑ ውሳኔው ላሻር ይገባል በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪዎች በሕጉ አግባብ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ባለመቅረባቸው በፅሁፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል።
የጉዳዩን አመጣጥ ከዚህ በላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ፡-ተጠሪዎች ክስ የቀረበባቸውን የኮንትሮባንድ ወንጀል ስላለመፈፀማቸው በመከላከያ ማስረጃ አስረድተዋል ተብሎ በነፃ እንዲሰናበቱ መወሰኑ በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም?የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል ።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በስር ፍርድ ቤት የመከላከያ ማስረጃ ያላቀረቡ መሆኑንና 1ኛ ተጠሪ ደግሞ ለክሱ መሰረት የሆኑትን እቃዎች ወደ ደቡብ ሱዳን ላያስገቡ ሲሉ እቃዎቹ መያዛቸውን ሳይክዱ አጥብቀው ሲከራከሩ የነበሩት እቃዎቹ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት የተፈፀመባቸው ናቸው በሚል ምክንያት ሁኖ ይህንኑ ለማስረዳት በጋምቤላ ክልል የሚገኘው የላሬ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ብር 600.00(ሰድስት መቶ ብር) የከፈሉ መሆኑን የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃ ያቀረቡ መሆኑንና የበታች ፍርድ ቤቶች ለተጠሪዎች ነፃ መለቀቅ መሰረት ያደረጉትም ይህንኑ የሰነድ ማስረጃ መሆኑን ነው።አመልካች የሚከራከረው ደግሞ ከኢትዮጵያ ግዛት ወደ ውጪ አገር በሚወጡ እቃዎች ላይ ቀረጥና ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን የፍድራል መንግስት ከመሆኑም በላይ ተከፈለ የተባለው ገንዘብ በእቃዎቹ ላይ ላከፈል ይገባ የነበረውን የቀረጥና ታክስ መጠን አይደለም፤ክልሎች በተለምዶ ለኮቴ ብለው የሚያስከፍሉ ነው በማለት መሆኑንም ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል በመሰረቱ ቀረጥና ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ህግ መንግስት በአንቀጽ 96፤97እና 98 ድንጋጌዎች ተለይቶ ተቀምጧል። እንዲሁም በእነዚህ የሕገ መንግስት ድንጋጌዎች አግባብ በፍድራል መንግስት ስልጣን የሆኑትን የታክስ ጉዳዩችን በተመለከተ ስልጣን የተሰጠው አካል በሕግ ተቋቁሞ በሕጉ የተሰጠውን ስልጣንና ሐላፊነት በመውጣት ላይ የሚገኝ ሲሆን የአዋጅ ቁጥር 578/2000 በተለይ ሲታይም የፍድራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተሰጣቸው ኃላፊነቶችና ተግባሮች በአንቀጽ6 ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ። ከኢትዮጵያ ግዛት ወደ ውጪ አገር በሚላኩ ወይም ከውጪ አገር ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ቀረጥና ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን ያለው የፍድራል መንግስት መሆኑን የኢፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 96(1) ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል።ከዚህ አንጻር ስንመለከተውም በፍድራል መንግስት ታክስና ቀረጥ እንዲያስከፍል በሕግ ስልጣን ከተሰጠው ተገቢው ቀረጥና ታክስ መከፈሉን መቆጣጠርና በሕጉ የተሰጠውን ኃላፊነት ሁሉ መወጣት ያለበት ይኼው አካል መሆኑ ከዚሁ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ እና ከአዋጅ ቁጥር 578/2000 አንቀጽ 6(8)፣9 እና 10 ድንጋጌዎች እንዲሁም ከአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 15(1)፣ 82 (1ሀ))((ለ)) ድንጋጌዎች ይዘት መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በመሆኑም በሕጉ አግባብ ስልጣን ባለው አካል ያልተከፈለ ቀረጥና ታክስ እንደተከፈለ የሚቆጠርበት የሕግ አግባብ የለም። በሕጉ አግባብ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈፀመበትን እቃ ወደ ውጪ ማስወጣትም ሆነ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 2(6)፣(2(11)፣2(17) እና 91 ድንጋጌዎች መሰረት የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው። ቀረጥና ታክሱን የከፈለው ሰው ከሐሣቡ በላይ የወንጀል ተጠያቂነት የልለበት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ወደዚህ ድምዳሜ የሚደረሰው ግን ተገቢው ቀረጥና ታክስ ከፋዩ ወገን መንግሥታዊ አካሉ ስልጣን ያለው መሆኑን በማመን ቀረጥና ታክሱን መክፈሉ ሲረጋገጥ ነው።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመጣ እቃዎቹ ወደ ደቡብ ሱዳን ላገቡ ሲሉ የተያዙ ሲሆን በእቃዎቹ ቀረጥና ታክስ የመሰብሰብ ሕጋዊ ስልጣን ያለው የፍድራሉ መንግሥት መሆኑን የሚያስገነዝብ ሲሆን ላከፈል ይገባ የነበረው ቀረጥና ታክስ መጠንም ብር 250,759.16 ሣንቲም መሆኑን አመልካች ጠቅሶ የተከራከረበትና ማስተባበያ ማስረጃዎች ያልቀረቡበት ጉዳይ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ከፈሉ የተባለው ገንዘብ በጉዳዩ ላይ ቀረጥና ታክስ ለመሰበሰብ ስልጣን በልለው ለክልሉ የወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ገቢ የሆነ ከመሆኑም በላይ መጠኑም ብር 600.00 /ስድስት መቶ ብር/ ብቻ መሆኑን ተጠሪው ያቀረቡት የሰነድ ማስረጃ ያረጋግጣል።
ይህ ደግሞ በእቃዎቹ ላይ ተገቢው ቀረጥና ታክስ በሕጉ ስልጣን በተሰጠው አካል ተሰብስቧል ለማለት የማይቻል ከመሆኑም በላይ 1ኛ ተጠሪ እቃዎቹ ከውጪ አገር የገቡና የተከፈለባቸው ቀረጥና ታክስ ምን ያህል እንደሆነ የሚታወቅ እንደመሆኑ መጠን ወደ ውጪ ሲወጡ ላከፈል ይችል የነበረውን የቀረጥና ታክስ መጠን እንዲሁም ስልጣን ያለውን አካል አያውቁም ለማለት የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን የሚያስገነዝበን ነው። በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ታክስና ቀረጥ የመሰብሰብና ሕጉን የማስከበር ኃላፊነት ያለውን አካል አግባብነት ካላቸው ሕጐች አንፃር ሣይመለከቱና 1ኛ ተጠሪ ከፈልኩ የሚሉት የገንዘብ መጠን በእቃዎቹ ላከፈል ይገባ የነበረውን የገንዘብ መጠን ያህል ያለመሆኑን በማስረጃዎቹ መረጋገጡን ሣያገናዝቡ ተጠሪዎችን ነፃ ማሰናበታቸው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ውሣኔ ሁኖ አግኝተናል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የጋምቤላ ከተማ ዙሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.05823 በቀን 10/03/2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.01557 በቀን 08/05/2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት በአብላጫ ድምጽ የፀናው ውሣኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/.ቁ. 195(2)(ሀ) መሰረት ተሽሯል።
ተጠሪዎች በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91(1) ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ የተላለፉ ጥፋተኞች ናቸው በማለት ወስነናል።
No topics extracted.