No summary available.
ሐምል 29 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- አቶ ተክለብርሃን ዘገየ /ጠበቃ መረሳ ፍስሐ ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1.አቶ ሸምሰዲን አክመል 2. አቶ ሬድዋን ኸይረዲን 1ኛ ተጠሪ ከጠበቃ አበራ አንጃ 3. አቶ መሐመድ አክመል 4. በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 8 አስተዳደር ጽ/ቤት - ነ/ፈጅ ፍጹም ካሳዩ ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የመንግስት የንግድ ቤት የተከራይነት መብትን የሚመለከት ክርክር ሲሆን አመልካች በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ06/10/2004 ዓ.ም በተጠሪዎቹ ላይ ባቀረቡት ክስ አመልካች በወረዳ 8 የሚገኘውን ቁጥሩ 144/495/145/516 የሆነውን የንግድ ቤት ከ4ኛ ተጠሪ ተከራይተው የንግድ ስራ ሲሰሩበት መቆየታቸውን እና ይሁን እንጂ 4ኛ ተጠሪ ውሉን አላግባብ ያቋረጠባቸው መሆኑን የሚገልጽ ሆኖ 4ኛ ተጠሪ ውሉን ከአመልካች ጋር እንዲቀጥል እና ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተመለከቱት ተጠሪዎች ደግሞ የንግድ ቤቱን እና በሱቁ ውስጥ የሚገኙትን ንብረቶች እንዲያስረክቡ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው።ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተመለከቱት ተጠሪዎች ፍርድ ቤቱ ክሱን ለማየት የሚያስችል የስረ ነገር ስልጣን የለውም የሚል መቃወሚያ በማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ ይህንኑ የመጀመሪያ ደረጃ የመቃወሚያ ነጥብ መርምሮ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በባለቤትነት የሚያሰተዳድራቸውን ቤቶች የሚመለከት በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 መሰረት ጉዳዩን የማየት ስልጣን የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች እንጂ የፍድራል ፍርድ ቤቶች አለመሆኑን እና የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ በ23/03/2001 ዓ.ም የሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉምም ይህንኑ የሚያስገነዝብ መሆኑን ገልጾ ጉዳዩን የማየት የስረ ነገር ስልጣን የለኝም በማለት አመልካች ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተመለከቱት ተጠሪዎች በሱቁ ውስጥ ያሉትን ንብረቶች ያስረክቡኝ በሚል ያቀረቡትን ጥያቄ በተመለከተ መዝገቡ በሬጅስትራር ጽ/ቤት በኩል ጉዳዩን ለማየት ለተመደበው ችሎት እንዲያስተላልፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠውን የብይን ክፍል ሲያጸናው ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተመለከቱት ተጠሪዎች በሱቁ ውስጥ ያሉትን ንብረቶች ያስረክቡኝ በሚል አመልካች ያቀረቡትን ጥያቄ በተመለከተ መዝገቡ በሬጅስትራር ጽ/ቤት በኩል ጉዳዩን ለማየት ለተመደበው ችሎት እንዲመራ የተሰጠውን የብይኑን ክፍል ግን በመሻሩ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ አመልካች በተጠሪዎች ላይ የመሰረቱት ክስ ተጠሪዎቹ በአመልካች የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ ንብረትና ይዞታ ላይ በግብረአበርነት እየፈጸሙት ያለው ሁከት በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 1149(1) መሰረት ተወግዶ ሀብትና ንብረቴን ለቀው ያስረክቡኝ የሚል ሆኖ እያለ የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይህን መሰል ጉዳይ የማከራከር ስልጣን የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ነው በማለት የመወሰኑን እና ውሳኔው በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጽናቱን አግባብነት ተጠሪዎች ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል። የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡-
ክስ የቀረበበት ጉዳይ የሚወድቀው በፍድራል ፍርድ ቤቶች ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር ነው በማለት የተሰጠው የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ወይስ አይደለም?
ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተመለከቱት ተጠሪዎች በሱቁ ውስጥ ያሉትን ንብረቶች ያስረክቡኝ በሚል አመልካች ያቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ ከዋናው የዳኝነት ጥያቄ ተነጥሎ በፍድራል ፍርድ ቤቶች እንዲታይ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ወይስ አይደለም?
የሚሉትን ነጥቦች መሰረት በማድረግ አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለጉዳዩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል።
በዚህም መሰረት የመጀመሪያውን ነጥብ በተመለከተ ተጠሪዎቹ የሁከት ተግባር ፈጥረውብኛል በማለት አመልካች የሚከራከሩት 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የንግድ ሱቃቸው ተቀጣሪዎች ሆነው እያለ መመሪያ ቁጥር 4/2004 መውጣቱን ምክንያት አድርገው የንግድ ሱቁን ከአመልካች የተከራዩ አስመስለው ለ4ኛ ተጠሪ በማቅረብ የተከራይነት መብቱ አላግባብ ወደ ራሳቸው እንዲዛወር አድርገዋል፤4ኛ ተጠሪም በአመልካች እና በልሎች ተጠሪዎች መካከል ያለውን የግንኙነት ዓይነት በአግባቡ ሳያጣራ ከአመልካች ጋር የነበረውን ውል በማቋረጥ ውሉን ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር አድርጓል፤3ኛ ተጠሪም የ1ኛ ተጠሪ ወንድም በመሆን በሱቁ ውስጥ ተገኝቷል በማለት መሆኑን ከክርክራቸው ተገንዝበናል።እንደሚታየው የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ በቀጥታ ከመመሪያ ቁጥር 4/2004 አፈጻፀም ጋር የተያያዘ ነው።1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የአመልካች ነበር በተባለው የንግድ ሱቅ የገቡት አመልካች እንደሚከራከሩት በሰራተኝነት ነው ወይስ ተጠሪዎቹ እንደሚከራከሩት የንግድ ቤቱን ከአመልካች በመከራየታቸው ነው? የሚለው አከራካሪ ጭብጥ ጭምር ከመመሪያው አፈጻጸም ጋር ተያይዞ የሚታይ እና ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ተመርምሮ ውሳኔ የሚሰጥበት ነው።የንግድ ቤቱ ተከራይ ከነበሩት ከአመልካች እና እንደ አመልካች አባባል በሰራተኛነት፤እንደ ተጠሪዎች አባባል ደግሞ በተከራይነት ወደ ንግድ ሱቁ ገብተዋል ከተባሉት ተጠሪዎች መካከል በመመሪያ ቁጥር 4/2004 መሰረት የተከራይነት መብት ላያገኝ የሚገባው ማነው? የሚለው ጥያቄ በመሰረቱ በመመሪያው ላይ የተመለከቱትን ዝርዝር መስፈርቶች መሰረት አድርጎ ምላሽ የሚያገኝ የመመሪያ አፈጻጸም ጉዳይ ከሚሆን ውጪ ከሁከት ድርጊት ጋር ግንኙነት ያለው ጉዳይ አይደለም።
መመሪያውን መሰረት አድርጎ የሚነሳ የንግድ ቤት የተከራይነት መብት ጥያቄ ከከተማው አስተዳደር አስፈጻሚ አካላት የመቆጣጠር ስልጣን እና ተግባር ጋር እንዲሁም የከተማው አስተዳደር ከሚያስተዳድራቸው የመንግስት ቤቶች ጋር የተያያዘ እስከሆነ እና የከተማው አስተዳደር አካልም በተከሳሽነት የተሰየመ እስከሆነ ድረስ ደግሞ የዚህ ዓይነት ጉዳዮችን ተቀብሎ የማስተናገድ የስረ ነገር ስልጣን የከተማው ፍርድ ቤቶች ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 361/1995 በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር በአንቀጽ 41(1) (ለ) እና (ረ) ስር በግልጽ የተመለከተ በመሆኑ የዚህ ዓይነቱ ክስ የሁከት ስም ተሰጥቶት በመቅረቡ ብቻ በፍድራል ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር ላወድቅ የሚችልበት የህግ አግባብ አይኖርም።አመልካች ጠቅሰው የሚከራከሩበት በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይም ከመመሪያ ቁጥር 4/2004 አፈጻጸም ጋር ግንኙነት ያለው ባለመሆኑ በዚህ መዝገብ ለተያዘው ክርክር ተፈጻሚነት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።
በመሆኑም ክስ የቀረበበት ጉዳይ የሚወድቀው በፍድራል ፍርድ ቤቶች ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር ነው በማለት የተሰጠው የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።
ሁለተኛውን ነጥብ በተመለከተ የአመልካች ዋነኛው የዳኝነት ጥያቄ አላግባብ የተወሰደብኝ የንግድ ቤቱ የተከራይነት መብት ላመለስልኝ ይገባል የሚል ሲሆን ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተመለከቱት ተጠሪዎች በሱቁ ውስጥ ያሉትን ንብረቶች ያስረክቡኝ በሚል የቀረበው ጥያቄ ዋናውን ጥያቄ ተከትሎ የቀረበ ተጨማሪ የዳኝነት ጥያቄ ነው።ይህ ተጨማሪ የዳኝነት ጥያቄ በመሰረቱ የሚወድቀው በፍድራል ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር ነው።ይሁን እንጂ የዳኝነት ጥያቄው የቀረበው ብቻውን ወይም ራሱን ችሎ ሳይሆን ዋነኛውን የዳኝነት ጥያቄ ተከትሎ ነው።የዚህ ዓይነት ጉዳዮችን በተመለከተ በአንድ ክስ ውስጥ ብዙ አቤቱታዎች ቀርበው ከነዚሁ በከፊል ዋናውን ክስ የሚመለከቱ በከፊል ደግሞ ዋናውን ክስ መነሻ አድርገው ቅርንጫፍ ነገሮችን የሚመለከቱ በሆነ ጊዜ የፍርድ ቤቱ ስልጣን የሚወሰነው ከፍተኛ ግምት ያለውን አቤቱታ መሰረት አድርጎ በመከተል ስለመሆኑ በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 17(2) ስር የተደነገገ በመሆኑ የአመልካች የንብረት ያስረክቡኝ ጥያቄ የንግድ ቤቱን የተከራይነት መብት ከሚመለከተው ዋነኛው የዳኝነት ጥያቄ ተነጥሎ ለብቻው ላታይ የሚችል አይደለም።የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአመልካችን የንብረት ያስረክቡኝ የዳኝነት ጥያቄ ጭምር ከዋናው ጉዳይ ጋር በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መታየት እንደሚገባው ገልጾ መመለስ ሲገባው ተነጥሎ በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታይ ትዕዛዝ መስጠቱም ሆነ ይግባኙ የቀረበለት ፍርድ ቤትም በዚህ ረገድ ግልጽ የሆነ ውሳኔ አለመስጠቱ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
ሲጠቃለል አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ በ07/03/2005 ዓ.ም ተሰጥቶ በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ በ04/02/2006 ዓ.ም ተሻሽሎ የጸናው ውሳኔ በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
በተራ ቁጥር 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ ክስ የቀረበበት ጉዳይ የሚወድቀው በፍድራል ፍርድ ቤቶች ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር ነው በማለት የተሰጠው የውሳኔ ክፍል በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል።
በተራ ቁጥር 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተመለከቱት ተጠሪዎች በሱቁ ውስጥ ያሉትን ንብረቶች ያስረክቡኝ በሚል አመልካች ያቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ ከዋናው የክስ ምክንያት ተነጥሎ በፍድራል ፍርድ ቤቶች እንዲታይ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተመለከቱት ተጠሪዎች በሱቁ ውስጥ ያሉትን ንብረቶች ያስረክቡኝ በሚል አመልካች ያቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 17(2) በተመለከተው መሰረት የንግድ ቤቱን የተከራይነት መብት ከሚመለከተው ዋናው የዳኝነት ጥያቄ ጋር በአንድነት በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦ በአንድነት ላስተናገድ የሚገባው ነው በማለት ወስነናል።
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤቶች ይላክ።
የሰበር ክርክሩን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.