No summary available.
መጋቢት 26 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙሰጠፋ አህመድ አመልካች፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማርች ፕሮጀክት፡- ነ/ፈጅ አላዮ አምበርብር ቀረቡ ተጠሪ፣- 1. ቤተልሕም ሽፈራው 2. አሸናፊ ሀደራ ጠበቃ ግንቡ መኮንን ቀረቡ 3. ሮማን ታደሰ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥል።
ጉዳዩ በአመልካችና በተጠሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት የሚገዛበትን የሕግና ዳኝነት የሚሰጠውን አካል በተመለከተ በግራ ቀኙ መካከል የተነሳውን ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪዎች ባሁኑ አመልካችና በበሽታዎች መከላከል እና ቁጥጥር ማዕከል ላይ በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው። የክሳቸው ማመልከቻ ይዘትም ባጭሩ፡- በአሁኑ አመልካች መስሪያ ቤቱ በተለያየ ጊዜና በተለያየ የስራ መደብ ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተው አመልካች የስር 1ኛ ተከሳሽ የነበረው የበሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል የሰጠውን ውክልና በመጠቀም በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ከተደነገገው ውጪ የስራ ቅነሳ ያደረገባቸው መሆኑን ዘርዝረው እርምጃው ሕገ ወጥ ተብሎ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍሐቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሁኑ አመልካች ለተጠሪዎች ክስ በሰጠው መልስም፡- አመልካች መስሪያ ቤት በአዋጅ የተቋቋመና በመንግስት በሚመደብለት አመታዊ በጀት የሚተዳደር የፍድራል መንግስት መስሪያ ቤት ነው፣ የፍድራል መንግስት የአስተዳደር መስሪያ ቤቶችና ሰራተኞች የስራ ግንኙነትን በተመለከተ ደግሞ ራሱን የቻለ የሰራተኞች ሕግ እና አስተዳደር ፍርድ ቤት ያለ በመሆኑ ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚታይበት አግባብ የለም በማለት ተከራክሯል። 1ኛ ተከሳሽ የነበረው አካል ግን በሕጉ አግባብ ጥሪ ተደርጎለት ባለመቅረቡ ጉዳዩ በልለበት እንዲታይ ተደርጓል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም አመልካች መስሪያ ቤት በበጀት የሚተዳደር የመንግስት መስሪያ ቤት በመሆኑ ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 የሚዳኝና በመደበኛ ፍርድ ቤትም የሚታይ አይደለም በማለት መዝገቡን የዘጋው ሲሆን ተጠሪዎች በዚህ የስር ፍርድ ቤት ብይን ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች በኤች.አይ.ቪ መከላከል ላይ ጥናት አድርጎ ባቀረበው የምርመራ ውጤት መሰረት በስር 1ኛ ተከሳሽ በነበረው አካል ፈንድ ተደርጎለት በራሱ ስራ የሚሰራ ተቋም እንጂ የአመልካች ወኪል አይደለም። ስለዚህ አመልካች በመንግስት የተመደበለትን በጀት መሰረት አድርጎ መደበኛ የመማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር የሚያካሂድ አካል አይደለም፣ አመልካች ተጠሪዎችን በመንግስት ሰራተኝነት የቀጠራቸው መሆኑን በማስረጃ አስደግፎ አላስረዳም የሚሉትን ምክንያቶችን አስፍሮ በአመልካችና በተጠሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 የማይሸፈንበት እንደዚሁም ክርክር የተነሳ እንደሆነ በመደበኛ ፍርድ ቤት የማይዳኝበት ምክንያት አይኖርም ሲል ደምድሞ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮ በፍሬ ጉዳዩ ላይ አከራክሮ ዳኝነት እንዲሰጥበት ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት መልሶ ልኮለታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካች የሰበር መሰረታዊ ይዘትም፡- አመልካች የፍድራል መንግስት መስሪያ ቤት ሆኖ ሰራተኞቹን የሚያስተዳድረው በሲቪል ሰርቪስ ህግ መሰረታዊ መርሆዎች መሰረት ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 515/1999 ተመልክቶ እያለ እንዲሁም ተጠሪዎች በአዋጅ ቁጥር 515/1999 መሰረት መብቱን ለፍድራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍ/ቤት ማቅረብ ሲገባቸው ለመደበኛ ፍርድ ቤት ማቅረባቸው ትክክል ነው ተብሎ ጉዳዩን በይግባኝ በተመለከተው በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መወሰኑ ያላግባብ ነው በማለት ተከራክሯል። አቤቱታው ተመርምሮ በሰበር ችሎቱ ላታይ የሚገባው ነው በመባሉ ምክንያት ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው በሰጡት የጽሑፍ መልስ፤ የአመልካች አቤቱታ የህግ መሰረት የለውም፣ ተጠሪዎች የተቀጠሩት አመልካች በሚያከናውነው የፕሮጀክት ስራ በመሆኑ ጉዳዩ የሚገዛው በአዋጅ ቁጥር 377/1999 እንጂ በአዋጅ ቁጥር 515/1999 አይደለም፣ አመልካች በኮንትራት የተቀጠሩትን የመንግስት ሰራተኞችን ጉዳይ ለመግዛት በሚመለከተው አካል የወጣ መመሪያ ጉዳዩ ላገዛ ይገባል በማለት የሚያቀርበው ክርክርም ተጠሪዎች በመመሪያው መሰረት የተቀጠሩት መሆኑን የቅጥር ውሉ በማያመላክትበት ሁኔታ የቀረበ የክርክር ነጥብ በመሆኑ ተቀባይነት የልለው መሆኑን ገልጸው ጉዳዩ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የሚታይ ነው ተብሎ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መወሰኑ ሕጉን መሰረት ያደረገ ነው ሲሉ ተከራክረዋል። አመልካች በበኩሉ የሰበር አቤቱታውን በማጠናከር የመልስ መልሱን ሰጥቷል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀ ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ፡- የበታች ፍ/ቤቶች ጉዳዩን ለመዳኘት ሥልጣን የልላቸው መሆኑን አመልካች ያነሳውን መቃወሚያ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎ መወሰኑ ተገቢ ነው ? ወይስ አይደለም? የሚለው ጭብጥ ሆኖ ተገኝቷል።
በመሰረቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር በ214/2003 አንቀጽ 2(1) እና (3) ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መረዳት የሚቻለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የፍድራል መንግስት መስሪያ ቤት ሆኖ የተቋቋመ መሆኑ ነው። ዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 እና በፍድራል ዩኒቨርስቲዎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 210/2003 መሰረት የሚተዳደር መሆኑን ተጠቃሹ ደንብ በግልጽ የሚደነግገው ጉዳይ ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 5(1)ደግሞ ዩኒቨርሲቲው በፍድራል መንግስት በጀት የሚተዳደር መሆኑን፣ በአዋጁ አንቀጽ 29 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ደግሞ የተቋሙ ተቀጣሪ ሰራተኞች አይነትን የሚያመለክቱ ድንጋጌዎች እንዲሁም ቅጥሩ ስለሚመራበት አግባብ የሚገልፁ ድንጋጌዎች ተቀምጠው እናገኛለን። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተቋቋመባቸው ተግባሮች አንዱ ምርምርና ጥናት ማካሄድ መሆኑ ይታወቃል። ይህን ለማከናወን ደግሞ ፕሮጀክት ቀርጾ ሰራተኛን ከመቅጠር ጀምሮ ተገቢውን ሁሉ የሚፈጽም መሆኑ ይታመናል። እንዲህ ከሆነ ተጠሪዎች የተቀጠሩበት ፕሮጀክት በዩኒቨርሲቲው የሚተዳደር እንጂ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት አለው ላባል የሚችል አይደለም።
ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አመልካች ፕሮጀክት በአዋጅ ቁጥር 650/2001 እና በደንብ ቁጥር 210/2003 አግባብ የሚተዳደር ሆኖ እያለ ለምርምር ስራ የሚቀጠሩ ሰራተኞች የሚያቀርቡትን አቤቱታ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የመቀበልና ውሣኔ የመስጠት ስልጣን ለመደበኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ ነው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው ለዩኒቨርሲቲው በሕጉ አግባብ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር ባገናዘበ መልኩ ነው። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መደበኛ ፍርድ ቤቶች ለማየት እንደህጋዊ ምክንያት አድርጎ ከወሰደባቸው ምክንያቶች አንዱ አመልካች ተጠሪዎች በኮንትራት የተቀጠሩ ሰራተኞች ስለመሆናቸው በማስረጃ አላስደገፈም በማለት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ነጥብም ቢሆን የተጠሪዎች ግንኙነት በመንግስት በጀት በሚተዳደር መስሪያ ቤት ስር ባለው አካል ጋር የተመሰረተ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 515/1999 እና በመንግስት የበጀት መስሪያ ቤቶች የቅጥር ሁኔታዎችን በሚደነግጉት ደንቦችና መመሪያዎች አንጻር ስልጣን ባለው አካል እንዲታይ ከሚደረግ በስተቀር ጉዳዩን በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት ለመዳኘት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት አይደለም። በመንግስት በጀት በከፊልም ሆነ በሙሉ የሚተዳደሩ መስሪያ ቤቶች የተቀጠሩ ሰራተኞች ግንኙነታቸው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ የማይገዛ መሆኑን የተጠቃሹ አዋጅ አንቀጽ 3 (2)(ሰ) ድንጋጌ ጋር ከአዋጅ ቁጥር 515/1999 አንቀጽ 3 ድንጋጌ ጋር አዛምደን ስንመለከተው የምንረዳው ጉዳይ ነው። በመንግስት መስሪያ ቤት በኮንትራት የሚቀጠሩ ሰራተኞችን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 515/1999 አንቀጽ 22(3) የኮንትራት ሰራተኛ የቅጥር አፈጻጸም መመሪያ ያወጣል ተብሎ የተደነገገ ሲሆን በሕጉ ስልጣን የተሰጠው የፍድራል ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ በሕጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት “የፍድራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የጊዜያዊ /ኮንትራት/ ሰራተኞች ቅጥር አፈጻጸም መመሪያ“ የሚል ርዕስ የተሰጠበትን ፣ በመግቢያውም ለፍድራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ስለሚቀጠሩ ጊዜያዊ /ኮንትራት/ ሰራተኞቹ አቀጣጠር፣ መብቶችና ግድታዎች በግልጽ የሚያስቀምጥ መመሪያ ማውጣት ማስፈለጉን፣ የጊዚያዊ ሰራተኞች ምልመላና መረጣ በችሎታ፣ በግልጽነት ከአድሎ ነጻ በሆነ ውድድር ላይ እንዲመሰረት ለማድረግ፣ በቀጣሪና በተቀጣሪ መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች ፍትህ ለመስጠት እንዲረዳ እና በሁሉም የፍድራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ግልጽ የሆነ አፈጻጸም እንዲኖር ለማድረግ ተብሎ ዓላማው ተለይቶ የተቀመጠለት መመሪያን አውጥቶ ከህዳር ወር 2000 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውል አድርጓል።
በአመልካችና በተጠሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት በዚህ መመሪያ የሚገዛ መሆን ያለመሆኑን ላለይ የሚችለው ደግሞ ጉዳዩ ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ ውጪ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ሲቀርብ ነው። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ጉዳዩ ላታዩ የሚገባው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 ሳይሆን በአዋጅ 650/2001፣ ደንብ ቁጥር 214/2003 እና ደንብ ቁጥር 210/2003 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 515/1999 በተዘረጋው ስርዓት ሆኖ አግኝተናል። በዚህም መሰረት ተከታዩን ወስነናል።
በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሰኔ 13 ቀን 2006 ዓ.ም. የተሰጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1)መሰረት ተሽሯል።
ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 515/1999 መሰረት በተዘረጋው ስርዓት የሚታይ እንጂ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት በስራ ክርክር ችሎት የሚታይ አይደለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.