No summary available.
መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንገሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ግርማ አያልው ዋልታንጉስ ቀረቡ ተጠሪ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጽ/ቤት ነ/ፈጅ ቁምነገር ደጉ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የአ/አ/ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ሰለጠየቁ ነው። ጉዳዩም የመንግስትሰራተኞች የሰራ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩም የተጀመረው በአ/አ/ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ አስተዳደር ፍ/ቤት ነው በዚያ ደረጃ አመልካች ይግባኝ ባይ ተጠሪ ደግሞ መልስ ሰጪ በመሆን ተከራክሯል። አመልካች በ17/04/2005 ዓ.ም በተፃፈ ለአስተዳደር ፍ/ቤት ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ አመልካች ሰራተኞችን በስርዓት መምራት አልቻለም፣ የስራ ግድታውን በአግባቡ አልተወጣም በሚል እና እንዲሁም ላፕቶፕ ኮምፒውተር ሣልረከብ ተረክበሃል በሚል የተጠሪ መስሪያ ቤት የዲሲፕላን ኮሚቴ ያለምንም ማስረጃ ያለአግባብ ጥፋተኛ ካደረገኝ በኋላ ከስራ እንዲሰናበት በማለት የሰጠው ውሣኔ ስህተት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው ውሣኔው ተሽሮ ወደ ስራ እንዲመለስ ጠይቋል።
ጉዳዩን የተመለከተው የአስተዳደር ፍ/ቤቱም በበኩሉ በቀረበው ይግባኝ አቤቱታ ላይ ግራ ቀኙን አስቀርቦ እንዲከራከሩ ካደረገና እንዲሁም በመስሪያ ቤቱ ዲስፕላን ኮሚቴ ክርክር ደረጃ ተጠሪ አሰምቶ የነበረውን ምሰክሮችም አስቀርቦ በድጋሚ ቃላቸውን ከተቀበለ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ማስረጃ ከመዘነ በኋላ አመልካች ፈጽመዋል ከተባሉት የዲስፕላን ጥፋቶች ውስጥ ስለ ላፕቶፕ ኮምፒውተርን በተመለከተ አመልካች ኮምፒውተሩን ከመ/ቤቱ ተቀብሎ አለመመለሱ በበቂ ማሰረጃ ስላልተረጋገጠ በዚህ ረገድ ለቀረበበት የዲስፕላን ክስ ተጠያቂ ላሆን አይገባም በማለት ከወሰነ በኋላ ልሎች ጥፋቶችን በተመለከተ ግን ማለትም አመልካች ከሰራተኞች ጋር ያለው መልካም ግንኙነት አናሣ ስለመሆኑና ከሰራተኞች ጋር ተባብሮ በስምምነት መሰራት አለመቻል በሚመለከት የቀረበበትን የዲስፕላን ጥፋቶች መፈጸሙ በሚገባ በማስረጃ ተረጋግጦበታል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ካሰፈረ በኋላ እና እነዚህን ጥፋቶች በተመለከተም በ2 ወር የደመወዝ ቅጣት እንዲቀጣ ሲል በተጠሪ መ/ቤት የዲስፕላን ኮሚቴ የተሰጠውን የሰንብት ውሣኔ በማሻሻል ወሰኗል።
በአሁኑ ተጠሪ ቅሬታ አቅራቢነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የከተማ አስተዳደሩ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በበኩሉ ግራ ቀኙን አስቀርቦ ከሰማ በኋላ የአስተዳደር ፍ/ቤቱን ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 348/1/ መሰረት በማጽናት ወስኗል። በልላ በኩል አሁንም ባአሁኑ ተጠሪ ሰበር አቤቱታ አቅራቢነት ጉዳዩን የተመለከተው የከተማ አስተዳደሩ ሰበር ችሎት በበኩሉ ግራ ቀኙን አስቀርቦ እንዲከራከሩ ካደረገ በኋላ ጉዳዩን በመመርመር አመልካች ላፕቶፕ ኮምፒዩተሩን ወስዶ አለመመለሱ የተጠሪ መ/ቤት የዲስፕላን ኮሚቴ በሰነድና በሰው ማስረጃ በበቂ ሁኔታ አረጋግጦ እያለ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ ግን ይሄንን አላአግባብ ውድቅ በማድረግ የሰጠው ውሳኔ ማስረጃን መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት መሆኑንና እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤትም ይሄንኑ ስህተት ማረም ሲኖርበት ማጽናቱ እንዲሁ መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈፀሙን ከገለፁ በኋላ የአስተዳደር ፍ/ቤቱንና የከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱን ውሳኔ በማሻሻል በተጠሪ መ/ቤት ዲስፕላን ኮሚቴ የተሰጠውን ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ በማጽናት ወስኗል፡ አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይሄንኑ በከተማ አስተዳደሩ ሰበር ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ሲሆን መሰረታዊ ይዘቱም፡- የስር አስተዳደር ፍ/ቤቱ የቀረበውን ማስረጃ በመመርመር እና በመመዘን አመልካች የመ/ቤቱን ላፕቶፕ መውሰዱ በማስረጃ በበቂ ሁኔታ አልተረጋገጠም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ የሰጠው ውሳኔ በከተማ አስተዳደሩ ሰበር ችሎት “አመልካች አከራካሪውን ላፕቶፕ ወስዶ አለመመለሱ ተረጋግጦበታል” በማለት የበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ መቀየሩ በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ የማስረጃ ምዘናን ተግባር መሰረት በማድረግ ስለሆነና ውሳኔው ከዚህ አኳያ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ተሽሮ በአስተዳደር ፍ/ቤቱ እና በከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱ የተሰጠው ውሳኔ ይፅናልኝ የሚል ነው። አቤቱታውም በሰበር አጣሪ ችሎቱ ተመርምሮ ለሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ ላታይ ይገባል በመባሉ ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሁፍ ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ባጭር ባጭሩ ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን እኛም በበኩላችን የከተማ አስተዳደሩ ሰበር ችሎት የአስተዳደር ፍ/ቤቱንና የከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱን ውሳኔ የለወጠው በህግ ከተሰጠው መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበትን ውሳኔ የማረም ስልጣን ውጭ በማውጣት መሆን አለመሆኑን በጭብጥነት ይዘን ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
በመጀመሪያ ደረጃ የአ/አ/ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት የሚል ወገን ካለ ይሄንኑን ለከተማ አስተዳደሩ ሰበር ችሎት ማቅረብ እንደሚችልና ሰበር ችሎቱም በበኩሉ የመጨረሻ ውሳኔ ባገኙ ጉዳዮች ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የህግ ስህተት ካለ ይሄንኑን አይቶና መርምሮ ለማረም ስልጣን እንደተሰጠው ከተሻሻለው የአ/አ/ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 42(2) ድንጋጌ ይዘት የምንገነዘበው ጉዳዩ ነው።
በልላ በኩል በተያዘው ጉዳይ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ የተጠሪ መስሪያ ቤት ዲስፕላን ኮሚቴ ላፕቶፕ ኮምፒውተርን በሚመለከት የቀረበውን የዲስፕላን ክስ በተመለከተ የሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔ በይግባኝ ስልጣኑ ተጠቅሞ ላለውጥ የቻለው ግራ ቀኙ በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ክርክር መሰረት በማድረግ በዲስፕላን ኮሚቴ ክርክር ደረጃ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው የነበሩ የተጠሪ መ/ቤት ሰራተኞች በድጋሚ አስቀርቦ ቃላቸውን እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ አመልካች አከራካሪውን ላፕቶፕ ስለመውሰዱ በማስረጃ ተረጋግጦበታል? ወይስ አይደለም? የሚለውን አከራካሪ የነገር ጭብጥ በማስረጃ በድጋሚ እንዲጣራ በማድረግ እና እነዚህ የቀረቡትን ማስረጃዎችም ከተያዘው ጭብጥ አንፃር አገናዝቦ በመመርመርና በመመዘን ተገቢ ነው ያለውን ክብደት ለማስረጃዎቹም በመስጠትና በስተመጨረሻም አመልካቹ ላፕቶፑን ስለመውሰዱ በበቂ ማስረጃ አልተረጋገጠም የሚል የፍሬ-ነገር ድምዳሜ ላይ ከደረሰ በኋላ ስለመሆኑ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ግልባጭ ያስረዳል። ይህ የፍሬ-ነገር ድምዳሜም በአ/አ/ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ተቀባይነት አግኝቷል።
ሆኖም የአ/አበባ ከተማ አሰተዳደር ሰበር ችሎት በበኩሉ ይሄንን ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ላፕቶፕ ኮምፒውተር በአመልካች አለመወሰዱ በማስረጃ ተጣርቶና እንዲሁም ማስረጃውም ተመዝኖ የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበትን ፍሬ ነገር እንዳለ ተቀብሎ በህግ ረገድ ብቻ በስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የህግ ስህተት ካለ ያንን ብቻ አይቶ ማረም ሲገባ በህግ ተወስኖ ከተሰጠው የስልጣን ገደብ ውጭ በመውጣትና የማስረጃ ምዘና ተግባር ውስጥ በመግባት አመልካች አከራካሪውን ላፕቶፕ ወስዶ አለመመለሱ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ በበቂ ሁኔታ ተረጋግጦበታል በማለት የፍሬ ነገር ክርክርን ለማጣራትና ማስረጃን ለመመዘን በህግ ስልጣን ከተሰጠው የአስተዳደር ፍ/ቤቱ የተለየ የፍሬ ነገር ድምዳሜ ላይ በመድረስ የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ለውጦ በተጠሪ መስሪያ ቤት ዲሲፕላን ኮሚቴ የተሰጠውን የስንብት ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ በማፅናት የሰጠው ውሳኔ ከአዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 42 (2) ድንጋጌ ይዘት ፣መንፈስና አላማ አኳያ ውሳኔው መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል።
በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የአ/አ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 2ዐዐ5 በ7/12/2005 ዓ.ም በአብላጫ ድምፅ የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ሰ/ሥ/ህ/ቁ.348(1)መሰረት ተሽሯል።
በአ/አ/ከ/አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ አስተዳደር ፍ/ቤት በመ/ቁ.643/05/ በ2/72005 ዓ.ም ተወስኖ በአ/አ/አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በመ/ቁ.17945 በ7/8/2005 በሰጠው ውሳኔ እንዲፀና የተደረገው ፍርድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.348 (1) መሰረት ፀንቷል።
ግራ ቀኙ የሰበር ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
የውሳኔ ግልባጩ ለሰር ፍ/ቤቶች ይድረስ።
No topics extracted.