No summary available.
መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ረዳት ሳጂን አህመድ ለገሰ ---ጠበቃ አድምጠው በለጠ ቀረቡ ተጠሪ፡- የፍድራል ዐቃቤ ሕግ --- ዐ/ህግ መኩሪያ አለሙ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በመሰረተው ክስ መነሻ ነው። ክሱም በስር ፍርድ ቤት በስድስት ምድብ ተከፍሎ የቀረበ ሆኖ አመልካች ጥፋተኛ የተባለው በአምስት ክሶች ነው። አመልካች ጥፋተኛ የተባለባቸው ክሶችም እንደሚከተለው በአጭሩ የተገለጹ ናቸው።
የ1ኛው ክስ አመልካች በ1996 ዓ.ም. የወጣውን በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 27(1)እና 598(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ወደ ውጪ ለመላክ የሚያስችል ምንም አይነት ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበል 05/06/07 ክልል ልዩ ቦታው ቂርቆስ ቴል አካባቢ ሚያዝያ 08 ቀን 2005 ዓ.ም. የግል ተበዳይ ራቂያ አደም የተባለችውን ከሰሜን ጎንደር ወደ አዲስ አበባ እንድትመጣ በማድረግ አመልካች በተከራየው ቤት ውስጥ ለሁለት ሳምንታት እንድትቀመጥ በማድረግ ወደ አረብ አገር እልክሻለሁ ብሎ ህክምና እንድትወስድ ከተደረገ በኋላ ከአመልካች ጋር በስር ፍርድ ቤት ተከሶ የነበረው 2ኛ ተከሳሽ የሕክምና ውጤቷን ፖስፖርትና የአሻራ ውጤት በመውሰድ ይኼው ተከሳሽ ቪዛውና የአየር ቲኬት በማምጣት ለመሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ብር 800.00 ለአሁኑ አመልካች ሰጥታ ለመሄድ በመዘጋጀት ላይ ሳለች ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም በደረሰ ጥቆማ ሳትሄድ የቀረች በመሆኗ ተከሳሾች ወንጀል ለማድረግ ጀምረው የወንጀሉ ድርጊት እስከ መጨረሻው ለመከታተል ያልቻሉ በመሆናቸውና በሕገ ወጥ መንገድ ኢትዮጲያዊን ለስራ ወደ ውጪ አገር መላክ ሙከራ ወንጀል ተከሰዋል የሚል ነው። 2ኛው ክስ ደግሞ አመልካቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 27(1)እና 598(1)ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ውጪ አገር የመላክ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው በ1ኛው ክስ በተጠቀሰው ቦታ ቀኑ በውል ባልታወቀበት መጋቢት ወር 2005 ዓ.ም.
ከቀኑ 10፡00 አካባቢ የግል ተበዳይ ናስራ መሐመድ ከትግራይ ክልል በማምጣት ወደ ውጪ አገር ለመሄድ እንደምትፈልግ ስትገልጽለት እኔ እልክሻለሁ በማለት በተከራየበት ቤት ውስጥ አንድ ወር ከአንድ ሳምንት አስቀምጧት የሜዲካል ውጤቷን ወስዶ ወደ ኦማን ነው የምትሄጂው ሲላት ወደዚያ አልሄድም ስትለዉ ቪዛው ለኦማን ነው የተሰራው በማለት የከለከላት እና ወደ ኦማን ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንዳለች የአየር ትኬት ሲመጣ ብር 1000.00 እስከ 1500.00 እንድትከፈል በመግለጽ በመጠባበቅ ላይ እንዳለች በደረሰው ጥቆማ መሰረት ወንጀሉ ፍጻሜ ሳያገኝ የቀረ በመሆኑ አመልካቹ በፈጸመው በሕገ ወጥ መንገድ የኢትዮጵያዊያንን ለስራ ወደ ውጪ አገር መላክ ሙከራ ወንጀል ፈጽሟል የሚል ነው። ልላው አመልካች ጥፋተኛ የተባለበት 4ኛ ክስ ሲሆን የክሱ ይዘት ሲታይም፡- በ1ኛው ክስ በተጠቀሰው ቦታ መጋቢት 28 ቀን 2005 ዓ.ም. የግል ተበዳይ እሸቱ ቱፋን ከሳውዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ በምትገባበት ወቅት አመልካቹ ወደ ተከራየበት ቤት በመውሰድና ከዚያም ወደ ሆስፒታል በመውሰድ እንድትመረመር ካደረገ በኋላ ኩዌት ላከኝ ስትለው ሕክምና ያደረግሽው ለሳውዲ አረቢያ ስለሆነ ኦማን ነው የምልክሽ በማለት ፖስፖርት እና ሜዲካል ውጤቱን ከተቀበላት በኋላ ሞገስ ለተባለው ግለሰብ በመስጠት ይህ ግለሰብም ከዚያው ስለመጣ ውል እንዋዋል ብሐት ውል ለመዋዋል ለመሄድ በዝግጅት ላይ ሳለ ወንጀሉ ፍጻሜ ሳያገኝ የተቋረጠ መሆኑን ጠቅሶ አመልካቹ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 27(1) 598/1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል የሚል ነው። ልላው አመልካች ተከሶ ጥፋተኛ የተባለበት ክስ ደግሞ በ5ኛ ምድብ የተጠቀሰው ሲሆን ይዘቱም፡- አመልካቹ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 27(1)እና 598(1) ድንጋጌዎች በመተላለፍ በአንደኛው ክስ በተጠቀሰው ቦታ ሚያዝያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. የግል ተበዳይ ሕይወት ተስፋን ከሰሜን ጎንደር ወደ አዲስ አበባ እንድትመጣ በማድረግ ወደ ውጪ ለስራ እልክልሻለሁ በማለት የአሻራና የህክምና ምርመራ እንድታደርግ አድርጎ፣ የአሻራ ውጤት፣የህክምና ውጤት እንዲሁም ፖስፖርት በመቀበል ወደ ውጪ እልክሻለሁ፣ ስትሄጂ ብር 1500.00 ትከፍያለሽ በማለት ለመሄድ በመጠባበቅ ላይ ሳለች ለፖላስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ወንጀሉ ፍጻሜ ሳያገኝ የቀረ መሆኑን ተጠቅሶ አመልካቹ በሕገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ውጪ አገር የመላክ ሙከራ ወንጀል መፈፀሙን የሚገልጽ ነው።
ልላው ክስ በምድብ 6 ስር የተጠቀሰው ሆኖ አመልካቹ የወንጀል ህጉን አንቀጽ 27 እና 598(1) የተመለከተውን በመተላለፍ በ1ኛው ክስ በተጠቀሰው ቦታ ሚያዝያ 01 ቀን 2005 ዓ.ም. የግል ተበዳይ ሐጅራ ኡስማንን ከመተማ ከተማ ስትደውል ቪዛው መጥቶልሻል ነይ በማለት እንድትመጣ ካደረገ በኋላ ወደ ተከራየበት ቤት በመውሰድ ያለቀልሽ በመሆኑ ብር 800.00 ትከፍያለሽ በማለት ክፍያውን ለመክፈል በመስማማት ለመሄድ በዝግጅት ላይ ሳለች ለፖላስ በደረሰው ጥቆማ ወንጀሉ ፍጻሜ ሳያገኝ የቀረ መሆኑ ተዘርዝሮ አመልካቹ በሕገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ውጪ አገር የመላክ ሙከራ ወንጀል መፈፀሙን የሚያሳይ ነው። የአሁኑ አመልካችም ክሶቹን ክዶ በመከራከሩ አቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል።
ከዚህም በኋላ አመልካች በዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ወንጀሉን መፈፀሙ መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ ገልጾ አመልካች እንዲከላከል መብቱን ጠብቆለት አመልካችም የመከላከያ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል። ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ያስያዘው ጭብጥ እና የመከላከያ ማስረጃዎቹ አሰምቷል። ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ያስያዘው ጭብጥ እና የመከላከያ ማስረጃዎቹ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው በማለት የመከላከያ ማስረጃዎችን ክብደት ሳይሰጥ አልፎ አመልካችን በአምስቱ ክሶች ጥፋተኛ አድርጓል።ቅጣቱን በተመለከተም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ተቀብሎ ከቅጣት አወሳሰን መመሪያ ጋር በማገናዘብ በእያንዳንዱ ክስ ተገቢ ነው ያለውን የእስራት እና የገንዘብ መቀጮ ከአስቀመጠ በኋላ በድምሩ ደግሞ 25(ሃያ አምስት) አመት ፅኑ እስራት እና ብር 37,500.00 መምጣቱን ፣ ይህ የእስራት ቅጣት በእርከን 37፣ የገንዘብ መቀጮ ደግሞ በእርከን 9 የሚመደብ ሆኖ ወንጀሉ ተደራራቢ በመሆኑ ምክንያትም አንድ እርከን ከፍ እንደሚል ተቀብሎና በዚህም ስልት መሰረት የእስራት ቅጣቱ በእርከን 38፣የገንዘብ መቀጮ ደግሞ በእርከን 10 ስር እንደሚወድቅ ደምድሟል። ከዚህ በኋላ ደግሞ አመልካች ሪከርድ የልለበት፣የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ በቅጣት ማቅለያነት ይዞ እያንዳንዳቸው ምክንያቶች ሁለት ሁለት እርከን እንደሚያስቀንሱለት እንዲሁም ወንጀሉ ሙከራ መሆኑም ሁለት እርከን እንደሚያስቀንስ ገልጾና በአጠቃላይ በስድስት እርከን መቀነስ ያለበት መሆኑን ደምድሞ የእስራት ቅጣቱን በእርከን 32 ስር ባለው ፍቅደ ስልጣን ውስጥ በአስራ ሶስት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ፣ የገንዘብ መቀጮ ደግሞ ብር 2000.00 ላሆን ይገባል በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢያቀርብም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(1)መሰረት ተሰርዟል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ድርጊቱ ስለመፈፀሙም በአግባቡ አልተረጋገጠም፣ በአንድ የወንጀል ማድረግ ሐሣብ በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ ለተፈፀመ ድርጊት ስድስት ክሶች ቀርበው በአምስቱ ጥፋተኛ ተብሎ ለእያንዳንዱ ክስ ቅጣት ተጥሎ መደመሩ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60(ሀ)እና (ሐ)ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ውጪ ነው በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምረናል። እንደመረመርነውም የዚህን ችሎት ምላሽ እንዲያገኝ ተብሎ በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ ክሱ በግል ተበዳዮች ቁጥር መቅረቡንና ቅጣቱ በተደራራቢ ወንጀሎች አንጻር ታይቶ ከብዶ የመወሰኑን አግባብነት የሚመለከት በመሆኑ ከዚሁ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ ተመልክተናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች የተከሰሰው በአንድ መዝገብ ሆኖ ክሶቹ በስድስት ምድብ የተከፈሉ መሆኑንና የተጠቀሰበት የሕግ ድንጋጌም የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 32(1)(ሀ)፣27 እና 598(1)ሆኖ የክሱ ዝርዝር ይዘቱም ባጭሩ ሲታይ አመልካች ምንም ሕጋዊ የሆነ ፈቃድ ሳይኖረው የግል ተበዳዮችን ከተለያዩ ቦታዎች በማምጣት ወደ ውጪ አገር እልካችኋለሁ፣ ስራም አስቀጥራችኋለሁ በሚል ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡና ከተከራየበት ቤት እንዲቆዩ በማድረግ የተለያየ መጠን ያለውን ገንዘብ ለመቀበል ጠይቆ ወደ ውጪ ለመላክ በዝግጅት ላይ እያለ በፖላስ የተያዘ መሆኑን ነው። አመልካች ክሱን የካደ ሲሆን ዓቃቤ ሕግ አሉኝ ባላቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች አመልካች የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን ማስረዳቱን የስር ፍርድ ቤቶች አረጋግጠዋል።
አመልካች በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት አጥብቆ የሚከራከረው በአንድ የወንጀል ሐሳብ በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ ለተፈፀመ ድርጊት በተለያዩ ክሶች ልጠየቅ አይገባም በማለት ነው። በእርግጥ አመልካች በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ በርካታ ሰዎችን ጭኖ ወደ ውጪ አገር እልካችኋለሁ በማለት ማጓጓዝ ላይ እንዳለ መያዙን የክርክሩ ሂደት ያረጋግጣል።
በመሰረቱ የተደራራቢ ወንጀሎች ትርጉም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60(ሀ)እና (ለ)ስር የተቀመጠ ሲሆን የዚሁ አንቀጽ ፊደል “ሐ“ድንጋጌ ሙሉ ይዘት ሲታይም አንድ ሰው በአንድ አይነት የወንጀል ሀሳብ ወይም ቸልተኝነት የፈጸመው ወንጀል አንድን የሕግ ድንጋጌ ብቻ የሚጥስ ቢሆንም አንድ አይነት ጉዳት ያስከተለው ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ሲሆን እንደተደራራቢ ወንጀሎች ላቆጠር የሚገባ መሆኑንያስገነዝባል። ሕግ አውጪው ይህንኑ ድንጋጌ በ1949 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ ያስቀምጥ ከነበረው ሁኔታ በተለየ መልኩ እንዲገባ ያደረገበት ምክንያትም ነባሩ የወንጀል ሕግ በዚህ ረገድ የነበረው ይዘትና መንፈስ በሕግም ሆነ በፍትህ ረገድ ተቀባይነት ላያገኝ እንደማይገባው ፣በነባሩ ህግ ማብራሪያ የጻፉት ምሁራንም የሕጉን አቋም ያልደገፉት ሆኑን መሰረት አድርጎ ስለመሆኑ ከኢ.ፍ.ዲ.ሪ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት ሰፍሮ የምናገኘው ጉዳይ ነው፣ ከዚህ ሕጉ ሲወጣ ከነበረው የሕግ አውጪ ሀሣብም ሆነ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60(ሐ)ድንጋጌ በቀላሉ መገንዘብ የሚቻለው ሕጉ ጥበቃ የሚያደርገው የእያንዳንዱን ሰው መብትና ጥቅም መሆኑን ነው። ስለሆነም በአንድ የወንጀል ማድረግ ሐሳብ ተመሳሳይ ድንጋጌ ተጥሶ በበርካታ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ የሆነ ጉዳት መድረሱ ከተረጋገጠ የድርጊቱ ፈጻሚ በተደራራቢ ወንጀሎች የሚጠየቅ ሲሆን ሕጉ በዚህ ጊዜ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ ያስቀመጠው በቅጣት አወሳሰን ጊዜ በጠቅላላው ሕግ ከተቀመጠው የቅጣት አይነት ጣሪያ ያለማለፍን ስለመሆኑ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184(1)(ሀ)ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው። የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60(ሐ)ድንጋጌ ትርጉምና አተገባበሩ ከላይ በተመለከተው አግባብ ስለመሆኑም ይህ ችሎት በሰ/መ/ በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1)መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ ትርጉም ሰጥቶበታል። ሲጠቃለልም ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች የዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች አመልካች የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን በበቂ ሁኔታ ያረጋገጡ መሆኑን በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁጥር 141 ስር በተቀመጠው የማስረጃ ምዘና ስርዓት መሰረት መዝነው ከአረጋገጡና አመልካች የመከላከያ ማስረጃ የልለው መሆኑን በግልጽ ከአስታወቀ ይህንኑ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አመልካችን ለወንጀል ድርጊቶቹ ኃላፊ ነው ሲሉ የሰጡት ውሳኔ በጉዳዩ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎችን መሰረት ያደረገ መሆኑን የውሳኔ አሰጣጡ ሂደት በግልጽ የሚያሳየው ጉዳይ ሆኖ ስለአገኘነውና አመልካቹ ለእያንዳንዱ ክስ ተጠያቂ መደረጉ በአግባቡ ነው።
ቅጣቱን በተመለከተም ለእያንዳንዱ ክስ በተናጠል ተወስኖ በጠቅላላው ተደምሮ ከ25/ሃያ አምስት አመት/ ጽኑ እስራት እና ብር 37,500.00ተደርጎ መወሰኑ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23(2)፣58፣60፣(ሐ)፣92፣184(1)(ሀ)እና32(1)(ሀ)፣27(1)፣598(1)ድንጋጌዎችንይዘትና መንፈስ እንዲሁም ከላይ ከተጠቀሰው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንጻር ተገቢ እንጂ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም። ይሁን እንጂ አመልካች የቅጣት መጠኑ ከብዶ የተወሰነ መሆኑን በቅሬታ ነጥብነት የጠቀሰ መሆኑን ስለተገነዘብን የስር ፍርድ ቤት ለአመልካች በቅጣት ማቅለያነት የያዛቸውን የሪከርድ ያለመኖርና የቤተሰብ አስተዳዳሪ የመሆኑ ምክንያቶች የሚያስቀንሱት የእርከን መጠን ላታይ የሚገባው ሆኖ አግኝተናል። በመሰረቱ እንደ ቅጣት መመሪያው መወሰን እንዲቻል በአመልካች ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ከግራ ቀኙ ቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶች ጋር ተገናዝቦ ላታይ የሚገባው ነው። በዚህም መሰረት አመልካች ጥፋተኛ ከተባለበት ድንጋጌ እና ከአድራጐቱ አፈጻጸም አንጻር ሲታይ በቅጣት መመሪያው አንቀጽ 13 መሰረት የወንጀሉ ደረጃ ዝቅተኛ ሆኖ ተደራራቢ በመሆኑ ምክንያት በእርከን 38 ላይ የሚወድቅ ሲሆን የስር ፍ/ቤቱ እንዳረጋገጠው የአሁን አመልካች ወንጀል ሪከርድ ያልቀረበበትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኑ ሁለት የቅጣት ማቅለያ ላያዝለት ስለሚገባውና ጥፋተኛ የተባለበት ድንጋጌ ከሚያስከትለው ቅጣት ዓይነትና መጠን አኳያ በእነዚህ ሁለት የማቅለያ ምክንያቶች መሰረት በድምሩ አራት እርከን እንደሚያስቀንስ የስር ፍርድ ቤት ገልጿል። ሆኖም በቅጣት አወሳሰን መመሪያው በአንቀጽ 16(7)እና16 8 ስር እንደሰፈረው የቅጣት ዓይነትና መጠን ሬንጅ እድሜ ልክ በመሆኑ ለአንድ የቅጣት ማቅለያ መቀነስ ያለበት እርከን ሶስት ነው። ይህ ስልት ሲያዝ በሁለት የቅጣት ማቅለያዎች መቀነስ ያለበት ስድስት እርከን ሆኖ ሙከራ በመሆኑ ደግሞ ሁለት እርከን መቀነስ ያለበት በመሆኑ በጠቅላላው ስምንት እርከን ሲቀነስ ከእርከን 38 ወደ እርከን 30 መውረድ የግድ የሚል ነው ። በዚህ እርከን ለፍ/ቤቱ የተሰጠው ፍቅደ ስልጣን ደግሞ ከአስራ አንድ አመት እስከ 13 ዓመት ከሁለት ወር እስራት ስለሆነ በዚህ መሰረት የአሁን አመልካች ለፈፀመው ጥፋት በ11 ዓመት /በአስራ አንድ ዓመት/ ጽኑ እስራት ላቀጣ የሚገባ ሆኖ ስላገኘነው የስር ፍ/ቤቶች የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳለ በመቀበል በእስራት ቅጣት አጣጣል ረገድ የፈፀሙትን መሰረታዊ የህግ ስህተትን ግን አርመን የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተናል።
ተሰጥቶ በፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ህዳር 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የጸናው ውሳኔ በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ. 195/2/ለ/2/መሰረት ተሻሽሐል።
የአሁን አመልካች በአምስት ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል።
ለዚህ ጥፋቱ የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ባወጣው ቅጣት አወሳሰን መመሪያ አንጻር ታይቶ ላቀጣ የሚገባው በ11 ዓመት /በአስራ አንድ ዓመት/ጽኑ እስራት እና በብር 2000.00የገንዘብ መቀጮ ነው በማለት የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2)(ለ-2)መሰረት አሻሽለን ወስነናል።
በተሻሻለው የቅጣት ውሳኔ መሰረት ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ለመ/ቤት ትዕዛዝ ይድረሰው ብለናል። ይጻፍ፡
No topics extracted.