No summary available.
የሰ/መ/ ሚያዚያ 24 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ዘፈሩ ወልደ ትንሣኤ አብርሃ ጠበቃ ሽፈራው በላይ ቀረቡ ተጠሪ፡- የፍድራል ዐቃቤ ህግ አልቀረበም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል ።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት የጥፋተኝነት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው።ጉዳዩ በቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል መፈጸም ጥፋተኛ በሆነ ሰው ላይ የተሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ህጋዊነት የሚመለከት ነው ከሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
ከሳሽ ተከሳሹ በወንጀል ህግ አንቀጽ543 ንዑስ አንቀጽ 2 የተመለከተውን በመተላለፍ የሰው ህይወት ጤናና ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ግድታ ያለበት ሆኖ እያለ ጥፋት በሆነ ቸልተኝነት 25/01/2006 ዓ.ም ከምሽቱ አራት ሰዓት በየካ/ክፍለ ከተማ ቀበል 13/14 ለም ሆቴል ፊት ለፊት አልኮል ጠጥቶ ሲያሽከረክር ለእግረኛ ቅድሚያ በመከልከል ሲያሽከረክር ከፊት በነበረው የሰልዳ ቁጥር 2-42769 ለጊዜው ማንነቱ ያልታወቀው ገጭቶ የሞት አደጋ ያደረሰበት በመሆኑ በቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል ፈፅሟል በማለት ክስ አቅርቧል።
ተከሳሽ የወንጀሉን ድርጊት ፈጽሜአለሁ ጥፋተኛ ነኝ። ሆኖም በወቅቱ መጠጥ አልጠጣሁም ነበር ሟችን የገጨሁት በላዳ መኪና ተከልሎ መንገድ ሲያቋርጥ ነው። ከዚያም ሟችን ወደ ሆስፒታል ወስጄው ነበር ላተርፍ አልቻለም በማለት ተከራክሯል ። ዐቃቤ ህግ መጠጥ የመጠጣቱ ጉዳይ ወሳኝ ነጥብ አይደለም ። በእምነቱ መሰረት ፍርድ ይሰጥልኝ በማለት አመልክቷል ። ፍርድ ቤቱ አመልካች /ተከሳሽ/ በወንጀል ህግ አንቀጽ 543 (2) የተመለከተውን በመተላላፍ ለእግረኛ ቅድሚያ በመከልከል በቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል የፈፀመ ጥፋተኛ ነው ብሎ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል ።
የቅጣት ውሳኔውን በተመለከተ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ተከሳሽ አልኮል ጠጥቶ ሲያሽከረክር አደጋ ላያደርስ እንደሚችል ዕውቀት ያለው በመሆኑ የሞት አደጋውን ያደረሰው በታወቀ ቸልተኝነት ነው ብሎ በመደምደም በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት በሁለት ዓመት ከስድሰት ወር እስራትና ብር 3000 መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል ውሳኔውን ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም አጽንቶታል። አመልካች ጥር 19 ቀን 2006 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ እኔ አደጋው በደረሰበት ጊዜ አልኮል መጠጥ የጠጣሁ መሆኑን በማመን የስጠሁት የእምነት ቃል የለም። ዐቃቤ ህግም ይህንን የሚያሰረዳ ማስረጃ አላቀረበም።ዐቃቤ ህጉ በዕምነት ቃሉ መሰረት ጥፋተኛ ይባልልኝ ብሐል ። ስለዚህ የሥር ፍርድ ቤት በክርክሩ ሂደት ያልታመነ ወይም በማስረጃ ያልተረጋገጠ ጉዳይ (አልኮል ጠጥቶ ያሽከረከረ ሰለነበረ)በማለት ቸልተኝነቱ የሚታወቅ ቸልተኝነት ነው በማለት ያወጣው ደረጃና የሰጠው የቅጣት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት አመልክቷል። ተጠሪ በበኩሉ አመልካች ለእግረኛ ቅድሚያ በመከልከል የሞት አደጋ ያደረሰ በመሆኑ የቅጣት ውሳኔው የህግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል ።
ከሥር የክርክር አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለጸ ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት የቅጣት ውሳኔ የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሻሽሎ ያወጣውን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ከምሽት አራት ሰዓት ሟች በላዳ መኪና ተከልሎ መንገድ ለማቋረጥ ሲሞክር የገጨው መሆኑን አመልካች ለስር ፍርድ ቤት ከሰጠው የእምነት ቃል ይዘት ተረድተናል።አመልካች በወቅቱ የአልኮል መጠጥ ያልጠጣ መሆኑን ለሥር ፍርድ ቤት በግልጽ አስመዝግቧል።ተጠሪም አመልካች የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ አላሽከረከረኩም በማለት የሰጠውን ቃል በመቀበል ማስረጃ ማቅረብ ሣያስፈልገኝ በእምነት ቃሉ መሰረት የጥፋተኝነት ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት እንዳሳሰበ ለመረዳት ችለናል፤ይህም አመልካች በዕምነት ቃሉ ያረጋገጠውን ወይም ዐቃቤ ህግ በማሰረጃ ያላስረዳውን ፍሬ ጉዳይ ማለትም አመልካች ሟችን ገጭቶ የሞት አደጋ ያደረሰበት የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ ሲያሽከረክር ነው በማለት የስር ፍርድ ቤት በቅጣት ውሳኔው መግለጹ በዚህ ምክንያት ቸልተኛነቱም በግልጽ የታወቀ ቸልተኝነት በማለት መፈረጁ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 134(1) ድንጋጌ የተከተለ ሆኖ አላገኘነውም።
የአመልካች የወንጀል አድራጊነት የፈጸመው በወንጀልሕጉ አንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ (1)ሀ በተመለከተው ሁኔታ አይደለም። አመልካች በቸልተኝነት የሞት አደጋውን ያደረሰው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) በተመለከተው ሁኔታ መሆኑን ለጥፋተኝነት ውሳኔው መሰረት የሆነው አመልካች ለሥር ፍርድ ቤት የሰጠው የእምነት ቃል ያሳያል ። አመልካች ጥፋተኛ ተብሎ የሚቀጣው በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 134(1) መሰረት በሰጠው የእምነት ቃል መሰረት ከሆነ የበታች ፍርድ ቤቶችአመልካች ከሰጠው የእምነት ቃል ውስጥ አመልካቹን የሚጠቅመውን ክፍል በመተው፤በአመልካች በዕምነት ቃሉ ያላስመዘገበውና ቅጣት የሚያከብድበትን ሁኔታ በቅጣት ውሳኔው በማሰፈሩ ቅጣቱን መወሰናቸው የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሻሽሎ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 እና የወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 134 (1) ድንጋጌ ይዘትና መሰረታዊ አላማ ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል።
አመልካች ጥፋተኛ የተባሉት በወንጀል ህግ አንቀጽ 543 ንዑስ አንቀጽ 2 በመተላለፍ ነው።
አመልካች የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው በወንጀል ህግ አንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) በተመለከተ ሁኔታ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህም የአመልካች ቸልተኛነት የሟችአስተዋጾ በልለበትና ባልታወቀ ቸልተኛነት የተፈጸመና በእስራት መቀጮ እርከን 8 በገንዘብ መቀጮ እርከን 4 ላይ የሚወድቅ ነው። ይህም ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር እስከ አንድ ዓመት ከስምንት ወር ባለው የቅጣት ሬንጅ ውስጥ የሚያስቀጣ ነው። በመቀጮም እስከ ብር 5000 የሚያስቀጣ ነው።
አመልካች ሁለት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ያሉት መሆኑን በውሳኔው አስፍሯል ። ይህም ሁለት እርከን ለመቀነስ የሚያስችል ነው።ስለሆነም ነፃነትን በሚያሳጣ ቅጣት እርከን ስድስት ሥር እና ገንዘብ መቀጮን በሚያስቀምጠው እርከን ሁለት ሥር የሚወድቅ ነው። በመሆኑም በዚህ ወንጀል ውስጥ በተሰጠው እርከን ሁለት ሥር የሚወድቅ ነው። በመሆኑም በዚህ ሬንጅ ውስጥ በተሰጠው ፍቅደ ሥልጣን መሰረት አመልካች በአንድ ዓመት እስራትና በብር 2000 /ሁለት ሺህ ብር/ መቀጮ ላቀጣ ይገባል በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡትን የጥፋተኝነት ውሳኔ በማፅናት የቅጣት ውሳኔውን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 195 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ(2))መሰረት በማሻሻል ውሳኔ ሰጥተናል ።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ እና የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት በመዝገብ የሰጠው የጥፋተኛነት ውሳኔ በማፅናት የቅጣት ውሳኔውን በወ/መ/ሥ/ሥ/ህግ ቁጥር 195 ንዑስ አንቀፅ 2(ለ) መሰረት አሻሽለናል።
አመልካች በዚህ ጉዳይ እጁ ከተያዘችበት ቀን ጀምሮ በሚታሰብ በአንድ ዓመት እስራትና በብር 2000 (ሁለት ሺህ ብር ) መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥተናል ።
በዚህ ሰበር ችሎት የቅጣት ውሳኔው የተሻሻለ መሆኑን አውቆ ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ለክፍሉ ማረሚያ ቤት ይፃፍ ።መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.