No summary available.
ግንቦት 07 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ሰለሞን ደሣለኝ ጠበቃ ግደይ ገድሉ ቀረቡ ተጠሪ፡- የደቡብ ክልል ዐ/ህግ አልቀረበም።
መዝገቡን ተመርምሮ ተከታዩን ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ በቼክ የማጭበርበር ወንጀልን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩም የተጀመረው በሀዋሳ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰበር ተጠሪ በአመልካች ላይ ባቀረበው ወንጀል ክስ መነሻነት ነው። ተጠሪ በስር ፍ/ቤት በአመልካች ላይ በ3 መዝገቦች ያቀረበባቸው ክሶች ዝርዝር፤-
አመልካችም ፍ/ቤት ቀርቦ ክሱ ተነቦለት እንዲረዳ ከተደረገበኋላ ከክሱ ላይ የሚያቀርበው መቃወሚያ እንደልለው ገለፆ ድርጊቱን መፈፀሙን አምኗል።ሆኖም ግን ድርጊቱን የፈፀምኩት የግል ተበዳዮቹን ለማጭበርበር አስቤ ሳይሆን ጨረታ አሸንፍ ስለነበር ገንዘብ ከመንግስት እስኪለቀቅልኝ ድረስ ቼኩን በዋስትና ይዘው ገንዘቡ ሲለቀቅ እንዲወስዱ ተብሎ ነበር በማለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።በመቀጠልም ፍ/ቤቱ የዐ/ህግን የሰነድና የሰው ምስክሮችን አድምጦ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ አመልካች ወንጀሉን እንዲከላከል ትዕዛዝ ሰጥቷል። ሆኖም ግን አመልካች የበኩሉን መከላከያ ማስረጃ በማቅረብ ወንጀሉን ባለመከላከሉ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ በሦስቱም ወንጀሎች ስር አመልካችን ጥፋተኛ ካደረገበኋላ ቅጣትን በተመለከተም ለእያንዳንዱ ወንጀል አመልካች በ5 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ከወሰነ በኋላ ቅጣቶቹም በማረሚያ ቤት በኩል ተጀምረው እንዲፈጸሙ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አመልካችም በተሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ እና ፍ/ቤቱም በበኩሉ ግራ ቀኙን ተከራካሪ ወገኖች አስቀርቦ በጉዳዩ ላይ እንዲከራከሩ ካደረጋ በኋላ ጉዳዩን በመመርመር የስር ፍ/ቤቱን የጥፋተኝነት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ካፀና በኋላ ቅጣትን በተመለከተ ግን በ2002 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 መሰረት በማድረግ ሦስቱም ወንጀሎች በተመሳሳይ በደረጃ 5፤የእስራት ቅጣት መነሻም እርከን 14 ስር ለእያንዳንዱ ወንጀል 2 ዓመት ከ6 ወር መነሻ ቅጣት ወስኖና እነዚህንም በአንድነት በመደመር ለሦስቱም ተደራራቢ ወንጀሎች 7 ዓመት ከ6 ወር የእስራት ቅጣት ወስኗል።በመቀጠልም የቅጣት ማክበጃ አሰተያየትን በተመለከተ ቅጣቱ እንዲከብድ ተብሎ በዓ/ህግ በኩል የቀረበ አስተያየት የለም በማለት ካለፈ በኋላ የቅጣትማቅለያን ምክንያትን በተመለከተ ደግሞ የቀረበው አስተያየት በማስረጃ አልተረጋገጠም በማለት የአመልካችን ጥያቄ ሳይቀበለው አልፎ በመነሻ ቅጣቱ 7 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጣ ሲል በበታች ፍ/ቤት የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ በማሻሻል ወሰኗል ይህ ውሳኔም በክልሉ ሰበር ችሎትም መሰረታዊ የህግ ስህተት የለውም ተብሎ ተቀባይነት አግኝቷል።
አሁን ለዚህ ሰበር ችሎት የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይሄንኑ በስር ፍ/ቤቶች በተሰጡት ውሳኔዎች ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈፅሞበታልና ስህተቱ ይታረምልኝ የሚል ሲሆን አቤቱታውም በሰበር አጣሪ ችሎት ተመርምሮ አመልካች በፈፀመው የወንጀል ድርጊት ምክንያት የደረሰው የጉዳት መጠን እና በስር ፍ/ቤት የተወሰነው ቅጣት ተመጣጣኝነት፤እንዲሁም በአመልካች የቀረቡት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች የመታለፋቸውን አግባብነት ከወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ 2/2006 አኳያ ለመመርምር ሲባል አቤቱታው ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ዐ/ህግም ቀርቦ የበኩሉን መልስ እንዲሰጥበት ተደርጓል። በዐ/ህግ በኩል የቀረበው መልስ ይዘትም ፤- በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተሻሽሎ የተወሰነውና በክልሉ ሰበር ችሎትም ተቀባይነት አግኝቶ በትዕዛዝ እንዲፀና የተደረገው የቅጣት ውሳኔ ተገቢ እና የሚነቀፍ ባለመሆኑ የቀረበው የሰበር አቤቱታ ውድቅ ተደርጐ እንዲወሰንለት ጠቅሶ መከራከሩን የሚያሳይ ሲሆን አመልካችም የሰበር አቤቱታውን በማጠናከር የመ/መልሱን ሰጥቶበታል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በበኩላችን አቤቱታው ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ ሲደረግ ተይዞ ከነበረው ጭብጥ አንፃር በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን የቅጣት ውሳኔ አግባብነት ብቻ በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
በመሰረቱ የቅጣት አወሳሰንን በተመለከተ የፍድራል ጠ/ፍ/ቤት የቅጣት አወሳሰንን ትክክለኛነት እና አንድ ወጥነት ለማረጋገጥም ሆነ ሰለመቆጣጠር እንዲቻል የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ (Manual) ማውጣት ስልጣን የተሰጠው ስለመሆኑ ከኢ.ፍ.ዲ.ሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 88(4) ድንጋጌ ይዘት መገንዘብ ይቻላል።የፍ/ጠ/ፍ/ቤትም በዚህ መሰረት ከዚህ ቀደም የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ.1/2002 አውጥቶ ከግንቦት 9 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራበት የነበረ ስለመሆኑ ይታወቃል።ሆኖም ግን በኋላ ላይ ይህን መመሪያ ማሻሻል በማስፈለጉ የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ.2/2006 በምትኩ ወጥቶ ከ1/2/2006ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ መዋሉም የሚታወቅ ነው።ቅጣትን በሚመለከት ደግሞ አዲሱ የወንጀል ህግ ከመውጣቱ በፊት በተፈፀመ ወንጀል ከተፈረደበት እና ሆኖም ግን ወንጀሉ በተፈፀመበት ጊዜ ስራ ላይ ከነበረው ወንጀል ህግ ይልቅ አዲሱ ህግ ለተከሳሹ ቅጣትን የሚያቀልለትና ተከሳሹን የሚጠቅም ሆኖ ከተገኘ ይሄው በአዲሱ ህግ ላይ ያለው ቅጣት የሚፈጽምበት ስለመሆኑ ከወንጀል ህጉ ቁ. 6 ድንጋጌ ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በተያዘው ጉዳይም ምንም እንኳ አመልካች እነኝህን ወንጀሎች የፈጸመው የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ.2/2006 ዓ.ም ከመውጣቱ በፊት ቢሆንም ይህ ጉዳይ በዚህ ሰበር ችሎት ታይቶ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ከበፊቱ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ. 1/2002 ይልቅ በኋላ ተሻሽሎ ወጥቶ በአሁኑ ጊዜ ተፈፃሚነት ያለው የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ.2/2006 አመልካች የሚጠቅም ሆኖ ከተገኘ ይሄው በጉዳዩ ላይ ተፈጻሚነት ላኖረው ሰለሚገባ በዚሁ መሰረት በአመልካች ላይ የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ አግባብነት ተመርምሯል።
አመልካች በሦስቱም ቼኮች የሚያዝበትን ገንዘብ ከባንክ ሳይኖረው የተለያዩ ቼኮችን በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ ሦስት ግለሰቦች አውጥቶ ሰጥቷል ተብሎ ጥፋተኛ የተባለው የቼኮቹ ገንዘብ መጠን እንደቅደም ተከተላቸው ብር 12,786፤20,000 እና ብር 37,972 የያዙ ስለመሆናቸው የሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ግልባጭ በግልፅ ያስረዳሉ።ይህም በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 አንቀጽ መሰረት የእያንዳንዱ ተደራቢ ወንጀል ደረጃ እና የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን እንደቅደም ተከተላቸው በ1ኛ ና 2ኛ ተደራራቢ ወንጀሎች የተገለፀው የገንዘብ መጠን በደረጃ 3 እና የእስራት መነሻ ቅጣቱም በእርከን 9 ስር የሚወድቁ ሲሆን በ3ኛ ተደራቢ ወንጀል የተገለጸው የገንዘብ መጠን ደግሞ በደረጃ 4 እና እርከን 11 ስር የሚወድቅ ሆኖ አግኝተነዋል።
በመመሪያው አንቀጽ 22(1)(ሀ) መሰረት ደግሞ ለእያንዳንዱ ተደራቢ ወንጀል ለብቻቸው ላወሰን የሚገባው መነሻ ቅጣትም እንደቅደም ተከተላቸው 1 ዓመት ከ6ወር፤1 ዓመት ከ6 ወር እና 2 ዓመት እስራት ሆኖ ተወስኗል።እነዚህ መነሻ የእስራት ቅጣቶችም በአንድ ላይ ሲደመር 5 ዓመት ሲሆን ይህም ከፍ ሲል በተገለፀው ተመሳሳይ የመመሪያው ድንጋጌ መሰረት በእርከን 20 ስር ይወድቃል።
በልላ በኩል የቅጣት ማክበጃ ምክንያትን በተመለከተ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱ በዐ/ህግ አስተያየት አልቀረበም በሚል ምክንያት ሰላለፈ እና በዚህ ነጥብ ላይም በዐ/ህግ በኩል የቀረበ ቅሬታ ባለመኖሩ በዚሁ የሚታለፍ ይሆናል። የቅጣት ማቅለያን በተመለከተ ግን ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱ ሳይቀበለው ያለፈው የቀረበው ምክንያት በማስረጃ አልተረጋገጠም በሚል ምክንያት መሆኑን ተገንዝበናል።ይሁን እንጂ አመልካች ለዚህ ሰበር ክርክር መነሻ የሆኑትን ተደራራቢ ወንጀሎች ከመፈጸሙ በፊት የወንጀል ሪከርድ ያልቀረበበት እና የዘወትር ፀባዩም መልካም ስለመሆኑና እንዲሁም ይሄንን ወንጀል ከፈፀመም በኋላ በመፀፀት ለግል ተበዳይ ገንዘብ መክፈል የጀመረ ስለመሆኑ በከፍተኛ ፍ/ቤት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።እነዚህ በበታች ፍ/ቤት የተረጋገጡት ሁለት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 82(1)(ሀ)፣5(ሰ) እንዲሁም በመመሪያው አንቀጽ 23 መሰረት መነሻ የቅጣት እርከኑን ከእርከን 20 ወደ እርከን 18 እንዲቀል ያደርጋሉ።
በመመሪያው መሰረት የእርከን 18 መነሻ ቅጣት 3 ዓመት ከ7 ወር ሲሆን መድረሻው ደግሞ 4 ዓመት ከ4 ወር በመሆኑ በዚሁ ፍቅደስልጣን ውስጥ ደግሞ የወንጀል አፈፃፀሙ ልዩ ሁኔታ ግምት ውስጥ ገብቶ እንዲታይ ከተደረገ በኋላ አመልካች በ4 ዓመት እስራት ቅጣት ላቀጣ የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል።
ሲጠቃለልም የአመልካች ቅጣት ውሳኔ ላመረመር የሚገባው በኢ.ፍ.ዲ.ሪ.ወንጀል ህግ አንቀጽ 6 ስር እንደተመለከተው በ2006 ዓ.ም ከጥቅምት ወር ጀምሮ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተሻሽሎ በወጣው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሰረት መሆን ስላለበት በዚህ መሰረት በስር ፍ/ቤቶች በአመልካች የተሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ብቻ አሻሽለን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 195(2)(ለ)(2) መሰረት ፀንቷል።
በዚህ ጉዳይ በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በሰበር ሰሚ ችሎት በመ.
በ7/09/05 ዓ.ም ተወስኖ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ በ23/12/05 ዓ/ም በትዕዛዝ እንዲፀና የተደረገው የ7 ዓመት ከ6 ወር እስራት ወደ 4 ዓመት እስራት በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 195(2)(ለ)(2) መሰረት ተሻሽሎ ተወስኗል።
No topics extracted.