No summary available.
መጋቢት 09 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የደቡብ ብሕር በሕረሰቦች ሕዝቦች ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ክልል አቃቤ - የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ መኩሪያ ቡሎ - የቀረበ የለም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ በወንጀል ጉዳይ የተሰጠ የእስር ቅጣት አፈፃፀሙ የሚገደብበትን የሕግ አግባብ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም፡- ተጠሪ በ1996 ዓ/ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 27(1) እና 540 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ከልላ ካልተያዘው ግብረ አበር ጋር በመሆን አቶ ላልሞ ላግድ የተባለውን የግል ተበዳይ በክላሽ መሳሪያ አራት ጥይት ተኩሶ ስቷል፤
ከተሰወረ በኋላም ተይዟል በማለት ዘርዝሮ የመግደል ሙከራ ወንጀል ፈፅሟል የሚል ሲሆን የአሁኑ ተጠሪ ክደው ተከራክረው አቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቶ ክሱን ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ ተገንዝቦ ተጠሪ ክሱን እንዲከላከሉ መብታቸውን ተጠብቆላቸው የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን አቅርበው አሰምተዋል። በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ማስረጃዎችን መርምሮ ተጠሪ የአመልካችን ማስረጃዎች በመከላከያ ማስረጃዎቹ አላስተባበሉም በማለት ተጠሪን ክስ በቀረበባቸው ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ አድርጎ ቅጣቱን በተመለከተም የግራ ቀኙን አስተያየት ተቀብሎ ከሕጉ ጋር አገናዝቦ መመልከቱን ከጠቀሰ በኋላ በሶስት አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል። ሆኖም የእስራት ቅጣት አፈፃፀሙን በተመለከተ ተጠሪ ታማሚ መሆናቸውን ሐኪም አረጋግጧል፤ በግል ተበዳይም የደረሰ ጉዳት የለም በሚል ምክንያት በሁለት አመት ገደብ እንዲሆን ወስኗል። በዚህ የእስራት ቅጣት እንዲገደብ ተብሎ በተሰጠው የውሳኔ ክፍል የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከሩ በኋላ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ/ም የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ጠቅሶ የስር ፍርድ ቤት ቅጣቱ እንዲገደብ የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል። ከዚህም በኋላ አመልካች የሰበር አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡በተጠሪ ላይ የተጣለው የሶስት አመት ፅኑ እስራት ቅጣት የተገደበው ሕጉ የሚጠይቃቸው መስፈርቶች ሳይሟሉና አግባብነት የልለው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተጠቅሶ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮም ከድርጊቱ አፈፃፀም እና ተጠሪ የግል ተበዳይን ይቅርታን ያልጠየቁ፣ ካሳም ያልከፈሉ ከመሆናቸው አንጻር ሲታይ የእስራት ቅጣቱ መገደቡ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 197 ድንጋጌ አንፃር ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው በሰጡት መልስ ድርጊቱን ያልፈፀሙ መሆኑን፣ ይግባኝ ያልጠየቁበት ምክንያትም በአቅመ ደካማነታቸው የተነሳ መሆኑንና የእስራት ቅጣቱ የተገደበው ባለባቸው በሽታ ስለመሆኑ በማስረጃ ተረጋግጦ ነው በማለት ዘርዝረው ውሳኔው እንዲጸናላቸው ጠይቀዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንጻር ጉዳዩን ለሰበር ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
በመሰረቱ በተከሳሽ ላይ የተወሰነ የቅጣት ውሳኔ ከመገደቡ ወይም የገደብ ውሳኔው ከመሻሩ በፊት የቅጣት ገደብ ስለሚከለከልበትና ስለሚሻርበት ሁኔታ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 194 እና 197 ስር የተደነገጉትን ድንጋጌዎች ይዘትና ዓላማ ማገናዘብ አስፈላጊ ነው። የወንጀል ሕጉ በተወሰነ ገደብ ቅጣትን ማቆም የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ከአንቀጽ 190 እስከ 200 ስር አስፍሮ ይገኛል።
የወንጀል ሕጉአንቀጽ 190 ሲታይም ከእስር በገደብ መለቀቅ ማለት ፍርድ ቤት አንድ ጥፋተኛ የተባለን ሰው ለጥፋቱ መነሻ የሆኑትን ምክንያቶችን በጠቅላላው በመመልከት በጥፋተኛው ላይ የተወሰነውን ቅጣት ለጊዜው በገደብ እንዲታገድ በማድረግ የወንጀለኛውን ጠባይ ለማረምና ለማሻሻል እንዲሁም ወደ መደበኛ ማህበራዊ ኑሮው ለመመለስ ጠቃሚ መሆኑን አረጋግጦ ከእስር እንዲፈታ የሚደረግበት አግባብ መሆኑን ያስገነዝባል።
በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ተከሳሽ የቅጣት አፈፃፀም እንዲገደብ ፍ/ቤቶች ትዕዛዝ መስጠት የማይችሉባቸው ሁኔታዎችም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 194 በዝርዝር ተመልክተዋል።በልላ አገላለፅ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን በገደብ የሚያስቆመው የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲሆን እነዚህም፡- ወንጀለኛው ቀድሞ ያልተቀጣ ሆኖ ጠባዩም አደገኛነት እንደልለው የሚታመንበት እንደሆነ፣ ጥፋቱ በመቀጮ፣ በግድታ ስራ ወይም ከሶስት አመት የማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኝነቱን ካረጋገጠ በኋላ ለወደፊት ጠባዩን ለማረም እንደሚችል እምነት ላጣልበት የሚችል መሆኑና በዚህ ውሳኔ ብቻ እስከ መጨረሻው ላሻሻል የሚችል መሆኑን ያመነበት እንደሆነ አስተያየት ከሰጠ በኋላ ቅጣት ሳይወስን የተወሰነ የፈተና ጊዜ ላሰጠው የሚችልበት አግባብ መኖሩን ሕጉ ያሳያል። እንዲሁም ጥፋተኛው አስቀድሞ የተፈረደበት ቢሆንም ባይሆንም የተፈረደበትን ቅጣት ከመፈፀሙ በፊት ለተወሰነ ጊዜ ቅጣቱ ታግዶለት አመሉ ቢፈተን ሁለተኛ ጥፋት ከማድረግም የሚታገድ መሆኑና ስለጠባዩም መሻሻል አንድ ፅኑ ማስጠንቀቂያ ብቻ የሚበቃ መሆኑ ፍርድ ቤቱ ያመነበት እንደሆነ ቅጣቱ ከአፈፃፀም ታግዶ እንዲቆይ ላያዝ እንደሚችል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 192 ይዘትና መንፈስ ያሳያል። ከላይ የተመለከቱትን የገደብ አሰጣጥ ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ ግን ፍርድ ቤቱ በሕጉ የተመለከቱትን ቅድመ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ በማየት የተሟሉ መሆናቸውን ላያረጋግጥ ይገባል። በዚህ አግባብ የገደብ ውሳኔ ካልተሰጠ የወንጀል ሕጉን መሰረታዊ አላማ ለማሳካት የማይቻል መሆኑ ይታመናል።
የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 196 ስር እንደአስቀመጠው ፍርድ ቤቱ ለጥፋተኛው የሚሰጠውን የፈተና ጊዜ የሚወሰነው የወንጀሉን ከባድነት፣ በወንጀል ድርጊት መደጋገም ላደርስ የሚችለውን ጉዳትና በጥፋተኛው ላይ ላጣልበት የሚችለውን እምነት ከግምት ውሰጥ በማስገባት ስለመሆኑ ሕጉ ያሳያል። የተከሳሹን የገደብ ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ከመቀበሉ በፊትም ተከሳሹ ቀድሞ የነበረውን ጠባይ ፣ የአኗኗርና የስራውን ሁኔታ ምን አይነት እንደነበር ፍርድ ቤቱ መረጀ መሰብሰብ እንደሚችልም ሕጉ ያስገነዝባል። የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 197/1/ ሲታይም ፍርድ ቤቱ ቅጣቱ እንዳይፈፀም ለማድረግ በቅድሚያ ላሟሉ የሚችሉትን ሁኔታዎች አስቀምጦ እናገኛለን።
እነዚህም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛው በመልካም ጠባይ እንደሚመራ ካመነ፣ ጥፋተኛው እንዲፈፀም የተሰጠውን ግድታ እንደሚቀበል ካረጋገጠ ፣ ጥፋተኛው በሚቻለው መንገድ ሁሉ በጥፋቱ የደረሰውን ጉዳት እንደሚክስ ወይም ለተበዳዩ እንደሚከፍል እና ለዚሁ ጉዳይ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የፍርድ ቤቱን ወጪ እንደሚከፍል ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ ስለመሆናቸው ሕጉ በግልጽ ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛው ለገባበት ግድታ አፈፃፀም መተማመኛ ዋስትና እዲያቀርብ እንደሚያደርግ ተጠቃሹ አንቀጽ በንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ ስር አስፍሮ ይገኛል።
እንግዲህ ህግ አውጭው አንድ ሰው በወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ቅጣት ሳይጣል ጥፋተኛ ነህ በማለት ብቻ ላታለፍ የሚችልበትን እንዲሁም ጥፋተኛነቱ ተረጋግጦ ቅጣቱ ከተጣለ በኋላ ደግሞ የእስራት ቅጣቱ ሳይፈፀም ተገድቦ የሚቆይበትን አግባብ በግልፅ የዘረጋ መሆኑን ከአንቀፅ 190 እስከ 200 ድረስ ያሉትን የወንጀል ህግ ድንጋጌዎችን በማየት የምንረዳው ጉዳይ ሲሆን አንድን ጥፋተኛ በተወሰነ ገደብ ከእስር ለመፍታት ግን በህጉ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች የተሟሉ መሆኑን ፍ/ቤቱ አስቀድሞ ማረጋገጥ ያለበት ጉዳይ ነው። ስለሆነም የገደብ ውሳኔው በዘፈቀደ የሚሰጥ ሳይሆን ህጋዊ ሁኔታዎች መሟላታቸው በሚገባ ተረጋግጦ የሚሰጥ ነው። በህግ ተለይተው የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ ደግሞ የዳኝነት አካሄድ የግድ የሚለው ጉዳይ ነው።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም የሰር ፍ/ቤት በተጠሪ ላይ የጣለውን የሶስት አመት ጽኑ እሰራት ቅጣት በሁለት አመት የገደበው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 197 ስር የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን መርምሮ ስለመሆኑ የውሣኔው ግልባጭ አያሣይም። ይልቁንም ፍርድ ቤቱ አጽንኦት የሰጠው የተጠሪን በሽተኛ መሆን በሐኪም መረጋገጡንና በግል ተበዳይ ላይ የደረሰ ጉዳት ያለመኖሩ ነው። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተጠሪ መልካም ጠባይ እንደሚመራ ስለማመኑ፣ ተጠሪ እንዲፈጽም የተሰጠውን ግድታ እንደሚቀበል ማረጋገጡን፣ ተጠሪ በሚቻለው መንገድ ሁሉ በጥፋቱ የደረሰውን ጉዳት እንደሚክስ ወይም ለተበዳዩ እንደሚከፍልና ለዚሁ ጉዳይ በተወሰነ ጊዜ ውሰጥ የፍርድ ቤቱን ወጪ እንደሚከፍል ማረጋገጫ ስለመስጠቱ በቅጣት ፍርድ ላይ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 197 አግባብ ያስቀመጠው ነገር የለም። የተጠሪ በሽተኛ መሆን ደግሞ ሕጉ ከአስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ በግልጽ ያልተጠቀሰ ሲሆን በግል ተበዳይ ላይ የደረሰ ጉዳት ያለመኖሩም ድርጊቱ ሙከራ ሁኖ አራት ጥይት ተተኩሶ የተሣተ እንደመሆኑ መጠን ለገደብ ውሣኔው የግድ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ምክንያት አይደለም። ተጠሪ ከግል ተበዳይ ጋር ይቅርታ ማውረዳቸውም ያልተረጋገጠ ሲሆን ይልቁንም እስከዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት በተደረገው ክርክር ስለአጥፊነታቸው አምነው ያቀረቡት ክርክር የለም። ይህም ተጠሪ የተጣለባቸው ቅጣት ከመፈጸሙ በፊት ለተወሰነ ጊዜ ቅጣቱ ታግዶላቸው አመላቸው ቢፈተን ሁለተኛ ጥፋት ከማድረግ የሚታገዱ ናቸው ብሎ ለመደምደም የማይቻል መሆኑን በግልጽ የሚያሣይ ነው። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የስር ፍርድ ቤትን ውሣኔ ለማጽናት መሰረት የደረገው የዚህ ችሎት አሰገዳጅ ትርጉም ሲታይም ከዚህ ጉዳይ በመሰረታዊ ነጥቦቹ ተመሣሣይነት የልለው ነው። በ
የተሰጠው የሕግ ትርጉም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በገደብ አወሣሰን በሕጉ የተቀመጡትን መስፈርቶች ባገናዘበ መልኩ ዳኝነት መስጠቱን የሰበር ሰሚ ችሎቱ በማረጋገጥ የሰጠው ከመሆኑ ውጪ በሕጉ የተመለከቱትን መሰፈርቶችን ሣይከተል የተሰጠ ውሣኔን የተቀበለ ባለመሆኑ ለጉዳዩ አግባብነት የልለው ሁኖ አግኝተናል።
ሲጠቃለልም ከላይ በዝርዝር በገለጽናቸው ምክንያቶች በተጠሪ ላይ የተጣለው የሶስት አመት ጽኑ እሰራት በሁለት አመት የታገደው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 197 ስር የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ሣይሟሉ በመሆኑ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቅጣት ገደብ የውሣኔ ክፍል ሕጉን ያልተከተለ ሲሆን የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ እና የሰበር ችሎትም ይህንኑ የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የውሣኔ ክፍል ማረም ሲገባቸው ማለፋቸውና ውሣኔውን ሙሉ በሙሉ ማጽናታቸው መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ መጋቢት 27 ቀን 2005 በተጠሪ ላይ የተወሰነው የሶስት አመት ጽኑ እሰራት ቅጣት ውሣኔ ላገደብ ይገባል ተብሎ ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም በክልሉ ሰበር ችሎት በመ/ ነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም የፀናው የውሣኔ ክፍል ብቻ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195/2/መ/ መሰረት ተሽሯል። ለፍርድ ቤቶቹ የውሣኔው ግልባጭ ይድረሣቸው ብለናል።
በዚህ በኩል የእሰራት ቅጣት ውሣኔው አፈፃፀም እንዲገደብ በበታች ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሣኔ ተሽሮ ተጠሪ የሶስት አመት ጽኑ እሰራት መፈጸም ያለባቸው በማረሚያ ቤት ነው ብለናል። የክፍሉ ፖላስ ተጠሪን ይዞ ለሀዋሣ ማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ፣ የሀዋሣ ማረሚያ ቤትም ከክፍሉ ፖላስ ተጠሪን ተረክቦ ተጠሪ በጉዳዩ ላይ ቀድሞ የታሰሩትን ጊዜ ታሣቢ በማድረግ የሶስት አመት ጽኑ እሰራት ቅጣትን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ብለናል። ይፃፍ።
No topics extracted.