No summary available.
ሰኔ 02 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ፅጋቡ ወላይ ገብሩ- VC ስላልሰራ መቅረቡን ማረጋገጥ አልተቻለም።
ተጠሪ፡- የትግራይ ክልል ዐቃቤሕግ - VC ስላልሰራ መቅረቡን ማረጋገጥ አልተቻለም።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የወንጀል ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በመሰረተው ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም አመልካች ከሚላኒየም ድቨሎፕመንት ፕሮጀክት ጋር ከመቐል ወደ ሓውዜን ሲሚንቶ እንዲያጓጉዝላቸው የማጓጓዝ ሃላፊነት ተሰጥቶት በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት አጓጉዞ በጊዜው ላያስረክባቸውና ለህዝብ ልማት ላይ ላያውል የሚገባውን እምነት አጉድሎ ሲሚንቶውን ሽጦ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ በ1996 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675(1) ድንጋጌን ተላልፏል የሚል ሲሆን የአሁኑ አመልካች ክሱ ተነቦለት እንዲረዳው ከተደረገ በኋላ ስለእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቅ በክሱ ላይ ተቃውሞ የልለው መሆኑን ገልጾ የድርጊት አፈጻጸሙን በተመለከተ ግን በመጓጓዣ ዉሉ መሰረት ሲሚንቶውን መረከቡንና መሸጡን አምኖ ሆኖም አስጫኙ ያልከፈለው ገንዘብ ስለነበረ ይህንኑ ገንዘብ አስቀርተው ቀሪውን እንዲረከብ ጥያቄ ሲያቀርብ ተቀባይነት ያጡ መሆኑን ገልፀው ጉዳዩ በፍትሐብሕር እንጂ በወንጀል ላያስጠይቀኝ አይችልም በማለት ተከራክረዋል። ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የክልተ በለሳ ወረዳ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ ጉዳዩ የፍትሐ ብሕር እንጂ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል አይደለም በማለት አመልካችን በነጻ አሰናብቶታል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለምስራቅ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማቅረቡ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፅንቷል። ከዚህም በኋላ ተጠሪ የሰበር አቤቱታውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ሰሚንቶውን የሸጠው በውሉ መሰረት ሳያስረክበው የቀረ መሆኑ ተረጋግጧል በሚል ምክንያት አመልካችን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 675(1) ስር ጥፋተኛ አድርጎታል። ቅጣቱን በተመለከተም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት በመቀበልና ድንጋጌው ደረጃ ያልወጣለት መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ቅጣቱን ከአሰላ በኋላ አመልካች በሁለት አመት ከሶስት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት አድራጎቱ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው በማለት ድምዳሜ ላይ የደረሰው ከስልጣኑ ውጪ ማስረጃ መዝኖ ከመሆኑም በላይ በማስረጃ የተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች የአመልካች አድራጎት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 675(1) ስር የተመለከቱትን የወንጀሉን ማቋቋሚያዎችን የሚያሟሉ አይደሉም የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም የአመልካች አድራጎት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 675(1) የሚያስጠይቅ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል በዚህ ችሎት ቀርቦ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ መጥሪያ ደርሶት ባለመቅረቡ በጽሑፍ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የአመልካች አድራጎት የሚሸፈነው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 675 (1) ድንጋጌ ስር ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል።
ከላይ እንደተመለከተው በዐቃቤ ሕግ ክስ የተመለከተውን ድርጊት አመልካች አልፈጸምኩምበማለት ያልተከራከረ ሲሆን አጥብቆ የሚከራከረው በመጓጓዣ ውሉ መሰረት ላከፈለኝ የሚገባው ገንዘብ በሲሚንቶው አስጫኙ ድርጅት ስላልተከፈለ ሲሚንቶውን ሽጦ የመጓጓዣውን ገንዘብ አመልካች ከቀነሰ በኋላ ቀሪውን ገንዘብ ከሰሚንቶ አስጫኝ ድርጅት ለመመለስ ጥረት አድርጎ ድርጅቱ ቀሪውን ገንዘብ ላቀበለው ያልቻለ መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ ፍትሐ ብሕራዊ እንጂ የወንጀል ተጠያቂነትን አያስከትልም በማለት ነው።በርግጥ አመልካች ይህንኑ ቃሉን በመከላከያ ማስረጃዎቹም ያረጋገጠው ፍሬ ነገር መሆኑን ክሱን የሰማው የወረዳው ፍርድ ቤትም ሆነ ጉዳዩን በይግባኝ የሰማው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም እንደዚሁ የተሰማውን ማስረጃ በመመዘን ሲሚንቶው የተሸጠበትን ሁኔታ እርግጠኛ ሆኗል። የሲሚንቶው መሸጥ ድርጊት ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለው ፍሬ ነገር በአመልካች ካለመካዱም በላይ የፍሬ ነገር ጭብጥን በማስረጃ የማጣራት እና የተሰማውን ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ያላቸው የወረዳው ፍርድ ቤት እና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክርክሩን በዚህ መልክ በመምራት መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።እነዚህ ፍርድ ቤቶች የአመልካች ድርጊት የወንጀል ተጠያቂነትን አያስከትልም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሱት አመልካች በመጓጓዣ ውሉ መሰረት ያልተከፈለውን ገንዘብ ለማግኘት ሲል ሲሚንቶውን ሽጦ ከመጓጓዣ ዋጋ የተረፈውን ለሲሚንቶው አስጫኝ ድርጅት ለመመለስ አመልካች ጥረት ቢያደርግም ድርጅቱ ገንዘቡን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ ተረጋግጧል በሚል ሲሆን የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ግን አመልካች ሲሚንቶውን እንዲሸጥ የውል ስምምነት የተደረገው መጋቢት 10 ቀን 2003 ዓ/ም ሁኖ ከዚህ ቀን በፊት ያለው ውል ደግሞ ይህንኑ መብት እንደማይሰጠው፣ሲሚንቶውም የተሸጠው ከመጋቢት 10 ቀን 2003 ዓ/ም በፊት ሁኖ የቀደመው ሕጋዊ ውል ባለበት ሁኔታ መሆኑ ተረጋግጧል በሚል ምክንያት የአመልካች አድራጎት የእምነት ማጉደል ወንጀል ነው በማለት ደምድሟል።ይህ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ድምዳሜ ፍሬ ነገርን በማጣራትና ማስረጃውን በመመዘን የተያዘ ሳይሆን በክርክሩ ሂደት የቀረቡት ማስረጃዎች ያረጋገጧቸው ፍሬ ነገሮችን በመለየት የተያዘ በመሆኑና በክርክሩ ሂደት የቀረቡት ማስረጃዎች ያረጋገጧቸውን ፍሬ ነገሮች የበታች ፍርድ ቤቶች ባግባቡ ሳይዙና ሳይመለከቱ ቀርተው በዚህ ረገድ ቅሬታው በስርዓቱ መሰረት ለሰበር ሰሚ ችሎት ቢቀርብና ችሎቱም ይህንኑ ቅሬታ ተቀብሎ በዚህ ረገድ የተፈፀመውን ስህተት ቢያርም የመሰረታዊ ሕግ ስህተት መመዘኛን የሚያሟላ አይደለም የሚል ቅሬታ የሚነሳበት ጉዳይ አይደለም።ምክንያቱም የአንድ የህግ ድንጋጌ ትክክለኛ ትርጉም እና አተገባበር የሚኖረው በህጉ አግባብ የተቆጠሩት ማስረጃዎች ያረጋገጡት ፍሬ ነገሮች ከእነ ሙሉ ይዘታቸው ታይተውና ተመዝነው እንጂ ማስረጃዎቹ ያረጋገጡትን ፍሬ ነገር በመተው ላሆን አይገባምና።ስለሆነም አመልካች በዚህ ረገድ ያነሳው ቅሬታ ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ አልተገኘም።
ቀጥሎ መታየት ያለበት የሕግ ጥያቄ አመልካች በገባው የእቃ ማጓጓዝ ውል መሰረት ሲሚንቶውን በሙሉ በጥንቃቄ በማጓጓዝ፣ በተወሰነው ጊዜና ሥፍራ አድርሶ ለተቀባዩ የማስረከብ ግድታውን አለመወጣቱ አመልካችን በፍታሐብሕር ተጠያቂ ከመሆን አልፎ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ በእምነት ማጉደል ወንጀል የሚያስጠይቃቸው ነው ወይስ በልላ ድንጋጌ? የሚለው መሰረታዊ ነጥብ ነው። ከዚህ አንጻር የወንጀል ህጉ በንብረት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚዘረዝርበት ምእራፍ ሁለት በልዩ ሁኔታ በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚዘረዝረው ክፍል አንድ ሥር የተደነገገው የዕምነት ማጉደል ወንጀል መሰረታዊ ባህሪ ይዘትና የሚያስከትለው ኃላፊነትን የሚዘረዝር ድንጋጌ ነው። የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንዑስ አንቀጽ አንድ ድንጋጌ ሙሉ ይዘቱ ሲታይም፡ " ማንም ሰው ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለልላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የልላ ሰው የሆነውንና ለአንድ ለተወሰነ ግልጋሎት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዋጋ ያለውን ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ያደረገ ፣ ወይም ለልላ ሰው ያደረገ ፣ የወሰደ ፣የሰወረ ወይም ለራሱ ወይም ለልላ ሰው አገልግሎት ያዋለ ወይም ይህን የመሳሰለውን ማናቸውንም አድራጎት የፈጸመ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል" በማለት ያስቀምጣል። የተጠቃሹ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 የተከሣሹ ወንጀል ሃሣብ ግምት የሚደነግግ ሲሆን ይዘቱም ተከሣሹ ሲጠየቅ በእምነት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዕቃ ወይም ጥሬ ገንዘብ ለመመለስ ወይም ለመክፈል ወይም ዕቃው ያለበትን ሁኔታ ለማሳየት ወይም ለተገቢው አገልግሎት ያዋለው መሆኑን ማስረዳት ካልቻለ ለራሱ ወይም ለልላ ሰው ያልተገባ ጥቅም ማዋል ሃሣብ እንዳለው ይቆጠራል የሚል ነው።
ከላይ የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ድንጋጌ ሙሉ ይዘት ሲታይ አመልካች በገባው የእቃ ማጓጓዝ ውል መሰረት ሲሚንቶውን በማጓጓዝ በተወሰነው ጊዜና ሥፍራ አድርሶ ለተቀባዩ የማስረከብ ግድታውን ያልተወጣ በመሆኑ በእምነት ማጉደል ወንጀል ተጠያቂ የሚሆን ስለመሆኑ አይደነግግም።የድንጋጌው ይዘት አንድ ሰው አንድን ንብረት ለአንድ አገልግሎት ለማዋል በኃላፊነት ተረክቦት ንብረቱን ለተባለው አገልግሎት ሳያውል ሲቀር በዕምነት ማጉደል ወንጀል የሚጠየቅ መሆኑን የሚመለከት እንጂ በማጓጓዝ ውል መሰረት በልምድ መሰረት የሚገባውን ሙሉ ጥንቃቄ አድርጐ እቃውን በማጓጓዝና በተወሰነው ጊዜና ሥፍራ አድርሶ ለተቀባዩ የማስረከብ ግድታውን ያልተወጣ አጓዥ በዕምነት ማጉደል ወንጀል እንዲጠየቅ የድንጋጌው ይዘትና መንፈስ የማያሣይ በመሆኑ በዚህ በኩል የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰበት ድምዳሜ ተገቢ ሁኖ አልተገኘም። በልላ በኩል በማጓጓዝ ውል መሰረት በልምድ መሰረት የሚገባውን ሙሉ ጥንቃቄ በማድረግ እቃውን ማጓጓዝና በተወሰነው ጊዜና ሥፍራ አድርሶ ለተቀባዩ የማስረከብ ግድታውን ሳይወጣ አመልካች ሲሚንቶውን መሸጡና የሸጠውም ያልተከፈለውን የማጓጓዣ ዋጋ ለራሱ ለማድረግ ስለመሆኑ ተረጋግጧል። ማንም ሰው በዕምነት ማጉደል ወንጀል የሚጠየቀው ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ የልላ ሰው የሆነውንና ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት የተሰጠውን ዋጋ ያለው ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ያደረገ ወይም ለልላ ሰው ያደረገ የወሰደ፣ ያስወሰደ፣ የሰወረ ወይም ለራሱ ወይም ለልላ ሰው አገልግሎት ያዋለ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው። የአመልካች አድራጎት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንዑስ አንቀጽ 3 በሚደነግገዉ የወንጀል ሃሣብ ግምት የማይሸፈን መሆኑን ከድንጋጌው ይዘትና መንፈስ እንዲሁም በአመልካችና በሲሚንቶው አስጫኝ ድርጅት መካከል ከነበረው የውል ግንኙነት ለመረዳት የሚቻል ሁኖ አግኝተናል። ይሁን እንጂ አመልካች የመጓጓዣ ዋጋውን ሲሚንቶውን ሽጦ ለራሱ ማድረጉ ከስምምነት የመነጨ አድራጎት ያለመሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ይህ የአመልካች መብት በሲሚንቶ አስጫኙ ድርጅት በውሉ መሰረት ካልተፈጸመም አመልካች ያላቸው መብት በሕግ አግባብ መብታቸውን ማስከበር ነው።ከሕግ ውጪ መብት አለኝ በማለት የልላውን ሰው መብት ለራስ ጥቅም ማዋል ደግሞ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መብትን ማስከበር ሲሆን ይህም የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል አድራጎት መሆኑን ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 436(ለ) ስር ከተደነገገው ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
አንድ ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የሚቀጣው የህግ፣ የግዙፍ ተግባርና የሞራል ሁኔታ በአንድነት ተጣምረው መገኘታቸው ሲረጋገጥ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ ስር ሰፍሯል። በያዝነው ጉዳይም የአመልካች አድራጎት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 675(1) ስር የተዘረዘሩት የህግ የሃሣብ ሁኔታዎች ያልተሟሉ ቢሆንም አድራጎቱ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 436(ለ) ስር የሚሸፈን ሁኖ ስለአገኘነው የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን የጥፋተኛነት ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 113(2) እና 195(2)(ለ 2) ድንጋጌዎች አግባብ በማሻሻል አመልካች ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መብት ማስከበር ወንጀል የፈጸመ በመሆኑ ጥፋተኛ ነው በማለት ወስነናል።
አመልካች መቀጣት ያለበት በዚህ ችሎት ጥፋተኛ በተባለበት ድንጋጌ ስር ሲሆን ድንጋጌው የሚያስቀጣው ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ሲሆን እኛም የአመልካችን አድራጎትና የቅጣትን መሰረታዊ ዓላማ እንዲሁም አመልካች በስር ፍርድ ቤት ያስያዛቸውን ሪከርድ ያልቀረበበት መሆኑንና የቤተሰብ አስተዳዳሪነቱን የሚመለከቱትን የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተናል።ቅጣቱን ደረጃ ላልወጣላቸው የወንጀል ድንጋጌዎች ደረጃ የሚወጣበትን አግባብ መሰረት በማድረግ አስልተናል።ይህን ሁሉ መሰረት ስናደርግ አመልካች የታሰረበት ጊዜ በቂ ሁኖ እንዲፈታ ማድረጉ አመልካችን የሚያርም ልሎች መሰል ወንጀሎችን የሚያስጠነቅቅ ሁኖ አግኝተናል።ሲጠቃለልም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ የአመልካችን አድራጎት በሚሸፈነው ድንጋጌ ረገድ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ውሳኔው በከፊል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል።
ውሣኔ
የትግራይ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ጥር 29 እና 30 ቀን 2005 ዓ/ም የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ህ/ቁጥር 195(2)(ለ ) መሰረት ተሻሽሐል።
የአመልካች አድራጎት በወንጀል የሚያስጠይቅ ሁኖ የሚሸፈነውም በወንጀል ሕግ አንቀጽ 675(1) ሳይሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 436(ለ) ስር ነው በማለት አመልካች ለዚሁ አድራጎቱ የታሰረው ጊዜ በቂ ነው በማለት ወስነናል።
አመልካች የታሰረው ጊዜ ለአድራጎቱ በቂ ነው ተብሎ በዚህ ችሎት መወሰኑን አውቆ በልላ ወንጀል የማይፈለግ መሆኑን አረጋግጦ ከእስር እንዲፈታው ለመቐል ማረሚያ ቤት የመፍቻ ትዕዛዝ ይላክለት ብለናል።ይፃፍ፡፤
No topics extracted.