No summary available.
ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- መኮንን ወለላው ካሳ ጠበቃ ዘነበ አሰፋ ቀረቡ ተጠሪ፡- የፍድራል ሥነ ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ህግ ዋልተንጉስ ፍቅሬ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።
የአቤቱታው መነሻ የአሁኑ አመልካች የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ/ም ለስር ፍርድ ቤት ያቀረቡት ማመልከቻ ሲሆን ይዘቱም፡- በመ/ እና በመ/ በሆኑ መዛግብት በወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ተብለው የተለያዩ መጠን ያላቸው የእስራት ቅጣት እና የገንዘብ መቀጮዎች እንደተወሰኑባቸው ገልጸው ቅጣቶች እንደገና ተጣምረው በወንጀል ሕግ አንቀፅ 186 መሰረት በአንድነት ተጠቃለው ይወሰኑልኝ በማለት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። የስር ፍርድ ቤትም የአመልካችን ጥያቄ በኮ/መ/ በመቀበል ከተመለከተው በኋላ ጉዳዩን መርምሮ በአራቱም መዝገቦች በአመልካቹ ላይ ተወስነውበት የነበሩት ቅጣቶች በአንድነት ተጠቃለው ተደምረው በ24 አመት ከ3 ወር ጽኑ እስራት እና በብር 22,500 የገንዘብ መዋጮ እንዲቀጣ የሚል ውሳኔ በመስጠት ማረሚያ ቤቱንም በአንድነት ተጠቃሎ በተወሰነው ቅጣት መሰረት እንዲያስፈፅም አዟል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔን አፅንቶታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካቹ የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-የበታች ፍርድ ቤቶች አራቱን መዝገቦች በማሰባሰብና በማጣመር በወንጀል ሕግ አንቀጽ 186(3) መሰረት አይቶ መወሰን ሲገባቸው ያለአግባብ በመደመር ቅጣቱን ከፍ አድርጎ የወሰኑባቸው ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60(ሀ) ድንጋጌ ውጪ መሆኑንና ቅጣቱን በተመለከተውም በሕግ አግባብ ተቀባይነት ያገኙት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ግንዛቤ ውስጥ ገብተው በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት የቅጣት መጠኑ ያለመሰላቱን የሚገልፅ ነው።አቤቱታው ተመርምሮም የበታች ፍርድ ቤቶች ለወንጀል ሕግ አንቀጽ 186(3) የሰጡት ትርጉም ተገቢ መሆን ያለመሆኑንና የቅጣት መጠኑ የተወሰነው የቅጣት አወሳሰን መመሪያን መሰረት አድርጎ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 186(3) መሰረት የቅጣት ይጣመርልኝ ጥያቄ ከቀረበ በየመዝገቦቹ የተወሰኑትን ቅጣቶች መደመር ሳይሆን በአንድነት በማጠቃለል እንደገና በአዲስ መልክ ቅጣቱ ተሰልቶና ተቀባይነት ያገኙት የቅጣት ማቅለያዎች ሁሉ ታይተው ጉዳዩ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60(ሀ) ለአንድ የወንጀል ሐሳብ አንድ ቅጣት ከመሆኑ እና ከቅጣት መመሪያ ድንጋጌዎች አንፃር ታይቶ ቅጣቱ ላወሰን የሚገባው ነው በማለት ነው።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአሁኑ አመልካች በፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በአራት የክስ መዝገቦች ቀርበውባቸው እንደነበር፣ በወ/መ/ ቀርበውበት በነበሩት 2 ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ የተወሰነበት የ9 ዓመት ጽኑ እስራት እና የብር 15,000 መቀጮ፣ በወ/መ/ በቀረበበት አንድ ክስ ጥፋተኛ ተደረጎ የተወሰነበት የ5 ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት እና የብር 7000 መቀጮ እንዲሁም፣ በወ/መ/ቁ. 65858 በቀረቡበት ሁለት ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ የተወሰነበት የ10 ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት እንዳለ የፀኑና ያለቀላቸው መሆኑን፣ በወ/መ/ቁ.87280 የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በአመልካቹ ላይ ቀርበው በነበሩ ሁለት ክሶች ጥፋተኛ አድርጓቸው የ2 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እና የብር 1000 መቀጮ ወስኖባቸው የነበረ ቢሆንም አመልካች ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርበው በአንዱ ክስ ብቻ ጥፋተኛ ተብለው የ6 ወር ቀላል እስራት ቅጣት እና የብር 500 መቀጮ የተወሰነባቸው መሆኑን ነው።
በመሰረቱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 186(3) በአንድነት ተጣምረው መታየት የነበረባቸው የወንጀል ክሶች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ወይም ችሎቶች በተናጠል ታይተው የተለያዩ ቅጣቶች በተወሰኑ ጊዜ የጠቅላላ ቅጣቱ አወሳሰን ከዚህ በላይ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሰረት ይሆናል ብሎ ከተጠቃሹ ድንጋጌ በላይ ወደ ተገለፁት ድንጋጌዎች የሚያጣቅስ ሲሆን እነዚህ ድንጋጌዎች ሲታዩ በተለያዩ ፍ/ቤቶች ወይም ችሎቶች በተናጠል ታይተው የተለያዩ ቅጣቶች ተወስነው በተገኙ ጊዜ እንደገና በአዲስ መልክ እያንዳንዱ ቅጣት ተሰልቶና የቅጣት ማቅለያዎች ሁሉ ታይተው መወሰን አለበት የሚል መንፈስ ያላቸው አይደሉም።ይልቁንም ሕጉ ጥፋተኛው በፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች በአንድ ጊዜ ቢፈረድበት ኖሮ ላወሰንበት ይችል ከነበረው ከፍተኛ ቅጣት ሳያልፍ እንደሚወሰን የሚያስረዳ ነው። ስለተደራራቢ ወንጀሎች ቅጣት አወሳሰን የሚመለከተው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 184(1)(ለ)"ም" ሲታይም ጥፋተኛው ተደራራቢ ወንጀሎች ፈፅሞ በተገኘ ጊዜ በተደራራቢነት ለተፈፀሙ ለእያንዳንዱ ወንጀል በተናጠል ተገቢው የቅጣት መጠን ተወስኖ የሁሉም እንደሚደመር እና ቅጣቶችም ተደምረው ለወንጀሉ አይነት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ከተደነገገው ከፍተኛ ቅጣት መብለጥ እንደማይችል ያስቀምጣል። በሕጉ ጠቅላላ ክፍል የፅኑ እስራት ከፍተኛው ቅጣት ሃያ አምስት አመት ስለሆነ በጽኑ እስራት የሚያስቀጡት ተደራራቢ ወንጀሎች ቅጣቶች ተደምረው ከሃያ አምስት አመት ላበልጡ እንደማይችሉ ደግሞ ይሄው ድንጋጌ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 108(1) ድንጋጌ ይዘት ያሳያል። የእነዚህ ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ ይዘቱና መንፈሱ ደግሞ ቅጣቶቹ ተደምረው ከሃያ አምስት አመት በሚበልጡበት ጊዜም ሃያ አምስት አመት ላይ እንዲያቆም ፍርድ ቤቱ እንዲቆም የሚያስገድድ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
እንግዲህ ከላይ ከተገለጹት ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለው ጥፋተኛው ከፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ የየትኛውም ወንጀል ቅጣት የቀሪዎችን ወንጀሎች ቅጣት የሚያጠቃልል ካልሆነና ወንጀሎቹ በእስራት የሚያስቀጡ ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች ከሆኑ ለእያንዳንዱ በተደራራቢነት ለተፈፀመው ወንጀል ተገቢ የሆነው ቅጣት ተወስኖ ሁሉም እንዲደመር የሚደረግ መሆኑን እና ምንጊዜም ቢሆን ለእስራቱ ዓይነት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ከተደነገገው ጣሪያ ቅጣት ማለፍ አይቻልም ተብሎ መደንገጉ ነው።ይህም መታየት ያለበት አጥፊው ጥፋተኛ የተባለበት ልዩ ድንጋጌ የሚያስቀምጠው የቅጣት ጣሪያ ሳይሆን በሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተደነገገው ጣሪያ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። እንዲሁም አንድ ሰው የፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ከፊሎቹ የሚያስቀጡት በቀላል እስራት፣ ከፊሎቹ ደግሞ በፅኑ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች በሚሆኑበት ጊዜ የቅጣት አወሳሰኑ ቅጣቶችን ለመደመር እንዲያመች ሁለት ዓመት ቀላል እስራት እንደ አንድ ዓመት ፅኑ እስራት ይቆጠራል ተብሎ በሕጉ በግልጽ ተቀምጧል።
ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተውም ከላይ በተጠቀሱት አራት መዝገቦች በአመልካች ላይ በተለያየ ጊዜ ተነጣጥለው የተወሰኑበት የተለያዩ ቅጣቶች ተጣምረው ይወሰኑልኝ በሚል ያቀረበውን ጥያቄ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተቀብሎ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የተወሰነበትን የ6 ወር ቀላል እስራት ወደ 3 ወር ጽኑ እስራት በመለወጥ የአራቱም መዝገቦች ቅጣቶች በአንድነት በማጠቃለል ደምሮ የ24 ዓመት ከ3 ወር ፅኑ እስራት ቅጣት እንዲፈፀም ከመወሰን ወጪ በሕጉ ስለጽኑ እስራት የተቀመጠውን ጣሪያ በማለፍ የወሰነው ቅጣት የለም። አመልካች በመጀመሪያ ይህንኑ የቅጣቶች ይጣመሩልኝ ጥያቄ ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ችሎቱ አመልካቹን ጥያቄውን ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ማቅረብ አለብህ ብሎ የመለሰው ወይም የመራው የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የአራቱንም መዝገቦች ቅጣቶች አሰባስቦ እንደገና በመከለስ አዲስ የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥ ሳይሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 186(3) በተከተለ መንገድ እንዲያይ ስለመሆኑም የይግባኝ ሰሚው ችሎት ውሳኔ በግልጽ ያሳያል። አስቀድሞ በየመዝገቦቹ ቅጣቶቹ በተናጠል በሚወሰኑበት ጊዜ ሁሉም ነገሮች ታይተው ለፈፀማቸው ወንጀሎች ይመጥናሉ ተብለው የተወሰኑ መሆናቸው በበታች ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ ጉዳይ ሲሆን የቅጣቶች አፈጻጸምን በተመለከተም ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 186(3)፣ 184(1(ለ)) እና 108(1) ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንፃር ተደምረው እንዲፈፀም ማድረግ የድንጋጌዎቹን ትክክለኛ ትርጉም አተገባበር የተከተለ ነው ከሚባል በስተቀር መሰረታዊ የሕግ ስህተት ነው ላባል የሚችልበትን ምክንያት አላገኘንም። ስለሆነም በዚህ ረገድ የተሰጠው የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚነቀፍ ባለመሆኑ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ቅሬታ አልተቀበልነውም።
ልላው አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩበትና ለዚህ ችሎት እንዲታይ የተያዘው ነጥብ የቅጣት አሰላሉን የሚመለከተው ነጥብ ነው። አመልካች በስር ፍርድ ቤት ተቀባይነት ያገኙት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች መሰረት ተደርጎ ቅጣቱ ያለመሰላቱንና የቅጣት መጠኑ ከቅጣት አወሳሰን መመሪያው ውጪ ከፍ የተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል። ይሁን እንጂ አመልካች በተለያዩ ጊዜ ፣በተለያየ ሰነድና በተለያየ ቦታ ለፈጸሟቸው ተደራረቢ ወንጀሎች በተለያዩ መዛግብት ጥፋተኛ ተብለው ቅጣቱ ሲወስን አለኝ የሚሐቸው ሕጋዊ የቅጣት ማቅለያ ምክያንቶች ተይዘውላቸው ቅጣቱ መሰላቱን የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ ሲሆን ቅጣቱ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 186(3) ድንጋጌ አግባብ ታይቶ እንዲወሰን ሲደረግ ወይም መዝገቦቹ ተነጣጥለው ሲወሰኑ የተያዙት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች እንደገና የሚታዩበት የሕግ አግባብ የለም።በአመልካች ጥያቄ አግባብ ቅጣቱ እንዲሰላ ማድረግ ለአንድ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ሁለት ጊዜ ዋጋ የመስጠት ውጤትን የሚያስከትል በመሆኑ በሕግ ተቀባይነት የልለው ሲሆን አመልካቹ መዝገቦቹ ተነጣጥለው ሲታይ ቅጣቱም ተነጣጥሎ ሲወሰን በተለያዩ መዝገቦች ተመሳሳይ የቅጣት ማቅለያ እንዲያዙ መደረጉ በውጤቱ አመልካችን ጠቅሟቸዋል ከሚባል በስተቀር የመብት መጣበብን አስከትሎባቸዋል ለማለት የሚያስችል ሁኖ አልተገኘም። በመሆኑም በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካቹ ቅሬታም የሕግ መሰረት ያለው ባለመሆኑ አልተቀበልነውም።
ሲጠቃለልም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል ለማለት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ስላላገኘን ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሐምል 09 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 04 ቀን 2006 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 195(2)(መ) መሰረት ፀንቷል።
በጉዳዩ ላይ የበታች ፍርድ ቤቶች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 186(3) ሲተርጉሙም ሆነ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወጣውን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ተግባራዊ ሲያደርጉ የፈፀሙት ስህተት የለም ብለናል።
በአመልካች ላይ የተጣለው ቅጣት የጸና መሆኑን አውቆ ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ይድረስ ብለናል።
No topics extracted.