No summary available.
ሚያዝያ 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡-
ጉዳዩ የወንጀል ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የአሁኖቹ አመልካቾች ክሱ በቀረበበት በትግራይ ብ/ክ/መንግስት ማዕከላዊ ዞን በአብይ ዓዲ ከ/ፍ/ቤት እንደቅደም ተከተላቸው 1ኛ፣2ኛ፣3ኛ፣4ኛ፣5ኛእና 6ኛ ተከሳሽ የነበሩ ናቸው።
ተጠሪ በ06/02/2005 ዓ.ም. አሻሽሎ ያቀረበባቸው ክስ ይዘት ባጭሩ፡-ተከሳሾቹ በወ/ሕ/አ. 32(3) እና 539(1)(ሀ) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በ15/09/2004 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን በኦምበራ መጠቃ ንዑስ ወረዳ ልዩ ስሙ ሳልጎል በሚባል ቦታ በግፍ ሰው ለመግደል አስበውና አቅደው ከበታች መሬት በኩል ስራ በመስራት ላይ በነበሩት ሰዎች ላይ የድንጋይ ናዳ እያወረዱ ሲያደናቅፉ ከቆዩ በኃላ በጉዳዩ ላይ ለመግባባት ከታች በኩል የነበሩት ሰዎች መጥተው ሲያናግሯቸው ምን አመጣችሁ? በሚል ምክንያት ሟች ነጋሽ መኮንን ይባል የነበረውን ሰው 1ኛ ተከሳሽ በድንጋይ ጭንቅላቱን መትቶ ከመሬት ላይ ሲጥለው 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ ጭንቅላቱን በተለያየ ቦታ ላይ በድንጋይ በመምታት ከሃያ ሜትር በላይ ርቀት ወዳለው ገደል በእጁ ገፍትሮ በመወርወር፣ቀሪዎቹ ተከሳሾች ደግሞ ሟችን ከጥቃት ለማስጣል የመጡትን ሰዎች በመከላከል 3ኛ፣4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ገላጋዮችን በድንጋይ ጭንቅላታቸውን በተለያዩ ቦታዎች እየፈነከቱ በማባረር፣6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ደግሞ አባዲ ስዩም፣ብርሃነ አሰፋ እና ገዳሙ ገ/እግዚአብሕር የተባሉትን ሰዎች በድንጋይ በመምታት፣ልብሶቻቸውን በመጨምደድ እና እጆቻቸውን በመጠምዘዝ እንዳያገላግሉ በመከልከላቸው፤ሟችም በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ25/09/2004 ዓ.ም. ሕይወቱ በማለፉ ተከሳሾቹ አባሪ ተባባሪ በመሆን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ አሰቃቂ የግድያ ወንጀል አድርገዋል የሚል ነው።
አመልካቾቹ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደርጎ የእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ ወንጀሉን አላደረግንም በማለታቸው ተጠሪ አራት ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል።ፍ/ቤቱም የተጠሪን የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኃላ ተጠሪ እንደክሱ አቀራረብ ያስረዳ መሆኑን ገልጾ 2ኛ አመልካች በክሱ በተጠቀሰበት ድንጋጌ ስር፤ቀሪዎቹ አመልካቾች ደግሞ በወ/ሕ/አ.32(3) እና 540 ስር እንዲከላከሉ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 142 መሰረት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በዚህ ትዕዛዝ መሰረት አመልካቾቹ ድርጊቱን ያልፈጸሙ መሆናቸውን እና ሟች የወደቁት በራሳቸው መሆኑን ያስረዱልናል በማለት በድምሩ ስምንት የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበው ያሰሙ ሲሆን ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ የመከላከያ ምስክሮቹ ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት እና ከተፈጸመ በኋላ የነበረውን ሁኔታ ገልጸው ከመመስከራቸው በስተቀር ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ በቦታው ያልነበሩ በመሆኑ ምስክርነታቸው የተጠሪን ማስረጃ ለማስተባበል የሚችል አይደለም በማለት ይከላከሉ በየተባሉበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል።በመቀጠልም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለ በኋላ በ2ኛ አመልካች ላይ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት፣በ1ኛ እና በ6ኛ አመልካቾች በእያንዳንዳቸው ላይ የአስራ ሁለት ዓመት ጽኑ እስራት፣በ3ኛ፣በ4ኛ እና በ5ኛ አመልካቾች በእያንዳንዳቸው ላይ የስድስት ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት መነሻ አድርጎ ከወሰነ በኃላ የቀረበባቸው የቀድሞ ሪከርድ አለመኖሩን በማቅለያ ምክንያትነት ይዞ ቅጣቱን በማቅለል በ2ኛ አመልካች ላይ የሃያ ዓመት ጽኑ እስራት፤በ1ኛ እና በ6ኛ አመልካቾች በእያንዳንዳቸው ላይ የአስራ አንድ ዓመት ጽኑ እስራት፤በ3ኛ፣በ4ኛ እና በ5ኛ አመልካቾች በእያንዳንዳቸው ላይ የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት በመጣል ውሳኔ ሰጥቷል።
አመልካቾች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የክልሉ የበላይ ፍ/ቤቶች የቀረበላቸውን ይግባኝ እና አቤቱታ ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ለስር የመ/ደ/ፍ/ቤት ከቀረበው ማስረጃ አንጻር 2ኛ አመልካች በወ/ሕ/አ. 539(1)(ሀ) ስር፤ቀሪዎቹ አመልካቾች ደግሞ በወ/ሕ/አ.32(3) እና 540 ስር ጥፋተኛ ልንሰኝ አይገባም በማለት ያቀረቡትን ቅሬታ ተጠሪ ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩን መርምረናል።
በዚህም መሰረት በክሱ በተገለጸው ዝርዝር መሰረት ሟች ነጋሽ መኮንን ይባል የነበረውን ሰው 1ኛ አመልካች በድንጋይ ጭንቅላቱን መትቶ ከመሬት ላይ ሲጥለው 2ኛ አመልካች ደግሞ ጭንቅላቱን በተለያየ ቦታ ላይ በድንጋይ የመታው ከመሆኑም በላይ ቀጥሎም ከሃያ ሜትር በላይ ርቀት ወዳለው ገደል በእጁ ገፍትሮ የወረወረው መሆኑ እና ተበዳዩም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በደረሰበት በዚሁ ጉዳት ምክንያት ለሞት የበቃ መሆኑ በተጠሪ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ መረጋገጡን እና አመልካቾቹ በመከላከያ ምስክሮቻቸው ከድርጊቱ መፈጸም በፊትና ከተፈጸመ በኃላ ስለነበረው ሁኔታ ከማስመስከር ውጪ ድርጊቱን ስላለመፈጸማቸው ያቀረቡት ቀጥተኛ መከላከያ አለመኖሩን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል። በ2ኛ አመልካች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔው የተሰጠው በወ/ሕ/አ.539(1)(ሀ) ስር መሆኑን በተመለከተም ቢሆን አመልካቹ በ1ኛ አመልካች በድንጋይ ከጭንቅላቱ ላይ ተመትቶ ወድቆ የነበረውን ሟች በድንጋይ ከጭንቅላቱ ላይ ከመታው በኃላ ከሃያ ሜትር በላይ ርቀት ወዳለው ገደል የወረወረው መሆኑ እና ሟችም ለሞት የበቃው በዚሁ በሁለቱ አመልካቾች በደረሰበት ጉዳት ምክንያት እንደሆነ የተረጋገጠ በመሆኑ እና ይህ 2ኛው አመልካች የፈጸመው አድራጎት የአፈጻጸም ሁኔታ ደግሞ የአመልካቹን ጨካኝነት እና የአፈጻጸሙን አሰቃቂነት በግልጽ የሚያመለክት በመሆኑ ድርጊቱ የሚሸፈንበትን ድንጋጌ አስመልክቶ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።በመሆኑም በ1ኛ እና በ2ኛ አመልካቾች ላይ የተሰጠውን የጥፋተኝነትም ሆነ የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አላገኘነውም።
ቀሪዎቹን ማለትም 3ኛ፣4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ አመልካቾችን በተመለከተ እነዚህ አመልካቾች የተከሰሱት በወ/ሕ/አ. 32(3) እና 539(1)(ሀ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብለው ሲሆን ይከላከሉ የተባሉትና የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠባቸው ደግሞ በወ/ሕ/አ. 32(3) እና 540 ስር ነው።እነዚህ አመልካቾች አድርገዋል ተብለው በክሱ የተጠቀሰባቸው ግዙፋዊ ድርጊት ሟችን ከ1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች ጥቃት ለማስጣል የመጡትን ሰዎች በመከላከል ልብሶቻቸውን እየጨመደዱና እጆቻቸውን እየጠመዘዙ እንዲሁም በድንጋይ ጭንቅላታቸውን በተለያየ ቦታዎች እየፈነከቱ አባረዋል የሚል ነው።ቀደም ሲል እንደተገለጸው አመልካቾቹ ድርጊቱን አልፈጸምንም በማለት የካዱ ቢሆንም ከበታች መሬት በኩል በስራ ላይ የነበሩትና ከላይኛው መሬት በኩል የድንጋይ ናዳ የወረደባቸው ሰዎች ከሟች ጋር ወደቦታው በመጡበት ጊዜ አመልካቾቹ በእነዚሁ ሰዎች ላይ በክሱ የተመለከተውን ድርጊት መፈጸማቸው በተጠሪ ምስክሮች የተረጋገጠባቸው መሆኑን እና ከ1ኛ እና ከ2ኛ አመልካቾች ጋር በተመሳሳይ ጭብጥ ያቀረቡት መከላከያ ከላይ ስለ 1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች ከተገለጸው ጋር በተመሳሳይ ምክንያት ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን ከመዝገቡ ግልባጭ መገንዘብ የተቻለ በመሆኑ የተሰጠባቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።ይሁን እንጂ በክስ ማመልከቻውም ሆነ በተጠሪ ምስክሮች በተገለጸው መሰረት በአንድ በኩል በ1ኛ እና በ2ኛ አመልካቾች፤በልላ በኩል ደግሞ በቀሪዎቹ አመልካቾች መፈጸማቸው የተረጋገጠው ግዙፋዊ የወንጀል ድርጊቶች ከየተፈጸሙበት የጊዜ ቅደም ተከተል አንጻር ሲታዩ በ3ኛ፣4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ አመልካቾች መፈጸሙ የተረጋገጠው ግዙፋዊ የወንጀል ፍሬ ነገር በወ/ሕ/አ. 32 በተመለከተው መሰረት በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በግድያ ወንጀሉ መሳተፋቸውን የሚያረጋግጥ መሆን አለመሆኑ በአግባቡ መጤን የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል።
ቀደም ሲል እንደተገለጸው በ3ኛ፣4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ አመልካቾች ሟችን ከ1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች ለማስጣል የመጡትን ሰዎች ደብድበው አባረዋል ከመባላቸው ውጪ እራሳቸው ሟችን በቀጥታ የመቱ ስለመሆኑ በክስ ማመልከቻው ላይ አልተገለጸም።ይህ ፍሬ ነገር በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ.111(1)(ለ) እና 112 ስር በተመለከተው የክስ አቀራረብ ስርዓት መሰረት በክስ ማመልከቻው ላይ የተመለከተ ወይም ክሱ እንዲሻሻል የተደረገ እስካልሆነ ድረስ ደግሞ ሟችን የደበደቡት 3ኛ፣4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ አመልካቾች ጭምር ስለመሆናቸው በተጠሪ ምስክሮች የተገለጸው ፍሬ ነገር በእነዚህ አመልካቾች ላይ ውጤት እንዲኖረው ላደረግ የሚችልበት የህግ አግባብ የለም።በክስ ማመልከቻውም ሆነ በተጠሪ ምስክሮች በተገለጸው መሰረት እነዚህ አመልካቾች ሟችን ከ1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች ለማስጣል የመጡትን ሰዎች ደብድበው አባረዋል የተባሉት 1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች በሟች ላይ በክሱ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት ከፈጸሙ በኋላ በመሆኑ 3ኛ፣4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ አመልካቾች መፈጸማቸው የተረጋገጠው ግዙፋዊ የወንጀል ፍሬ ነገር ራሱን የቻለ ልላ ወንጀል የሚያቋቁም ነው ከሚባል በቀር ከ1ኛ እና ከ2ኛ አመልካቾች ጋር በየትኛውም ደረጃ ወይም ዓይነት የሚገለጽ የግድያ የወንጀል ሀሳብ በመጋራት ተጎጂዎቹ ሟችን ከጥቃት እንዳያስጥሉ ለመከላከል በማሰብ የተፈጸመ ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።በመሰረቱ በወንጀል ጉዳይ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ ተከሳሹን ጥፋተኛ ሆኖ ያስገኘው ሕግ በፍርዱ ውስጥ መገለጽ እንደሚገባው በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 149 የተመለከተው ድንጋጌ የጥፋተኝት ውሳኔው የሚሰጥበት ድንጋጌ መፈጸሙ ከተረጋገጠው የወንጀል ፍሬ ነገር ጋር በጥንቃቄ መነጻጸር እንደሚገባው የሚያስገነዝብ በመሆኑ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍ/ቤት 3ኛ፣4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ አመልካቾችን በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ በማድረግ የሰጠው ውሳኔም ሆነ ይህንኑ በማጽናት በክልሉ የበላይ ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ በመዝገቡ የተረጋጠውን ፍሬ ነገር መሰረት ያደረገ ሆኖ አልተገኘም።
በልላ በኩል ለወንጀሉ ምክንያት የሆነው ግጭት የተፈጠረው በላይኛው የመሬት ክፍል በስራ ላይ የነበረው አመልካቾቹ የሚገኙበት ቡድን ከመሬቱ በታችኛው ክፍል በስራ ላይ በነበረው እና ተጎጂዎቹ በሚገኙበት ቡድን ላይ በተደጋጋሚ የድንጋይ ናዳ በማውረዱ ምክንያት ተጎጂዎቹ በዚሁ ድርጊት ተነሳስተው አመልካቾች ወደ ሚገኙበት አካባቢ በመምጣታቸው ምክንያት መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ ሲሆን ይህም ግጭቱ የተከሰተው አመልካቾቹ ይገኙበት በነበረው ቡድን ጠብ አጫሪነት መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል ነው። አመልካቾቹ ድንጋዮችን በመያዝ በዚህ ዓይነቱ ድርጊት ውስጥ በመሳተፍ በተጎጂዎቹ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውም በወ/ሕ/አ. 577(1) እና (3) ስር የተመለከተውን የአምባጓሮ ወንጀል ማድረጋቸውን የሚያመለክት በመሆኑ በአመልካቾቹ መፈጸሙ በፍሬ ነገር ደረጃ በተረጋገጠው መሰረት የጥፋተኝነት ውሳኔው የተሰጠበት ድንጋጌ ከወ/ሕ/አ.32(3) እና 540 ወደ ወ/ሕ/አ. 577(1) እና (3) ላለወጥ የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል።
3ኛ፣4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ አመልካቾች ጥፋተኞች የተባሉበት የአምባጓሮ ወንጀል በወቅቱ በስራ ላይ በነበረው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 ደረጃ ካልወጣላቸው ወንጀሎች መካከል የሚካተት ሲሆን ድርጊቱ የተፈጸመው በሁለቱም ቡድኖች ውስጥ የሚገኙት ሰዎች በእርሻ ስራ ላይ ይገኙ በነበሩበት ጊዜ መሆኑን ከግምት በማስገባት በመመሪያው አንቀጽ 13(2) በተመለከተው መሰረት በአፈጻጸሙና በክብደቱ ወንጀሉ በዝቅተኛ ደረጃ ላመደብ የሚገባው መሆኑን ተገንዝበናል።በድንጋጌው ስር በዝቅተኛ ደረጃ ለተመደበ ወንጀል በቅጣት አወሳሰን መመሪያው የተቀመጠው ፍቅደ ስልጣን እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ሲሆን ከዚህ ፍቅድ ስልጣን ውስጥ መነሻ ተደርጎ ላወሰድ የሚገባው የቅጣት መጠን የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ሆኖ ተገኝቷል።ይህ የቅጣት መጠን በቅጣት መመሪያው አባሪ አንድ በእርከን 20 ስር የሚወድቅ ሲሆን ከመዝገቡ ግልባጭ መገንዘብ እንደሚቻለው በተጠሪ በኩል የቀረበ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት የለም። የቅጣት ማቅለያን በተመለከተ 3ኛ፣4ኛ እና 5ኛ አመልካቾች የቀረበባቸው ሪከርድ አለመኖሩን ገልጸው አንድ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ማስመዝገባቸውን እና 6ኛ አመልካች የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን በመግለጽ ተጨማሪ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ማስመዝገባቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።የቅጣት መነሻው ከአንድ ዓመት በላይ እና ከሰባት ዓመት በታች በሆነ ጊዜ በእያንዳንዱ የማቅለያ ምክንያት መነሻ ተደርጎ የተያዘው የቅጣት መጠን በሁለት እርከን እንደሚቀነስ በቅጣት አወሳሰን መመሪያው በአንቀጽ 16(6) በተደነገገው መሰረት ተፈጻሚ የሚደረገው የቅጣት መጠን ላወሰን የሚገባው 3ኛ፣4ኛ እና 5ኛ አመልካቾችን በተመለከተ በእርከን 18 እንዲሁም 6ኛ አመልካችን በተመለከተ በእርከን 16 በተመለከተው ፍቅድ ስልጣን መሰረት መሆኑን ተገንዝበናል።
ሲጠቃለል በአመልካቾቹ ላይ የተሰጠው ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
በማዕከላዊ ዞን በአብይ ዓዲ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 01450 በ24/05/2005 ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች እንደቅደም ተከተሉ በመ.ቁ.57452 በ08/09/2005 ዓ.ም. እና በመ.ቁ. 59621 በ23/11/2005 ዓ.ም. በትዕዛዝ የጸናው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 195(2)(ለ)(2) መሰረት ተሻሽሐል።
በተ.ቁ. 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ 1ኛ እና 2ኛ አመልካቾችን በተመለከተ የተሰጠው የጥፋተኝነትም ሆነ የቅጣት ውሳኔ ክፍል ፀንቷል።
በተ.ቁ. 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ በ3ኛ፣4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ አመልካቾች ላይ በወ/ሕ/አ.
32(3) እና 540 ስር ተሰጥቶ የነበረው የጥፋኝነት ውሳኔ ተሻሽሎ ተጠቃሾቹ አመልካቾች ጥፋተኞች ላባሉ የሚገባው በወ/ሕ/አ. 32(1) (ሀ) እና 577(1) እና (3) ስር ነው በማለት ወስነናል።
በተሻሻለው የቅጣት ውሳኔ መሰረት በዚህ ጉዳይ የታሰሩት የሚታሰብላቸው ሆኖ 3ኛ፣4ኛ እና 5ኛ አመልካቾች እያንዳንዳቸው በሶስት ዓመት ከሰባት ወር ጽኑ እስራት፤6ኛው አመልካች ደግሞ በሶስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስነናል።
በዚህ ውሳኔ መሰረት እንዲያስፈጽም የውሳኔው ግልባጭ አመልካቾቹ ለሚገኙበት ማረሚያ ተቋም ይላክ።
የውሳኔው ቅጂ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.