No summary available.
ሚያዝያ22ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ልዑል ዘወድ - ጠበቃ አቶ ትዕዛዙ አበበ - ቀረቡ ተጠሪ፡- አጀመራ የወርቅ ግብይት ኃ/የተ/የግ/ማህበር - አልቀረቡም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የዋስትና ግድታ ውል ክርክርን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩም የተጀመረው የአሁን ተጠሪ ባአሁኑ አመልካችና የዚህ ሰበር ክርክር ተካፋይ ባልሆነውና የስር 1ኛ ተከሳሽ አቶ ገ/ኪዳን በርሄ በተባለ ግለሰብ ላይ በጋምቤላ ህዝቦች ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት የአኙዋሃ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት በመሰረቱት ክስ ነው። ተጠሪ ስር ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ አቤቱታ፡- የስር 1ኛ ተከሳሽ በተጠሪ ድርጅት ውስጥ በወርቅ ገዥነትና ተቆጣጣሪነት ሲሰራ በነበረበት ጊዜ ለወርቅ ግዥ ከማህበሩ ከወሰደው ገንዘብ ውስጥ ብር 57,406 አጉድሎ በመገኘቱ እና በዚህም ምክንያት ተከሳሹ ገንዘቡን ለማህበሩ ከከፈለ በኃላ ስራውን እንዲያቆም ተብሎ የነበር ቢሆንም ሆኖም ግን በመካከላቸው በቀን 25/12/2004 ዓ.ም በተደረገው ስምምነት መሰረት ተከሳሹ የጎደለውን ገንዘብ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ለማህበሩ መልሶ ለመክፈልና ለወደ ፊቱም ስራውን በታማኝነት ለመስራት ተስማምተዋል። በተስማማው መሰረት ግድታውን የማይወጣ ከሆነና በዚህ ምክንያት ለሚመጣው ኃላፊነትም የአሁኑ አመልካችን በዋስነት አቅረበዋል። ይህ እንዲህ ሆኖ ሳለ የስር ተከሳሹ አሁንም በድጋሚ ከማህበሩ ብር 80,000 በቀን 10/2/2005 ዓ.ም ከወሰደ በኋላ መጀመሪያ አጉድሎ ካልተከፈለው ጋር በድምሩ ብር 124,995 በገባው ግድታ መሰረት ስላልከፈለ ይሄንኑ ገንዘብ ከዋሱ ጋር እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት አመልክተዋል።
የስር 1ኛ ተከሳሹም ቀረቦ በሰጠው መልስ፡- እዳው መኖሩን አምኖ ነገር ግን ከማህበሩ ያልተከፈለው ኮሚሽን ስላለ ሂሳቡ ተሰልቶ ከታወቀ በኃላ እዳው እንዲከፈል ይታዘዝልኝ የሚል ይዘት ያለው መከራካሪያ ማቅረቡን የውሳኔ ግልባጩ ያሳያል እንዲሁም የአሁኑ አመልካችም ቀረቦ በሰጠው መልስ፡- ለብር 57,406 ተራ የሆነ ዋስትና ግድታ መግባቱን አምኖ ሆኖም ግን ዋና ባለ እዳ እያለ ለዚህም ቢሆን ልጠየቅ እንደማይገባና ለብር 80,000 ደግሞ ከመጀመሪያውም የዋስትና ግድታ አለመግባቱን ጠቅሶ መከራከሩን የስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ያመለክታል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የአኙዋሃ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ተከራከሪ ወገኖች ክርክር ከሰማ በኃላ የፍ/ብ/ህ/ቁ.1776 በዋቢነት ጠቅሶ ሁለቱም የስር ተከሳሾች በተጠሪ ጥያቄ መሰረት ገንዘቡን ይክፈሉ በማለት ወስኖባቸዋል። በስር ተከሳሾች አመልካችነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በበኩሉ ግራ ቀኙን ተከራካሪ ወገኖች አስቀርቦ ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍ/ቤቱን ውሳኔ በማፅናት ወስኗል። ቀጥሎም በአሁን አመልካች የቀረበለትን የሰበር አቤቱታ የተመለከተው የክልሉ ሰበር ችሎት በበኩሉ አቤቱታውን መርምሮ የሰበር ቅሬታው ለሰበር ሰሚ ችሎት አያስቀርብም በማለት መዝገቡን ዘግቷል።
አሁን በአመልካች የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይሄንኑ በሰር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ውሣኔ በመቃወም ለማስለወጥ ሲሆን የሰበር ቅሬታውም በዋናነት አመልካች የዋሰትና ግድታውን የፈረመው ለብር 57,406 እዳ ብቻ ሆኖ ሣለ የስር ፍ/ቤቶች የፍ/ብ/ህ/ቁ. 1922 ድንጋጌን በሚጥስ መልኩ የዋስትና ግድታ ከተገባበት እዳ መጠን በላይ ለሆነ ገንዘብና ለብር 124,995 አመልካችን ተጠያቂ ማድረጋቸው ተገቢ ካለመሆኑም በላይ አመልካች የገባው የዋስትና ግድታ አይነትም ተራ ዋሰትና ከመሆኑም አኳያ ዋናው ባለእዳ እዳውን መክፈል የማይችል መሆኑ ሣይረጋገጥ አመልካች ዋሰትና የተገባበትን ገንዘብ እንዲከፍል በስር ፍ/ቤቶች መወሰኑ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1934 ድንጋጌ አኳያ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ስላለበት ስህተቱ ታርሞ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
አቤቱታውም በሰበር አጣሪ ችሎቱ ተመርምሮ አመልካች የዋስትና ግድታ ከገባው ብር 57,4ዐ6 በተጨማሪ ዋናው ባለእዳ ከዋሰትና ውሉ በኋላ ላጐደለው ገንዘብ ብር 80,000 ኃላፊ ነው ተብሎ በስር ፍ/ቤቶች የመወሰኑን አግባብነት ከፍ/ብ/ህ/ቁ. 1922 እና 1924/1/ ድንጋጌዎች አንፃር ለመመርመር ሲባል አቤቱታው ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ ተደርጐ ተጠሪም ቀርቦ በቀረበው አቤቱታ ላይ በጽሑፍ መልሱን ሰጥቷል መሰረታዊ ይዘቱም በአመልካች አስቀድሞ የተገባው የዋስትና ግድታ ዋናው ባለእዳ በኃላ ላይ ላጐደላው ብር 80,000 ጭምር በፍ/ብ/ህ/ቁ.1925(1) ድንጋጌ መሰረት በዋሱ ላይ ኃላፊነትን የሚያስከትል በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው የሰበር አቤቱታ ውድቅ ተደርጐ በስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ የተፈጠረ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የለም በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው።አመልካችም በበኩሉ የሰበር አቤቱታውን በማጠናከር የመ/መልሱን ሰጥቶበታል ።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በበኩላችን የሰበር አቤቱታውን ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ ሲደረግ ተይዞ ከነበረው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
በመሰረቱ የዋስትና ግድታ ግልፅ መሆን እንዳለበት እና ኃላፊነቱም ግድታ ከተገባለት እዳ ወሰን ለማለፍ እንደማይችል እና እንዲሁም ይህ ለአፈፃፀሙ ግድታ የተገባለት የእዳ መጠን ወይም የገንዘብ ልክ በዋስትና ውሉ ካልተገለፀ ዋስትናው ፈራሽ እንደሚሆን ከፍ/ብ/ህ/ቁ1922(2)(3) ድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ ይቻላል።ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለሰ ደግሞ ዋናው ባለእዳ የሆኑት አቶ ገ/ኪዳን በርሕ ያጉደሉትን ገንዘብ ብር 57,406 በተቀመጠው ቀን ገደብ መሰረት ለተጠሪ ካልከፈሉ የአሁኑ አመልካች ተያዥ ወይም ዋስ ሆኖ ገንዘቡን ለተጠሪ ለመክፈል በመስማማት የዋስን ግድታ በቀን 25/12/2004 ዓ.ም በተፃፈ ውል መግባቱን ከክርክሩ ሂደት ለመገንዘብ ተችሐል ።
ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው አመልካች በገባው ዋስትና ውል (በ25/12/2004 ዓ/ም በተፈረመው ሰነድ) ላይ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ብር 57,406 ብቻ መሆኑን እንጂ ከዚህ ውጭ ዋስትና የተገባለት ልላ የገንዘብ መጠን በዋስትና ውሉ ላይ አልተገለፀም። እንዲህ ከሆነ ደግሞ አመልካች በግልፅ ለተጠቀሰው ገንዘብ ብር 57,406 ብቻ ካልሆነ ከዚህ ውጭ በዋስትና ውሉ ላይ ላልተመለከተው እና በኋላ ላይ ዋናው ባለዕዳ ከተጠሪ ማህበር በቀን 10/2/2005 ዓ/ም ወስዶ አጉድሐል ለተባለው ብር 80,000 አመልካች በዋስትና ውሉ መሰረት በኃላፊነት ላጠየቅ እንደማይችል ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1922 ድንጋጌ ይዘት መገንዘብ አያዳግትም።
በእርግጥ ገና ለወደፊት ላደርስ ለሚችል ግድታ አፈፃፀምም ዋስ ለመሆን እንደሚቻል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1925(1) ስር የተመለከተ ቢሆንም እንኳ ይህም ከዋስትና ውል ፎርም ጋር በተያያዘ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1922 ድንጋጌ ስር የተመለከተውን መስፈርት ላያሟላ ይገባል። ምክንያቱም ለወደፊቱ ለሚመጣ ግድታም ለሚገባ የዋስትና ውል ለምን ያህል እዳ መጠን ወይም ገንዘብ ልክ እንደተገባ በውሉ ካልተገለፀ ዋሱንም ያለአግባብ ላጐዳ የሚችል ከመሆኑም በላይ ይህ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1925(1) ድንጋጌም ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1922(3) ድንጋጌ ጋር በተጣጣመ ተፈፃሚነት እንዲኖረው ላደረግ ይገባል። ከዚህ አኳያ በአመልካች የተፈረመው የዋስትና ውል ከብር 57,406 በስተቀር ገና ወደፊት ዋናው ባለእዳ ላያጐድል የሚችለውን እዳንም ጭምር ላያካትት ይችላል ቢባልም እንኳን ለምን ያህል እዳ መጠን ወይም የገንዘብ ልክ እንደሆነ በውሉ ስላልተገለፀ ተጠሪ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1925(1) ድንጋጌን በምክንያትነት ጠቅሶ ያቀረበው ክርክር ከዚህ በላይ በተገለፀው ምክንያት ተቀባይነት ያለው ሆኖ አላገኘንም በመሆኑም የስር ፍ/ቤቶች አመልካችን በዋስትና ውሉ ላይ ከተገለፀው የገንዘብ መጠን ብር 57,406 ወሰን በማለፍ ኃላፊ በማድረግ የሰጡት ውሳኔ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1922 ድንጋጌ ይዘት አኳያ ስህተት ያለበትና ላታረም የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል።
በልላ በኩል ግን አመልካች ዋናው ባለ እዳ እዳውን መክፈል የማይችል መሆኑ ሳይረጋገጥ በእኔ ላይ በስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1934 ድንጋጌን ያገናዘበ አይደለም በማለት ያቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ ይህ ክርክር እንደአግባብነቱ በአፈፃፀም ጊዜ የሚታይ ከመሆኑም በላይ አመልካችም ባለገንዘቡ አስቀድሞ የዋናውን ባለእዳ ንብረት ለማፈላለግ እና በእሱ ላይ ክርክሩን ለመቀጠል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1936(1) ስር እንደተመለከተው የሚያስፈልገውን ወጭ አስቀድሞ ለባለገንዘቡ መስጠቱ ባልተገለፀበት ሁኔታ ክርክሩ ተቀባይነት ላኖረው የሚገባ አይደለም። በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የአኙዋሃ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት በመ/ቁ 0068/2005 በቀን 14/10/05 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ//05 በ17/11/05 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ እና እንዲሁም የክልሉ ሰበር ችሎት በመ//05 በ6/2/06 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
አመልካች በገባው ዋስትና ግድታ መሰረት ላጠየቅ የሚገባው ለብር 57,406 (ሃምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ስድስት ብር) ብቻ ነው በማለት ወስነናል። አመልካች ከዚህ በላይ ላለው የዋናው ባለዕዳ ዕዳ በኃላፊነት ላጠየቅ አይችልም ብለናል።
አመልካች የገባው የዋስትና ግድታ ዓይነት ተራ ዋስትና በመሆኑ አመልካች ይሄንን የተጠቀሰውን ገንዘብ (57,406) ብር ለመክፈል የሚገደደው ዋናው ባለዕዳ መክፈል ካልቻለ ብቻ ነው ብለናል።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
በዚህ መዝገብ ላይ ተሰጥቶ የነበረውን የአፈፃፀም እግድ ተነስቷል። መነሳቱም ተገልፆ አፈፃፀሙን ለያዘው ፍ/ቤት ይተላለፍ።
የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሻሻሉን እንዲያውቁ የውሳኔ ግልባጭ ይድረሳቸው።