No summary available.
ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ክፍሉ ገ/ማርያም - ጠበቃ አቶ መለሰ ጉርሙ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ አስመረት መኮንን - ጠበቃ ጎሳዬ ጉርሙ ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የቤት ይለቀቅልኝ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ አመልካች በቦረና ዞን በቡል ሆራ ወረዳ ፍ/ቤት 1ኛ ተከሳሽ በነበሩት የአሁኗ ተጠሪ ላይ በ24/06/2002 ዓ.ም አዘጋጅተው ባቀረቡት ክስ ነው።2ኛ ተከሳሽ የነበረው የዚህ ሰበር ክርክር ተካፋይ ያልሆነው የከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት ነው።የክሱም ይዘት ባጭሩ፡-ከሳሽ በቡል ሆራ ከተማ ከአባታቸው ከአቶ ገ/ማርያም ዳኜ በውርስ የተላለፈላቸው 900 ካ.ሜ ይዞታ ያለው ቤት እንዳላቸው፣1ኛ ተከሳሽ በዚሁ ቤት በዝምድና መልክ በከሳሽ ፈቃድ ገብተው ሲኖሩ ከሳሽ በማያውቁት ሁኔታ የቤቱን የባለቤትነት ስም ወደራሳቸው አዛውረው እንደተገኙ፣ከሳሽ ይህ መፈጸሙን ያወቁት በ15/06/2002 ዓ.ም እንደሆነ የሚገልጽ ሆኖ 2ኛ ተከሳሽ አላግባብ የፈጸመውን የስም ዝውውር ሰርዞ ወደነበረበት እንዲመልስ እና 1ኛ ተከሳሽም ቤቱን ለቀው እንዲወጡ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው።
1ኛ ተከሳሽ በ08/08/2002 ዓ.ም በሰጡት የተሻሻለ መልስ አባታቸው በ1972 ዓ.ም ከሞቱ ከ30 ዓመት በኋላ ከሳሽ ያቀረቡት የውርስ ቤት ይለቀቅልኝ ጥያቄ በይርጋ እንደሚታገድ፣በቤቱ የገቡት ከሳሽ እንደሚሉት በዝምድና መልክ ወይም በጥገኝነት ሳይሆን ከልጃቸው ዳኜ ክፍሉ ጋር በ1994 ዓ.ም ጋብቻ በመፈጸማቸው እንደሆነ፣በጋብቻውም ሁለት ልጆችን እንደወለዱ፣ዳኜ ክፍሉ በ1996 ዓ.ም በሞት እንደተለየ፣ከሳሽ ቤቱን ከእናታቸው እና ከወንድሞቻቸው መግዛታቸውን (ድርሻ መክፈላቸውን) ገልጸው ልጃቸው ጋብቻ ከመፈጸሙ አስቀድሞ በ1981 ዓ.ም በስጦታ እንደሰጡት፣ስጦታውን የሚቃወም ካለ እንዲቀርብ የከተማው አስተዳደር ቁጥሩ 489/1981 በሆነ እና በ04/03/1981 በወጣ ማስታወቂያ ጥሪ አድርጎ ተቃዋሚ ባለመቅረቡ ስሙን ወደ ሟች ዳኜ ክፍሉ እንዳዛወረ፣ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግብሩ ሲከፈል የነበረው በሟች ስም፣እርሱ ከሞተ በኋላ ደግሞ በ1ኛ ተከሳሽ ስም በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1168 መሰረት በቤቱ ላይ መብት ያላቸው ሟች ልጃቸው እና 1ኛ ተከሳሽ እንጂ ከሳሽ እንዳልሆኑ በመግለጽ የተከራከሩ ሲሆን ክሱ በተሰማበት ጊዜም ከጋብቻቸው በኋላ ሰባት ክፍል ቤቶችን ከሟች ባለቤታቸው ጋር መስራታቸውን በመግለጽ አስመዝግበዋል።2ኛ ተከሳሽ በበኩሉ በ30/06/2002 ዓ.ም በሰጠው መልስ ቤቱ ቀደም ሲል ጀምሮ በሟች ዳኜ ክፍሉ ስም ተመዝግቦ የነበረ መሆኑን እና ስሙን ወደ 1ኛ ተከሳሽ ስም ላያዛውር የቻለው 1ኛ ተከሳሽ የሟች ልጆችን ወራሽነት እና የራሷን ሚስትነት በመ.ቁ. 84/96 በ07/04/1996 ዓ.ም በማረጋገጥ ከቡል ሆራ ወረዳ ፍ/ቤት ባቀረበችው ማስረጃ መሰረት መሆኑን ገልጾ ፍ/ቤቱ እንዲያሰናብተው ጠይቋል።
ፍ/ቤቱም ክሱን እና የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኋላ አጠቃላይ ክርክሩን መርምሮ ከሳሽ ክስ ያስነሳውን ቤት ለልጃቸው ዳኜ ክፍሉ በስጦታ በመስጠታቸው የከተማው አስተዳደር ቁጥሩ 489/1981 የሆነ እና በ04/03/1981 የወጣ ማስታወቂያ አውጥቶ ተቃዋሚ ባለመቅረቡ በስጦታ ውሉ መሰረት የቤቱ የባለቤትነት ስም ወደ ዳኜ ክፍሉ ተዛውሯል ከማለት ውጪ ከ1ኛ ተከሳሽ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2444፣881፣882 እና 883 ድንጋጌዎች መሰረት የሕጉን መስፈርቶች አሟልቶ የተደረገ የስጦታ ውል በማስረጃነት ያላቀረቡ በመሆኑ ስጦታን አስመልክቶ የቀረበው ክርክር ተቀባይነት እንደልለው፣የቤቱ ግብር ለ15 ዓመታት ሳያቋርጥ የተከፈለ ባለመሆኑ 1ኛ ተከሳሽ በመከራከሪያነት ያቀረቡት የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1168 ድንጋጌ ለክርክሩ ተፈጻሚነት እንደልለው እና የከሳሽ የወራሽነት መብትም በፍ/ብ/ሕ/ቁ.1000(2) መሰረት በይርጋ የሚታገድ እንዳልሆነ ገልጾ 1ኛ ተከሳሽ ቤቱን ለቀው እንዲያስረክቡ እና 2ኛ ተከሳሽም የባለቤትነት ስሙን በከሳሽ ስም እንዲመዘግብ ውሳኔ ሰጥቷል።
በ1ኛ ተከሳሽ ጠያቂነት ይግባኙን የተመለከተው የቦረና ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ቤቱ በስጦታ የተላለፈ መሆኑን ስልጣን ያለው የከተማው አስተዳደር ማረጋገጡን፣ግብሩም በሟች ዳኜ ክፍሉ እና ከእርሱ ሞት በኋላ ደግሞ በ1ኛ ተከሳሽ ስም በአጠቃላይ ከ1988 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ የተከፈለ መሆኑን፣እነዚህ ማስረጃዎች ሀሰተኛ ስለመሆናቸው ከሳሽ አሳማኝ እና ተጨባጭ ክርክር አቅርበው ማስተባበል አለመቻላቸውን እና የከሳሽ የወራሽነት መብትም በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1000(1) መሰረት በይርጋ የሚታገድ መሆኑን ገልጾ የወረዳ ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር 1ኛ ተከሳሽ ቤቱን ላለቁ አይገባም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።ከሳሽ በተራቸው ባቀረቡት ይግባኝ ሳቢያ የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የከሳሽ የክስ ነጥብ 1ኛ ተከሳሽ ቤቱን አላግባብ ወደ ራሷ ስም አዛውራለች የሚል እንጂ የወራሽነት ክርክር ባለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1000(1) የተመለከተው የይርጋ ድንጋጌ ለክርክሩ አግባብነት እንደልለው ጭምር በመግለጽ የዞኑን ከ/ፍ/ቤት ውሳኔ ሽሮ የወረዳ ፍ/ቤት ውሳኔ በማጽናት ውሳኔ ሰጥቷል። ጉዳዩ በመጨረሻ የቀረበለት የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ሰበር ችሎት ክርክሩን ከሰማ በኋላ ይርጋን አስመልክቶ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የያዘው አቋም የሚነቀፍ አለመሆኑን ገልጾ ነገር ግን ሟች ዳኜ ክፍሉ ቤቱን በስጦታ አግኝቷል ወይስ አላገኝም? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ሟች ዳኜ ክፍሉ እና እርሱ ከሞተ በኋላ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ በአጠቃላይ ከ1988 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ የቤቱን ግብር ለ15 ዓመታት በተከታታይ ወይም ሳይቋረጥ የከፈሉ በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1168 መሰረት የቤቱ ባለቤት እንደሚሆኑ ገልጾ የይግባኝ ሰሚ ችሎቱን ውሳኔ በመሻር የዞኑን ከ/ፍ/ቤት ውሳኔ አጽንቷል።
No topics extracted.
አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት ይዘቱ ከላይ የተመለከተው የክልሉ ሰበር ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካች አከራካሪውን ቤት ለሟች ልጃቸው ዳኜ ክፍሉ በስጦታ እንዳልሰጡ በሚከራከሩበት እና የቤቱ ግብር ለ15 ዓመታት ተከፍሐል ለተባለውም የተከፈለው በተከታታይና ሳይቆራረጥ አለመሆኑን እና በክርክር ላይ የነበሩበትን ጊዜ(ዓመት) ጭምር ያካተተ መሆኑን በሚከራከሩበት የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የይግባኝ ሰሚውን ችሎት ውሳኔ የመሻሩን አግባብነት ከፍ/ብ/ሕ/ቁ.1168(1) ድንጋጌ አንጻር ተጠሪዋ ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልካች ክስ ያስነሳውን ቤት ከእናታቸው እና ከወንድሞቻቸው መግዛታቸውን (ድርሻ መክፈላቸውን) ገልጸው ልጃቸው ጋብቻ ከመፈጸሙ አስቀድሞ በ1981 ዓ.ም በስጦታ አስተላልፈውለታል በማለት ተጠሪዋ የተከራከሩ ቢሆንም ስጦታውን የሚቃወም ካለ እንዲቀርብ የከተማው አስተዳደር በቁጥር 489/1981 በ04/03/1981 ያወጣውን ማስታወቂያ ከማቅረብ ውጪ በሕጉ አግባብ የተቋቋመ የስጦታ ውል ስለመኖሩ ተጠሪዋ የስጦታ ውሉን በማስረጃነት በማቅረብ ማስረዳት አለመቻላቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የይግባኝ ሰሚውን ችሎት ውሳኔ ሽሮ የከ/ፍ/ቤት ውሳኔን በውጤት ደረጃ ለማጽናት የቻለው ግብሩ ለ15 ዓመታት በተከታታይ የተከፈለ መሆኑ ሟች ባለቤቷን እና ተጠሪዋን የቤቱ ባለቤት ያደርጋቸዋል በማለት ነው።በ1988 ዓ.ም የተቆረጠው የግብር ካርኒ ግብሩ የተከፈለው ለ1988 ዓ.ም ብቻ ሳይሆን ከ1988 ዓ.ም በፊት ለነበሩት ሶስት ዓመታት ጭምር እንደሆነ ከግራ ቀኙ የሰበር ክርክር መገንዘብ የተቻለ በመሆኑ የቤቱ ግብር በሟች ባለቤቷ እና በተጠሪዋ ስም የተከፈለው ክርክሩ የተጀመረበትን 2002 ዓ.ም ሳይጨምር ከ15 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል። በመሆኑም ግብሩ ለ15 ዓመታት ተከፍሐል የተባለው ግራ ቀኙ ክርክር የጀመሩበትን ዓመት ጭምር በመቁጠር ነው በማለት አመልካች ያቀረቡት ክርክር በግራ ቀኙ ክርክር የተረጋገጠውን ፍሬ ነገር መሰረት ያደረገ ሆኖ አልተገኘም።
ግብሩ ለ15 ዓመታት ተከፍሐል ቢባል እንኳ የተከፈለው በተከታታይ ወይም ሳይቋረጥ ባለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1168 ድንጋጌ በዚህ ጉዳይ ተፈጻሚነት ላኖረው አይገባም በማለት አመልካች ያቀረቡትን የክርክር ነጥብ በተመለከተ እንደተባለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለእጅ (ባለይዞታ) የሆነ ሰው የዚሁ ንብረት ባለቤት መሆን የሚችለው ግብሩን ባለማቋረጥ 15 ዓመት በስሙ ከከፈለ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1168(1) በግልጽ ይደነግጋል። በተያዘው ጉዳይ ግብሩ በሟች እና በተጠሪዋ ስም የተከፈለው ከ15 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ቢሆንም የተከፈለው ግን ለእያንዳንዱ ዓመት በተናጠል ብቻ ሳይሆን የተወሰኑ ዓመታትን አጠቃሎ በአንድ ደረሰኝ በመክፈል ጭምር መሆኑ ተረጋግጧል።አመልካች የሚከራከሩትም የሁለት ወይም የሶስት ዓመታት ግብር ተጠቃሎ የተከፈለባቸው ደረሰኞች ተቀባይነት ያገኙት አላግባብ ነው በማለት ነው።በመሰረቱ ባለይዞታው የንብረቱ ባለቤት መሆን የሚችለው ግብሩን ለ15 ዓመታት ባለማቋረጥ ከከፈለ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1168(1) የተቀመጠው ድንጋጌ ዓይነተኛ ዓላማ ስውር ወይም አሻሚ በሆነ መንገድ የተደረገ ይዞታ ሕጋዊ ውጤት ላኖረው እንደማይገባ እና በአንጻሩ ባለይዞታው ግብሩን በተከታታይ የከፈለው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብት እንዳለው በማመን እንዲሁም በልሎች ዘንድም የዚህኑ ዓይነት ግምት ለማሳደር በሚያስችል ሁኔታ መሆኑን ማረጋገጥ ነው።በተያዘው ጉዳይ ግብሩ በሟች እና በኋላም በተጠሪ በተከታታይ ሲከፈል የነበረው ቤቱ ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ በሟች እጅ፣እርሱ ከሞተበት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በተጠሪ እጅ መሆኑ በተረጋገጠበት እና በከተማው አስተዳደርም ቤቱ ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ተመዝግቦ የሚታወቀው በሟች እና ከእርሱ ሞት በኋላ ደግሞ በተጠሪ ስም መሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ በመሆኑ ይዞታው አሻሚ ወይም ስውር ነበር ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም።ይህ ሁሉ ሲደረግ አመልካች ይኖሩ የነበረው በዚያው ከተማ እና ቀበል ክልል ውስጥ ስለመሆኑ በክርክሩ የተረጋገጠ በመሆኑ አመልካች ቤቱ በተጠሪ ስም መመዝገቡን እና ግብር መከፈሉን ያወቅሁት በ15/06/2002 ዓ.ም ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር ሕጋዊ ተቀባይነት ላሰጠው የሚገባ አይደለም።በክርክሩ እንደተረጋገጠው የአመልካች አባት አቶ ገ/ማርያም ዳኜ በ1972 ዓ.ም ከሞቱ በኋላ አመልካች የቤቱን ግብር በስማቸው የከፈሉት ከ1972 ዓ.ም እስከ 1975 ዓ.ም ድረስ ብቻ መሆኑም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
ሲጠቃለል የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የይግባኝ ሰሚውን ችሎት ውሳኔ በመሻር ሟች ዳኜ ክፍሉ እና ተጠሪ የቤቱን ግብር ለ15 ዓመታት ሳያቋርጥ የከፈሉ በመሆኑ እና ይህም በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1168 መሰረት በቤቱ ላይ የባለቤትነት መብት የሚያስገኝላቸው በመሆኑ ተጠሪ ቤቱን ለቀው ለአመልካች ላያስረክቡ አይገባም በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ፀንቷል፡ 2. የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
የሰበር ክርክሩ ያሰከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።