No summary available.
ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፉ አህመድ አመልካች፡- አቶ ሙሳ ደገፈ የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ ጥላሁን ደስታ /ጠበቃ ሽመልስ ከፍያለሁ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርደ ተሰጥቷል
ጉዳዩ የሁከት ይወገድልኝ ክርክርን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩም የተጀመረው በስሜን ሸዋ መስተዳድር ዞን አልላቱ ወረዳ ፍ/ቤት የሰበር አመልካች ከሳሽ በመሆን ተጠሪ ላይ ባቀረበው ክስ መነሻነት ነው።
አመልካች ጥቅምት 4 ቀን 2000 ዓ/ም በተፃፈ ለስር ፍ/ቤት በቀረበው ክስ አቤቱታ፡-በ1993 ዓ/ም ከአቶ ደስታ አያኔ እና ወ/ሮ ሽዋዬ ቡልቻ በልዋጭ ባገኘሁት ይዞታ ላይ ባህር ዛፍ ተክዬ በእጄ ያለውን ተጠሪ በ27/01/2000 ዓ/ም እንዳልጠቀምበት በመከልከል ሁከት ስለፈጠረብኝ ሁከቱ እንዲቆም ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት ጠይቋል።
ተጠሪም በበኩል ቀርቦ በሰጠው መልስ፡- ይህ ክርክር የቀረበበት ይዞታም ሆነ ባህር ዛፍ የአባቱ መሆኑን፤ተጠሪም ወራሽ በመሆን ይዞታው የተላለፈለት መሆኑንና ይህ በውርስ ያገኘው ይዞታ ደግሞ እንዳይነካበት መከልከሉ መብት እንጂ ሁከት ላባል እንደማይችል ጠቅሶ ተከራክሯል።
ፍ/ቤቱም በበኩሉ ግራ ቀኙን አከራክሮ ተጠሪ የፈጠረውን ሁከት እንዲያቆም በማለትውሳኔ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ተጠሪ ውሳኔውን በመቃወም ቅሬታውን ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በማቅረቡ እና ፍ/ቤቱም በበኩሉ ግራ ቀኙን አስቀርቦ ካከራከረ በኋላ አመልካች ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ይዞታ ከተጠሪ አባት በልዋጭ አግኝቸበታለሁ በማለት የጠቀሰው የውል ስምምነት ሰነድ (በ17/7/1993 ዓ.ም የተደረገ) ላይ ያለው ፊርማ የተጠሪ አባት አቶ ደስታ አያል መሆን አለመሆኑ ተጣርቶ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ በጉዳዩ ላይ ተገቢው ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ክርክሩን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 343(1) መሰረት መልሶ ለወረዳ ፍ/ቤቱ ልኳል።
የወረዳ ፍ/ቤቱም በበኩሉ በሰነዱ ላይ ያለው ፊርማ በፎሬንሲክ ሳይንስ እንዲመረመር ካደረገ በኋላ ፊርማው የተጠሪ አባት መሆን አለመሆኑን ለመለየት አልተቻለም በሚል የተገለፀለትን የምርመራ ውጤት ጭምር መሰረት አድርጐ ጉዳዩን መመርመሩን ከገለፀ በኋላ አመልካች ክርክር የቀረበበትን ይዞታ በልዋጭ አግኝቸበታለሁ በማለት የሚከራከረው ውል ላይ ያለው ፊርማ የተጠሪ አባት ፊርማ አይደለም ወደሚል መደምደሚያ ላይ የአመልካችን ክስ ውድቅ በማድረግ ወስኗል። አመልካችም በበኩሉ በውሳኔው ቅር በመሰኘት ቅሬታውን ለዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት እና የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ደረጃውን ጠብቆ ያቀረበ ቢሆንም በሁለቱም ደረጃ ቅሬታው ተቀባይነት አላገኘም ሆኖም ግን ጉዳዩን የተመለከተው የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ግራ ቀኙን አስቀርቦ ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ክርክር የቀረበበት ይዞታ ማን እጅ እንደነበር ማን ግብር ሲገብርበት እንደነበር በይዞታው ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር የተሰጠው ለማን እንደሆነ እና ተጠሪ ይዞታውን ሁከት ፈጥሮ መያዝ አለመያዙ በግራ ቀኙ የሰው ምስክሮች እና እንዲሁም ከሚመለከታቸው አስተዳደር አካላትም ተጠይቆ ተገቢ ማጣሪያ ከተደረገ በኋላ በጉዳዩ ላይ የመሰለውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ክርክሩን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.343(1) መሰረት በድጋሚ ወደ ወረዳ ፍ/ቤቱ መልሶታል። የወረዳ ፍ/ቤቱም በበኩሉ ጉዳዩ በተመራለት መሰረት በግራ ቀኙ ምስክሮች እና እንዲሁም የክፍሉ ቀበል አስተዳደር እና የወረዳውን አካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ጽ/ቤት ስለ ጉዳዩ ጠይቆ ካጣራ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች በይዞታው ላይ የተከለውን ባህርዛፍ እንዳይጠቀምበት በተጠሪ የተፈጸመበት መሰናክል ሁከት አይደለም ላባል የሚቻል ስለላልሆነ ተጠሪ ሁከቱን አቁሞ አመልካች ክርክር ባስነሳው ይዞታ ላይ ያለውን መብት እንዲጠቀምበት በማለት ወስኗል።፡ በተጠሪ አመልካችነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በበኩሉ ጉዳዩን መርምሮ ቅሬታው ተቀባይነት የለውም በማለት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.337 መሰረት ሰርዞታል። ቀጥሎ 2ኛ ይግባኙን የተመለከተው የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በበኩሉ ግራ ቀኙን አስቀርቦ ከሰማቸው በኋላ ጉዳዩን መርምሮ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.348(1) መሰረት የበታች ፍ/ቤቶችን ውሳኔ አጽንቷል። ሆኖም ግን ጉዳዩን ቀጥሎ በሰበር የተመለከተው የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ግራ ቀኙን አስቀርቦ ከሰማቸው በኋላ ይህ ክርክር የቀረበበት ይዞታ ወደ ተጠሪ ተመልሶ የይዞታ ማረጋገጫ ማስረጃም ተሰጥቶት ግብርም እየገበረበት በእጁ ባለው መሬት ላይ ተጠሪ ሁከት ፈጥሯል ለማለት የሚቻል ስላልሆነ የበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስሕተት ያለበት ነው በማለት ሽሮታል።
አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይሄንኑ የክልሉ ሰበር ችሎት ተጠሪ ሁከት ፈጥሯል ማለት አይችልም ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ የበታች ፍ/ቤቶችን ውሳኔዎች መሻሩ መሰረታዊ የህግ ስህተት ስላለበት ታየቶ ይታረምልኝ የሚል ሲሆን ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በበኩላችን ለዚህ ሰበር አቤቱታ መነሻ በሆነው ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነየህግስህተትተፈፅሞበታል ለማለት ይቻላል?
ወይስአይቻልም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ጉዳዩን መርምረናል። እንደመረመርነውይህ ለክርክሩ መነሻየሆነው ይዞታና ኋላም ባህር ዛፍ ተተክሎበታል የተባለው ይዞታነቱ በመጀመሪያ የተጠሪ አባት የአቶ ደስታ አያኔ የነበረ ስለመሆኑከ1993 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ግን በአመልካች ስም ግብር እየተገበረበት በእርሳቸው ይዞታ ስር መቆየቱን፣ መሬቱ በአመልካች ይዞታ ስር በቆየበት ጊዜ ባህር ዛፍ በአመልካች የተተከለበት መሆኑን፣ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀትም በ1998 ዓ.ም በአመልካች ስም ተሰጥቶ የነበረመሆኑን፣ሆኖም ግን ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ይዞታ ተጠሪ ከአባቴ አቶ ደሰታ አያኔ በውርስ ላተላለፍልኝ የሚገባ የውርስ ሀብት ነው በማለት እናቱ ወ/ሮ ሸዋዬ ቡልቻን በ1999 ዓ.ም ከሶ በ12/9/99 ዓ.ም ማስፈረዱን፣ በፍርዱ መሰረትም ይዞታውን በፍርድ አፈፃፀም ትዕዛዝ በ2001 ዓ.ም ውስጥ መቀበሉን ይሄንኑ ተከትሎምከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የይዞታው ግብር በተጠሪ ስም መገበሩንና እንዲሁም በ2002 ዓ.ም ውስጥ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀትም በስሙ የሰጠው ስለመሆኑ በስር ፍ/ቤት በማስረጃ መረጋገጡንና እንዲሁም በዚህ ሰበር ችሎት ክርክር ደረጃም ግራ ቀኙ ካደረጉት የጽሑፍ ክርክር ይዞታው በውርስ ለተጠሪ ይገባል ተብሎ በተሰጠው ፍርድ መሰረት ተጠሪ ይዞታውን በአፈፃፀም ለመረከብ በስር ፍ/ቤት አስከፍቶ በነበረው አፈፃፀም መዝገብ ላይ አመልካች በመቃወሚያ አቅራቢነት ጣልቃ ገብቶ በጉዳዩ ላይ ሲከራከሩበት ከቆዩ በኋላ እና በስተመጨረሻ የአመልካች የመቃወሚያ አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ተብሎ መወሰኑን ለመገንዘብ ተችሐል።
በመሰረቱ ይዞታው የተወሰደበት ወይም በይዞታው ላይ ሁከት የተነሣበት ሰው የተወሰደበት ነገር እንዲመለስለት ወይም የተነሣው ሁከት እንዲወገድለት እንዲሁም ስለደረሰበት ጉዳት ኪሣራ እንዲሰጠው ለመጠየቅ እንደሚቻል በፍ/ብ/ሕ/ቁ. አንቀጽ 1149 ንዑስ አንቀጽ 1 ስር ተመልክቷል። ይሁን እንጂ ተከሣሹ ለፈፀመው ድርጊት የሚፈቀድ መብት እንዳለው ማስረዳት ከቻለ በክሱ ኃላፊ ላሆን እንደማይገባ እንዲሁ ከፍ ሲል ከተጠቀሰው የሕጉ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 3 የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች በ1993 ዓ.ም በልዋጭ ባገኘሁት እና በይዞታዬ ስር በቆየ መሬት ላይ የተከልኩትን ባህርዛፍ ተጠሪ እንዳልጠቀምበት በማድረግ በ27/1/2000 ዓ.ም ሁከት ስለፈጠረብኝ ሁከቱ እንዲቆም የሚል ዳኝነት ላሰጠኝ ይገባል በሚል የሚከራከር ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ ክርክር ያስነሣው መሬት የአባቱ የነበረ መሆኑን ጠቅሶ ሆኖም ግን ይዞታውን በውርስ ስላገኘሁ እና ይህም በፍርድ ተረጋግጦ በኋላም በፍ/ቤት ትእዛዝ በአፈፃፀም የተረከብኩት ይዞታ ስለሆነ ድርጊቱ ሁከት ላባል አይችልም በሚል የሚከራከር መሆኑን ተገንዝበናል።
አመልካች በ1993 ዓ/ም በልዋጭ አግኝቼ በኋላም ባህርዛፍ ተክየበታለሁ የሚለውን ይዞታ በውርስ ለተጠሪ ይገባል ተብሎ በወረዳ ፍ/ቤቱ በ12/9/99 ዓ/ም ውሳኔ መሰጠቱ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሁከት ተፈጥሯል በተባለበት ጊዜ ይዞታው በፍ/ቤት አፈፃፀም ትዕዛዝ በተጠሪ እጅ ባይገባም ተጠሪ በፍ/ቤት ውሳኔ የይዞታው ባለመብት ሆኗል። እንዲሁም ሁከት ተፈጥሯል ከተባለበት ጊዜ በኋላ ቢሆንም ተጠሪ በፍርዱ መሰረት ይዞታውንም በአፈፃፀም እጁ አስገብቶ እና የይዞታ ማረጋገጫም በስሙ ተሰጥቶ እስከ አሁን ግብር በስሙ እየገበረበትና እየተጠቀመበት ያለ ስለመሆኑም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው ስለሆነም ሁከት ተፈጥሯል በተባለበት ጊዜም ቢሆን ተጠሪ አስቀድሞ በይዞታው ላይ በፍርድ የተረጋገጠ መብት ስለነበረው ይህ በተጠሪ ተፈፅሟል የተባለው ድርጊት ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1149(3) ድንጋጌ ይዘት አኳያ ተገናዝቦ ሲታይ ይሄንኑ በፍርድ የተረጋገጠለትን መብት ከማስፈፀም ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ከሚያሳይ በቀር ሁከት ላባል የሚችል ሆኖ አልተገኘም።
በመሆኑም የክልሉ ሰበር ችሎት ለክርክሩ መነሻ የሆነው ይዞታ በተጠሪ እጅ ገብቶ ባለበት ሁኔታ ሁከት አለ ማለት አይቻልም በማለት በውጤት ደረጃ በሰጠው ፍርድ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላላገኘን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የክልሉ ሰበር ችሎት በመ/ በ27/12/05 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት ፀንቷል።
የክልሉ ሰበር ችሎት በውጤት ደረጃ ሁከት የለም ሲል የሰጠው ውሳኔ በአግባቡ ነው ብለናል።
ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.