No summary available.
ግንቦት 07 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አብርሃ ሕሉፍ ገሰሰው ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ትበርህ ገብረሕይወት የቀረበ የለም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ በእርሻ መሬት ላይ የቀረበውን የይገባኛል ክስ መነሻ ያደረገ ክርክር የሚመለከት ነው።
ክርክሩ በመሬት ዳኝነት ሰጪ ጣቢያ ሲጀመር ከሣሽ የነበሩት ተጠሪ ሲሆኑ አመልካችን የከሰሱት በእርሻ መሬት ደልዳዮች (አከፋፋዮች) ተሸንሽኖ የተሰጠንን 50X25 ሜትር የሆነ መሬት ይልቀቁልኝ በማለት ነው።በዚህ መሰረትም የእርሻ መሬቱን ተገደው እንዲያስረክቡ ይወሰንላቸው ዘንድ ጠይቀዋል። አመልካች በበኩላቸው ለክሱ በሰጡት መልስ መሬቱን ከተጠሪ ቀድመው የተደለደሉትና በቋሚ ተክሎች አልምተው በመጠቀም ላይ የሚገኙት መሆኑንና ለተጠሪ የተሰጠበት አግባብም ሕጋዊ ያለመሆኑን በመቃወም ለሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት ጥያቄ አቅርበው መሬት ሸንሻኙ ክፍል ሳይቀበላቸው የቀረ መሆኑን ጠቅሰው መሬቱን እንድለቅ የሚደረግበት የሕግ ምክንያት የለም፤ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል። ክሱ የቀረበለት የመሬት ዳኝነት ጣቢያ ተከሣሽ (የአሁን አመልካች) መሬቱ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ቀድሞ ለአሁኑ አመልካች የተሰጠ መሆኑ ተረጋግጧል በማለት ክሱን ውድቅ አድርጎታል።
በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት በትግራይ ብ/ክ/መንግስት የቀይ ተኸላ ወረዳ ፍርድ ቤትም የመሬት ዳኝነት የሰጠውን ውሳኔ አፅንቶታል። በመጨረሻም ተጠሪ ለትግራይ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ በማቅረባቸው በዚህ ደረጃም ክርክሩ ተሰምቷል።የሰበር ችሎቱም ተጠሪ መሬቱን በድልድል ያገኙት መሆኑ ከተረጋገጠ አመልካች ቅሬታ ማቅረብና ጉዳያቸው መታየት ያለበት በአስተዳደሩ እንጂ በፍርድ ቤት ላሆን አይገባም በሚል ምክንያት የመሬት ዳኝነቱና የወረዳው ፍ/ቤት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ሽሮታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ላይ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-አከራካሪውን መሬት በሕጉ አግባብ ከተጠሪ ቀድሞ ከተሰጣቸው በኋላ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለተጠሪ የተሰጣቸው መሆኑ ተረጋግጦ እያለ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ መሻሩ ያላግባብ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታቸው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪ በሕጉ አግባብ ጥሪ ተደርጎላቸው ባለመቅረባቸው ጉዳዩ በልሉበት እንዲታይ ተደርጓል።
አቤቱታው በሰበር ችሎት እንዲታይ የተደረገው ክርክር ያስነሳው መሬት በመጀመሪያ ለአመልካች ከተሰጠ በኋላ እንደገና ለአሁኑ ተጠሪ ከተሰጠ በድጋሚ በላዩ ላይ ደርቦ ለሰጠው አካል ጥያቄው ከሚቀርብ በቀር በዳኝነት ላታይ የሚችል ጉዳት አይደለም የሚለውን መሰረት በማድረግ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ዳኝነት አግባብነት ለማየት ተብሎ ነው። በዚህ መሰረትም አቤቱታ የቀረበበትን ውሳኔ ከሥር ጀምሮ ከተደረገው ክርክር እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል።
ለክርክሩ መነሻ የሆነው መሬት ቀደም ሲል የተሰጠው ለአመልካች እንደሆነ እና በሱ ይዞታ ሥር ስለመቆየቱ እንዳላከራከረ ከሥር ጀምሮ ከተደረገ ክርክር እና ከተሰጡት ውሣኔዎች ይዘት ለመገንዘብ ችለናል። የመሬት ዳኝነት ጣቢያ በሰጠው ውሳኔ ላይ አመልካች መሬቱ ላወሰድበት አይገባም (አይችልም) የሚል መደምደሚያ ላይ የተደረሰው መሬቱ በህጉ አግባብ ለአመልካች ጥር 08 ቀን 2002 ዓ.ም በተሰጠበት ሁኔታ ከሕግ ውጪ ለአሁኑ ተጠሪ ተደርቦ ነሐሴ 20 ቀን 2002ዓ.ም መስጠቱ ያለአግባብ መሆኑ ተረጋግጧል በሚል ነው።የትግራይ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሁለቱም የሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ የሻረው አመልካች የመሬት አስተዳዳሪዎች ይዞታዬን ወስደው ለልላ ሰጥተውብኛል ካለ ማመልከት ያለበት በየደረጃው ለሚገኙ የአስተዳደር አካላት ነው ፤ ከዚህ ባለፈ ጉዳዩ በቀጥታ በፍ/ቤት የሚታይ አይደለም በማለት እንደሆነ ከውሣኔው ተገንዝበናል።
እንደምናየው ጉዳዩ በፍ/ቤት እንዲዳኝ ክስ ያቀረቡት ተጠሪ ናቸው። አመልካች መሬቱን የምለቅበት አግባብ የለም የሚል ክርክር ያቀረበ ሲሆን በመከላከያነትም የሕግ እና የፍሬ ነገር ነጥቦችን አንስቷል ክርክሩን በመጀመሪያ ደረጃ የሰማው የመሬት ዳኝነት ጣቢያ ፍ/ቤት እንደመሆኑ የግራ ቀኝ ወገኖቹን ክርክር ከሰማ በኋላ መሬቱ ለአሁኗ ተጠሪ መለቀቅ የለበትም ብሎ ወስኗል። ይህ ውሳኔ በፍ/ቤት የተሰጠ እንደመሆኑ በውሳኔው ያልተስማሙት ተጠሪ ይግባኙን ማቅረብ ያለባቸው በደረጃው ለተዋቀረው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ነው። አከራካሪው ጭብጥ ተጠሪ መሬቱን የተሰጡበት በሕጉ አግባብ ነው ወይ? የሚል በመሆኑ ክሱን የሰማው ፍ/ቤትም ሆነ ይግባኝ የሰሙት ፍ/ቤቶች ጭብጡን ከቀረበው የፍሬ ነገር እና የሕግ ክርክር አንፃር በማየት የየበኩላቸውን ውሳኔ ሰጥተዋል። ጥር 8 ቀን 2002 ዓ/ም ለአመልካች የተሰጠው መሬት ነሐሴ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ለተጠሪ ላሰጥ የቻለው በምን ሕጋዊ ምክንያት እንደሆነ አልተረጋገጠም። ይልቁንም ድልድሉ ተገቢ ያለመሆኑን ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ሥልጣን ያላቸው የመሬት ዳኝነቱና የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ድምዳሜ ያሳያል።
እነዚህ የዳኝነት አካላት መሬቱ ለተጠሪ የተደለደለ ከሕግ ውጪ ነው የሚል ምክንያት የሰጡት የትግራይ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት የተሻሻለ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም እንደገና ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 136/2000 አንቀጽ 31 “ን” በዋቢነት በመጥቀስ ነው። በበኩላችንም አዋጁንና ለማስፈፀም የወጣው የተሻሻለው የትግራይ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን ደንብ ቁ. 48/2000 “ን” ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ተመልክተናል። በአዋጁ አንቀጽ 5፣12፣14፣22 በመሬት የመጠቀም መብት የሚል ድንጋጌ የተቀመጠ ሲሆን ዝርዝር ሁኔታው ወይም አሰራሩም በተጠቃሽ ድንጋጌዎች ስር በተመለከቱት ንዑስ ድንጋጌዎች ስር በዝርዝር ተመልክቷል። በደንብ ቁጥር 48/2000 14፣15፣16 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ስር የገጠር መሬት መብት የሚገኝባቸውን መንገዶች የተዘረዘረ ሲሆን ከአንቀጽ 27 እስከ 29 ድረስም ለክርክሩ መነሻ የሆነውን የቦረቦር መሬት የማግኘት መብትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ተዘርዝረዋል። በመሆኑም በሕጉ አግባብ በድልድል ያገኘውን መሬት አንድ ሰው ላወስድበት የሚገባው በሕጉ የተመለከቱ ምክንያቶች ሲኖሩ ነው። በተያዘው ጉዳይ ግን ለአመልካች የተሰጠው ይዞታ ለተጠሪ ተደርቦ የተሰጠበት አግባብ ስለመኖሩ አልተረጋገጠም።
የትግራይ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በውሳኔው እንዳመለከተው የገጠር መሬትን የማስተዳደር ሥልጣን የተሰጠው በየደረጃው ለተዋቀሩ የአስተዳደር አካላት ቢሆንም እነዚህ አካላት የተሰጣቸውን ሥልጣን መተግበር ያለባቸው በአዋጁ እና በደንቡ በግልጽ በተቀመጡት ድንጋጌዎች መሰረት እንደሆነ ልብ ላባል ይገባል። ከላይ ተደጋግሞ እንደ ተገለፀው አመልካች የእርሻ መሬቱን አለቅም ያለው በአዋጁ እና በደንቡ የተጠበቀለትን መብት መሰረት በማድረግ ሲሆን ተጠሪ ክስ የመሰረቱበት ደግሞ ይህ በሕግ የተጠበቀለትን የአመልካች መብት በፍ/ቤት ውሳኔ ቀሪ እንዲሆንና መሬቱ እንዲለቀቅላቸው ነው። ፍ/ቤቶች ውሳኔ የሚሰጡት ሕግን መሰረት በማድረግ እንደሆነ ደግሞ በኢ.ፍ.ድ.ሪ ሕገ መንግሰት አንቀጽ 79(3) ከተቀመጠው ድንጋጌ እና የዳኝነት አመራር ስርዓትን በሚመለከት ከወጡት ህጎች መገንዘብ ይቻላል።
በመሆኑም የመሬት ዳኝነቱና የወረዳው ፍ/ቤት ለአመልካች የተሰጠው ድልድል ቀሪ የሚሆንበት አግባብ የለም በማለት የሰጡት ውሳኔ ተገቢ ሆኖ እያለ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ በዳኝነት እንደማይታይ አድርጐ መወሰኑ ከላይ የተጠቀሱትን የክልሉን የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሕጎችን አዋጅ ቁጥር 456/1997 ሰር የተረጋገጠውን የእርሻ መሬት ይዞታ መብትን እንዲሁም በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሰት አንቀጽ 37፣40(3) እና 79 ስር የተቀመጡትን ድንጋጌዎችንና በዚህ ረገድ በክልሉ ሕገ መንግስትም የሰፈሩትን ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ባላገናዘበ መልኩ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተናል።
በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
የትግራይ ብ/ክ/መ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 60917 ነሐሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
በሳንታ ገለበዳ ቀበል መሬት ዳኝነት ግንቦት 07 ቀን 2005 ተሰጥቶ በቀይሕ ተክላ ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 01471 ሰኔ 28 ቀን 2005 ዓ.ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል። በዚህ መሰረት አመልካች የእርሻ መሬቱን እንዲለቅ የሚገደድበት የሕግ ምክንያት የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርከር የወጣውን ወጪና ኪሣራ አመልካች የራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.