No summary available.
ግንቦት 06 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ተክለ ፃዲቅ ኤካ - ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1ኛ. አቶ መላኩ ፍሬው 2ኛ. ወ/ሮ በየነች ታደሰ የቀረበ የለም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የስጦታ ይፍረስልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪዎች ባሁኑ አመልካች ላይ በወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።የክሱ ይዘትም፡-ተጠሪዎችና ልሎች ልጆች የሟች ፍሬው ቦጋለ ኤካ እና የወ/ሮ አበራሽ ዳደና ልጆች መሆናቸውና እነዚህ ወላጆቻቸው ተከታትለው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን፣ በህይወት በነበሩበት ጊዜም በሟች አቶ ፍሬው ቦጋለ ስም ቦታ ተመርተው በሶዶ ከተማ ቤት መስራታቸውን፣ ይህንኑ ቤት የአሁኑ አመልካች ጥር 28 ቀን 2001 ዓ/ም በስጦታ ከሟቹ እንደአገኙና በሰነዱ ላይ የሟች ወ/ሮ አበራሽ ደደና ፊርማ በማስመሰል ጽፈው በሶዶ ከተማ ፍትህና ጸጥታ ጽ/ቤት በማስመዝገብ አስጸድቀው መገኘታቸውንና ይህም በባልና ሚስት የጋራ ንብረት ስጦታ መደረጉንና ተወላጆችን የነቀለ መሆኑን እንደሚያሳይና የሰጪው ተግባር ሕገወጥ መሆኑን ዘርዝረው ስጦታው እንዲፈርስ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስም፡- ክሱ በይርጋ እንደሚታገድና ስጦታውም በሕጉ አግባብ የተደረገና ስመ ሃብቱም ለስጦታ ተቀባዩ ዙሮ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል።ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም በአሁኑ አመልካች የቀረበውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ነጥብ ውድቅ አድርጎና ፍሬ ነገሩን መርምሮ ስጦታው ፈራሽ ነው በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ህዝቦች ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡የስጦታ ውሉ በሕጉ አግባብ የተደረገና ስመ ሃብቱም ለስጦታ ተቀባዩ የዞረ ሁኖ እያለ የስጦታ ውሉ ፈራሽ ነው ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው ጭብጥ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል? ወይስ አይቻልም? የሚለው ነጥብ ሁኖ አግኝቶታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪዎች በአሁኑ አመልካች ላይ ክስ የመሰረቱት የሟች አቶ ፍሬው ቦጋለ እና የወ/ሮ አበራሽ ዳደና ወራሾች መሆናቸውን ጠቅሰውና ሟቾች በጋብቻ ተሳስረው በነበሩበት ጊዜ በጋራ ያፈሩትን ቤት ሕጋዊ ባልሆነ የስጦታ ውል አመልካች መብት አለኝ በማለት ይዘው እንደሚገኙና ሟች አቶ ፍሬው ቦጋለ መብት ሳይኖራቸው በሚስታቸው ድርሻ ስጦታ ከሕግ ውጪ ያደረጉ ከመሆኑም በላይ ከድርሻቸው ተወላጆችን መንቀላቸውን በመግለፅ ዘርዝረው የስጦታው ውሉ እንዲፈርስ ይወሰንልን በሚል መሆኑን ነው። የአሁኑ አመልካች በበኩላቸው ለተጠሪዎች ክርክር በሰጡት መልስ ከተጋቢዎች መካከል አንዱ ሲሞት በሕይወት የቀረው ተጋቢ በጋራ ንብረት ላይ ሙሉ መብት እንዳለውና በስጦታ ለሚፈልገው ሰው ቢያስተላልፍ በሕግ ክልከላ እንዳልተደረገበት እንዲሁም ስጦታው በሟቹ ሙሉ ፈቃድ ሕጉን ተከትሎ የተፈፀመ በመሆኑ ፈራሽ ላሆን የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት የለም በማለት መከራከራቸውን ተረድተናል።ይህ ችሎት የቀረበለትን ጉዳይ ለስጦታ ውል አደራረግ አግባብነት ያላቸው የፍትሐብሕር ሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማያያዝ መርምሮአል። በዚህም መሰረት ሟች አቶ ፍሬው ቦጋለ ያደረጉት ስጦታ በባልና ሚስት የጋራ ሃብት በሆነው ቤት ላይ የተደረገ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ በስር ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ያገኘ ከመሆኑ አንጸር ሲታይ ስጦታው የሚያስከትለው የሕግ ውጤት ምንድነው? የሚለው የሕግ ነጥብ አስመልክቶ ሕጉ የሚለውን መመልከት ለውሣኔ አስፈላጊ ሆኖም አግኝቶታል።
ከሥር ፍ/ቤቶች ውሣኔዎች ለመገንዘብ እንደሚቻለው ተጠሪዎች ለስጦታው መፍረስ እንደ አንድ ምክንያት የጠቀሱት ቤቱ የባልና ሚስት የጋራ ሁኖ እያለ ባል ብቻ አደረጉ በተባለው ስጦታ ለአሁኑ አመልካች እንዲሰጥ መደረጉ ያላግባብ ነው የሚል ሲሆን አመልካች በዚህ ረገድ በስር ፍርድ ቤቶች ባቀረቡት ክርክር ከተጋቢዎች አንዱ በህይወት ከቀረ የጋራ ንብረት መብትን ጠቅልሎ ስለሚወስድ ስጦታ ማድረግ በሕግ ክልከላ አልተደረገም የሚል እንጂ ቤቱ የባልና ሚስት የጋራ ንብረት አይደለም በማለት ክደው ያለመከራከራቸውን ተረድተናል።ስለሆነም አከራካሪው ንብረት የባልና ሚስት የጋራ ንብረት መሆኑ በአመልካች በስርዓቱ መሰረት ማስተባበያ ክርክር ያልቀረበበት በመሆኑ በዚህ ሰበር ደረጃ አመልካች ቤቱ የጋብቻ ውጤት ስለመሆኑ ተጣርቶ አልተወሰነም በማለት ያቀረቡትን ቅሬታ አልተቀበልነውም።
ወደ ስጦታ ሕጋዊ መሆን ያለመሆን ነጥብ ስንመለስም፡- በመሰረቱ አንድ ሰው በራሱ ባልሆነና ላያዝበት በማይችል ንብረቱ ስጦታ ያደረገ እንደሆነ ስጦታው የሚኖረው ሕጋዊ ሁኔታ ምንድነው? የሚለው ጥያቄ በፍትሃ ብሕር ሕጉ ስለስጦታ በሚደነግጉ ከቁጥር 2427 እና ተከታይ ድንጌዎች በግልጽ ምላሽ ያገኘ ጉዳይ ነው።የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2427 ስለ ሥጦታ ትርጉም ሲያስቀምጥም ስጦታ አንድ ወገን ተዋዋይ ማለት ሰጪው፤ተቀባይ ተብሎ ለሚጠራው ለልላ ሰው ችሮታ በማድረግ አሳብ ከንብረቶቹ አንዱን የሚለቅበት ወይም ግድታ የሚገባበት ውል መሆኑን እንደሚያሳይ፣በዚህ ትርጉም ውስጥም ከንብረቶቹ የሚለው ቃል ስጦታ በሚደረገው ንብረት ላይ ስጦታ ሰጪው የባለቤትነት መብት ያለው መሆኑን የሚጠቁም ከመሆኑም በላይ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2451 ድንጋጌ በተለይ ሲታይም ስጦታ የሚደረገው ስጦታው በተደረገበት ቀን የሰጪው ገንዘብ ከሆነ ንብረት ላይ ብቻ መሆኑን መደንገጉም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው በመርህ ደረጃ ማንም ሰው ምንም መብት በልለው ንብረት ላይ የስጦታ ውል ያደረገ እንደሆነ የተሰጠው ስጦታ ዋጋ የማይኖረው መሆኑን ነው።ስለሆነም በሕግ ፊት የሚፀና ስጦታ ለማድረግ ሰጪው ስጦታ በተደረገበት ንብረት ላይ መብት ላኖረው ይገባል።በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች ስጦታው በሚስት ድርሻም ጭምር የተደረገ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ስጦታውን ፈራሽ የሚያደርግ ነው በማለት የደረሱበት ድምዳሜ ተገቢነት ያለው ሁኖ አግኝተናል።
ልላው መታየት ያለበት ነጥብ ስጦታው በሚስት ድርሻ ሕጋዊ ውጤት አያስከትልም ከተባለ በባል ድርሻ ወይም በስጦታ አድራጊ ድርሻ ላይ ያለው ውጤት ነው።ተጠሪዎች ስጦታው በዚህ ረገድ ላፈርስ ይገባል በማለት ከሚከራከሩባቸው ምክንያቶች አንዱ ሟች በህመም ውስጥ እንደነበሩ ገልፀው አመልካች የሟቹን መንፈስ ልልነትና አቅመ ደካማነቱን በመጠቀም ስጦታ አድራጊ ሕጻን የሆኑተወላጆቹን ያላግባብ ከውርስ ንብረቱ ላይ እንዲነቀሉ አድርገዋል በሚል ነው።አመልካች ተጠሪዎችም ሆኑ ልሎች የሟቹ ሕጋዊ ወራሾች ልላ የውርስ ንብረት ያላቸው ስለመሆኑ ገልፀው ያቀረቡት ክርክርም የለም።እንዲህ ከሆነ ደግሞ ስጦታው ተፈፃሚነቱ ሟቹ ከሞቱ በኋላ በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2428 እና 2438 ድንጋጌዎች አግባብ በውርስ ሕጉ ተወላጆቹን በተመለከተ በኑዛዜ ለመንቀል የሚቻል መሆን ያለመሆኑን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ የግድ የሚል መሆኑ ይታመናል።ይሁን እንጂ የስር ፍርድ ቤት ስጦታው ተወላጆቹን የውርስ ንብረት እንዳያገኙ የሚከለክል፣ከቅን ልቦና ውጪ የተደረገ መሆኑን ሟቹ የነበሩበትን የጤና ሁኔታ፣ስጦታው ከተደረገ በኋላ ሟቹ እስከ ሚያዝያ 13 ቀን 2001 ዓ/ም ብቻ የቆዩ መሆኑን ሁሉ ከክርክሩ ፍሬ ነገር ደምድሞ ስጦታውን ፈራሽ ነው ሲል መወሰኑን የውሳኔው ይዘት የሚያስገነዝብ በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት ፍሬ ነገሩን አጣርቶ በዚህ ረገድ የደመደመውንና ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም የተቀበለውን ይህንኑ የፍሬ ነገር ሁኔታ ይህ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀፅ 10 ተለይቶ ከተሰጠው ስልጣን አንጻር ሲታይ ለመለወጥ የሚያስችል መሰረታዊ የሆነ ህጋዊ ምክንያት የለም።ስለሆነም ስጦታው ከቅን ልቦና ውጪ የተደረገ ነው እስከተባለ ድረስ በስጦታ አድራጊው ድርሻ ጭምር ፈራሽ የማይሆንበት ሕጋዊ ምክንያት ያለመኖሩን ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2438(1) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ተገንዝበናል።
ልላው አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት ነጥብ ስጦታውን መነሻ በማድረግ የቤቱ ስመሃብቱ ወደ አመልካች ዙሮ እያለ የተጠሪዎች ክርክር ተቀባይነት ማግኘቱ ያላግባብ ነው የሚል ነው።ይሁን እንጂ በአንድ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ በአስተዳደር አካል የሚሰጥ የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር የባለቤትነት ግምት መነሻ ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195 ድንጋጌ ይዘት የምንረዳው ሲሆን ይህ ግምት ግን ደምዳሚ ያለመሆኑን የዚሁ ድንጋጌ ተከታይ የሆነው የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1196 ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል።በመሆኑም ስመ ሃብቱ የዞረበት መነሻ ያላግባብ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ የባለቤትነት ደብተር የያዘ ሰው በፍርድ ቤት ላከሰስ አይገባም የሚባልበት የሕግ አግባብ ስለልለ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረቡት ቅሬታም ተቀባይነት የልለው ሁኖ አግኝተናል።በአጠቃላይ የበታች ፍርድ ቤቶች ስጦታው ፈራሽ ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሰኔ 06 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል።
በ28/05/2001 ዓ/ም በሟች ፍሬው ቦጋለ ኤካ ተደረገ የተባለው ስጦታ ፈራሽ ነው ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.