No summary available.
ሐምል 17 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- ወ/ሮ አልማዝ በቀለ - ወኪል ቅጅነህ ለማ ቀረቡ።
ተጠሪ፡- አቶ ገዛኽኝ በቀለ - ከጠበቃ በጅጋ ሶሬቻ ጋር ቀረቡ።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
በዚህ መዝገብ የቀረበው ክርክር ስለውርስ ንብረት ክፍፍል ጥያቄን የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው በአዳአ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን ከሳሽ የአሁኑ ተጠሪ፣ተከሳሽ ደግሞ የአሁኗ አመልካች ነበሩ። ተጠሪ ታህሳስ 17 ቀን 2005 ዓ/ም አሻሽለው ባቀረቡት ክስ ሲሆን ወላጅ አባታቸው አቶ በቀለ ባልቻ ከዚህ አለም በሞት ህዳር 20 ቀን 2003 ዓ/ም መለያታቸውንና በህይወት በነበሩት ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ ቀበል 07 ውስጥ በካርታ ቁጥር 7/17/1 የሚታወቀውንና ቁጥሩ 290 የሆነው መኖሪያ ቤት ያፈሩ ቢሆንም ተጠሪንና አመልካችን ጨምሮ ስድስት ሕጋዊ ወራሾች እያሉ የአሁኗ አመልካች ብቸኛ ወራሽ በመምሰል ቤቱን ይዘው እንደሚገኙና የቤቱ ግምት 80,000.00 (ሰማንያ ሺህ) መሆኑን ጠቅሰው ከቤቱ ግምት የተጠሪ ድርሻ የሆነውን ብር 13,000.00 (አስራ ሶስት ሺህ) ድርሻቸውን እንዲያገኙ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል።የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስም፡- ክሱ በአስር አመት ይርጋ እንደሚታገድ፣ተጠሪ ድርሻዬ ይገባኛል ከማለት ውጪ ማስረጃ ያለማቅረባቸውን፣ወ/ሮ ጽጌ የሟች ልጅ ያለመሆናቸውንና እልፍነሽ፣ዝናሽ፣እና ፀሐይ ከተባሉት የሟች ወራሾች ጋር ፍርድ ቤት ቀርበው ስምምነት ማድረጋቸውን፣ በአከራካሪው ቤት ላይ በሟች ስም የባለቤትነት ደብተር የወጣው ተጠሪ ማዘጋጃ ቤቱን በማሳሳት መሆኑን፣ቤቱ ያለበት የቦታ ስፋትም 200 ካ/ሜትር ሳይሆን 400 ካ.ሜትር ሁኖ አከራካሪውን ቤት አባታቸው በሕይወት በነበሩበት ወቅት ሕዳር 27 ቀን 1985 ዓ/ም ከሃያ አመት በፊት ሰጥተዋቸው የሟቹ ወራሾችም ይኼው ተነግሯቸው ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን፣በቤቱ ላይ መብራት፣ስልክና ውሃ በስማቸው ማስገባታቸውንና ከሃያ አመት በላይ ሲጠቀሙበት ለነበሩት ንብረት ተጠሪ ወራሽ ነኝ በማለት ክስ ማቅረባቸው ተቀባይነት የልለው መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል።የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ በአመልካች በኩል የቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎችንም ሆነ የፍሬ ነገር ክርክሮችን ውድቅ አድርጎ አመልካች ለተጠሪ ድርሻቸውን ብር 13,000.00(አስራ ሶስት ሺህ) እንዲከፍሉ በማለት ወስኗል።አመልካች ለተጠሪ ብር 13,000.00(አስራ ሶስት ሺህ) እንዲከፍሉ በተሰጠው የውሳኔ ክፍል የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ለተጠሪ ላከፍሉ የሚገባው የውርስ ቤቱን የገበያ ዋጋን መሰረት ያደረገውን ድርሻ እንጂ በክሱ ጊዜ የተጠቀሰውን ግምት አይደለም በማለት ወስኗል።የአሁኗ በዚሁ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቤቱ የግል ነው የሚል ክርክር አቅርበው የነበሩ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካች ክርክር መስቀልኛ ይግባኝ የቀረበበት ባለመሆኑ ስነስርዓታዊ አይደለም ሲል አልፎታል።ከዚህም በኋላ አመልካች ይግባኛቸውን ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣የሰበር አቤቱታቸውን ደግሞ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-አከራካሪውን ቤት በ1985 ዓ/ም ከወላጅ አባታቸው ያገኙትና ከሃያ አመታት በላይ ሲጠቀሙበት የቆየ ሁኖ እያለ ተጠሪ ድርሻቸውን በገበያ ዋጋ እንዲወስዱ ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም አከራካሪው ቤት በሟች አውራሽ ፈቃድ ለመሰራቱ በፅሑፍ ሰነድ በቀረበበት የበታች ፍርድ ቤቶች ለአመልካች ስለሚከፈለው ግምት ያለመወሰናቸው እንዲሁም ተጠሪን ሳይጨምር ልሎች አራት ወራሾች ቀደም ሲል ውርሱ ሲጣራ ድርሻቸውን ለአመልካች መልቀቃቸው በስር ፍርድ ቤቶች ታልፎ የተጠሪ ድርሻ የቤቱ ግማሽ ነው ተብሎ መባሉና የወረዳው ፍርድ ቤት አመልካች ቤቱን አስቀርተው የተጠሪን ድርሻ ይክፈሉ በማለት የወሰነው በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች የመሻሩን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበውም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።ተጠሪ በሰጡት መልስም አመልካች በቤቱ ላይ አለኝ የሚሉትን መብት በተመለከተ ስርዓቱን ጠብቀው ይግባኝ ያላቀረበበት መሆኑን ጠቅሰው ቤቱ የግል ነው በማለት የሚያቀርቡት ተቀባይነት ላሰጠው አይገባም በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም ጉዳዩን ከውርስ ሕጉ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አከራካሪውን ቤት የሟች በቀለ ባልቻ የውርስ ንብረት ነው በማለት ተጠሪ በልጅነታቸው ድርሻቸው በተጠሪ እንዲሰጣቸው ክስ አቅርበው አመልካች ቤቱ የግል ነው የሚል ክርክር አቅርበው በወረዳው ፍርድ ቤት ተቀባይነት ካጡ በኋላ ፍርድ ቤቱ ለክሱ መሰረት ከሆነው የቤቱ ግምት ከብር 80,000.00(ሰማንያ ሺህ) ውስጥ ለስድስት ወራሾች እኩል ሲካፈል የሚመጣው ውጤት ብር 13,000.00(አስራ ሶስት ሺህ) አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍሉ መወሰኑን፣በዚህ ውሳኔ በከፊል ያልተስማሙት የአሁኑ ተጠሪ ቤቱ በሐራጅ ተሽጦ ድርሻዬን ላገኝ ይገባል በማለት ይግባኛቸውን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ተቀባይነት ያገኙ መሆኑን፣አመልካች በስርዓቱ መሰረት ቤቱ የግል ነው የሚለውን ይግባኝ ከወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ያላቀረቡ መሆኑንና ባሁኑ የክርክር ደረጃ ደግሞ ቤቱ የግል ነው የሚለውን ክርክር አጥብቀው የሚከራከሩ መሆኑን ነው።
በመሰረቱ በየርከኑ ባሉት ፍርድ ቤቶች የሚታየው ክርክር የሚመራው በስነ ስርዓት ህጉ በተዘረጋው ስርዓት መሆኑ ይታወቃል።ክርክሩን በመጀመሪያ ደረጃ ተመልክቶ በሰጠው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅሬታ ያለበት ወገን ቅሬታውን በይግባኝ ወይም በመስቀለኛ ይግባኝ ለማሳየት የሚችል ስነ ስርዓት ሕጉ ያሳያል።እነዚህ የቅሬታ አቀራረብ ስርዓቶች የየራሳቸው ሕጋዊ ውጤት ያላቸው ሲሆን በማን ላቀርቡ እንደሚገባም ስነ ስርዓት ሕጉ ያስገነዝባል። ይግባኝ ማለት በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በተሰጠው ፍርድ ቅሬታ ያለበት ወገን ይህንኑ ቅሬታውን በህጉ ስልጣን በተሰጠው የበላይ ፍ/ቤት አቅርቦ በማሣየት በስር ፍ/ቤት የተሰጠው ፍርድ እንዲሻሻል እንዲለወጥ፣ወይም ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲሆን ዳኝነት የሚጠየቅበት ሥርአት ነው። ይግባኝ ለተከራካሪ ወገኖች የተሰጠ መብት ቢሆንም ገደብ የለሸ ግን አይደለም። በልላ አገላለጽ በማናቸውም ፍርድ ወይም ትእዛዝ ላይ ሁሉ ይግባኝ ለማለት የማይቻልበት ሁኔታ ይኖራል።
ይህም በግልጽ በሕግ ላመለከት ይችላል። ለዚህ ዓይነት ሁኔታ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 320 ስር የተመለከተው ድንጋጌ በዋቢነት ላጠቀስ ይችላል። በመሆኑም በአንድ ፍርድ ወይም ትእዛዝ ላይ ይግባኝ ለማቅረብ መለኪያው ላሆን የሚገባው በተሰጠው ፍርድ ወይም ትእዛዝ ተከራካሪ ወገን መብት የሚጐዳ ሆኖ መገኘት ነው። በዚህም መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በተሰጠ ውሣኔ መብቱ ወይም ጥቅሙ የተነካ አላያም ግድታው ከፍ እንዲል የተደረገ ወገን የይግባኝ መብት ይኖረዋል። የይግባኝ ዓይነቱም ቀጥታ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ(cross-appeal) ላሆን ይችላል።
የይግባኝ ዓይነቱ ቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ ለይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሚቀርበው ፍርዱ የይግባኝ አቅራቢውን መብት በሚጐዳው መልክየሚነካ ሲሆን ብቻ ነው። የስር ፍ/ቤት ውሣኔ ከተከራካሪ ወገኖች የቀረቡለትን ሁሉንም የክርክር ነጥቦች መሰረት ያላደረገ ቢሆንም በውጤት ደረጃ ጠቃሚ ሁኖ ከተገኘ ለውሣኔው መሰረት ይሆን ነበር የሚባል ምክንያት ብቻ በመያዝ ይግባኝ ላል ይገባል ማለት የይግባኝ ሥርአትን መሰረታዊ ዓላማና መመዘኛውን እንዲሁም የፍትሐብሕር ሕግ ሥነ ሥርአትን ዓላማ ያገናዘበ አይሆንም። በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የመከራከሪያ ነጥቡን ያቀረበ እና ከመከራከሪያ ነጥቦቹ መካከል በአንዱም እንኳ ቢሆን በውሣኔው ውጤት ተጠቃሚ የሆነ ወገን በስር ፍ/ቤት ለውሣኔው መሰረት ባልሆነው መከራከሪያ ነጥብ ብቻ ቀጥታ ወይም መስቀለኛ ይግባኝ ሣያቀርብ መከራከሪያ ነጥቡን በበላይ ፍ/ቤት በመልሱ እስከአቀረበ ድረስ ተቀባይነት አያገኝም የሚባልበት የህግ ምክንያት የለም።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ቤቱ የውርስ ንብረት አይደለም፤የግል ነው የሚል ክርክር ክርክሩን በመጀመሪያ ደረጃ ለተመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤት አቅርበው ተቀባይነት አላገኙም።በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁት የአሁኑ ተጠሪ ሁነው አመልካች ቤቱ የግል ተብሎ መወሰን ሲገባ መታለፉ ያለግባብ ነው በማለት ቀጥተኛ ይግባኝ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ይግባኝ አላቀረቡም።እንዲህ ሳያደርጉ ቤቱ የግል ነው በማለት በይግባኝ መልሳቸው ላይ ክርክር ማቅረባቸው ተቀባይነት የሚያገኙበት አግባብ የለም።ምክንያቱም ከመሰረቱ በወረዳው ፍርድ ቤት በተሰጠው ውሳኔ ተጠቃሚ የነበሩ ስለመሆኑ ውሳኔው አያሳይም።ስለሆነም ተጠሪ በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ተቃውሞ በመቀበል አመልካች ቤቱ የግል ላሆን ይገባል በማለት ያቀረቡት ክርክርና የዚህ ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎትም በዚህ ረገድ የያዘው ጭብጥ የክርክሩን ሂደት ያላገናዘበ እና ስነ ስርዓታዊ ባለመሆኑ አልተቀበልነውም።
ልላው በዚህ ችሎት መታየት ያለበት ነጥብ አከራካሪው ቤት በሀራጅ እንዲሸጥ መወሰኑ የውርስ ንብረት ላከፋፈል የሚገባበትን የክፍፍል ስርዓት ያገናዘበ መሆን ያለመሆኑ ነው።በመሰረቱ የውርስ ንብረት ክፍፍል አሰራር የሚከናወንበትን መንገድ የፍትሐብሕር ሕጋችን ግልጽ ድንጋጌዎችን ይዞ እናገኛለን። የውርስ ንብረት ክፍፍል አሰራር በወራሾች መካከል በሚደረግ ስምምነት፣ ወራሾች ያልተስማሙ እንደሆነ ከእነርሱ መካከል አንዱ ተግቶ ያሰናዳው የክፍያ ሐሳብ እንዲፀድቅ ለዳኞች ቀርቦ በሚጸድቀው አግባብ ላከናወን እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1079 ድንጋጌ ይዘት ያሣያል። ሕጉ የመከፋፈሉ አፈፃፀም ደንብንም በቁጥር 1082 አስቀምጧል።በዚህ ድንጋጌ መሰረት ክፍያው የሚፈፀመው ሟቹ በፃፈው የኑዛዜ ቃል እንደሆነ፣ ስለክፍያው አፈፃፀም የተፃፈ ኑዛዜ ቃል ከልለ ደግሞ በሕጉ በተዘረጋ ስርዓት መሰረት መደረግ እንዳለበት ያሣያል። የክፍፍሉ ደንብ በሕጉ የሚከናወንበትን አግባብ የሚደነግጉት ድንጋጌዎች በቁጥር 1083 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ። ከእነዚህ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ ቁጥር 1086 ሲሆን ይህ ድንጋጌ የውርስ ንብረት የሚከፋፈልበትን መርህ የሚያስቀምጥ ሲሆን ዝርዝር ይዘቱ ሲታይም ክፍያው በመሰረቱ የሚደረገው እያንዳንዱ ወራሽ ከውርሱ ውስጥ ንብረት እየተሰጠው በአይነት ስለመሆኑና በአይነት የተመደቡት ድርሻዎች ትክክል ያልሆኑ እንደሆነ ተጨማሪ ገንዘብ በመስጠት እንደሚስተካከሉ የሚገልጽ ነው።
የድርሻዎቹን አመዳደብ ስርዓትም በተቻለ መጠን ለእያንዳንዱ ወራሽ በሚሰጠው የጎላ ጠቀሜታ ምርኩዝ ተደርጎ ላከናወን እንደሚገባ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1087/2/ ድንጋጌ ስር በግልጽ ሰፍሯል።ስለውርስ ንብረት ክፍፍል የሚደነግጉት ድንጋጌዎች አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ ሲታይ ክፍፍሉ በዓይነት እንዲሆን ማድረግ ቀዳሚ የክፍፍል ሥርዓት መሆኑን ያስገነዝባሉ። በመሆኑም በጨረታ የውርስ ንብረት በመሸጥ ወራሾች እንዲከፋፈሉ የሚደረገው ሕጉ በአስገዳጅነት ያስቀመጠው በአይነት የማከፋፈል መንገድ የማይቻል መሆኑና በሕጉ በልዩ ሁኔታ የተቀመጡት ሁኔታዎች መኖራቸው ሲረጋገጥ ነው።የውርስ ንብረት ወራሾች በአይነት እንዲከፋፈሉ ማድረግ ቅድሚያ የሚፈጸም የክፍፍል ስርዓት ስለመሆኑ ሕጉ ከአስቀመጠ ደግሞ ከወራሾቹ አንዱ ወይም ልላው ንብረቱ በጨረታ እንዲሸጥ በመፈለጉ ብቻ ንብረቱ በጨረታ እንዲሸጥ ላደረግ አይገባም።ሕጉ ለውርስ ንብረት ክፍፍል በአይነት የመከፋፈል ስርዓት በቅድሚያ እንዲከናወን ወይም መርህ ሁኖ እንዲቀመጥ የፈለገውም ሕብረተሰቡ ለውርስ ንብረት የሚሰጠውን የተለየ ቦታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ነው ተብሎ ይታሰባል። የውርስ ንብረት በሐራጅ የመሸጥ ስርዓት ተግባራዊ የሚሆንበትን አግባብ ሕጉ በቁጥር 1092 ድንጋጌ ከአስቀመጠው ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በዚህ ድንጋጌ መሰረት የውርስ ሀብት ውስጥ ከፍ ያለ ጉዳት ሳይደርስባቸው ላከፈሉ የማይችሉ ንብረቶች ያሉ እንደሆነና ከወራሾቹ መካከል ይህን የማይከፈል ሀብት ላወስድ የሚገባው የትኛው እንደሆነ በስምምነት ለመወሰን ያልቻሉ ከሆነ ስለመሆኑ ድንጋጌው ያሳያል። የዚህ ድንጋጌ ቀጣይ ስለመሆኑ የሚያስገነዝበው ቁጥር 1093 ድንጋጌ ሲታይም ከወራሾቹ መካከል አንደኛው ጥያቄ ባቀረበ ጊዜ ሽያጩ በወራሾች መካከል በሐራጅ ላደረግ እንደሚገባ፣ በወራሾች መካከል ስምምነት ከታጣም በሐራጅ ጨረታ ውስጥ ባዕድ ሰዎች እንዲገቡ ላደረግ እንደሚገባ እንደ የቅደም ተከተላቸው በንዑስ ቁጥር አንድና በንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌዎች ስር አስቀምጧል። ከላይ የተጠቀሱትን ድንጋጌዎች ጠቅለል አድርገን ስንመለከት የውርስ ንብረት ክፍፍል ስርዓት በሕጉ የተመለከቱትን መንገዶች በመጠበቅ ላከናወን ላገባ ስለመሆኑና በሕጉ የተመለከቱትን ሁኔታዎች ካላጋጠሙ በስተቀር ንብረቱ ከወራሾቹ እጅ በቀላሉ እንዲወጣ የማይደረግ መሆኑን ነው። ስለሆነም የውርስ ሀብት በጨረታ እንዲሸጥ ላደረግ የሚገባው በፍ/ሕ/ቁጥር 1093 ድንጋጌዎች ስር የተመለከቱት ሕጋዊ ምክንያቶች ሲኖሩ ነው።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የበላይ ፍርድ ቤቶች የውርስ ንብረት የሆነውን ቤት በጨረታ እንዲሸጥ የወሰኑት ከላይ የተመለከቱትን የውርስ ሕግ ድንጋጌዎችን ተከትለው ያለመሆኑን፣የወረዳው ፍርድ ቤትም ተጠሪ ድርሻቸውን እንዲያገኙ ያደረገው የገበያ ዋጋን መሰረት ባደረገ መልኩ ያለመሆኑን ከውሳኔዎቹ ይዘት ተገንዝበናል።
ስለሆነም ሁሉም የበታች ፍርድ ቤቶች የውርስ ንብረት ክፍፍሉን በተመለከተ የሰጡት ውሳኔ ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ አልተገኘም።ክፍፍሉላከተለው የሚገባውን ስርዓት ስንመለከተውም ተጠሪ ቤቱ በአይነት ላካፈል የሚችል መሆኑን ጠቅሰው የክፍፍሉ ስርዓትም በውርስ ድንጋጌዎች መሰረት እንዲከናወን ዳኝነት ያለመጠየቃቸውን ከክርክሩ ተገንዝበናል። አመልካች ደግሞ ቤቱን እንዲያስቀሩ በወረዳው ፍርድ ቤትም ተወስኖላቸው የነበረ ሲሆን ቤቱ በጨረታ ላሸጥ ይገባል ተብሎ ከተሰጠው ውሳኔም ስርዓቱም ጠብቀው በመከራከር ላይ የሚገኙ መሆኑንና የጠየቁት ከፍተኛው ዳኝነትም ቤቱ የግል ላባል ይገባል የሚል መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተናል።በመሆኑምቤቱ በሐራጅ ተሸጦ ወራሾች ድርሻቸውን እንዲከፋፈሉ ከማድረግ ይልቅ የቤቱን የገበያ ዋጋ መሰረት በአደረገ መልኩ ከአመልካች ውጪ ያሉት የሟቹ ወራሾች እንዲሰጣቸውና አመልካች ቤቱን እንዲያስቀሩ መወሰኑ በውርስ ህጉ የተመለከቱትን የውርስ ንብረት ክፍፍልን የሚገዙትን ድንጋጌዎችን ይዘት፣ መንፈስና ዓላማ ያገናዘበ ሁኖ አግኝተናል።
ሲጠቃለልም የሟች አቶ በቀለ ባልቻ ንብረት የሆነውን አከራካሪውን ቤት ወራሾች እንዲከፋፈሉ ተብሎ መወሰኑ ተገቢ ቢሆንም የአከፋፈል ሥርዓት ግን በውርስ ሕጉ የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ያልተከተለ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሁኖ አግኝተናል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በአዳአ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ የካቲት 06 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሚያዝያ 10 ቀን 2005 ዓ/ም ተሻሽሎ በኦሮሚያ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ሰኔ 04 ቀን 2005 ዓ/ም ፣በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሰረት ተሻሽሐል።
የሟች አቶ በቀለ ባልቻ ንብረት የሆነውና በቢሾፍቱ ከተማ ቀበል 07 ክልል ውስጥ የሚገኘው፣በካርታ ቁጥር 7/17/1 ቁጥሩ 290 የሚታወቀው ቤት የውርስ ቤት ነው ተብሎ አመልካችንና ተጠሪን ጨምሮ ለስድስት ወራሾች እንዲከፋፈል ተብሎ መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል።ክፍፍሉን በተመለከተ ግን የቤቱ የገበያ ዋጋ ከታወቀ በኋላ የተጠሪንም ሆነ የልሎች ወራሾችን ድርሻ አመልካች ከፍለው ቤቱን በአይነት እንዲያስቀሩ፣ይህን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ግን በጨረታ ተሽጦ ሁሉም ወራሾች ድርሻ ገንዘባቸውን እኩል እንዲከፋፈሉ በማለት ወስነናል። የአዳአ ወረዳ ፍርድ ቤት በዚህ ችሎት ውሳኔ እንዲያስፈጽም በማለት የውሳኔ ግልባጭ ይተላለፍለት ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ትእዛዝ ጥቅምት19 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል።ለሚመለከታቸው አካላት ይጻፍ።