No summary available.
ሐምል 18 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች:-
ተጠሪ:- 1.ወ/ሮ አስናቀች ቦጋለ 2.ማቆያ ቦጋለ የቀረበ የለም።
3.ስንቅነሽ ቦጋለ 4.ፋኖሴ ቦጋለ ቀረቡ።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
በዚህ መዝገብ የቀረበው ክርክር ስለውርስ ንብረት ክፍፍል የተደነገጉትን የውርስ ሕግ ድንጋጌዎችን መሰረት አድርጎ የቀረበ የፍርድ መቃወሚያን የሚመለከት ነው። ለጉዳዩ መነሻ የሆነው ነገር ሟች አቶ ቦጋለ ታደሰ ጥቅምት 09 ቀን 1990 ዓ/ም ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ በኋላ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ያፈሩት በበቆጂ ከተማ ቀበል 02 ክልል ውስጥ በ147.4 ካ.ሜትር ቦታ የሰፈረውን አራት ክፍል ቤት የውርስ ድርሻ ይገባናል የሚለው የአመልካቾችና የአሁኑ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ የተጠቀሱት ተጠሪዎች ጥያቄ ነው። ሁሉም ተጠሪዎች የሟች አቶ ቦጋለ ታደሰ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች መሆናቸው የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።አመልካች ደግሞ የተጠሪዎች እህት የሆኑትና የሟቹ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ የነበሩት የወ/ሮ ደመቀች ቦጋለ ልጆች ሁነው እናታቸውን ተክተው አያታቸውን አቶ ቦጋለ ታደሰን ለመውረስ ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑን መዝገቡ ያሳያል። አሁን ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለው የልሙና ቢላቢሎ ወረዳ ፍርድ ቤት የአሁኑ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ የተጠቀሱት ተጠሪዎች የሟቹን ውርስ ንብረት እኩል እንዲካፈሉ ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ የአሁኑ አመልካቾች በተተኪ ወራሽነት የሚያገኙትን መብት የሚነካ ነው በማለት የአሁኑ አመልካቾች ለወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረቡት የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ በወረዳው ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎ በበላይ ፍርድ ቤቶችም ተቀባይነት ማጣቱ ያላግባብ ነው የሚለው አቤቱታ ነው። የአሁኑ አመልካቾች ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሶስት የተጠቁስት ተጠሪዎች 4ኛ ተጠሪን በመክስስ የሟች አቶ ቦጋለ ታደሰን የውርስ ንብረት እንዲካፈሉ በልሙና ቢላቢሎ ወረዳ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ እናታችን ወ/ሮ ደመቀች ቦጋለን በመተካት ልናገኝ የሚገባንን ድርሻ ያስቀረ ነው በማለት ፍርድ ለመቃወም አቤቱታቸውን ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ/ም ፅፈው ለወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን የወረዳው ፍርድ ቤትም የአሁኑ ተጠሪዎች በአመልካቾች የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ ላይ መልስ እንዲሰጡበት አድርጎ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ የተጠቀሱት ተጠሪዎች የአመልካቾችን የፍርድ መቃወሚያ ደግፈው አመልካቾች የእናታቸውን ድርሻ ቢያገኙ ተቃውሞ የልላቸው መሆኑን ገልፀው የተከራከሩ ሲሆን የአሁኗ 4ኛ ተጠሪ ግን በወረዳው ፍርድ ቤት የተሰጠውና ለፍርድ መቃወሚያ መሰረት የሆነው ፍርድ በተጠሪዋ ይግባኝ ባይነት ለአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ በመ/ ነሀሴ 18 ቀን 2004 ዓ/ም በተሰጠው ፍርድ ሙሉ በሙሉ ተሽሮ የመጨረሻ ፍርድ ማግኘቱን ገልጸው መቃወሚያው ውድቅ ላሆን ይገባል ሲሉ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት አንስተው ተከራክረዋል።
የፍርድ መቃወሚያውን በመጀመሪያ ደረጃ ያስተናገደው የልሙና ቢላቢሎ ወረዳ ፍርድ ቤትም 4ኛ ተጠሪ ያቀረቡትን መቃወሚያ በመቀበል በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በተሻረ ውሳኔ የፍርድ መቃወሚያውን ለማስተናገድ ስልጣን የልለው መሆኑን ጠቅሶ የአመልካቾችን የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 245(2) ድንጋጌን ጠቅሶ ጥቅምት 26 ቀን 2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት ውድቅ አድርጎታል።በዚህ ብይን የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ይግባኛቸው በመ/ ታህሳስ 05 ቀን 2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተዘግቶባቸዋል።እንዲሁም አመልካቾች የሰበር አቤቱታቸውን ለኦሮሚያ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበውም በመ/ በሆነው ሐምል 23 ቀን 2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የበታች ፍርድ ቤቶች በሰጡት ብይን ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ አቤቱታቸው ውድቅ ሁኖባቸዋል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ነሀሴ 18 ቀን 2004 ዓ/ም ለፍርድ መቃወሚያ የሆነውን ፍርድ የሻረበት ፍርድ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ በሆነው ህዳር 29 ቀን 2005 ዓ/ም ተሽሮ በጉዳዩ ላይ የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ጸንቶ እያለ የፍርድ መቃወሚያ የሚቀርብበት ፍርድ የለም ተብሎ አቤቱታቸው ውድቅ መደረጉ ያላግባብ ነው፣ የውርስ ንብረት ድርሻ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያጣውም አከራካሪውን ንብረት በእጃቸው አስገብተው ለብዙ አመታት ከተጠሪዎች ጋር እኩል ሲጠቀሙበት የነበረ ሁኖ እያለ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ብይን ሕጉን መሰረት ያላደረገ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪዎች ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።በዚህም መሰረት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ያሉት ተጠሪዎች አመልካቾችን ደግፈው የሚከራከሩ ሲሆን 4ኛ ተጠሪ ግን አመልካቾች አለን የሚሉት ውሳኔ በተጠሪዋ አቤት ባይነት፣ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ በተጠቀሱት ተጠሪዎች ደግሞ ተጠሪነት በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲታይ ቆይቶ በዚህ ችሎት ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሶስት የተጠቀሱት ተጠሪዎች የውርስ ንብረት ይገባናል ጥያቄ በሕጉ አግባብ በተመለከተው የይርጋ ድንጋጌ ያልቀረበ ሁኖ ተገኝቷል በሚል ምክንያት ክሱ በይርጋ ቀሪ የሆነ ነው ተብሎ በመ/ መስከረም 13 ቀን 2006 ዓ/ም የተወሰነ ሲሆን በውጤቱም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 29 ቀን 2002 ዓ/ም የሰጠውን ውሳኔ የሻረ መሆኑን ገልፀው አመልካቾች የፍርድ መቃወሚያ የሚያቀርቡት ፍርድ የለም ሲሉ ተከራክረዋል።አመልካቾች የሰበር አቤቱታቸውን አጠናክረው የመልስ መልሳቸውን አቅርበዋል።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም ጉዳዩን ከውርስ ሕጉ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምሯል።ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ቀርቦ እንዲመረመር ሲባል የተያዘው ጭብጥ የአመልካቾች መቃወሚያ ጉዳዩ ተፈፅሟል ተብሎ ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ለመመርመር ተብሎ ሲሆን እኛም ጉዳዩን ከዚሁ ጭብጥ አንጻር በማየት ጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት የሚቻል መሆኑን ያለመሆኑን መርምረናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአሁኑ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተጠሪዎች በአሁኗ 4ኛ ተጠሪ ላይ ያቀረቡት የውርስ ንብረት ይገባናል ክርክር በመጨረሻ ላይ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ታይቶ የከሳሾች ክስ በሶስት አመት የይርጋ ጊዜ የታገደ ነው ተብሎ በመ/ በሆነው መስከረም 13 ቀን 2006 ዓ/ም ውሳኔ ያገኘ ሲሆን በዚህም ውሳኔ መሰረት በወረዳ ፍርድ ቤት የተሰጠና የአመልካቾችን መብት ይነካል የተባለ ውሳኔ ጭምር የተሻረ መሆኑን ውሳኔው የሚያሳይ መሆኑን፣ከዚህም በኋላ በዚህ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ የአሁኑ 1ኛ፣2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች አመልካች፣4ኛ ተጠሪ ደግሞ ተጠሪ ሁነው ተሰይመው ጉዳዩን ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አቤቱታ የሥር ከሳሾች አቅርበውበት አጣሪ ችሎት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም በማለት በመ/ በሆነው ህዳር 23 ቀን 2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት የመጨረሻ ትዕዛዝ የሰጠበት ጉዳይ መሆኑን ነው።
ወደ ሕጉ ስንመጣም በመሰረቱ አንድ የፍትሐብሕር ክርክር የሚመራበት ሥርዓት የሚገዛው በ1958ቱ የፍትሐብሕር ሥነ ሥርኣት ሕጋችንና በክልሎች ስራ ላይ ባሉት አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሆኑ እሙን ነው።የ1958ቱ የፍትሐብሕር ስነ ሥርዓት ሕጋችን ከያዛቸው ስርዓቶች መካከል በፍርድ ላይ የሚቀርበው ተቃውሞ እና በፍርድ አፈጻጸም ጊዜ በተያዘ ወይም በተከበረ ንብረት ላይ የሚቀርበው ጣልቃ ገብነትን የሚገዙት ድንጋጌዎች ይገኙበታል።እነዚህ አቤቱታዎችን የሚገዙት ድንጋጌዎች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 እና 418 ስር የተመለከቱት ናቸው።የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 አንድ የክርክሩ ተካፋይ መሆን የሚገባው ሰው የክርክሩ ተካፋይ ሳይሆን ውሳኔ ተሰጥቶ ከሆነ እና ውሳኔውም ያረፈው በአንድ የክርክሩ ምክንያት በሆነ ንብረት ላይ ሁኖ ይህንኑ የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነ ወገንን መብትና ጥቅም የሚነካ መሆኑ ከተረጋገጠ ፍርዱ ይኸው ወገን ባለበት እንዲታይና በሕግና በማስረጃ የተደገፈ ሁኖ ሲገኝ እንዲነሳለት የሚደነግግ ነው።አቤቱታው የሚቀርብበት ሥርዓትም በቁጥር 359 ስር በተመለከተው መንገድ መሆን እንደአለበት የተቀመጠ ሲሆን ይህ ድንጋጌ የመቃወሚያ አቤቱታ አቀራረብ በክስ አመሰራረት አይነት ሁኖ ማስረጃ ዝርዝር ሁሉ ይህንኑ ስርዓት ማሟላት እንደአለበት ያስገነዝባል። የዚህ ድንጋጌ ይዘቱና መንፈሱ ሲታይ ክርክሩ መኖሩን ከጅምሩ እያወቀ ውጤቱን በመጠበቅ ከፍርዱ በኋላ የፍርድ መቃወሚያ የሚያቀርበውን ወገን አቤቱታውን በመቀበል ለማስተናገድ አስፈላጊ ያለመሆኑን ሁሉ ያስገነዝባል። ይህም የክርክር አቀራረብ በቅን ልቦና የተመሰረተ ሁኖ በአነስተኛ ወጪ፣ ጉልበትና አጭር ጊዜ ፍትሐዊነት ያለውን ውሳኔ ለመስጠት የሚቻልበት አግባብ እንዲኖር እና ሕግ አውጪ ከፈለገበት አላማ ጋር መጣጣም ያለበት መሆኑም የሚታመን ነው። እንግዲህ አቤቱታውን የሚያቀርበው ወገን የቅን ልቦና ተከራካሪ ሁኖ መሰረታዊ መብቱን ማስከበር የሚችልበት የስነ ስርዓት ሕግ አግባብ እንዲኖር ሕግ አውጪ የፈለገ ሲሆን ይህንኑ መመዘኛ የሚያሟላ አቤቱታ አቅራቢ የሚቃወመው ፍርድ ዋጋ ያለው፣ያልተፈፀመ መሆን እንደአለበትም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ድንጋጌ ይዘት ያስረዳል።በልላ አገላለፅ የፍርድ መቃወሚያ የሚቀርብበት ፍርድ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ያልተሻረና አፈጻጸሙም ያልተጠናቀቀ ላሆን እንደሚገባ ሕጉ ያሳያል።
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ ደግሞ አመልካቾች በተተኪ ወራሽነት የምናገኘውን መብት የነካ ነው የሚሉት ፍርድ በመጨረሻ ላይ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሻረ ከመሆኑም በላይ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ የመጨረሻ እልባት የተሰጠበት በመሆኑ የፍርድ መቃወሚያ የሚቀርብበት ፍርድ በወረዳው ፍርድ ቤት መዝገብ ላይ አለ ለማለት የሚቻልበት ምክንያት የለም።ስለሆነም ዋጋ ያለው ፍርድ በወረዳው ፍርድ ቤት የልለ መሆኑ ከተረጋገጠ የአመልካቾች የፍርድ መቃወሚያ በወረዳው ፍርድ ቤት የሚስተናገድበት አግባብ የለም።ከዚህ አንፃር ስንመለከተው የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ውጤቱ ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ለማለት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
በልሙና ቢላቢሎ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 26 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ታህሳስ 05 ቀን 2005 ዓ/ም፣በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ሀምል 23 ቀን 2005 ዓ/ም በትዕዛዝ የፀናው ብይን ውጤቱ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሰረት ጸንቷል።
አመልካቾች የፍርድ መቃወሚያ ያቀረቡበት ፍርድ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ተሸሮ የመጨረሻ እልባት በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎትም ያገኘ በመሆኑ አቤቱታቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት የሚስተናገድ አይደለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።