No summary available.
ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996"ን" መሰረት አድርጎ የቀረበን የስራ ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካቾች ባሁኑ በተጠሪ ላይ በአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።የአመልካቾች የክስ ይዘትም ባጭሩ፡-ከተጠሪ ጋር መስርተው የነበረውን የስራ ውል የአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) ድንጋጌን መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጡረታ መብት እንዲጠበቅላቸው መስከረም 25 ቀን 2005 ዓ/ም ወስኗል በሚል ምክንያት ለአመልካቾች የስራ ውል ማቋረጫ ደብዳቤ የሰጣቸው መሆኑን፣እድሜአቸው ስልሳ አመት ሳይሞላ በጡረታ እንዲሰናበቱ መደረጉ ከሕግ ውጪ መሆኑን ጠቅሰው የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጠው መልስም አመልካቾች በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) ድንጋጌ መሰረት በሚንኒስትሮች ምክር ቤት በተወሰነው መሰረት የጡረታ መብት ተጠብቆላቸው የተሰናበቱ ስለሆነና በዚህ አግባብ የተሰናበተ ሰራተኛ ደግሞ የስራ ስንብትም ሆነ ካሳ የሚከፈልበት የሕግ አግባብ የልለ መሆኑን ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል። የወረዳው ፍርድ ቤትም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠውን ውሳኔ እንዲቀርብ አድርጎ ከተመለከተ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካቾች በጡረታ እንዲወጡ መደረጉ መረጋገጡንና በጡረታ የወጡት ሰራተኞች ደግሞ የሚተዳደሩት በመንግሰት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 714/2003 መሰረት መሆኑን ጠቅሶ ጉዳዩን ለማየት ፍርድ ቤቱ ስልጣን የለውም ሲል መዝገቡን ዘግቶታል።በዚህ ብይን የአሁኑ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ይግባኛቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት የተሰረዘባቸው ሲሆን የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግን ችሎቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የአመልካቾች ጥያቄ የጡረታ እድሜ ሳይደርስ ጡረታ እንድንወጣ ተደርጓል የሚል በመሆኑና ይህም በፍርድ ቤት ላታይ የሚችል ያለመሆኑን ከጠቀሰ በኃላ የአመልካቾች ጉዳይ እድሜ ስላልደረሰ በጡረታ መውጣት አይገባንም የሚል በመሆኑ በፍርድ ቤት የሚታይ አይደለም በማለት የስር ፍርድ ቤትን ብይን ውጤቱን አጽንቶታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የአመልካቾች የክስ ይዘት ስንብቱ ከሕግ ውጪ ጡረታ እድሜ ደርሷል የሚል ይዘት ያለው ሲሆን ለሕገ ወጥ የስራ ውል ማቋረጥ የሚከፈሉት ክፍያዎች እንዲከፈሉ ይወሰንልን ዳኝነት የሚጠይቅ ሁኖ ሳለ የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ በፍርድ ስልጣን ስር የሚወድቅ አይደለም በማለት መወሰናቸው ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የችሎቱን ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ላዳኝ የሚችል አይደለም ተብሎ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መወሰኑ በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚል ነው።፡ ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካቾች ክስ የመሰረቱት የሥራ ውሉ በዕድሜ ምክንያት እንዲቋረጥ መደረጉ ከሕግ ውጪ ስለሆነ ለሕገ ወጥ የሥራ ስንብት የሚከፈሉ ክፍያዎች እንዲከፍሉ ይወሰንልን በሚል መሆኑን፣ተጠሪ ደግሞ አመልካቾች መሰናበታቸውን ሳይክድ ስንብቱ ሕጋዊ ነው የሚልበትን ምክንያት ጠቅሶ በዚህ ረገድ ማስረጃ አቅርቦ መከራከሩን ነው።ስለዚህ ከዚህ የግራ ቀኙ ክርክር በጭብጥነት ተይዞ ዳኝነት የሚፈልገው ጉዳይ ስንብቱ ሕጋዊ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነው።
በመሰረቱ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ የሥራ ስንብት የሚደረግባቸው ምክንያቶች ተለይተው የተቀመጡ ሲሆን ስንብቱ አከራካሪ ሁኖ ሲገኝም ዳኝነት የሚሰጡ አካላት የትኞቹ እንደሆኑ አዋጁ ያሳያል።በአዋጁ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይን አከራከሮ ለመወሰን ስልጣን የተሰጣቸው አካላት የሚመለከቷቸው የክርክር አይነቶች ተገልጸዋል። መደበኛ ፍርድ ቤቶች የአሰሪና ሰራተኛን ክርክር በቀጥታ ሲቀርብላቸው ወይም ደግሞ በይግባኝ ሲመጣላቸው ለማስተናገድ እንደሚችሉ የአዋጁ አንቀፅ 138 እና 139 ድንጋጌዎች ያሳያሉ።መደበኛ ፍርድ ቤት በቀጥታ ለማየት ሥልጣን የሚኖረው ግል የሥራ ክርክሮችን ሲሆን የግል የሥራ ክርክር የሚባለው በአዋጁ አንቀጽ 138 (1) ላይየተገለፁት እናተመሣሣይውጤት ያላቸውክርክሮች ናቸው። በመደበኛ ፍርድ ቤቶች በይግባኝ ላታዩ የሚችሉት ጉዳዮች ደግሞ ቦርዱ ያያቸውን ጉዳዮች፣ በሥልጣን ላይ የሚቀርብን መቃወሚያ፣ የማህበር ምዝገባን ክልከላ፣ ሚኒስቴሩ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ያለን ቅሬታ፣ የሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪው በሰጠው ውሳኔ ላይ፣ ሚኒስቴሩ እገዳንና የማህበር ስረዛን በተመለከተ በሰጠው ውሳኔ ላይ ስለመሆኑ አዋጁ ያሳያል።
ጉዳዩ የግል የስራ ክርክር ወይም የወል የስራ ክርክር መሆኑን መሰረት አድርጎ የሚለይበት የሕግ አግባብና በዚህ ረገድ የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣንን መወሰን እንደተጠበቀ ሁኖ የስራ ውሉ የተቋረጠው በበቂ ምክንያት መሆን አለመሆኑ ጉዳዩን ለመዳኘት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት ስልጣን በተሰጠው አካል የሚወሰን ይሆናል። ልሎች ሕጎችም የስራ ውል መቋረጥን ላያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶችን በዝርዝር ደንግገው ላያስቀምጡ ይችላሉ። በመሆኑም ከውሉ መቋረጥ ጋር ተያይዞ ክርክር ከተነሳ ይህንኑ ጉዳይ የሚዳኘው አካል ለስንብቱ ምክንያት የሆነው ነገር መኖር ያለመኖሩን መመርመርን የግድ የሚለው ይሆናል።
የአዋጅ ቁጥር 377/1996 የስራ ውል ስለሚቋረጥበት ምክንያቶችና ሁኔታዎችን በአንቀጽ 23፣ ከአንቀጽ 26 እስከ 30 ተደንግገው ይገኛሉ። በተጨማሪም በሕብረት ስምምነት መሰረት ያለማስጠንቀቂያ ውሉን ለማቋረጥ የሚያበቃ ምክንያት ተደርጎ የተወሰደ ጉዳይም በአሰሪው ተነሳሽነት ያለማስጠንቀቂያ ውሉን ላያቋርጥ የሚችል መሆኑ በአንቀጽ 27/1/ተ/ ስር ተደንግጎ ይገኛል። በአዋጁ አንቀጽ 24 እንደተመለከተው ውሉ በሕግ የሚቋረጥበት ምክንያቶች በአብዛኛው ከሁለቱም ወገን ቁጥጥር ውጭ ያሉ ሲሆን የስራ ውል ሁለቱም ፈቃደኝነት የሚገቡበት እንደመሆኑ ሁሉ ሁለቱም በፈቃደኛነት ከተስማሙ ውሉን ላያቋርጡ የሚችሉበት ሁኔታም በአንቀጽ 25 ስር ሰፍሮ ይገኛል ። ስለዚህ ከላይ በተገለጹት ቁጥሮች በተደነገጉት ምክንያቶችና ሁኔታዎች የሚፈጸም የስራ ውል መቋረጥ ሕጋዊ የስራ ውል መቋረጥ ሲሆን ከነዚህ ውጭ የሚደረጉ የስራ ውል መቋረጥ በሕገ ወጥነት የሚፈረጁ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 42 ድንጋጌ ስር ተመልክቷል። በዚህም ላይ በመመስረት የሚያስከትሉት ውጤቶች የሚለያዩ በመሆኑ በተናጥል የሚያስከትሉትን ውጤት ከሕጉ አግባብ በማየት ዳኝነትን መስጠት ይጠይቃል።
ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከት የአመልካቾች የዳኝነት ጥያቄ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው፣የጡረታ እድሜያችን ሳይደርስ በጡረታ እንድንወጣ ተደርጎ ውሉ ተቋርጧል የሚል ነው።አመልካች ደግሞ በሕጉ አግባብ የሥራ ውሉ መቋረጡን ጠቅሶ የስንብት እርምጃው ሕጋዊ ነው በማለት ተከራክሯል።ከዚህ መረዳት የሚቻለው የተጠሪ ክርክር በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 24 እና አዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) መሰረት የቀረበ ሁኖ አመልካቾች ደግሞ እድሜያቸው ለጡረታ ስለመድረሱ ሳይክዱ በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) መሰረት የስራ ውል የሚቋረጠው የሰራተኛው የአገልግሎት ዘመን 25 አመት ያላነሰና እድሜው ከሃምሳ አመት ያላነሰ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ህልውና በማክተሙ፣ የሰው ኃይል ብዛቱ ከሚፈልገው በላይ በመሆኑ ወይም ከፕራይቬታይዜሽን ጋር በተያያዘ ከሥራ እንዲሰናበት ከተደረገና አገልግሎቱ ከ25 ዓመት ያላነሰና ዕድሜው ከ50 ዓመት ያላነሰ ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲወሰን ነው በሚል ነው።ይህም ስንብቱ ከህግ ውጪ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ክርክራቸውን ማቅረባቸውን የሚሳይ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ስንብቱ በሕግ አግባብ የተደረገ መሆን ያለመሆኑን ከመመርመር የሚያግደው አይደለም።ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) ድንጋጌ አግባብ አመልካቾች በጡረታ እንዲገለሉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ማስወሰኑ የተካደ ፍሬ ነገር አይደለም።በዚህ ረገድ አመልካቾች በዚህ ሰበር ደረጃ ያቀረቡት የመልስ መልስ ይዘት ሲታይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉዳዩ መወሰኑን አምነው ተጠሪ ይህንኑ ውሳኔ አሳስቶ ያስወሰነ መሆኑን የሚያሳይ እንጂ ውሳኔው የለም በማለት ያቀረቡት ክርክር የለም።በመሆኑም አመልካቾች በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) መሰናበታቸው ከተረጋገጠ ይኼው ውሳኔ በሕጉ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት እስካልተለወጠ ድረስ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት የሚከራከሩበት አግባብ የለም።በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካቾች ጥያቄ የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ የስራ ስንብት ነው በሚል የቀረበና ውጤቱም በአዋጁ አንቀጽ 39 እና ተከታይ ድንጋጌዎች አግባብ እንዲታይ የቀረበ መሆኑን በማገናዘብ ጉዳዩ የመደበኛ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት የሚታይ ነው በማለት ክርክሩን ማየት ሲገባቸው ጉዳዩ በፍርድ ቤት ስልጣን ስር የሚወድቅ አይደለም በማለት የሰጡት የውሳኔ ክፍል ተቀባይነት የልለው ሁኖ አግኝተናል።
ይሁን እንጂ አመልካቾች በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) መሰረት ከስራ የተሰናበቱና የጡረታ መብታቸውም ተከብሮ አበሉን በመቀበል ላይ እንደሚገኙ በተጠሪ በኩል የቀረበውን ክርክር ግልጽ ማስተባበያ ያላቀረቡና በዚህ ረገድ ስልጣን ባለው አካል የተሰጠው ውሳኔም በስርዓቱ መሰረት ጥያቄ ቀርቦ ውድቅ የሆነበት አግባብ ስለመኖሩ የክርክሩ ሂደት የማያሳይ በመሆኑ የተጠሪ እርምጃ ሕጋዊ ነው? ወይስ አይደለም? በሚለው እና በውጤቱ ላይ ክርክር እንዲካሄድ ማድረግ የስነ ስርዓት ሕጉን አላማ ያገናዘበ ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ ስላልተገኘ በዚህ ችሎት በዚህ ረገድ ድምዳሜ መያዙ ተገቢ ሁኖአል።በመሆኑም አመልካቾች በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) መሰረት በተሰጠ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ በጡረታ የተገለሉና የጡረታ መብትም ተጠቃሚ መሆናቸው ያልተካደ በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤቶች ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው ከውጤት አንፃር ሲታይ የሚነቀፍ ሁኖ አልተገኘም።በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ ሀምል 11 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ነሀሴ 09 ቀን 2005 በትዕዛዝ፣በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ታህሳስ 14 ቀን 2006 ዓ/ም ምክንያቱ ተለውጦ በፍርድ የፀናው ብይን በውጤት ደረጃ ሲታይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል።
አመልካቾች በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 19(7) አግባብ ተሰናብተው የእድሜ ልክ የጡረታ መብት ተከፋይ መሆናቸው የተረጋገጠ ስለሆነ የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ላባል የሚችል አይደለም ብለናል።በዚህም ምክንያት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 35(1(ሀ) እና 44፣40(1) እና (2)፣36 እና 38 እንዲሁም 43(3) እና 44(4) ድንጋጌዎች አግባብ የጠየቋቸው የክፍያ አይነቶች ላከፈሐቸው አይገባም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.