No summary available.
የካቲት 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ ጥሩወርቅ መንግስቴ - ጠበቃ አቶ ስዩም አዳሙ ቀረቡ ተጠሪ፡- የተገጣጣሚ ህንፃ አካላት ማምረቻ ድርጅት - ጠበቃ አቶ መንግስቱ ኃይሉ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ክርክሩን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩም የተጀመረው በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁኑ አመልካች በተጠሪ ላይ በመሰረቱት ክስ ነው። የክሱ ፍሬ-ነገርም ባጭሩ፡- ከሳሽ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ በግዥ አቅርቦት እና ሽያጭ መመሪያ የሥራ ኃላፊነት ላይ ተመድበው በመስራት ላይ እንዳሉ ባላወቁትና ባልተረዱበት ሁኔታ የስራ ውላቸው ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ ከ24/05/2004 ዓ/ም ጀምሮ የተቋረጠ ለመሆኑ በ25/05/2004 ዓ/ም የተፃፈ ደብዳቤ በ3/6/2004 ዓ/ም የደረሳቸው መሆኑን ጠቅሰው የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈላቸው ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ሲሆን የስር ተከሳሽ የሆነው የአሁኑ ተጠሪም ቀርቦ በሰጠው መልስ፡- ከሳሽ ላከፍሉን ይገባል በማለት ያቀረቡት የተለያዩ ክፍያዎች ጥያቄ በስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 37 መሰረት የስራ ውሉ ከተቋረጠበት ከ24/05/04 ዓ/ም ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት 30/11/2004 ዓ/ም ያለው ጊዜ ከ6 ወር በላይ ስለሆነ ክሱ በይርጋ ቀሪ ይሆናል በማለት የመጀመሪያ መቃወሚያ በማቅረብ ተከራክሯል። ጉዳዩን የተመለከተው የፍድራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በበኩሉ የቀረበውን የይርጋ መቃወሚያ ከድርጅቱ የስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንቡ አኳያ አገናዝቦ መመርመሩን ከገለጹ በኋላ የሥራ ውሉ የተቋረጠው በ24/05/04 ዓ/ም ስለመሆኑ በስር ከሳሽ ያልተካደ መሆኑን፣ ክሱ ደግሞ የቀረበው በ30/11/04 ዓ/ም መሆኑን ከመዝገቡ መገንዘቡንና የተከሳሽ ድርጅት የስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 37(3) መሰረት አንድ የሥራ መሪ የስራ ውሉ በተቋረጠ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ጥያቄውን ካላቀረበ መብቱ በይርጋ እንደሚታገድ የተደነገገ መሆኑን ካሰፈረ በኋላ ከሳሽ ክሱን ያቀረቡት የስራ ውሉ ከተቋረጠ ከ6 ወር በኋላ ነው የሚል ድምዳሜ ሀሳብ ላይ ከደረሰ በኋላ ክሱ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 244(2)(ሰ) እና 245(2) መሰረት በይርጋ ቀሪ ይሆናል በማለት መዝገቡን በብይን ዘግቷል። በአሁኗ አመልካች ይግባኝ አቤቱታ አቅራቢነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት በበኩሉ ይግባኙን ከመረመረ በኋላ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 337 መሰረት ሰርዞታል።
አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይሄንኑ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ብይንና ትዕዛዝ በመቃወም ሲሆን መሰረታዊ ይዘቱም የሥራ ውሉ የተቋረጠበት ደብዳቤ አመልካች የደረሰው በ3/6/2004 ዓ/ም መሆኑ እየታወቀ እና ከዚህ ቀን ጀምሮ ክሱ በስር ፍ/ቤት እስከቀረበበት ሐምል 24 ቀን 2004 ዓ/ም ድረስ ያለው ጊዜ ሲቆጠር ደግሞ 6 ወር የማይሞላ መሆኑ እየታወቀ ክሱ በስር ፍ/ቤቶች በይርጋ ቀሪ ነው ተብሎ መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ውሳኔው ተሽሮ እና ጉዳዩ ወደ ስር ፍ/ቤት ተመልሶ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
አቤቱታውም ተመርምሮ ያስቀርባል በመባሉ ተጠሪም ቀርቦ የበኩሉን መልስ በፅሁፍ ሰጥቷል።
አመልካችም የመልስ መልስ ሰጥተዋል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ባጭር ባጭሩ ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን እኛም በበኩላችን በአመልካች የቀረበው የዳኝነት ጥያቄ በስር ፍ/ቤቶች በይርጋ ቀሪ ነው መባሉ በአግባቡ መሆን አለመሆኑን በጭብጥነት ይዘን ጉዳዩን መርምረናል።
እኛም ጉዳዩን እንደተመለከትነው አመልካች የሚከራከሩት የይርጋ ጊዜው መቆጠር ላጀምር የሚገባው የስራ ውሉ ከተቋረጠበት ቀን ጀምሮ ሳይሆን የስራ ውሉ የተቋረጠበት ደብዳቤ ከደረሰኝ ከ3/6/2004 ዓ/ም ጀምሮ መሆን አለበት በሚል ሲሆን ተጠሪም በበኩሉ የሥራ ውሉ መቋረጫ ደብዳቤ ለአመልካች የደረሰው በ3/6/2004 ዓ/ም መሆኑን ሳይክድ ሆኖም ግን በተጠሪ ድርጅት የስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 37 ድንጋጌ መሰረት አንድ የሥራ መሪ የመብቱን ጥያቄ ለማቅረብ ከሚችልበት ቀን ጀምሮ እስከ 6 ወር ጊዜ ድረስ ጥያቄውን ካላቀረበ መብቱ በይርጋ ይታገዳል በሚል ስለሚደነግግ እና አመልካችም ከዚህ አኳያ አሉኝ የሚሉትን መብት ለማቅረብ የሚችሉት የስራ ውሉ ከተቋረጠበት ከ24/05/04 ዓ/ም ጀምሮ መሆኑ በግልጽ በተደነገገበት ሁኔታ አመልካች የሥራ ውሉ መቋረጫ ደብዳቤ ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ መሆን አለበት በሚል ጠቅሰው ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት የለውም በሚል የሚከራከር መሆኑን ተገንዝበናል።
በመጀመሪያ ደረጃ ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ ማለትም የመብቱ ጥያቄ ስለሚቀርብበት የይርጋ ጊዜን አስመልክቶ ተፈፃሚነት ያለው ይሄው በተጠሪ ድርጅት የስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ የተመለከተው የ6 ወራት የጊዜ ገደብ ስለመሆኑ አከራካሪ ባይሆንም ሆኖም ግን የይርጋ አቆጣጠሩን መነሻ ጊዜ በተመለከተ ተጠሪም በበኩሉ ለዚህ ሰበር ችሎት በሰጠው መልስ ይሄንኑን መነሻ በማድረግ ክርክሩን እንዳቀረበው የፍ/ብ/ህ/ቁ፣ 1846 ድንጋጌ ለዚህ ጉዳይም አግባብነት ያለው ስለመሆኑ የሚታመን ነው። ይህ የተጠቀሰው ድንጋጌም “የይርጋ መነሻ ጊዜ” በሚል ርዕስ የተሰየመ ሲሆን የድንጋጌው ሙሉ ይዘትም የይርጋ ቀን መቆጠር የሚጀምረው ግድታውን ለመጠየቅ ተገቢ ከሆነው ወይም ውሉ የሚሰጠው መብት ከተሰራበት ጀምሮ ነው የሚል ነው።
ከዚህ አኳያ የተያዘውን ጉዳይ ስንመረምረውም በመጀመሪያ ደረጃ የአመልካች ስራ ውል የተቋረጠው ከ24/05/04 ዓ/ም ጀምሮ ስለመሆኑ አከራካሪ አይደለም። የስራ ውሉ መቋረጫ ደብዳቤም ለአመልካች የደረሰው በ3/06/2004 ዓ/ም ስለመሆኑም እንዲሁ ግራ ቀኙን ያከራከረ ጉዳይ አይደለም። እንዲህ ከሆነ እና ከ3/06/2004 ዓ/ም በፊትም አመልካች የስራ ውሉን አስቀድሞ የተቋረጠ መሆኑን በልላ አግባብ ታውቆ ነበር በሚል ከተጠሪ የቀረበ ክርክር በልለበት ሁኔታ ደግሞ አመልካች የስራ ውሉ መቋረጡን መነሻ በማድረግ መብቷን የማስከበር እንቅስቃሴ ልትጀምር የምትችለው የስራ ውሉ የተቋረጠበት ደብዳቤ ከደረሳት እለት ጀምሮ መሆኑ ነው።
ይህም ከ3/6/2004 ዓ/ም ጀምሮ መሆኑ ነው። ከዚህ ቀን ጀምሮ ክሱ ለስር ፍ/ቤት እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ (ሐምል 30 ቀን 2004 ዓ/ም) ያለው ሲቆጠር ደግሞ 6 ወር ያላለፈ በመሆኑ በተጠሪ ድርጅት የሥራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 37 ድንጋጌ መሰረት ክሱ በይርጋ ቀሪ ላሆን የሚችል አይደለም። ስለሆነም በፍድራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተሰጠው ብይንና ይሄንኑን ብይን በማፅናት በፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1846ና የተጠሪ ድርጅት ስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 37 ድንጋጌን ይዘት፣ መንፈስና አላማን ያላገናዘበ ስለሆነ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ በ21/07/05 ዓ/ም የሰጠው ብይንና ይሄንኑን በማፅናት የፍድራሉ ከፍ/ፍ/ቤት በኮ/መ/ በ11/02/06 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የኮ/መ/ የሆነውን በማንቀሳቀስና ግራ ቀኙን አስቀርቦ ክርክሩ ከቆመበት ጀምሮ በማከራከር በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥበት ዘንድ ክርክሩን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል። ይፃፍ።
የሰበር ክርክሩን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.