No summary available.
መጋቢት 23 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ አልማዝ ባዛ - አልቀረቡም።
ተጠሪ፡- የደቡብ መንገዶች ባለስልጣን - ነ/ፈጅ ፍፁም አዲስ ቀረበ።
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበችውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የደረጃ እድገት አላግባብና ከሕግ ውጭ ተከልክያለሁ በማለት የቀረበውን ጥያቄ የሚያመለክት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ አመልካች ያቀረበችው ክስ ነው። ከሳሽ ተከሳሽ በመስከረም 1 ቀን 2005 ዓ.ም የደረጃ እድገት ማሰታወቂያ አውጥቷል። ተከሳሽ በማስታወቂያው የማኔጅመንት የመጀሪያ ዲግሪና ዜሮ አመት የሥራ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች ለዕድገት መወዳደር እንደሚችሉ ገልጿል። እኔም በማኔጅመንት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪና አሥር አመት የሥራ ልምድ ያለኝ በመሆኑ ለእድገት ለመወዳደር ተመዝግቤ የተሰጠውን ፈተና አልፍና ተወዳድሬ በአንደኝነት አልፍአለሁ። ሆኖም ተከሳሽ ያለምንም በቂ ምክንያት የተወዳደርኩበትን የሥራ መደብና እድገት እንዳላገኝ ያደረገኝ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በፍርድ መብቴን እንዲያስከብርልኝ በማለት ክስ አቅርባለች። ተጠሪ በበኩሉ በተከሳሽነት ቀርቦ የመጀመሪያ ክስ መቃወሚያ ያቀረበ ሲሆን ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተ አመልካች የተወዳደረችበትን እድገት አለማግኘቷ ተገቢ ነው። የዕድገት ማስታወቂያው የወጣው ሥራ አስኪያጅ ሣያውቀውና ሣይፈርምበት ነው። የእድገት ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ሥራ አስኪያጅ አልተቀበለውም በመሆኑም የከሳሽ ክርክር የህግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክረዋል።
የሥር ፍርድ ቤት የተጠሪን የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ ውድቅ አድርጐታል።
የከሳሽን የዳኝነት ጥያቄ በተመለከተ ከሳሽ ተከሳሽ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት መስፈርቱን በማሟላት ከልሎች ሁለት ተወዳዳሪዎች ጋር በድርጅቱ የተሰጠውን ፈተና ተፈትና ልሎቹን ተወዳዳሪዎች በመብለጥ ያለፈች መሆኑ በእድገት ኮሚቴው ቃለ ጉባኤ በግልፅ ሰፍሯል። ከሳሽ በፈተናውና ልሎች መስፈርቶችን በማሟላት የእድገት ማስታወቂያ ለወጣበት የሥራ መደብ መመደብ የምትችል መሆኑ ቢረጋገጥም የተከሳሽ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በቂና ቀጥተኛ የስራ ልምድና ብቃት ያለው ሰው ስላልተገኘና የእድገት ውድድሩም አራት ወራት ያህል እንደፈጀ በመግለጽ የእድገት ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ያደረገው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ሕግና የህብረት ስምምነቱን በሚቃረን መንገድ በመሆኑ ተወዳድራ ባለፈችበት የሥራ መደብ እንዲመድባት በማለት ወስኗል። ከሳሽ በህግ መሰረት የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግላት የጠየቀችውን ጥያቄም በአግባቡ በማጣራት የደመወዝ ማስተካከያ እንዲያደርግላትና ጥቅማጥቅም እንዲያከብርላት በማለት ወስኗል።
ተጠሪ ይግባኝ ለሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የከፍተኛው ፍርድ ቤት የተጠሪን ይግባኝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል። ተጠሪ በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታ ለክልሉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አቤቱታ አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ተጠሪ /አመልካች /ተወዳድራ ያለፈችበት እድገት በድርጅቱ ሥራ አስኪያጅነት ያልፀደቀ በመሆኑ ተጠሪ የደረጃ እድገቱ ላሰጠኝ ይገባል በማለት ክስ ለማቅረብ አትችልም በማለት የሥር ፍርድ ቤትና የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል።
አመልካች 06/03/2006 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሰራተኞችን ለማወዳደር አስቀድሞ ያወጣውንና በዕድገት ማስታወቂያው የዝርዝር መስፈርት ሳያገናዝብ ያለበቂ ምክንያት የዕድገት ኮሚቴው በተሰጠው መሥፈርት መሰረት አወዳድሮ ያቀረበለትን ውጤት ውድቅ ማድረጉ በፍርድ ታይቶ ላታረም የሚገባው ሆኖ እያለ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት እንደማይታይ አድርጐ የሰጠው ትርጉምና ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ የክልሉ መንግስት ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት ላያደርግልኝ የሚገባውን የደመወዝ ማስተካከያ የነፈገኝ ሆኖ እያለ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ መሻሩ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክታለች ። ተጠሪ በበኩሉ 22-04-2006 ዓ.ም በተፃፈ መልስ የዕድገት ኮሚቴ ቃለ ጉባኤ ተፈፃሚ የሚሆነው በሥራ አስኪያጁ ሲፀድቅ ነው። ይህም በሕብረት ስምምነቱ የተገለፀ በመሆኑ የአመልካች የሰበር አቤቱታ የሕግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክረዋል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የእድገት ውድድሩን ያልተቀበለው በመሆኑ ከሳሽ እድገት ይሰጠኝ በማለት መጠየቅ አትችልም በማለት የሰጠው የሕግ ትርጉምና ውሳኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?የሚውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ለእድገት የተወዳደረችበት የሪከርድና ማህደር ሱፐርቫይዘር የሥራ መደብ በእድገት ለመወዳደር በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለውና ዜሮ አመት የሥራ ልምድ የሚያስፈልግ መሆኑ ተጠሪ ከመስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም ባወጣው የእድገት ማስታወቂያ ሰነድ የተገለፀ መሆኑ በሥር ፍርድ ቤትና በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተረጋግጧል። አመልካች በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪና የአስር አመት የስራ ልምድ ያላት በመሆኑ በእድገት ውድድር ተመዝግባ ከልሎች ሁለት ሰራተኞች ጋር ተፈትና ብልጫ ያለው ውጤት በማግኘቷ እድገቱ እንዲሰጣት የተጠሪ ድርጅት የእድገት ኮሚቴ ቃለጉባኤ በማረጋገጥ የውሳኔ ሀሳብ ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ያቀረበ በመሆኑ በሥር ፍርድ ቤት ተረጋግጧል።
የድርጅቱ ዕድገት ኮሚቴ ቃለጉባኤ የውሳኔ ሀሳብ የደረሰው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ “ውድድሩ ቀጥተኛ የሥራ ልምድ ያለውና ብቃት ያለው ሰው ያላስገኘና ጊዜውም ከአራት ወር በላይ ስለሆነው ውድቅ ቢሆን የተሻለ ነው” የሚል ይዘትም ያለው ውሳኔ በመስጠት አመልካች የተወዳደረበትንና ያለፈችበትን እድገት እንዳታገኝ ያደረጋት መሆኑን ከበታች ፍርድ ቤትቶች ውሳኔ ተረድተናል። አመልካች በዳኝነት ታይቶ እንዲታረምላት የምትጠይቀው የተጠሪ ሥራ አስኪያጅ የእድገት ኮሚቴው አወዳድሮ ያቀረበውን ውጤትና የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ያደረጉበት ምክንያት የሕግ መሰረት የልለው ነው በማለት ነው።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አመልካች በውድድሩ ያገኘችው ውጤትና የእድገት ኮሚቴው ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በድርጅቱ ያልፀደቀ በመሆኑ፣ ለተወዳደረችበት የሥራ መደብ አልፋለች ብሎ ለመደምደም አይቻልም። ስለዚህ የበታች ፍርድ ቤቶች ሥራ አስኪያጅ ያላፀደቀውን የእድገት ውድድር ውጤት መሰረት በማድረግ ውሳኔ መስጠታቸው ተገቢ አይደለም በሚል ምክንያት መሆኑን ተገንዝበናል።
ይህም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ውሳኔ፣ አንድ ድርጅት ለእድገት ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ተወዳድሮ በውጤቱ የእድገት ማስታወቂያ የወጣበትን የሥራ መደብ መመደብ የሚገባው መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፣ በቂና ምክንያታዊ ባልሆነ ማናቸውም ምክንያት የሰራተኛውን ውጤት አልቀበልም በማለት ቢወሰን ፍርድ ቤቶች የሥራ አስኪያጁ ውሳኔ የህግ መሰረት ያለው በቂና ምክንያታዊ መሆኑን የመመርመርና ሥራ አስኪያጁ ስህተት ሰርቶም ከሆነ በፍርድ የማረም ስልጣን የላቸውም የሚል አንድምታዎች ትርጉም ያለው ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህም የአንድ ድርጅት የእድገት ኮሚቴ፣ የእድገት አሰጣጥ ደንብና ሥርዓት በመከተል ለእድገት ለመወዳደር ያቀረቡትን ሰራተኞች ዕውቀትና ክህሎት ለመመዘን ድርጅቱ ያስቀመጣቸውን የብቃት መመዘኛ መስፈርቶች የተሟሉ መሆኑን በማረጋገጥ በውድድሩ ከፍተኛ ውጤት ያመጣውን ሰራተኛ በመለየት፣የቀረበለትን የእድገት ውድድር ውጤትና የውሳኔ ሀሳብ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ውድቅ ቢያደርገው ሰራተኛው ጉዳዩን በፍርድ እንዲታይለት ለመጠየቅና ክስ ለማቅረብ ይቻላል ወይስ አይቻልም? ፍርድ ቤቱስ ይህንን ጉዳይ በዳኝነት በማየት አስገዳጅነት ያለው ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን አለው ወይስ የለውም? የሚሉትን የሕግ ጥያቄዎች የሚያስነሳ ነው።
በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ በሰራተኛ ዕድገት ዝውውርና ሥልጠና በሚመለከት አሰሪው የሚወስዳቸው እርምጃዎች በፍርድ ላታዩና ላያልቁ የሚችሉ ጉዳዮች እንደሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 142 ንዑስ አንቀጽ 1/ሰ/ እና ከአንቀጽ 147 ንዑስ አንቀጽ 1/ሀ/ ድንጋጌዎች ይዘትና ይህ ሰበር ችሎት ስለ ግል የሥራ ክርክርና ስለ ወል የሥራ ክርክር፣ የክልልም ሆነ የፍድራል የሥራ ክርክር ችሎቶች የግል የሥራ ክርክሮችን በዳኝነት አይተው የመወሰን ሥልጣን ያላቸው መሆኑን በማስፋፋት በስር መዝገብ ከሰጠው አስገዳጅ ትርጉም ለመረዳት ይቻላል።
ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች ሥራ አስኪያጁ የእድገት ውድድሩን ውጤት ያልተቀበለው ያለበቂ ምክንያትና ከሕግ ውጭ ነው በማለት በሥር ፍርድ ቤት ያቀረባቸው የዳኝነት ጥያቄ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ አንቀጽ 138፣አንቀጽ 142 ንዑስ አንቀጽ 1/ሰ/ እና አንቀጽ 147 ንዑስ አንቀጽ 1/ሀ/ እንዲሁም ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት ያደረገ ነው።
የሥር ፍርድ ቤትም የአመልካችን የዳኝነት ጥያቄ በመቀበል አመልካች የእድገት ውድድሩን ውጤት አልቀበልም፣ አመልካች ተወዳድራ ባለፈችበት የሥራ መደብ አልመድብም የሚልበትን ምክንያትና ማስረጃ እንዲያቀርብ በማድረግ ውሳኔ መስጠቱ ከላይ የተገለፁትን የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎች በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 37 መሰረት ሰራተኛው ያለህጋዊ በቂ ምክንያት አሰሪው በዘፈቀደ እድገት ሲከለክለው በፍርድ እንዲታይለት የመጠየቅና ፍትህ የማግኘት መብቱን የሚያስከብር ትክክለኛ የዳኝነት አካሄድ ሆኖ አግኝተነዋል።
የተጠሪ ሥራ አስኪያጅ፡ የዕድገት ኮሚቴው ያቀረበውን የሰራተኞችን የዕድገት ውድድር ውጤት ውድቅ ያደረገው፣ ኮሚቴው ሰራተኞችን ያወዳደረው የእድገት አሰጣጥ ደንብና ሥርዓትን ሣይከተል /ወይም / በመጣስ ነው። ወይም ኮሚቴው የእድገት ማስታወቂያ ለወጣበት የሥራ መደብ ሰራተኞች ላኖራቸው የሚገባውን ዕውቀትና ክህሎት ለመመዘን ድርጅቱ ያወጣቸውን የብቃት መመዘኛ መስፈርቶች ሣይከተልና ሣያሟላ ነው። በሚል ምክንያት እንዳልሆነ የሥር ፍርድ ቤት በውሳኔው በግልፅ ያሰፈረው የተጠሪ ሥራ አስኪያጅ የውሳኔ ሀሳብ ለመረዳት ችለናል።
በአንፃሩ የተጠሪ ሥራ አስኪያጅ፣ አመልካች የተወዳደረችበት የሪከርድና ማህደር ሱፐርቫይዘርነት የሥራ መደብ የሚያስፈልገው በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪና ዜሮ አመት የሥራ ልምድ መሆኑ ተገልፆ የእድገት ማስታወቂያው እንዲወጣ ያደረገና ውድድሩም በዚሁ መሰረት የተከናወነ ሆኖ እያለ በውድድሩ ቀጥተኛ የሥራ ልምድ ያለው ሰራተኛ አልተገኘም በማለት በመጀመሪያ በመወዳደሪያነት ያላስቀመጠውን መስፈርት ጠቅሶ የአመልካችን እድገትም በቂና ህጋዊ ምክንያት ሣይኖረው አልቀበልም በማለታቸው ጉዳዩን የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል።
ከላይ ከተገለፀው በተጨማሪ የእድገት ማስታወቂያ ለወጣበት የሚያስፈልገው የትምህርት ዝግጅት በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ መሆኑን ተጠሪ በማስታወቂያው የገለፀና አመልካችም በተጠሪ የተጠየቀውን ትምህርት ዝግጅት /በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ/ ያላትና መስፈርቱን ያሟላች ሆኖ እያለና፣ በተጠሪ አመልካች ዕውቀት ክህሎት ለመመዘን የራሱን ፈተና አውጥቶ አመልካች ከልሎች ሁለት ሰራተኞች ጋር ተወዳድራ ማለፏ ተረጋግጦ እያለ፣ ሥራ አስኪያጁ ውድድሩ “ ብቃት ያለው ሰው “አላገኘንም በማለት በውሳኔው መግለፁ፣ ተጠሪ ራሱ ያወጣቸው የብቃት መመዘኛዎችና የትምህርት ዝግጅት ለሚላቸው አመልካች እድገቱን ላለመስጠት ያለበቂና ህጋዊ ምክንያት እንቢተኛ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑ የሥር ፍርድ ቤትና የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ የእድገት ውድድሩን ለማከናወን የእድገት ማስታወቂያው ከወጣ በኋላ ያለፉትን አራት ወራት እድገቱን በውድድሩ አሸናፊ ለሆነችው አመልካች ላለመስጠት እንደምክንያት ማቅረቡ፣ የሕግ መሰረትና ድጋፍ ያለው ሆኖ አላገኘነውም።
በአጠቃላይ ተጠሪ አመልካች ለዕድገት ተወዳድራ ያለፈችበት የሥራ መደብ ላይ ላለመመደብና እድገቱን ላለመስጠት በሥራ አስኪያጁ በኩል ያቀረባቸው ምክንያቶች በበቂ ምክንያት የተደገፈና የህግ መሰረት ያላቸው አይደሉም። በአንፃሩ ተጠሪ የእድገት ማስታወቂያ ሲያወጣ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶችና መመዘኛዎች የሚጥሱ ናቸው።
አሰሪው የሰራተኞችን ብሕረሰብ ፣ፆታ፣ሀይማኖት፣ፓለቲካ አመለካከትና ልላም ሁኔታ መሰረት በማድረግ ልዩነት ማድረግ የማይፈቅድለት መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ/2/ ተደንግጓል። አመልካች ተጠሪ ሴት በመሆኗ ምክንያት ተጠሪ እድገቱን እንዳልሰጣት በመግለጽ የምትከራከር ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ እድገቱን ለአመልካች ያልሰጣት ሴት በመሆኗ ምክንያት ሣይሆን በልሎች ተጨባጭና አሳማኝ ምክንያቶች መሆኑን የማስረዳት ኃላፊነቱን ያልተወጣ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸውም ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል።
የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦች ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ተሻሽሐል።
የደረጃ እድገቱን በተመለከተ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል።
ተጠሪ አመልካችን በእድገት ማስታወቂያ መሰረት ተወዳድራ ባለፈችበት የሥራ መደብ ላመድባት እና የስራ መደቡ የሚያስገኘውን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ላከፍላት ይገባል በማለት ወስነናል።
አመልካች የጠየቀችው ውዝፍ የደመወዝ ማስተካከያ ጥያቄ በዚህ ሰበር ችሎት በጭብጥነት ያልተያዘ በመሆኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰጠው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.