No summary available.
የሰ/መ/ ሚያዚያ 21 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ኢትዮ ቴልኮም ደቡብ ምዕራብ እና ጋምቤላ ሪጅን -አልቀረበም ተጠሪ፡- ወ/ሮ ሳባ መንገሻ- አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ሆኖ በአሁን የሰበር ተጠሪ ከሳሽነት የተጀመረው በጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ነበር። ከሳሽ አሻሽለው ባቀረቡት ክስ፡በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ ከ29/02/1999 ዓ/ም ጀምሮ ተቀጥሬ እየሰራሁ የቆየሁ ቢሆንም በራሴ ፍላጎት የሥራ ውልን ለማቋረጥ በ22/10/2004 ዓ/ም የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ ለተከሳሽ የሰጠሁ ሲሆን ተከሳሽ ድርጅትም ማስጠንቀቂያውን በጻፍኩበት ቀን የሥራ ውልን በማቋረጡ በእጄ ያሉትን ንብረቶች ባስረክብም መክፈል የሚገባቸውን ክፍያዎች ለመክፈል ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣በ2004 ዓ/ም የሥራ ዘመን ለቋሚ ሰራተኞች የከፈለውን ቦነስ የ2 ወር ደመወዝ፣የማስጠንቀቂያውን የአንድ ወር ጊዜ ሳይጠብቅ የሥራ መልቀቂያ በመስጠቱ በወሩ መክፈል የነበረበትን ደመወዝ፣የስንብት ክፍያ፣ክፍያ ለዘገየበት የ3 ወር ደመወዝ፣የ56 ቀናት የአመት ፈቃድ በገንዘብ ተለውጦ፣ በድምሩ ብር 24,594 እንዲከፍል ይወሰንልኝ ብለዋል።
ተከሳሹም ለክሱ የበኩሉን መልስ ከሰጠ በኋላ የወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን በመመርመር ከሳሽ ከጠየቋቸው ክፍያዎች ውስጥ የተወሰኑትን ውድቅ በማድረግ በድምሩ ብር 12,593.74 ተከሳሽ እንዲከፍል የወሰነ ሲሆን በሥር ተከሳሽ ድርጅት ይግባኝ ጠያቂነት ጉዳዩን የመረመረው የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ጉድለት የለበትም ሲል በማጽናቱ አመልካችም የሰበር አቤቱታውን ለዚህ ችሎት አቅርቧል።
ተጠሪዋም ለሰበር አቤቱታው የበኩላቸውን መልስ የሰጡ ሲሆን አመልካችም የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- አመልካች ለዚህ ችሎት ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ተገቢውን ደረጃ ጠብቆ የቀረበ ነው? ወይስ አይደለም?የሚለውን ጭብጥ ይዘን እንደሚከተለው መርምረናል።
አመልካች የሰበር አቤቱታውን በቀጥታ ለዚህ ችሎት ያቀረበው የጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማጽናቱ ነው። በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት በሚቀርብ በግል የሥራ ክርክር ጉዳይ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑን በአዋጁ አንቀጽ 139(1) የተደነገገ ሲሆን ከአንቀጹ መረዳት የሚቻለውም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ከሰጠው ውሳኔ የተለየ ውሳኔ ቢሰጥ እንኳን እንደልሎች የፍትሃብሄር ጉዳዮች ለቀጣይ የይግባኝ ክርክር የማይቀርብ መሆኑን ነው። ይሁን እንጂ በአንቀጹ በዚህ መልክ መጠቀሱ ጉዳዩን በሰበር ችሎት ከመታየት የሚያስቀር አይደለም።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንደመሆኑ መጠን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በህግ የተሰጠውን ሥልጣን መመልከት ተገቢ ይሆናል።
የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልል ጉዳዮች የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ ሲገኝ የማረም ሥልጣን ያለው መሆኑን በኢ.ፍ.ዲ.ሪ.ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3)(ለ) ከተደነገገው መገንዘብ የሚቻል ሲሆን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ህገ መንግስት አንቀጽ 64(ሐ)፣ እንዲሁም የክልሉን ፍርድ ቤቶች እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 26(1)(ሰ) በተመሳሳይ ሁኔታ ተደንግጎ እናገኛለን። ጉዳዩ የቀረበላቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ በሰበር እንዲታይለት አመልካች አቤቱታውን ለክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሳያቀርብ በቀጥታ ለዚህ ችሎት ያቀረበበትን ምክንያት በአቤቱታው በግልጽ ባያሰፍርም አመልካች በፍድራል መንግስት የተመዘገበ አካል በመሆኑ እና በፍድራል መንግስቱ አካላት የተመዘገቡ ወይም የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶችና ማህበሮችን በሚመለከት የሚነሡ ክርክሮችን የማየት የሥረ ነገር ሥልጣን የፍድራል ፍርድ ቤቶች ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5(6) በመደንገጉ፤ እንዲሁም የክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበትን የመጨረሻ ውሳኔ በሰበር ማየት የሚችለው ጉዳዩ የክልል በሆነ ጊዜ ብቻ ነው ከሚል ድምዳሜ በመነሳት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ሆኖም ጉዳዩን ይህ ችሎት በተመሳሳይ ጉዳይ በሰበር መ/ቁ/ 95298 ከሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም አንጻር መመርመር የሚገባ ነው። ችሎቱ በተጠቀሰው የሰበር መዝገብ በሰጠው ፍርድ፡- በፍድራል መንግስቱ አካላት የተመዘገቡ ወይም የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች እና ማህበሮችን በሚመለከት የሚነሱ ክርክሮችን የማየት የሥረ ነገር ሥልጣን የፍድራል ፍርድ ቤቶች ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5(6) የተደነገገ ቢሆንም በልላ በኩል ደግሞ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይን በተመለከተ በክልሎች ውስጥ የሚነሱ የግል የሥራ ክርክር ጉዳዮችን ተቀብሎ የማየት የሥረ ነገር ሥልጣን የተሰጠው ለክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 138(1) በመደንገጉ እና ድንጋጌውም በአዋጅ ቁጥር 25/1988 የተደነገገውን ዓይነት ተከራካሪ አካላትን ማንነት ግንዛቤ ውስጥ ካለማስገባቱም ልላ ድንጋጌው የተካተተበት አዋጅ ቁጥር 377/1996 የወጣው፤ ከአዋጅ ቁጥር 25/1988 በኋላ ከመሆኑ አንጻር የአሰሪና እና ሰራተኛ ጉዳይ ክርክር የተለየ ባህርይ ከግምት ውስጥ በማስገባት ህግ አውጪው ማናቸውም በክልሎች ውስጥ የሚነሳ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ በተከራካሪ ወገኖች (አካላት) ላይ ተመስርቶ ጉዳዩ የክልል እና የፍድራል መሆኑ ከግምት ውስጥ ሳይገባ በክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታይ መደንገጉን እንደሚያሳይ፤ አንድ ጉዳይ የተነሳው በክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ በተነሳበት ክልል የሰበር ችሎት የተደራጀ እስከሆነ ድረስ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ሳይታይ እና ውሳኔው የመጨረሻ መሆኑ ሳይረጋገጥ በቀጥታ ለፍድራል ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ ላስተናገድ የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት እንደማይኖር አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቷል። በዚህ በተያዘው ጉዳይም ምንም እንኳን አመልካች የፍድራል መንግስት አካል ቢሆንም ከዚህ በላይ በተሰጠው የህግ ትርጉም መሰረት የሰበር አቤቱታውን ለፍድራል ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከማቅረቡ አስቀድሞ ጉዳዩ በተጀመረበት ክልል ላለው ለኦሮሚያ ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ማቅረብ ያለበት ሆኖ በመገኘቱ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
አመልካች ለዚህ ችሎት ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ያላገኘ በመሆኑ ተገቢውን ደረጃ ጠብቆ የቀረበ አይደለም ስንል ውድቅ አድርገናል።
ይህ ውሳኔ መብቱን የሚጠይቅ ወገን በህጉ መሰረት አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ከማቅረብ የሚያግደው አይደለም ብለናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ።
No topics extracted.