No summary available.
መጋቢት 08 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን መሃል ሜዳ ደንበኞች አገልግሎት ጽ/ቤት -ነ/ፈጅ ተስፋዬ አያልው ቀረቡ።
ተጠሪ፡- አቶ ሙሉጌታ ወ/ጊዩርጊስ - ቀረቡ።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996"ን" መሰረት አድርጎ የቀረበን የግል የስራ ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀረመው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በመሓል ሜዳ ወረዳ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።የተጠሪ የክስ ይዘትም ባጭሩ፡-ከአመልካች ጋር የመሰረቱት የስራ ውል ግንኙነት ከሕግ ውጪ የተቋረጠባቸው መሆኑን ጠቅሰው ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሐቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም ተጠሪ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ከማህደራቸው ጋር አያይዘው መገኘታቸው በተደረገው መጣራት ተረጋግጦና የድርጅቱ የዲሲፕላን ኮሚቴ ተጠሪን ተገቢ ነው ያለውን ቅጣት በመቅጣት ወደ ስራ እንዲመለሱ ቢወሰንም የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ የኮሚቴውን ውሳኔ ሽረው አመልካች ከስራ እንዲሰናበቱ መወሰናቸውን፣ውሳኔውም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27(1(ሐ)) እና በድርጅቱ የህብረት ስምምነት አባሪ ቁጥር 4 አንቀጽ 2 ቁጥር 2.3 መሰረት ተጠሪ የማጭበርበር ወይም የማታለል ድርጊት መፈፀማቸው በመረጋገጡ የተሰጠ በመሆኑ ሕጋዊ ስለሆነ ወደ ስራ ላመለሱ አይገባም ሲል ተከራክሯል።የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና የሰነድ ማሰረጃ መርምሮ የአመልካች መስሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ የኮሚቴውን ውሳኔ በደብዳቤ መሻራቸው ስለውሳኔ በሕጉ የተሰጠውን ትርጉም ያላገናዘበና ሕጋዊ ያለመሆኑን፣ተጠሪ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማህደራቸው ተያይዞ የተገኘባቸው መሆኑ ቢረጋገጥም የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ውሳኔ የድርጊቱን ክብደትና ቅለት ያላገናዘበ ነው በማለት እርምጃውን ሕገ ወጥ ነው ብሎ ተጠሪ ወደ ምድብ ስራቸው እንዲመለሱ ወይም በአማራጭ ካሳ ተከፍሐቸው ላሰናበቱ ይገባል በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤት የድርጅቱን የበላይ ኃላፊ ውሳኔ የውሳኔ አጻጻፍ ስርዓትን የተከተለ አይደለም በማለት የደረሰበት ድምዳሜ የበላይ ኃላፊው በዲሲፕላን ኮሜቴ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ሥልጣን ያላገናዘበ በመሆኑ የማይቀበለው መሆኑን ጠቅሶ ካለፈ በኋላ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ውጤት በተመለከተ ግን ተጠሪ የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ ከማህደራቸው አያይዘው ከመገኘታቸው ውጪ ያገኙት ጥቅም ስለመኖሩ አመልካች ያቀረበው ክርክርም ሆነ ማስረጃ ያለመኖሩን ገልፆ አጽንቶታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ተጠሪ የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ አቅርበው በማህደራቸው አያይዘው መገኘታቸው ተረጋግጦ እያለ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያገኙት ጥቅም የለም ሲል የአመልካችን እርምጃ ሕገወጥ ነው በማለት የወረዳው ፍርድ ቤት ተጠሪ ወደ ምድብ ስራቸው እንዲመለሱ ወይም ካሳ ተከፍሐቸው እንዲሰናበቱ ሲል የሰጠውን ውሳኔ ማፅናቱ ያለግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ በመታዘዙ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሑፍ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የአመልካች የስንብት እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ተጠሪ ወደ ምድብ ስራቸው እንዲመለሱ ወይም ካሳ ተከፍሐቸው እንዲሰናበቱ መወሰኑ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ድርጅት ተጠሪ ከማህደራቸው የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ አያይዘው የተገኙ መሆኑን ተጠሪን ከስራ አግዷቸው በተገቢው መንገድ አጣርቶ ያረጋገጠው ጉዳይ መሆኑን፣የዲሲፕላኑን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የድርጅቱ ኮሚቴም ጉዳዩን አጣርቶ ተጠሪን የአንድ ወር ደመወዝ ቅጣት፣የአንድ አመት የደረጃ እድገትና የዝወውር ቅጣት አሳልፎ ተጠሪው ወደ ምድብ ስራቸው እንዲመለሱ ሲል የሰጠው ውሳኔ በድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ውድቅ ተደርጎ አመልካች ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉን፣ተጠሪ ከአመልካች ጋር የመሰረቱት የስራ ውል በሕግ አግባብ ላቋረጥ ችሐል በማለት አመልካች የሚከራከረው ተጠሪ የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ በማህደራቸው አይይዘው የማጭበርበር ወይም የማታለል ድርጊት ለመፈጸም የሞከሩ መሆኑ በሚገባ በማስረጃዎች ተረጋግጧል በማለት መሆኑን፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ለድርጊቱ ተጠያቂ ላሆኑ አይችሉም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው ተጠሪ በተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ ከማህደራቸው ከማያያዛቸው ውጪ በማስረጃው ያገኙት ጥቅም የለም በሚል ምክንያት መሆኑን ነው።
እንግዲህ ከላይ ከተገለፀው የፍርድ ቤቶች የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት መገንዘብ የሚቻለው ተጠሪ በግል ማህደራቸው የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ አያይዘው መገኘታቸው በሁሉም ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ ሁኖ በዚህ ማስረጃ ተጠሪ ጥቅም አግኝተዋል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ግን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግልጽ አንስቶ ተጠሪ ያገኙት ጥቅም የለም ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶ የአመልካችን እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ሲል የወሰነ መሆኑን ነው።ይሁን እንጂ የማታለል ወይም የማጭበርበር ተግባር በሙከራ ደረጃ መቅረቱ የድርጊቱን ወንጀል መሆን ቀሪ የማያደርገው ሲሆን ጥቅም ማግኘት ወይም በልላው ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ ተግባሩ ከስራ ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት የግድ መሟላት ያለባቸው ፍሬ ነገሮች መሆናቸውን የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27(1(ሐ)) ድንጋጌ ይዘት አያሳይም።በመሆኑም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ በተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ ያገኙት ጥቅም ስለመኖሩ አልተረጋገጠም የሚለውን ምክንያት የያዘው ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈፃሚነት ያለው ሕግ በመመዘኛነት ያላስቀመጠው ነጥብ በመሆኑ ሕጋዊ አይደለም።አመልካች ለጉዳዩ ተፈጻሚነት አለው በማለት የሚጠቅሰው የድርጅቱ የሕብረት ስምምነት ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27(1(ሐ)) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ለተጠሪ የተሻለ ጥበቃ የሚያደርግ መሆኑም አልተረጋገጠም።ይልቁንም የህብረት ስምምነቱ አባሪ ቁጥር 4 አንቀጽ ቁጥር 2.3 ስር አንድ ሰራተኛ በስራ ላይ የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የማታለል ወይም የማጭበርበር ተግባር ፈጽሞ ሲገኝ የማይገባውን ጥቅም እንዲመልስ ተደርጎ እንዲሰናበት እንደሚደረግ እንጂ የማታለል ወይም የማጭበርበር ተግባር ጥቅም ካላስገኘ ስንብት እንደማይከናወን በግልጽ ያለማስቀመጡን ከክርክሩ ሂደት የተረዳን ሲሆን ተጠሪም በዚህ ረገድ ያቀረቡት ማስተባበያ ክርክርም ሆነ ማስረጃ የለም።ማናቸውም ሰራተኛ የማጭበርበር ወይም የማታለል ሙከራ መፈፀሙ ከተረጋገጠ ድርጊቱ ሕገ ወጥ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 27(1(ሐ)) ስር ከተመለከተው ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ሲሆን በአንቀጽ 27(1(ሐ)) ስር የተመለከቱትን ሕገ ወጥ ድርጊቶችን መፈፀም ደግሞ የስራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ስለመሆኑ በግልጽ ተመልክቷል።በመሆኑም ተጠሪ የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ በማህደራቸው አያይዘው መገኘታቸው በበታች ፍርድ ቤቶች በተደረገው የፍሬ ነገር ማጣራትና የማስረጃ ምዘና የተረጋገጠ ሁኖ እያለ በዚሁ በሕጉ ያልተመለከተውን መመዘኛ፤ በተሳሳተ ማስረጃ ተጠሪ ያገኙት ጥቅም የለም ተብሎ የአመልካች እርምጃ ሕገ ወጥ መባሉ በሕጋዊ ምክንያት ያልተደገፈ መሆኑን ተገንዝበናል።ስለሆነም ተጠሪ ከስራ የተሰናበቱት በአዋጁ አንቀፅ 27(1(ሐ)) ድንጋጌ መሰረት በመሆኑ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ላባል የሚችልበት አግባብ የለም።በዚህም ምክንያት የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27(1(ሐ)) ድንጋጌን የጣሰ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘን ተከታዩን ወስነናል።
ውሣኔ
በመሃል ሜዳ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/7 መስከረም 03 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በሰሜን ሸዋ መስተዳድር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/5 ህዳር 20 ቀን 2006 ዓ/ም ምክንያቱ በከፊል ተለውጦ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሸሯል።
አመልካች ተጠሪን ያሰናበተው በሕጉ አግባብ ስለሆነ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ብለናል።
ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.