No summary available.
የሰ/መ/ ሚያዝያ 06 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር-ሰናይት ፋሲካ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ መርዓዊ መስፍን መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የአሰሪ እና ሰራተኛ ሆኖ በአሁን የሰበር ተጠሪ ከሳሽነት የተጀመረው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ነበር። ክሱም፡- በተከሳሽ አክሲዮን ማህበር ከህዳር 8 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ተቀጥሬ እያገለገልኩ ሳለሁ ተከሳሽ ሚያዚያ 13 ቀን 2004 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ የህመም ዕረፍት ሳይሰጥህ ተሰጥቶኛል በሚል ለ10 ተከታታይ ቀናት ከሥራ ቀርተሃል በሚል ከሥራ አግዶኝ ለ32 ቀናት ያህል ከቆየ በኋላ ከሥራ ማሰናበቱን ስላስታወቀኝ ወደ ሥራ እንዲመልስ ካልሆነም በስሜ የተጠራቀመውን የጉድለት መጠባበቂያ ገንዘብ እና በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍል ይወሰንልኝ ብለዋል።
ተከሳሽ በበኩሉ በሰጠው መልስ፡- ከሳሽ የህመም ፈቃድ የተሰጣቸው ስለመሆኑ ማስረጃ ቢያቀርቡም ማስረጃውን ሰጥቷል የተባለው የሕክምና ተቋም ለከሳሽ የህመም ፈቃድ ያልተሰጣቸው መሆኑን የገልጸ ሲሆን፤ ከዚሁ ማስረጃ ውጪ ለ15 ቀናትም ከሥራ ለቀረቡት አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ባለማቅረባቸው በህጋዊ መንገድ ከሥራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፤ ወደ ሥራ ለመመለስ ያቀረቡት ጥያቄም ቢሆን ተቀባይነት ላያገኝ አይገባም። በአማራጭ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈላቸው የጠየቁትን በተመለከተም፡- ስንብቱ ህጋዊ በመሆኑ የስንብትክፍያ፣የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣እና ካሳ ላከፈላቸው አይገባም፤የዓመት ፈቃዳቸውንም ተጠቅመው ስለጨረሱ በገንዘብ ተለውጦ የሚከፈላቸው የለም፣የፕሮቪደንት ፈንድም የአገልግሎት ዘመናቸው ከ5 ዓመት በታች በመሆኑ ላከፈላቸው የማይገባ ከመሆኑም ልላ ከሳሽ ያለባቸውን ዕዳ የማይሸፍን በመሆኑ የሚከፈል ገንዘብ አይኖርም፤የጉድለት ማሟያ ገንዘብም ቢሆን ለግል ጥቅም የሚከፈል ገንዘብ ካለመሆኑም በላይ ቀደም ሲል ከሚሰሩበት ከገንዘብ ቤት ክፍል ወጥተው በልላ ክፍል እየሰሩ ከሥራ የተሰናበቱ ስለሆነ ገንዘቡን የመጠየቅ መብት የላቸውም ሲል ተከራክሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም በሰጠው ፍርድ፡- ከሳሽ ከሥራ የቀሩት የህመም ፈቃድ ሳይኖራቸው መሆኑ ስለተረጋገጠ እና ከሥራ ለቀሩበትም በቂ ምክንያት ባለማቅረባቸው ስንብቱ ህጋዊ ነው ሲል ወስኗል። ከሳሽ ከጠየቋቸው ክፍያዎች ውስጥም፡- ተከሳሽ የሥራ ውሉን ያቋረጠው ለከሳሽ ማስጠንቀቂያ ላያሰጥ በሚችል ምክንያት ባለመሆኑ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ላከፈላቸው አይገባም፤የዓመት ፈቃድ ወደ ገንዘብ ተለውጦ እንዲከፈላቸው የጠየቁትም ቢሆን ያልወሰዱትን የዓመት ፈቃድ በግልጽ ለይተው ባለመጠየቃቸው ተቀባይነት የለውም ሲል ውድቅ ያደረገባቸው ሲሆን የጉድለት ማሟያ ገንዘብ ብር 2,141 በተመለከተም፡- ገንዘቡ ከሒሳብ ሥራ ጋር በተገናኘ ለሚከሰት ጉድለት የሚውል ሆኖ ሳለ ተከሳሽ ከከሳሽ የሚፈለግባቸው ዕዳዎች ናቸው በማለት የጠቀሳቸው ከዓመት ፈቃድ እና ከትምህርት ወጪ ጋር የተያያዙ ዕዳዎች ለጉድለት ማሟያ ከሚጠራቀም ገንዘብ ዓላማ አንጻር ዕዳዎች ናቸው ተብለው ስለማይወሰዱ እና ከሳሽም ከሒሳብ ወይም ከገንዘብ ሥራ ጋር በተያያዘ ያጎደሉት ገንዘብ ስለመኖሩ ተከሳሽ ባለማስረዳቱ ይህንኑ የጉድለት ሟሟያ ገንዘብ ለከሳሽ ላከፍል ይገደዳል ብሐል። የፕሮቪደንት ፈንድ ክፍያን በተመለከተም ደግሞ ከሳሽ ልዩ ልዩ ዕዳዎች አለባቸው በሚል ተከሳሽ የፕሮቪደንት ፈንዱን መክፈል እንደማይገባው ቢከራከርም ከሳሽ ዕዳ ካለባቸው ክስ አቅርቦ ከመጠየቅ ውጪ ይህንኑ ገንዘብ በማቻቻያነት ላይዝ አይገባም ሲል ወስኗል። ከሳሽ የሥራ ውል በህገ ወጥ መንገድ ተቋርጧል በማለት ተከሳሽ እንዲከፍሐቸው የጠየቋቸውን ልሎች ክፍያዎች ግን ስንብቱ የተደረገው በህጋዊ መንገድ ስለሆነ ተቀባይነት የላቸውም ሲል ውድቅ አድርጓል።
ተከሳሽም በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍርድ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ይግባኙን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/337 መሰረት በመዝጋት በማሰናበቱ የሰበር አቤቱታውን ለዚህ ችሎት አቅርቧል።
አመልካችም በሰበር አቤቱታው በዋናነት ያቀረበው ቅሬታ ነጥብ፡- ተጠሪው ያገለገሉት ከ5 ዓመት በታች በመሆኑ ያላቸው የፕሮቪደንት ፈንድ ራሳቸው ያጠራቀሙት ብር 4,828.03 ሲሆን ከአመልካች ባንክ የተበደሩት ገንዘብ፣ባንኩ በስማቸው በቅድሚያ የከፈለላቸው የዓባይ ግድብ ገንዘብ፣ መወሰድ ከሚገባቸው በላይ የወሰዱት ዓመት ፈቃድ በጥሬ ገንዘብ ተመላሽ መሆን ያለበት ፣ለትምህርት የተከፈለላቸው ገንዘብ በድምሩ ብር 12,397.54 እየተፈለገባቸው ሳለ እና ተጠሪውም አለባቸው ስለተባሉት ዕዳዎች መኖር እና አለመኖር በተመለከተ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ባላቀረቡበት እንዲሁም ስለዕዳዎቹ በመካከላችን መካካድ በልለበት ሁኔታ የሥር ፍርድ ቤቶች በራሳቸው ጊዜ አንስተው የፕሮቪደንት ፈንድ ለዕዳው በማቻቻያነት ላያዝ አይገባም ያሉት እና የጉድለት መጠባበቂያ ገንዘብም ለተጠሪው እንዲከፈላቸው የወሰኑት ተቀባይነት የለውም የሚል ነው።
ተጠሪው ለሰበር አቤቱታው የበኩላቸውን መልስ እንዲሰጡበት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ቢደረግላቸውም ባለማቅረባቸው መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- የጉድለት ሟሟያውን ገንዘብ አመልካች ለተጠሪው እንዲከፈላቸው የሥር ፍርድ ቤቶች የወሰኑት የሚነቀፍበት ምክንያት አለው? ወይስ የለውም?
ፍርድ ቤቶቹ ከተጠሪው ላይ የሚፈለግባቸው ዕዳ ካለ አመልካች ክስ አቅርቦ ከሚያስወስን በስተቀር በተጠሪው ስም የተጠራቀመውን የፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘብ አመልካች በራሱ ውሳኔ ለዕዳው ማቻቻያነት ላያደርገው አይችልም በሚል የወሰኑት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚሉትን ጭብጦች ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
የመጀመሪያውን ጭብጥ በተመለከተ፡- አመልካች የጉድለት ማሟያ ገንዘብ ስለሚከፈልበት ሁኔታ ሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ/ም ለፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በጻፈው ማብራሪያ በባንኩ የሰራተኞች ጥቅማ ጥቅም መመሪያ መሰረት ለጉድለት ማሟያተብሎ ለገንዘብ ከፋይና ገንዘብ ተቀባይ ሰራተኛ በሰራተኛው ስም የሚጠራቀም ገንዘብ መኖሩን፣ ገንዘቡም ለሰራተኛው የሚከፈለው ሰራተኛው ከቦታው ተነስቶ በስሙ ምንም ዓይነት ዕዳ አለመኖሩ ከተረጋገጠ ከ 6 ወር በኋላ እንደሆነ በመግለጹ ፍርድ ቤቱም ይህንኑ ማብራሪያ እና በግራ ቀኙ በኩል በዚሁ ነጥብ ላይ የተደረጉትን ክርክሮች በመመርመር አመልካች በተጠሪው ላይ ይፈለግባቸዋል ሲል ከዘረዘራቸው የትምህርት፣ያለአግባብ ወስደዋል የተባሉት የአመት ፈቃድ በገንዘብ ተለውጦ ላከፍሉ ይገባል የሚለውን እና ለዓባይ ግድብ በተጠሪው ስም የተከፈለና ተጠሪው እንዲተኩ የሚፈለግባቸውን ዕዳዎች የጉድለት ማሟያ ገንዘብ ከሚጠራቀምበት ዓላማ አንጻር በመመርመር የተጠቀሱት ዕዳዎች ተጠሪው ከሚሰሩበት የገንዘብ ከፋይ ወይም ገንዘብ ተቀባይ ሥራ ጋር ተያይዞ ከሚመጣው ዕዳ የሚለይ በመሆኑ እንደጉድለት ማሟያ ዕዳ ተደርጎ አይወሰድም፣ እንዲሁም አመልካች ከሂሳብ ወይም ከገንዘብ ሥራ ጋር በተያያዘ ተጠሪው የገንዘብ ጉድለት ዕዳ ያለባቸው ስለመሆኑ አላስረዳም በሚል ፍርድ ቤቶቹ የደረሱበት ድምዳሜ የግራ ቀኙ ወገኖች ካደረጉት ክርክር እና አመልካች ለሥር የመ/ደ/ ፍርድ ቤት ከላከው ማብራሪያ ላይ የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮች መሰረት ያደረገ በመሆኑ ፍርድ ቤቶቹ በዚህ ረገድ የሰጡት ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
ሁለተኛውን ጭብጥ በተመለከተ፡-ተጠሪው የተለያዩ ዕዳዎች ያሉባቸው ስለሆነ የተጠራቀመላቸውን የፕሮቪደንት ፈንድ የመክፈል ግድታ የለብኝም ሲል አመልካች መከራከሩን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍርድ ከሚያመላክት በስተቀር አመልካች ከተጠሪው የሚፈለጉ ዕዳዎች ናቸው በሚል የዘረዘሯቸውን በመካድ ዕዳ የለብኝም ሲሉ ያቀረቡት ክርክር ስለመኖሩ የሚያሳይ አይደለም። ሰራተኛው ያለበትን ዕዳ እስካልካደ ድረስም ደግሞ አሰሪው በሰራተኛው ስም የተጠራቀመውን የፕሮቪደንት ፈንድ ለዕዳው መክፈያ እንዲሆን የማድረግ መብት ያለው ስለመሆኑ ይህ ችሎት በሰበር መ/ቁ/71507 በቀን 10/07/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት ከሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም መገንዘብ የሚቻል ነው። በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች ተጠሪው ዕዳዎቹን በግልጽ ክደው ባልተከራከሩበት ሁኔታ አመልካች በተጠሪው ላይ ክስ አቅርቦ ዕዳዎቹን እንዲከፈሉ ከሚያስወስን በስተቀር የፕሮቪደንት ፈንዱን ለዕዳው ማቻቻያ ላያደረግ አይችልም ሲሉ የሰጡት የፍርድ ክፍል መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/06040 በቀን 01/09/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ፍርድ እና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/135717 በቀን 03/03/2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 348(1) መሰረት አሻሽለናል።
ፍርድ ቤቶቹ አመልካች በተጠሪው ላይ ክስ አቅርቦ ከሚያስወስን በስተቀር በተጠሪ ስም የተጠራቀመውን ፕሮቪደንት ፈንድ በተጠሪው ላይ ለሚፈለግባቸው ዕዳ ማቻቻያ ላያደርገው አይችልም ሲሉ የሰጡትን የውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 348(1) መሰረት ሽረናል።
የሥራ ውሉ የተቋረጠው በህጋዊ መንገድ ነው ሲሉ ፍርድ ቤቶቹ ከፕሮቪደንት ፈንድ ውጪ ያሉትን ልሎች ክፍያዎችን በተመለከተ የሰጡትን የውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348 (1) መሰረት አጽንተናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ አመልካች የራሱን ይቻል ብለናል።
No topics extracted.