No summary available.
የካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ዛምራ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /ጠበቃ ማሞ ካሳ ቀረቡ/ ተጠሪ፡- ሙሉጌታ አምባዬ /ጠበቃ አምዶም ታደለ ቀረቡ/ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በመቀል ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ ተከሳሽ በነበረው የአሁኑ አመልካች ላይ በ20/07/2005 ዓ.ም ባቀረቡት ክስ ነው። የክሳቸውም ይዘት ባጭሩ ከሳሽ ከ18/12/2003 ዓ.ም ጀምሮ በተከሳሽ ድርጅት ብር 4,000 የወር ደመወዝ እየተከፈላቸው በጄኔራል ፎርማንነት ተቀጥረው እስከ 15/07/2005 ዓ.ም ድረስ ሲሰሩ እንደነበረ ተከሳሽ ድርጅት በ11/07/2005 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ስራው አልቋል በሚል ምክንያት ከ15/07/2005 ዓ.ም ጀምሮ የስራ ውላቸው መቋረጡን እንደገለፀላቸው ይሁን እንጂ ተከሳሽ ድርጅት በተለያዩ ቦታዎች ኮንትራት የያዛቸው ስራዎች እንዳሉት ሲሰሩበት የነበረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ህንፃም እንዳልተጠናቀቀ፤ ርክክብም እንዳልተፈፀመ እና ስራው ባለማለቁ ከ70 በላይ ሰራተኞች በስራ ላይ እንደሚገኙ የተገለፀበት ሆኖ ስንብቱ ህገወጥ ነው ተብሎ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት ህገ ወጥ የስራ ስንብት የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች እና የበዓላት ቀናት ክፍያ ተከሳሹ እንዲፈፅምላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ሲሆን ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ ከሳሽ ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረገው የተቀጠሩበት የፕሮጀክት ስራ እየተገባደደና ለርክክብ እየተዘጋጀ በመሆኑ ምክንያት በአዋጁ አንቀፅ 30(1) እና (2) መሰረት በአግባቡ መሆኑን እና ሲሰናበቱ ተገቢ ክፍያዎች የተፈፀሙላቸው መሆኑን ገልፆ ክሱ ውድቅ ላደረግ ይገባል በማለት ተከራክሯል።
ፍ/ቤቱም ክሱንና የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኋላ አጠቃላይ ክርክሩን መርምሮ ተከሳሽ ሲሰራው ከነበረው የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተዛውሬ ወደ መቐል ፕሮጀክት የመጣሁ ስለሆነ ቋሚ ሰራተኛ ነኝ በማለት ከሳሽ የተከራከሩ ቢሆንም ከጎንደር ፕሮጀክት ወደ መቐል ፕሮጀክት ተዛውረው እንዲመጡ የተደረገው የጎንደር ፕሮጀክት አልቆ ወደ መቐል ፕሮጀክት በመዛወራቸው ሳይሆን ስራ በማበላሸታቸው ጥፋቱ እንዳይደገም በማስጠንቀቂያ በመሆኑ ምክንያት ቋሚ ሰራተኛ ነኝ በማለት ከሳሽ ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት እንደልለው፣ ከሳሽ የተቀጠሩት በአዋጁ አንቀፅ 10 መሰረት ለተወሰነ ስራ እንደሆነ ፣የተሰናበቱትም የፕሮጀክቱ የስራ መጠን ወደ መጠናቀቅ በመቃረቡና በከሳሽ ሲሰራ የነበረው ስራ በማለቁ መሆኑ በግራ ቀኙ ምስክሮች የተገለጸ በመሆኑ ምክንያት ስንብቱ ህጋዊ መሆኑን ገልፆ ክሱን ውድቅ በማድረግ የ18 ቀናት የበዓላት ቀናት ክፍያ ብር 4,799.99 ከ10% የጠበቃ አበል ጋር ተከሳሽ ለከሳሽ እንዲከፍል ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በውሳኔው ቅር በመሰኘት በስር ከሳሽ ጠያቂነት በቀረበለት ይግባኝ መነሻ የመቐል ከተማ ከ/ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የአዋጁ አንቀፅ 30 ተፈፃሚነት የሚኖረው አናጢዎችን ግንበኞችን ለሳኞችን እና የመሳሰሉትን የጉልበት ሰራተኞች በተመለከተ እንጂ ከሳሹ በነበረበት የጄኔራል ፎርማን የስራ መደብ ላይ የተመደቡትን ዓይነት ሰራተኞች በተመለከተ ጭምር አለመሆኑን እና ተከሳሽ ድርጅት ከሳሽን ከጎንደር ፕሮጀክት ወደ መቐል ፕሮጀክት አዛውሮ እንዳሰራው ሁሉ ወደልላኛው ፕሮጀክት አዛውሮ ማሰራት የማይችልበት ምክንያትመኖሩን እስካላስረዳ ድረስ ስንብቱ ህጋዊ ነው ላባል የሚችልበት አግባብ አለመኖሩን ገልጾ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት በስር ፍርድ ቤት ተሰጥቶ የነበረውን ውሳኔ ሽሮ ስንብቱ ህገ ወጥ በመሆኑ ተከሳሽ ድርጅት ህገ ወጥ ስንብት የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች ለከሳሽ እንዲፈጽም ውሳኔ ሰጥቷል።
አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት በማጣቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካች አስቀድሞ የጐንደር ዩንቨርሲቲ ህንፃ ኘሮጀክት እስከሚጠናቀቅ ብቻ ተቀጥሮ ሲሰራ ጥፋት ፈጽሟል ተብሎ ወደ ትግራይ ክልል ምክር ቤት ሕንፃ ኘሮጀክት ተዛውሮ እየሰራ እያለ መሰናበቱ ሕገወጥ ነው በማለት ላቀረበው ክስ ስንብቱ የተደረገው የሕንፃው ስራ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ነው በማለት አመልካች ያቀረበው ክርክር በስር ፍ/ቤቶች ሳይታይ ታልፎ አመልካች ዝውውር መፈፀሙ ተጠሪን ላልተወሰነ ጊዜ እንደቀጠረው ያስቆጥራል ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል። የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ውሳኔው መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን ለጉዳዩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል።
በዚህም መሰረት ቀደም ሲል እንደተገለፀው ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍ/ቤት የግራ ቀኙ ክርክር እና ማስረጃ ከሰማ በኋላ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ በመድረስ ውሳኔ ለመስጠት የቻለው ከሳሽ የተቀጠሩት በአዋጁ አንቀጽ 10 መሰረት ለተወሰነ ስራ መሆኑን የተሰናበቱትም የኘሮጀክቱ የስራ መጠን ወደመጠናቀቅ በመቃረቡና በከሳሽ ሲሰራ የነበረው ስራ በማለቁ መሆኑን በማስረጃ በማረጋገጥ መሆኑን እና የኘሮጀክቱ የስራ መጠን ወደመጠናቀቅ መቃረቡና በከሳሽ ሲሰራ የነበረው ስራ ማለቁ ደግሞ በከሳሽ ምስክሮች ጭምር የተገለፀ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።
ይ/ሰሚው የመቐል ከተማ ከ/ፍ/ቤት ይህንን የወረዳ ፍ/ቤት ሽሮ ስንብቱ ሕገወጥ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው የአዋጁ አንቀጽ 30 ተፈፃሚነት የሚኖረው የጉልበት ስራተኞችን በተመለከተ እንጂ ከሳሹ በነበረበት የጀኔራል ፎርማን የስራ መደብ ላይ የተመደቡትን ዓይነት ሰራተኞችን በተመለከተ ጭምር አለመሆኑን እና ተከሳሽ ድርጀት ከሳሽን ከጐንደር ኘሮጀክት ወደ መቀል ኘሮጀክት አዛውሮ እንዳሰራው ሁሉ ወደልላኛው ኘሮጀክትም አዛውሮ ማሰራት የማይችልበት ምክንያት መኖሩን እስካላስረዳ ድረስ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ላባል የሚችልበት አግባብ የለም በማለት ነው። በመሰረቱ አመልካች ተጠሪን ከጎንደር ወደ መቐል ፕሮጀክት ያዛወረው የጎንደር ፕሮጀክት በማለቁ ሳይሆን ተጠሪ ይሰሩበት በነበረው የጎንደር ፕሮጀክት ላይ የስራ አፈጻጸም ግድፈት በማሳየታቸው ከመሆኑ ውጪ የጎንደር ፕሮጀክት በማለቁ ምክንያት ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ አልተረጋገጠም። ተጠሪ ወደ መቀል ፕሮጀክት እንዲዛወሩ የተደረገው ይሰሩበት በነበረው የጎንደር ፕሮጀክት ላይ የስራ አፈጻጸም ግድፈት በማሳየታቸው ስለመሆኑ የወረዳው ፍ/ቤት የዝውውር ደብዳቤውን ጠቅሶ በውሳኔው ላይ በግልጽ አስፍሯል።
ይ/ሰሚው ፍ/ቤት በበኩሉ ይህንኑ ደብዳቤ በመጥቀስ አመልካች ተጠሪን ከጎንደር ወደ መቀል ፕሮጀክት አዛውሮ ሲያሰራ ነበር ከማለት በስተቀር የዝውውሩ ምክንያት በወረዳው ፍ/ቤት ውሳኔ ላይ የተገለጸው ስላለመሆኑ የገለጸው ነገር የለም። ይ/ሰሚው ፍ/ቤት የስር ፍ/ቤት ውሳኔን ለመሻር መነሻ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ የዝውውሩ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ዝውውሩን አስመልክቶ በወረዳው ፍ/ቤት ውሳኔ ላይ የተገለጸው ፍሬ ነገር ተቀባይነት የሚያጣበትን ምክንያት በውሳኔው ላይ በግልጽ ማስፈር ይጠበቅበታል። በመሰረቱ በተቀጠረበት ፕሮጀክት ላይ የስራ አፈጻጸም ግድፈት የፈጸመን ሰራተኛ አሰሪው ልላ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ወደ ልላ ፕሮጀክት ማዛወሩ ሰራተኛውን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ ተግባር አይደለም። በመሆኑም ይ/ሰሚው ፍ/ቤት የዝውውሩን ምክንያት ሳይጠቅስ ተከሳሽ ድርጅት ከሳሽን ከጎንደር ፕሮጀክት ወደ መቀል ፕሮጀክት አዛውሮ የማሰራቱን ሁኔታ ብቻ ነጥሎ ለውሳኔው ምክንያት ማድረጉ ተገቢውን የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት የተከተለ ሆኖ አልተገኘም።
በልላ በኩል የአዋጁ አንቀጽ 30 ተፈጻሚነት የሚኖረው የጉልበት ሰራተኞችን በተመለከተ እንጂ ከሳሹ በነበሩበት የጀኔራል ፎርማን የስራ መደብ ላይ የተመደቡትን ዓይነት ሰራተኞች በተመለከተ ጭምር አይደለም በማለት ይ/ሰሚው የደረሰበትን ድምዳሜ በተመለከተ በመሰረቱ የጀኔራል ፎርማን የስራ መደብ ከአመልካች ድርጅት አስተዳደራዊ ስራዎች ጋር የሚገናኝ ሳይሆን በቀጥታ በኮንስትራክሽን ወይም ከግንባታ ስራ ጋር የተያዘ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ተጠሪም ተሰማርተው የነበሩት በቢሮ ወይም በአስተዳደራዊ ስራዎች ላይ ሳይሆን በቀጥታ በፕሮጀክት ወይም በግንባታ ስራዎች ላይ ስለመሆኑ ያላስተባበሉት እና በክስ ማመልከቻቸውም ላይ የገለጹት ጉዳይ ነው።
በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 30 በተመለከተው መሰረት የሚከናወን ቅነሣ የጉልበት ሰራተኞችን እንጂ እንደአሁኑ ተጠሪ ዓይነት በጄነራል ፎርማን የስራ መደብ ላይ የተቀጠሩትን ሰራተኞች የሚመለከት አይደለም በማለት ይ/ሰሚው ፍ/ቤት የደረሰበት ድምዳሜ የአዋጁን ድንጋጌ ይዘትም ሆነ በክርክሩ የተረጋገጠውን ፍሬ ነገር መሰረት ያደረገ ሆኖ አልተገኘም። አመልካች የተሰማራበት የኮንስትራክሽን ስራ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ አንዱ ፕሮጀክት ሲያልቅ ተጠሪን ወደ ልላኛው ፕሮጀክት አዛውሮ ላያሰራው ይገባል በማለት በይ/ሰሚው ፍ/ቤት የተያዘውን አቋም በተመለከተ እንደተባለው አመልካች የተሰማራው በኮንስትራክሽን ስራ ላይ መሆኑ እና ስራውም ቀጣይነት ያለው መሆኑ የሚታወቅ እና በአመልካችም ያልተስተባበለ ነው። ይሁን እንጂ አመልካች እንደማንኛውም የኮንስትራክሽን ድርጅት ስራውን የሚያከናውነው በፕሮጀክቶች በመከፋፈል ነው። ፕሮጀክቶቹን በውድድር የሚያገኛቸው እንጂ እራሱ ፈጥሮ የሚያከናውናቸው አለመሆኑም የሚታወቅ ነው። ይህም አመልካቹ የሚያከናውናቸውን ፕሮጀክቶቹ የሚጀምርበትን ጊዜ የሚወስነው በራሱ ሣይሆን በሚገባበት የውል ግድታ መሰረት መሆኑን እና በተመሣሣይ ጊዜ ከአንድ በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶች ላኖሩት የሚችሉ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል ነው። በመሆኑም ለአንድ ፕሮጀክት የተቀጠረ ሰራተኛን ፕሮጀክቱ ሲያልቅ ወደ ልላ ፕሮጀክት አዛውሮ ለማሰራት በኮንስትራክሽን የሰራ ዘርፍ በተሰማራ አሰሪ ላይ በሕግ የተጣለ ግድታ አለመኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ማዛወር ቢኖርበት እንኳ ማዛወር የሚችለው በልላኛው ፕሮጀክት ውስጥ በተመሣሣይ የሰራ መደብ ክፍት ቦታ በተገኘ ጊዜ ነው። በተያዘው ጉዳይ ይ/ሰሚው ፍ/ቤት አመልካች ተጠሪን ወደ ልላ ፕሮጀክት አዛውሮ ላያሰራው ይችል ነበር ከማለት በስተቀር በልላኛው ፕሮጀክት የተጠሪ የሰራ መደብ ክፍት ስለመሆኑ እንኳ አላረጋገጠም። በመሆኑም ተከሣሽ ድርጅት ከሣሽን ከጐንደር ፕሮጀክት ወደ መቐል ፕሮጀክት አዛውሮ እንዳሰራው ሁሉ ወደ ልላኛው ፕሮጀክት አዛውሮ ማሰራት የማይችልበት ምክንያት መኖርን አላሰረዳም በማለት ይ/ሰሚው ፍ/ቤት የደረሰበት ድምዳሜ በህግም ሆነ በፍሬ ነገር ረገድ ሕጋዊ መሰረት ያለው ሆኖ አልተገኘም። ሲጠቃለል ይ/ሰሚው የመቀል ከተማ ከ/ፍ/ቤት በስር ፍ/ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ለመሻር የሚያስችል በቂ የህግም ሆነ የፍሬ ነገር ምክንያት ሳይኖር በማስረጃ በተረጋገጠው መሰረት የህግ አግባብ የተሰጠውን ውሳኔ በመሻር ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
በመቀል ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 09635 በ06/09/2005 ዓ.ም የተሰጠውን ውሳኔ ሽሮ ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት የመቀል ከተማ ከ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 13289 በ27/12/205 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሯል።
ስንብቱ ሕጋዊ ነው ሲል ክሱን ውድቅ በማድረግ የ18 ቀናት የበዓላት ቀናት ክፍያ ብር 4,799.99 (አራት ሺ ሰባት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ከ ዘጠና ዘጠኝ ሳንቲም) ከ10% የጠበቃ አበል ጋር ተከሻሽ ለከሳሽ እንዲከፍል የመቀል ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ቁ.
ዐ9635 በ06/09/2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 348 (1)መሰረት ፀንቷል።
ይፃፍ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.