No summary available.
ጥር 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ በኃይሉ ደቦጭ አንበሴ……… ጠበቃ ገ/እግዚአብሄር ኪዳኔ ቀረቡ ተጠሪ፡- ኢትዮጵያ ገብራት ትራንስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተወካይ አቶ ግርማ ሙለታ ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ አመልካች ተከሳሽ በነበረው የአሁኑ ተጠሪ ላይ በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ ነው። የክሱም ይዘት ባጭሩ ከሳሽ ከ20/05/2003 ዓ.ም.ጀምሮ በተከሳሽ ድርጅት በወር በብር 1,400 ደመወዝ ተቀጥረው በመስራት ላይ እያሉ ተከሳሽ ድርጅት ከ13/02/2004 ዓ.ም. ጀምሮ ካለክፍያ እና ካለስራ እንዳስቀመጣቸው የሚገልጽ ሆኖተከሳሽ ድርጅት የሰሩበትን የ4 ወር ደመወዝ እና ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ የስራ ስምሪት እንዲሰጣቸው፤ ይህ የሚታለፍ ከሆነ ደግሞ የ4ወር ውዝፍ ደመወዝ፣የስራ ስንብት ክፍያ፣የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣የዓመት ዕረፍት ክፍያ እና ክፍያ ለዘገየበት ተገቢውን ክፍያ እንዲፈጽም ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ሲሆን ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ ከሳሽን ደመወዝም ሆነ ስራ እንዳልከለከላቸው፣ከሳሽ የነሐሴ እና የመስከረም ደመወዝ ሳይቀበሉ የቀሩት ከጂቡቲ ዕቃ ጭነው ወደ ክልል ከተሞች ስለሚያዘዋውሩ በዚህ ሳቢያ በተፈጠረው ክፍተት እና በኋላም የሚፈለግባቸውን የ180 ላትር ነዳጅ ጉድለት ገቢ እንዲያደርጉ በ14/02/2004 ዓ.ም. በተጻፈ ሲጠየቁ ፈቃደኛ ስላልነበሩ እንደሆነ፣ከሳሽ የያዙት ተሽከርካሪ ችግር እንዳለበት በ12/11/2004 ዓ.ም.ባመለከቱት መሰረት ተሽከርካሪው ለጥገና ሲቆም ከሳሽ ጥገናውን መከታተል ሲገባቸው ትተው ወደ ቤታቸው እንደሄዱ፣ከሳሽ ከ14/02/2004 ዓ.ም. ጀምሮ በራሳቸው ምክንያት ከስራ የቀሩ ስለሆነ ላልሰሩት ስራ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት እንደልለው፣ተከሳሽ ድርጅት ከሳሽን ከስራ ባላሰናበተበት ሁኔታ የስንብት እና ተያያዥ ክፍያዎችን ለመክፈል እንደማይገደድ እና ከሳሽ የነሐሴ እና የመስከረም ወር ደመወዝ ተከፍሐቸው ከፈለጉ ስራ ላቀጥሉ እንደሚችሉ በመግለጽ መልስ ሰጥቷል።
ፍ/ቤቱም ክሱን ከሰማ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ምስክሮቻቸውን ይዘው እንዲቀርቡ በሰጠው ቀጠሮ ተከሳሽ በትዕዛዙ መሰረት ባለመፈጸሙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 199(1) መሰረት መብቱን በማለፍ በከሳሽ በኩል የቀረቡትን ምስክሮች ሰምቷል።ከዚህ በኋላ አጠቃላይ ክርክሩን መርምሮ ከሳሽ የስራ ውሉ ተቋርጦብኛል በማለት ያቀረቡት ክስ ባለመኖሩ የስራ ስንብት እና ተያያዥ ክፍያዎች እንዲፈጸሙላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ስነ ስርዓታዊ አግባብ እንደልለው፣ከሳሽ ጥቅምት 15 እና 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ወደ ድርጅቱ ግቢ እንዳይገቡ በድርጅቱ የጥበቃ ሰራተኞች መከልከላቸውን በምስክሮች ያስረዱ ቢሆንም የጥበቃ ሰራተኞቹ ክልከላውን የፈጸሙት ማን በሚባል ኃላፊ ትዕዛዝ እንደሆነ ከሳሽ እንዳላስረዱ በዝርዝር ገልጾ ተከሳሽ ድርጅት የነሐሴ እና የመስከረም ወር እንዲሁም ከሳሽ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ባስረዱት መሰረት ከጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም.
ደመወዝ ውስጥ እስከ ማስጠንቀቂያው ቀን ማለትም እስከ ጥቅምት 21 ቀን ድረስ ያለውን ደመወዝ ከፍሎ ለከሳሽ ስራ እና የስራ ስምሪት እንዲሰጣቸው በማለት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የፍ/ከ/ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በማጽናቱ ነው። የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካች ወደስራ ገበታቸው እንዳይገቡ በተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች መከልከላቸው እና የስርፍ/ቤት የስራ ውሉ ያልተቋረጠ መሆኑን በማረጋገጥ ለከሳሽ የስራ ስምሪት እንዲሰጣቸው መወሰኑ በተረጋገጠበት፣ነገር ግን አሰሪው በተግባር የስራ ስምሪት ባልሰጠበት ሁኔታ አመልካች ስራቸውን ተገደው ካቆሙበት ጊዜ ጀምሮ የተቋረጠባቸው ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያቀረቡትን የመብት ጥያቄ የስር ፍ/ቤቶች ውድቅ የማድረጋቸውን አግባብነት ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 54(2) አንፃር ተጠሪ ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ተደርጎ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለጉዳዩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል።
በዚህም መሰረት በፍትሐብሕር ክርክር አንድ ግድታ እንዲፈጸምለት የሚጠይቅ ሰው የግድታውን መኖር ማስረዳት እንደሚጠበቅበት እና በአንፃሩም ግድታ ፍርስ ነው ወይም ተለውጧል የሚለው ወገንም ይህንኑ የማስረዳት ግድታ እንዳለበት በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2001(1) እና(2) ድንጋጌዎች የተመለከተ ሲሆን ከዚህ ድንጋጌ አንፃር አመልካች በስራ ገበታቸው ላይ ለመገኘት ያልቻሉት ወደ ተጠሪ ግቢ ማለትም ወደ ስራ ቦታቸው እንዳይገቡ ጥቅምት 15 እና 16 ቀን 2004 ዓ.ም. በተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች ስለተከለከሉ መሆኑን በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት አቅርበው ባሰሟቸው ምስክሮች ማስረዳታቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል። በዚህ ረገድ ከአመልካች ለቀረበው የክርክር ነጥብ ተጠሪ በሰበር መልሱ ያቀረበው የማስተባበያ ክርክር የለም።
አመልካች ከ14/02/2004 ዓ.ምጀምሮ ከስራ የቀሩት በራሳቸው ምክንያት በመሆኑ ላልሰሩበት ጊዜ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ላኖረው አይገባም ከማለት በስተቀር አመልካች ከ14/02/2004 ዓ.ም ጀምሮ ከስራ የቀሩት በርግጥም በራሳቸው ምክንያት ስለመሆኑ ተጠሪ ያቀረበው ማስረጃ አለመኖሩን እና ይልቁንም ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ በተሰጠው ቀጠሮ ባለመቅረቡ መብቱ የታለፈ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ የሚያመለክት በመሆኑ ተጠሪ በሕግ የተጣለበትን ክርክሩን በማስረጃ የማስረዳት ግድታ ተወጥቷል ለማለት የሚቻል አይደለም።
የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት አመልካች ወደ ተጠሪ ግቢ ማለትም ወደ ስራ ቦታቸው እንዳይገቡ ጥቅምት 15 እና 16 ቀን 2004 ዓ.ም በተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች እንደተከለከሉ ማስረዳታቸውን ተቀብሎ እያለ በተጠሪ ክልከላ ምክንያት በስራ ገበታቸው ላይ መገኘትና መስራት ላልቻሉባቸው ጊዜያት ያለው ደመወዝ ታስቦ እንዲከፈላቸው አመልካች ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ ውድቅ ያደረገው የተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች የክልከላውን ድርጊት የፈጸሙት ማን በሚባል የስራ ኃላፊ ትዕዛዝ እንደሆነ አመልካች አላስረዱም በማለት መሆኑን የውሳኔው ይዘት ያመለክታል።ይሁን እንጂ ክልከላውን የፈጸሙት የጥበቃ ሰራተኞች የተጠሪ ሰራተኞች መሆናቸው እስከተረጋገጠ ድረስ ስራቸውን የሚያከናውኑት ከአሰሪ በሚሰጣቸው ትዕዛዝ እንደሆነ የሚታመን በመሆኑ የክልከላ ድርጊቱን የፈጸሙት ከተጠሪ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት እንደሆነ ይገመታል።ትዕዛዙን የሰጣቸው የተጠሪ የስራ ኃላፊ የሚያውቁት ትዕዛዙን የሰጡት የስራ ኃላፊ እና የተቀበሉት የጥበቃ ሰራተኞች ከመሆናቸው ውጪ አመልካች የትዕዛዝ ሰጪውን የስራ ኃላፊ ማንነት ላያውቁ የሚችሉበት መንገድም ሆነ እንዲያስረዱ የሚገደዱበት የሕግ አግባብ የለም።
ወደ ስራ እንዳይገቡ በተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች መከልከላቸውን ማስረዳታቸው ብቻ በቂ ሲሆን ይህንን ማስረዳታቸው ደግሞ ቀደም ሲል እንደተገለጸው በስር ፍ/ቤቶችም ቢሆን ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ ነው።ተጠሪም ቢሆን የጥበቃ ሰራተኞቹ የክልከላ ተግባሩን የፈጸሙት ከተጠሪ የስራ ኃላፊዎች የተሰጣቸው ትዕዛዝ ሳይኖር ነው በሚል ያቀረበው ክርክር የለም። በመሆኑም የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት አመልካች ወደ ተጠሪ ግቢ እንዳይገቡ በተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች እንደተከለከሉ ማስረዳታቸውን ተቀብሎ እያለ ከዚሁ ድምዳሜው ጋር በሚቃረን ሁኔታ የተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች የክልከላውን ድርጊት የፈጸሙት ማን በሚባል የስራ ኃላፊ ትዕዛዝ እንደሆነ አመልካች አላስረዱም በማለት የሰጠው ውሳኔ ሕጋዊ መሰረት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
በመሰረቱ ደመወዝ የሚከፈለው ለተሰራ ስራ ብቻ እንደሆን በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 54(1) ስር በመርህ ደረጃ የተደነገገ ቢሆንም ሰራተኛው ለስራ ዝግጁ ሆኖ እያለ ለስራው የሚያስፈልገው መሣሪያ እና ጥሬ ዕቃ ሳይቀርብለት በመቅረቱ ወይም በሰራተኛው ጉድለት ባልሆነ ምክንያት ሳይሰራ ቢውልም ደመወዙን የማግኘት መብት እንደሚኖረው በአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ(2) ስር በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል።በተያዘው ጉዳይ አመልካች በስራ ገበታቸው ላይ ለመገኘት ያልቻሉት በተጠሪው ክልከላ ምክንያት እንጂ የራሳቸው በሆነ ጉድለት ምክንያት አለመሆኑ ተረጋግጧል።እንዲህ ከሆነ ደግሞ አመልካች የክልከላው ተግባር ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ በስር ፍ/ቤት ውሳኔ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በአዋጁ አንቀጽ 54(2) ድንጋጌ መሰረት ደመወዛቸውን እንዲያጡ ላደረግ የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም።
ሲጠቃለል አመልካች ወደ ስራ ቦታቸው እንዳይገቡ በተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች እንደተከለከሉ ማስረዳታቸውን ተቀብሎ እያለ የጥበቃ ሰራተኞቹ የክልከላውን ድርጊት የፈጸሙት ማን በሚባል የስራ ኃላፊ ትዕዛዝ እንደሆነ አመልካች አላስረዱም በማለትበክልከላው ምክንያት በስራ ገበታቸው ላይ መገኘትና መስራት ላልቻሉባቸው ጊዜያት ያለው ደመወዝ ታስቦ እንዲከፈላቸው አመልካች ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት የሰጠው እና በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የጸናው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
የተነበበው እና በፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 129978 በ18/10/2005 በውሳኔ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
ከላይ ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ አመልካች ወደ ስራ ቦታቸው እንዳይገቡ በተጠሪ የጥበቃ ሰራተኞች እንደተከለከሉ ማስረዳታቸው በስር ፍ/ቤቶች ተቀባይነት ያገኘ ሆኖ እያለ የጥበቃ ሰራተኞቹ የክልከላውን ድርጊት የፈጸሙት በየትኛው የስራ ኃላፊ ትዕዛዝ እንደሆነ አመልካች አላስረዱም በማለት በክልከላው ምክንያት በስራ ገበታቸው ላይ መገኘትና መስራት ላልቻሉባቸው ጊዜያት ያለው ደመወዝ ታስቦ እንዲከፈላቸው አመልካች ያቀረቡትን የዳኘነት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.348(1) መሰረት ተሽሯል።
አመልካች በስራ ገበታቸው ላይ ለመገኘት ያልቻሉት በተጠሪው ክልከላ ምክንያት እንጂ የራሳቸው በሆነ ጉድለት ምክንያት እንዳልሆነ የተረጋገጠ በመሆኑ ከጥቅምት 22 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ውሳኔ እስከተሰጠበት ጊዜ ማለትም እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ደመወዝ ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 54(2) መሰረት ለአመልካች የመክፈል ግድታ አለበት በማለት ወስነናል።
ከላይ በተ.ቁ. 2 ስር ከተገለጸው ውጪ ያለው የስር ፍ/ቤቶች የውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ፀንቷል።
ተጠሪ ለቀጣዩ የስራ ስምሪት እንዲሰጣቸው ይወሰን ዘንድ አመልካች በሰበር አቤቱታቸው ያቀረቡትን ጥያቄ በተመለከተ በስር ፍ/ቤቶች በተወሰነው መሰረት ከሚያስፈጽሙ በቀር በስራ ስምሪት ረገድ በዚህ ችሎት የሚሰጥ ውሳኔ አይኖርም።
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.