No summary available.
የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ደረሰ ወርቄ ቀረቡ፤
ተጠሪ፡- በርሕ ሐጎስ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ጠበቃ ነገሰ ጋሹ ቀረቡ፤
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ አመልካች ተከሳሽ በነበረው የአሁኑ ተጠሪ ላይ በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ ነው። የክሱም ይዘት ባጭሩ፡- ከሳሽ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ በቶንጎ-ቤጊ-ጊዳሚ የመንገድ ስራ ኘሮጀክት ከ10/02/2003 ዓ.ም ጀምሮ በክላኒካል ነርስ የስራ መደብ በወር ብር 2346.00 ደመወዝ ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበረ፣ ኘሮጀክቱ በመጠናቀቁ ተከሳሽ ድርጅት ልሎች ሰራተኞችን በሙሉ ወደ ልላ ቦታ ሲያዛውር ከሳሽን በባዶ ካምኘ ማስቀመጡ አግባብ እንዳልሆነ በመግለጽ ከሳሽ በ17/ዐ8/2ዐዐ4 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ ለድርጅቱ በማሳወቃቸው ድርጅቱ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደሰጣቸው፣ ከሳሽ ማስጠንቀቂያውን በመቃወም የጽሁፍ ምላሽ በመስጠታቸው ተከሳሽ ድርጅት በ17/09/2004 ዓ.ም የስራ ውላቸውን እንዳቋረጠባቸው የሚገልጽ ሆኖ ስንብቱ ሕገወጥ ነው ተብሎ ተከሳሽ የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲፈጽምላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው።
ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ13/10/2004 ዓ.ም በተዘጋጀ መልስ የቶንጎ-ቤጊ የመንገድ ስራ ኘሮጀክት ስራ ተጠናቆ ሰራተኞች ወደ ጊዳሚ-ሙጊ የመንገድ ስራ ኘሮጀክት ሲዛወሩ ከሳሽም አብረው የተዛወሩ መሆኑን፣ በወቅቱ ከሳሽ ዝውውሩን ተቀብለው ጊዳሚ-ሙጊ በሚገኘው የተከሳሽ ድርጅት ካምኘ ውስጥ ስራ ጀምረው የነበረ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ በዚህን ጊዜ ክላኒኩን እየዘጉ ልላ ቦታ በመዋላቸው አደጋና ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰራተኞች የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ ጠፍቶ የነበረ መሆኑን፣ ከሳሽ ለከፊሉ ሰራተኛ ህክምና በመስጠት እና ለከፊሉ ደግሞ በመከልከል በአንድ ድርጅት ሰራተኞች መካከል ልዩነትን እና መከፋፈልን የፈጠሩ መሆኑን፣ በመጨረሻም ከሳሽ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት እንዲላኩ እና ከኘሮጀክቱም እንዲሰናበቱ በጠየቁት መሰረት የኘሮጀክቱን ክላኒክ ከዘጉበት እና ስራ አልሰራም ብለው ካቆሙበት ከ12/08/2004 ዓ.ም ጀምሮ ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረገ መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሯል።
ፍ/ቤቱም የተከሳሽን አንድ ምስክር ከሰማ በኋላ አጠቃላይ ክርክሩን መርምሮ ከሳሽ በ29/08/2004 ዓ.ም የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ በመቃወም ለተከሳሽ ድርጅት በ01/09/2004 ዓ.ም የጻፉት ደብዳቤ ድርጅቱ “…መጀመሪያ ወደ ቀጠረኝ መስሪያ ቤት መላክ ይህ የማይሆን ከሆነ ማሰናበት ይችላል።” የሚል አባባል ያዘለ ቢሆንም የደብዳቤው አጠቃላይ ይዘት ከሳሽ መሰናበት ስለምፈልግ አሰናብቱኝ ማለታቸውን የሚያመለክት አይደለም በማለት ይህንን ደብዳቤ መነሻ በማድረግ ተከሳሽ ድርጅት የወሰደው የስንብት እርምጃ ሕገወጥ ነው፤ በመሆኑም ሕገወጥ የስራ ስንብት እርምጃ የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች ተከሳሽ ለከሳሽ ላከፍልና የምስክር ወረቀት ላሰጣቸው ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። በስር ተከሳሽ አቅራቢነት የፍ/ከ/ፍ/ቤት የግራ ቀኙን የይግባኝ ክርክር ከሰማ በኋላ ከሳሽ ኘሮጀክቱ በመጠናቀቁ ተከሳሽ ድርጅት ልሎች ሰራተኞችን በሙሉ ወደ ልላ ቦታ ሲያዛውር እኔን በባዶ ካምኘ አስቀምጦኛል በማለት የተከራከሩ ቢሆንም የኘሮጀክቱ ስራ አለመጠናቀቁን ራሳቸው በ20/06/2004 ዓ.ም ለተከሳሽ በጻፉት ደብዳቤ መግለጻቸውን፣ በቅጥር ውላቸው ተራ ቁጥር 15 በተመለከተው መሰረት ተከሳሽ ድርጅት ከሳሽን አዛውሮ የማሰራት መብት ያለው ሆኖ እያለ ከሳሽ በ17/08/2004 ዓ.ም ለተከሳሽ በጻፉት ደብዳቤ አዲስ ድርድር እስካላደረግን ድረስ በሰራተኛው ላይ ለሚደርሰው ችግር ተጠያቂ አይደለሁም በማለት መግለጻቸው ክላኒኩን ዘግተው ያለስራ የሚንቀሳቀሱበት ጊዜ እንደነበረ በተከሳሽ ድርጅት የቀረበውን ክርክር የሚያጠናክር መሆኑን፣ በመጨረሻም ከሳሽ በ01/09/2004 ዓ.ም ለተከሳሽ በጻፉት ደብዳቤ ማኔጅመንቱ ጥያቄዬን የመመለስ ብቃት የለውም፣ ወደቀጠረኝ መ/ቤት መመለስ አለብኝ፣ ይህ ካልሆነ ልሰናበት ይገባል በማለት መግለጻቸው የስራ ውሉ የተቋረጠው ከራሳቸው በቀረበ ጥያቄ መሰረት እንደሆነ የሚያመለክት መሆኑን ገልጾ የስንብቱን ሕገወጥነት በተመለከተ የስር ፍ/ቤት ውሳኔን ሲሽር የ43 ቀን ደመወዝ፣ የትርፍ ሰዓት ማካካሻ አበል፣ የጉዞ አበል እና ክፍያ ለዘገየበት የተወሰነውን ገንዘብ በተመለከተ ውሳኔውን አጽንቷል።
አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ሰበር ችሎት ያቀረቡት ይዘቱ ከላይ የተመለከተው የይ/ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ከሳሽ በ01/09/2004 ዓ.ም ለተከሳሽ የጻፉትን ደብዳቤ ይዘት መሰረት በማድረግ ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት በአግባቡ የሰጠውን ውሳኔ ይ/ሰሚው ፍ/ቤት ደብዳቤውን በአግባቡ ሳይተረጉም የሰጠው ውሳኔ ከሕግ ውጪ ነው በማለት አመልካች ያቀረቡትን ቅሬታ ተጠሪ ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል። የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት የይ/ሰሚው ፍ/ቤት ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
በዚህም መሰረት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የተቋቋመ አንድ የስራ ውል በሰራተኛው አነሳሽነት እንደነገሩ አግባብ በማስጠንቀቂያ ወይም ያለማስጠንቀቂያ ላቋረጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎች በአዋጁ አንቀጽ 31 እና 32 ስር ተመልክተዋል። ተጠሪ ከስር ጀምሮ የሚከራከረውም አመልካችን ከስራ ያሰናበትኩት በእነዚሁ ድንጋጌዎች መሰረት አመልካች የስራ ውሉ እንዲቋረጥ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል ነው በማለት መሆኑን የክርክሩ ይዘት ያመለክታል። ይሁን እንጂ አመልካች በ01/09/2004 ዓ.ም ለተጠሪ የጻፉት ደብዳቤ አጠቃላይ ይዘት ሲታይ አመልካች ከተጠሪ ጋር የነበራቸውን የስራ ውል ለማቋረጥ ተነሳስተው በአዋጁ አንቀጽ 31 ወይም 32 በተመለከተው መሰረት የስራ ውላቸውን ለማቋረጥ መወሰናቸውን የገለጹበት ሳይሆን በ29/08/2004 ዓ.ም የተሰጣቸውን የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ በመቃወም ለድርጅቱ ምላሽ የሰጡበት መሆኑን ከመዝገቡ ግልባጭ መገንዘብ ይቻላል። አመልካች በዚሁ በ01/09/2004 ዓ.ም ለተጠሪ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ተጠሪ ድርጅት በአመልካች ደብዳቤ ላይ የተጠየቀውን ጥያቄ ተቀብሎ ተገቢውን መፍትሕ እንዲሰጣቸው፣ ይህን የማያደርግ ከሆነ ግን ማሰናበት እንደሚችል የገለጹት ሀሳብም ቢሆን ተጠሪ ልሎች መፍትሕዎችን መስጠቱን ትቶ ማሰናበቱን የሚመርጥ ከሆነ የማሰናበት እርምጃውን ከሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት ጋር መቀበል እንደሚገባው መጠየቃቸውን የሚጠቁም ነው ከሚባል በቀር በራሳቸው አነሳሽነት የስራ ውላቸውን ለማቋረጥ መፈለጋቸውን የሚያረጋግጥ ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።
በልላ በኩል በይ/ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ ላይ እንደሰፈረው አመልካች በስራው ላይ በነበሩበት ጊዜ የተጠሪን ጥቅም የሚጎዱ የተለያዩ ድርጊቶችን ይፈጽሙ የነበረ ስለመሆኑ ተጠሪ ከስር ጀምሮ የተለያዩ የክርክር ነጥቦችን ያቀረበ መሆኑን ከመዝገቡ ግልባጭ መገንዘብ የተቻለ ቢሆንም በመሰረቱ ተጠሪ አመልካችን ከስራ ያሰናበተው በዐ1/09/2004 ዓ.ም ለተጠሪ በጻፉት ደብዳቤ የስራ ውላቸውን ለማቋረጥ ጠይቀዋል በማለት እንጂ የስራ ውላቸውን ለማቋረጥ የሚያስችል ጥፋት ፈጽመዋል በማለት ባለመሆኑ አመልካች በስራው ላይ በነበሩበት ጊዜ የፈጸሙት ጥፋት መኖር አለመኖሩ እና ካለም መጠኑ እና የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት በዚህ መዝገብ በተያዘው ክርክር ላይ ላመረመር የሚችልበት ስነ ስርዓታዊ አግባብ የለም። በመሆኑም ይ/ሰሚው ፍ/ቤት ከሳሽ በ01/09/2004 ዓ.ም ለተከሳሽ በጻፉት ደብዳቤ ማኔጅመንቱ ጥያቄዬን የመመለስ ብቃት የለውም፣ ወደቀጠረኝ መ/ቤት መመለስ አለብኝ፣ ይህ ካልሆነ ልሰናበት ይገባል በማለት መግለጻቸው የስራ ውሉ የተቋረጠው ከራሳቸው በቀረበ ጥያቄ መሰረት እንደሆነ የሚያመለክት ነው በማለት ለደረሰበት ድምዳሜ አመልካች በስራው ላይ በነበሩበት ጊዜ የተጠሪን ጥቅም የሚጎዱ የተለያዩ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር የመባሉን ጉዳይ በተጨማሪ ምክንያትነት በመቀበል በውሳኔው ላይ ማስፈሩ ተገቢውን የክርክር አመራር ስርዓት የተከተለ ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።
ሲጠቃለል አመልካች በ01/09/2004 ዓ.ም ለተጠሪ የጻፉት ደብዳቤ የስራ ውላቸውን ለማቋረጥ መፈለጋቸውን የሚያረጋግጥ ነው በማለት ይ/ሰሚው ፍ/ከ/ፍ/ቤት የደረሰበት ድምዳሜ ይህንኑ ድምዳሜ መሰረት በማድረግ የስር ፍ/ቤት ውሳኔን ሽሮ የስራ ስንብት እርምጃው ሕጋዊ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ የደብዳቤውን እና የግራ ቀኙን አጠቃላይ የክርክር ይዘት ያላገናዘበ እና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት በመ/ በ29/08/2005 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ ሽሮ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ሲል የፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ/ በ26/11/2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የስራ ስንብት እርምጃው ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ ተጠሪ ለአመልካች የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲፈጽም እና የምስክር ወረቀት እንዲሰጠው የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ በ29/ዐ8/2005 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 348(1) መሰረት ፀንቷል።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.