No summary available.
ጥር 16 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ የሺሐረግ ታደሰ - ቀረቡ ተጠሪ፡- የአምቦ ማዕድን ውሃ አ/ማ አልቀረበም።
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ግንቦት 5 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበችውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የሥራ ውል መቋረጥን የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የተያዘው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ አመልካች ያቀረበችው ክስ ነው። ከሳሽ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ በተከሳሽ ድርጅት ተቀጥሬ በተለያየ የሥራ መደብ አገልግያለሁ። ከሳሽ ተከሳሽ እየሰራሁበት ባለው የፋይናሻል ኮንትሮል የሥራ መደብ ከአዲስ አበባ ወደ ሰንቀል ተዛውሬ እንድሰራ ደብዳቤ ፅፎልኛል። ከሳሽ በተከሳሽ ፈቃድና ተከሳሽ ጋር ውል ተዋውዬ በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ስከታተለው የነበረው የማስተርስ ትምህርት የመመረቂያ ጽሑፍ መስከረም 2003 ዓ.ም በፊት እንዳስረክብ ዩኒቨርሲቲው ያዘዘ መሆኑን ገልጬ ትምህርቴን ለሶስት ወር ዝውውሩን እንዲያዘገይልኝ ጠይቄው ተከሳሽ ፈቃደኛ አልሆነም። ከሳሽ ተከሳሽ የመጀመሪያውን አማራጭ እንቢተኛ ከሆነ የዓመት ረፍቴ እንዲሰጠኝና ትምህርቴን እንዳጠናቅቅ በፅሑፍ ጠይቄለሁ። ከሳሽ ያልተጠቀምኩበት አንድ መቶ ሃያ ቀናት ረፍት አለኝ። ተከሳሽ ፈቃድ እንዲሰጠኝ ላቀረብኩት ጥያቄ መልስ ባለመስጠቱ ዝምታው ጥያቄውን እንደተቀበለው በመውሰድ ትምህርቴን በመከታተል ላይ እያለሁ ከአምስት ቀናት በላይ ከሥራ ቀርተሻል በማለት ትምህርት ስጀምር የተዋዋለውን ውል የሚቃረን ህገ ወጥ እርምጃ የወሰደ በመሆኑ ደመወዜን ከፍሎ ወደ ሥራ እንድመለስ ይወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርባለች።
ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ አቅርቦ በብይን ውድቅ አድርጐታል። የመከላከያ መልሱን በተመለከተ አመልካች ትምህርቷን እስክታጠናቅቅ ዝውውሩ እንዲዘገይላት ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት የልለው መሆኑ ተገልፆላታል።
የዓመት ፈቃድ በተመለከተ፣ ከሳሽ ፈቃድ የምትወጣበት ጊዜ በዕቅድ የተያዘው እንደአውሮፖዊያን አቆጣጠር በዲሴንበር 2010 ሆኖ እያለ፣ ከዚያ በፊት የዓመት እረፍት እንዲሰጣት ያቀረበችው ጥያቄ ተገቢነት የለውም። በግልፅ ፈቃድ ሣይሰጣት፣ ከሥራዋ ለአምስት ቀንየቀረች በመሆኑ፣ የሥራ ውሉ የተቋረጠው በአግባቡ ነው በማለት ተከራክሯል።
የሥር ፍርድ ቤት ከሳሽ የመመረቂያ ፅሑፏን ለማጠናቀቅ የዓመት ፈቃድ እንዲሰጣት በፅሑፍ ጥያቄ አቅርባለች። ተጠሪ /ተከሳሽ/ ምላሽ ሣይሰጥ የቀረ መሆኑን በማስረጃ ተረጋግጧል። ከሳሽ የተከሳሽን ዝምታ የዓመት ፈቃድ ጥያቄውን እንደተቀበለው በመቁጠር ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ከሥራ ቦታ ሣትገኝ መቅረቷ ያለ ምክንያት እንደቀረች የሚያስቆጥራት አይደለም። ተከሳሽ የሥራ ውሉን ያቋረጠው ከህግ ውጭ በመሆኑ የስድስት ወር ደመወዟን ከፍሎ ወደ ሥራ ይመልሳት በማለት ውሣኔ ሰጥቷል። ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካች በግልፅ ፈቃድ ሣይሰጣት፣ ከሥራ ቦታ ያልተገኘች መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ የሥራ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ሽሮታል።
አመልካች ሐምል 30 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ትምህርት የጨረስኩት ተጠሪ ጋር ውል ተዋውዬ ትምህርቴን ተከታትዬ ባላጠናቅቅ ለትምህርት ያወጣውን ወጭ ለመክፈል ተስማምቼ ነው። አመልካች የዓመት ፈቃድ እንዲሰጠኝ ስጠይቅ የመመረቂያ ፅሑፍ እንዳጠናቅቅ ዩኒቨርሲቲው ያስቀመጠውን ቀነ ገደብ በመጥቀስ ነው።
ተጠሪ ለጥያቄው መልስ ሣይሰጥ ዝም ማለቱ እንደተቀበለው መቁጠር እንደ ጥፋት ላያዝብኝ የሚገባ አይደለም። ስለዚህ የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ በሰበር እንዲታረምልኝ በማለት አመልክታለች። ተጠሪ የዓመት ፈቃድ የሚሰጥበት ሥርዓት ሣይሟላና በግልፅ ፈቃድ ሣይሰጣት ወደ ተዛወረችበት ቦታ ያልሄደች በመሆኑ፣ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27/1/ለ መሰረት ከሥራ መሰናበቷ ህጋዊ ነው በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል። አመልካች የመልስ መልስ አቅርባለች።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች ተጠሪን ከሥራ ያሰናበታት በህግ አግባብ ነው በማለት የሰጠው ውሣኔ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ በዚህ መዝገብ የተረጋገጡ ፍሬ ጉዳዮችን መሰረታዊ ባህሪና ይዘት እንደዚሁም በአሰሪውና በሰራተኛው መካከል ላኖር የሚገባውን ግንኙነትና አንፃራዊ ግድታ መመርመር አስፈላጊ ነው። አመልካች ተጠሪ ፈቃድ ሰጥቶና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የድጋፍ ደብዳቤ ፅፎላት፣ ከተጠሪ ጋር ውል ተዋውላ የማስተርስ ትምህርት ስትከታተል እንደነበርና፣ ተጠሪ አመልካችን ከአዲስ አበባ ወደ ስንቀል ሲያዛውራት፣ አመልካች የመመረቂያ ፅሑፏን ለዩንቨርሲቲው የምታስረክብበት የትምህርት የጊዜ ሰልዳ ጋር ተገጣጣሚነት እንዳለው በበታች ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል። አመልካች በተጠሪ ፈቃድና ስምምነት የጀመረችው ትምህርት እስክታጠናቅቅ ዝውውሩ እንዲዘገይላት ተጠሪ ጠይቃ ተጠሪ ጥያቄዋን የማይቀበለው መሆኑን እንዳሳወቃት ተረጋግጧል።
በተጠሪ ድጋፍና ፈቃድ ለሶስት ዓመት ያህል ስትከታተለው የነበረው የማስተርስ ትምህርት ለማጠናቀቅ ለተጠሪ ያቀረበችው የመጀመሪያ ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኘው አመልካች፣ ዩንቨርስቲው ባወጣው የጊዜ ሰልዳ የመመረቂያ ፅሑፏን ለማቅረብና ትምህርቷን ለማጠናቀቅ እንድትችል ተጠሪ ያልተጠቀመችበትን የዓመት ፈቃድ እንዲሰጣት በፅሑፍ ጠይቃለች። ተጠሪ በዚህ አመልካች ላቀረበችው የዓመት ፈቃድ ጥያቄ በግልፅ አሉታዊ ምላሽ እንዳልሰጠ በበታች ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል። ይህም ያለበት አመልካችና ተጠሪ በሥራ ውል ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ብቻ ሣይሆን የአመልካችን የማስተርስ ትምህርት በተመለከተ፣ ከተጠሪ የሚፈለገውን ድጋፍ፣ ትብብርና እርዳታ አመልካች ትምህርቷን ስትከታተልና ትምህርቷን ተከታትላ ካጠናቀቀች በኋላ ያለባትን ግድታና ኃላፊነት የሚወሰን ልላ ልዩና ተጨማሪ የውል ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ተጠሪ ክዶ አልተከራከረም። በአንፃሩ አመልካች የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዕውቅና በሰጠውና ከተጠሪ ጋር ባደረገችው ውል መሰረት ትምህርቷን ስትከታተል የቆየች መሆኑ ግራቀኙ በበታች ፍርድ ቤቶች እና ግራቀኙ በሰበር ደረጃ ካቀረቡት ክርክር ለመረዳት ችለናል።
አመልካች የዓመት ፈቃድ ተሰጥቷት፣ በተጠሪ ድጋፍ ስትከታተለው የነበረውን የማስተርስ ትምህርት ለማጠናቀቅ በፅሑፍና በግልፅ ላቀረበችው ጥያቄ ተጠሪ በግልፅ የሰጠው አሉታዊ መልስ አለመኖሩ፣ ከላይ ከገለፅነው አመልካችና ተጠሪ መካከል ስለአመልካች የማስተርስ ትምህርት ከተደረገው ልዩና ተጨማሪ ውል አንፃር መታየት የሚገባው ነው። ተጠሪ አመልካች ለደቡብ አፍሪካ ዩንቨርስቲ ከፍተኛ ክፍያ እየተከፈለ ስትከታተል የቆየችውና የማስተርስ ትምህርቷን በአግባቡ እንድታጠናቅቅ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፍ እና ትብብር ያደርጋል፣ አመልካችም ትምህርቷን ለማጠናቀቅ የምታቀርበውን ጥያቄ በቅንነት በመመልከት ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይገመታል። ተዋዋይ ወገኖች በውል የገቡትን ግድታ በመተማመንና በቅንነት ውሉን ይፈፅማሉ ተብለው ላገመቱና በዚሁ መንገድ ትርጉም ላሰጥ እንደሚገባው በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 1732 ተደንግጓል።
ከዚህ አንፃር ሲታይ የተጠሪን ግልፅ የሆነ አሉታዊ ምላሽ ለመስጠት፣ አመልካች ጥያቄዎን እንደተቀበላት በመቁጠር ትምህርቷን ለማጠናቀቅ የግድ አስፈላጊ የሆነውን የመመረቂያ ፅሑፍ የማዘጋጀት፣ በሥራ ገበታዋ ላይ ሣትገኝ መቅረቷ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27 ንዑስ አንቀፅ1/ለ/ መሰረት ያለበቂ ምክንያት ከሥራ ቦታ እንደቀረች የሚያስቆጥር ሆኖ አላገኘነውም።
ውሣኔ
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠሪ አመልካችን ከሥራ ያሰናበታት ከሕግ ውጭ ነው በማለት በመዝገብ የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል።
ተጠሪ የአንድ ዓመት ደመወዝ በመክፈል አመልካችን ወደ ሥራ ላመልሳት ይገባል በማለት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 43 ንዑስ አንቀፅ 5 መሰረት ውሣኔ ሰጥተናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.