No summary available.
ግንቦት 06 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል አላ መሀመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የእንግላዝ ሕፃናት አድን ድርጅት ጠበቃ አቶ አይሸሽም መድፉ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ሽመልስ አለሙ አልቀረቡም መዝገብን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የአሳይታ ወረዳ ፍርድ ቤትና የአውሲረሱ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ የስራ ውል ጊዜው ከመድረሱ በፊት መቋረጡ የሚያስከትለውን ኃላፊነት የሚመለከት ነው።በወረዳው ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
1.የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው ክስ ነው።ተጠሪ አመልካች በጊዜያዊነት የቀጠረው መሆኑንና የስራ ውሉም የሚጠናቀቀው ነሀሴ 25 ቀን 2004 ዓ.ም መሆኑን ገልፆ፤
የሥራ ውሉ የሚቋረጥበት ጊዜ ሳይደርስና በቂ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ ተከሳሽ (አመልካች)የሥራ ውሉን ያቋረጠው ስለሆነ የ6 ወር ደመወዝ የካሳ ክፍያ፣ የማስጠንቀቂያ ክፍያ፣የአልጋ፣አበልና እና ልሎች ወጪዎች ላከፈሉኝ ይገባል በማለት ክስ አቅርቧል።አመልካች የሥራ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ የሥራ ውል መሆኑንና የሥራ ወሉን ያቋረጠውም ማስጠንቀቂያ በመስጠት መሆኑን ግልፆ፤ ስንብቱ ህጋዊ ነው።ከሳሽ (ተጠሪ)ያቀረበው የጥቅማ ጥቅም እና ልሎች ክፍያዎች ጥያቄ የህግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክሯል።የወረዳው ፍርድ ቤት አመልካች የአስራ ሁለት ቀናት ማስጠንቀቂያ በመስጠት የስራ ውሉን ያቋረጠና የሥራ ውሉን ያቋረጠው በውሉ የተገለፀው ጊዜ ማለትም ነሀሴ 21 ቀን 2004 ዓ.ም ከመድረሱ በፊት በመሆኑ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው ብሎ የስድስት ወር ደመወዝ ፤የካሳ ክፍያ፤የሶስት ወር ደመወዝ ክፍያ ለዘገየበት፤የማስጠንቀቂያ ክፍያና ልሎች የጥቅማ ጥቅምና አበል ክፍያዎች በድምሩ ብር 107,823.73 (አንድ መቶ ሰባት ሺ ስምንት መቶ ሃያ ሶስት ብር ከሰባ ሶስት ሳንቲም) አመልካች ለተከሳሽ እንዲከፍል ውሳኔ ስጥቷል ።
2.አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለአውሲረሱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል።አመልካች ለዚህ ሰበር ችሎት ባቀረበው የሰበር አቤቱታ የሥራ ውሉ የተቋረጠው ሀምል 25 ቀን 2004 ዓ.ም ነው። ከዚህ በፊት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፈናል።እንዲሁም ክፍያዎችን ፈጽመናል። በልላ በኩል በማስረጃ ያልተረጋገጠ የአበልና እና የአልጋ ክፍያ ተወስኖብናል ስለዚህ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ የሥራ ውል ሆኖ እያለ ተጠሪ ከጠየቀው በላይ ገንዘብ በላይ እንድንከፍል የተሰጠው ውሳኔ መስረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክተዋል።ተጠሪ በበኩሉ አመልካች የሥራ ውሉን ያቋረጠው ከህግ ውጭና የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍል የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል። አመልካች የመልስ መልስ አላቀረበም።
3.ከሥር የክርክሩ አመጣጥና ለሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች ተጠሪን ከህግ ውጭ ያሰናበተው ስለሆነ የስድስር ወር ደመወዝ የካሳ፡ ክፍያ የማስጠንቀቂያ ክፍያና ልሎች ክፍያዎች እንዲከፍል በማለት የሰጡት ውሳኔ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም ?የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ተጠሪን ለተወሰነ ጊዜ የቀጠረው መሆኑንና የሥራ ውሉ የሚጠናቀቀው ነሐሴ 24 ቀን 2004 ዓ.ም እንደነበር፤ተጠሪ በወረዳው ፍርድ ቤት ባቀረበው የክስ ማመልከቻ ገልጿል። አመልካች በስራ ውሉ የተገለፀው ጊዜ ሣይደርስና በቂ ምክንያት ሣይኖረው ሀምል 24 ቀን 2004 ዓ.ም የተጠሪን የሥራ ውል የአሰራ ሁለት ቀናት ማስጠንቀቂያ በመስጠት ያቋረጠው መሆኑን የወረዳው ፍርድ ቤት አረጋግጧል።ስለሆነም አመልካች ከነሐሴ 24 ቀን 2004 ዓ.ም በፊት ውሉን ለማቋረጥ የሚያስገድደው ምክንያት ወይም በተጠሪ በኩል ያልተፈፀመ ጥፋት ሣይኖርና ለተጠሪ የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ ሣይሰጠው የስራ ውሉን ማቋረጡ ከሕግ ውጭ ነው በማለት የወረዳው ፍርድ ቤት እና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አላገኘነውም።
አመልካች የተጠሪን የሥራ ውል በውሉ የተገለፀው ጊዜ ከመድረሱ በፊት ያለበቂ ምክንያት የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ ሣይሰጥ አቋርጧል ከተባለ ለተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት ላከፈል የሚገባው ክፍያ ምን መሆን አለበት የሚለውን ነጥብ ማየት አስፈላጊ ነው። የተጠሪ የሥራ ውል የሚቋረጥበት ጊዜ የቀረው አንድ ወር ብቻ እንደነበረ ከግራ ቀኙ ክርክርና የበታች ፍርድ ቤቶች ከሰጡት ውሳኔ ተረጋግጧል።ይህ ከሆነ አመልካች ለተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43(4)/ሀ መሰረት እንዲከፍል የሚገደደው ውሉ እስከ ሚቋረጥበት ድረስ ያለውና ተጠሪ ያቀረቡት የአንድ ወር ደመወዝ ማለትም ብር 8052.73/ስምንት ሺ ሃምሣ ሁለት ብር ከሰባ ሶስት ሣንቲም/ ነው። ከዚህ አንፃር ውሉ ነሐሴ 24 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም የሚጠናቀቅ መሆኑን ሣያገናዝቡ የበታች ፍርድ ቤቶች የስድስት ወር ደመወዝ ካሣ አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል።
አመልካች የተጠሪ የሥራ ውል ከሚጠናቀቅበት የጊዜ ገደብ ከአንድ ወር በፊት የሥራ ውሉን አቋርጧል።በዚህ ሁኔታ አመልካች ለተጠሪ ላከፍል የሚገባው የአንድ ወር ደመወዝ የማስጠንቀቂያ ክፍያ እንጂ የሶስት ወር ደመወዝ የማስጠንቀቂያ ክፍያ እንዲከፍል የሚገደድበት ህጋዊ ምክንያት የለም። የወረዳው ፍርድ ቤት ክፍያ ለዘገየበት በማለት የሶስት ወር ደመወዝ አመልካች እንዲከፍል የወሰነው የስራ ውሉ ከተቋረጠበት ሀምል 24 ቀን 2004 ዓ.ም በፊት ክፍያ ከፍለህ አላጠናቀክም በማለት ነው። ሆኖም አሰሪው ክፍያ እንዲከፍል የሚገደደው የሥራ ውሉ ከተቋረጠ በሰባት ቀናት ውስጥ መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 36 የተደነገገ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ክፍያ ለዘገየበት በማለት አመልካች ለተጠሪ የሶስት ወር ደመወዝ እንዲከፍል የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው።
7.የወረዳው ፍርድ ቤት አመልካች ተጠሪ በመስክ ሥራ በሚቆይበት ወቅት የሚከፍለው የአልጋ ክፍያ ብር 6417( ስድስት ሺ አራት መቶ አስራ ሰባት ብር)እንደዚሁም የሃያ ቀን የውሎ አበል ብር 2970 (ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ ብር) በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን በመግለፅ አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል የሰጠው ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት አላገኘንም። በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡትን የክፍያ ውሳኔ በማሻሻል ፤አመልካች ለተጠሪ የአንድ ወር ደመወዝ የካሣ ክፍያ ፤የአንድ ወር ደመወዝ የማስጠንቀቂያ ክፍያ እና ለአልጋ ክፍያና የውሎ አበል በጠቅላላው በድምሩ ብር 25,492.16 /ሃያ አምስት ሺ አራት መቶ ዘጠና ሁለት ብር ከአስራ ስድስት ሳንቲም /ላከፍል ይገባዋል በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ወስነናል።
1.የአፋር ክልል አሳኢታ ወረዳ ፍርድ ቤትና የአወስራሱ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ተሻሽሐል።
3.አመልካች ለተጠሪ ብር 25,492.16 /ሃያ አምስት ሺ አራት መቶ ዘጠና ሁለት ብር ከአሥራ ስድስት ሣንቲም) የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት ወስነናል።
4.በዚህ ፍርድ ቤት በ 23/04/2006 ዓ.ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል ።
5.በዚህ ፍርድ ቤት የወጡትን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ።
No topics extracted.