No summary available.
ሐምል 17 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመስል አመልካች፡- አቶ አብርሃም ታደለ ቀረቡ ተጠሪ፡- ጥቁር አባይ ትራንስፖርት ኃላ/የተ/የግል/ማህበር አልቀረብም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ታህሳስ 4 ቀን 2000 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው።ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክር የሚመለከት ነው።ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው።በስር ፍርድ ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክሯል።
የክርክሩ መነሻ አመልካች ያቀረበው ክስ ነው።በስር ፍርድ ቤት አመልካች በከሳሽነት ቀርቦ፤ተከሳሽ (ተጠሪ) ከህግ አግባብ ውጭ የስራ ውልን በማቋረጥ ከስራ ያሰናበተኝ በመሆኑ፤
በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ 377/96 መሰረት የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርቧል።ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ ከሳሽ አመልካች ለአንድ ወር በህክምና ላይ ከቆየበኋላ ወደ ስራ ባለመመለሱ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ/ም ማስታወቂያ አውጥተናል።ከዚያም ከሳሽ ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ቀላል ስራ ካልተሰጠኝ የሹፍርነት ስራ አልሰራም በማለት ለከሳሽ በማሳወቃቸው ከስራ በመቅረታቸው ከስራ የተሰናበት ስለሆነ ስንብቱ በህግ አግባብ የተደረገ ነው በማለት ተከራክሯል።
የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ከሳሽ በስራ ላይ እያለ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ወደ ዳግማዊ ሚኒላክ ሆስፒታል ታክሞ በተሰጠው ማስረጃ ጉዳቱ መኪና ማሽከርከር እንደማይከለክለው ተገልጿል።ሆኖም ከሳሽ በህዳር ወር 2005 ዓ/ም መኪና ጅቡቲ ይዞ ከሄደ በኋላ ባደረበት ህመም ምክንያት መኪናውን ለመመለስ ባለመቻሉ መኪናው ልላ ሹፍር ሄዶ እንዲያመጣ የተደረገ መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ የተከሳሽ ድርጅት የህክምና ተቋም የሆነው ከሳሽ በአከርካሪ ዲስክና በእጅ ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ስለሆነ ቀለል ያለ ስራ ላይ እንዲመደቡ የሚገልፅ ማስረጃ ሰጥቷቸዋል። የደጃዝማች ባልቻ የሰጠው ማስረጃም ይህንኑ የተከሳሹን የጤንነት ችግር የሚገልፅ ነው። ይህም የሚያሳየው ከሳሽ በህመም ላይ መሆናቸውንና ጤንነታቸው ስላልተሻሻለ ህክምና በመከታተል ላይ ያሉ መሆናቸውን ተከሳሽ እያወቀ ቀላል ስራ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ከስራ ያሰናበተ መሆኑን የሚያሳይ ሰለሆነ ስንበቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት ተከሳሽ ለከሳሽ የካሳ ክፍያና የሁለት ወር የማስጠንቀቂያ ክፍያ እንዲከፍል በማለት ወስኗል።
በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ተጠሪ ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ መልስ ሰጪ (አመልካች) የይግባኝ ባይ ድርጅት ጥር 29 ቀን 2005 ዓ.ም የህክምና ማስረጃ ከሰጣቸው በኋላ ለሶስት ሳምንታት ያህል ለአሰሪያቸው (ይግባኝ ባይ)ሳያቀርቡና ስራ ሳይገቡ ቆይተው፤የካቲት 23 ቀን 2005 ዓ/ም የህክምና ማስረጃውን አቅርበዋል።ይህም መልስ ሰጪ የተሰጣቸው የህክምና ፍቃድ ካለቀ በኋላ ለሃያ አንድ ቀናት ከስራ ቦታ የቀረ መሆኑን ስለሚያሳይ ይግባኝ ባይ የመልስ ሰጭ የሰራ ውል ያቋረጠው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) መሰረት ነው በማለት የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል።
አመልካች መጋቢት 17 ቀን 2006 ዓም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ አመልካች ከደረሰብኝ የጤንነት ችግር እንዳላገገምኩ፤ለተጠሪ አሳውቄዋለሁ።አንድ የጤንነት ችግርና ህመም ያጋጠመው ሰራተኛ ፤አሰሪው ከስራ ከማሰናበቱ በፊት የሚወስዳቸው እርምጃዎች የሚደነግገው የአዋጅ ቁጥር377/96 አንቀጽ 86 ነው።ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ግን ለጤነኛ ሰራተኞች ተፈፃሚነት ያለውን እና በእኔ ጉዳይ አግባብነት የልለውን አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) በመጥቀስ የሰጠውን ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል።ተጠሪ በበኩሉ ግንቦት 29 ቀን 2006 ዓ/ም በተፃፈ መልስ አመልካች የህክምና ፍቃዱ ካለቀ በኋላ ሃያ ቀናቶች ወደ ስራ ቦታው ያልመጣ በመሆኑ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት ተከራክሯል።አመልካች ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ አመልካች ከስራ ያሰናበተው በሕግ አግባብ ነው። በማለት የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚል ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች በስራ ላይ ጉዳት የደረሰበት መሆኑንና በዚህ ምክንያት የጤና ችግር ስለገጠመው የአንድ ወር የህመም ፈቃድ በአሰሪው(ተጠሪ) ተሰጥቶት እንደነበር ተረጋግጧል። አመልካች የተሰጠው የሕመም ፈቃድ እንዳበቃ ወደ ስራ ቦታ ባለመምጣቱ ተጠሪ ማስታወቂያ ማውጣቱንና አመልካችም ማስታወቂያው በወጣበት ቀን ማግስት ከስራ ቦታ በመገኘት ከህመሙ እንዳላገገመ ገልፆ፣ አመልካች ይሰራው የነበረውን የአሽከርካሪነት ስራ ለመስራት የማይችል በመሆኑ ቀላል ስራ ላይ እንዲመደብ በመግለፅ የተጠሪ የጤና ተቋም የሰጠውን ማስረጃ እንዳቀረበ ተረጋግጧል። ይህ ከሆነ፣ አመልካችን እንደማንኛው ጤነኛ ሰራተኛ በመቅጠር የተሰጠህ የህመም ፈቃድ ካለቀ በኋላ በተከታታይ አምስት ቀናት በስራ ቦታ አልተገኘህም በሚል ምክንያት የሚያባርርበት የሕግ መሰረት የለውም።
አመልካች የደረሰበት ጉዳት መኪና ማሽከርከር የማይከለክለው መሆኑ በዳግማዊ ሚኒላክ ሆስፒታል በተሰጠ ማስረጃ ተረጋግጧል። በማለት ሲሆን፣ አመልካች ጅቡቲ እያሽከረከረ የወሰደውን መኪና መመለስ ባለመቻሉ ምክንያት ልላ ሹፍር ተመድቦ መኪናውን ከጅቡቲ ያመጣ መሆኑ፣ አመልካችም የህመም ፈቃድ የተሰጠው መሆኑና አመልካች ያጋጠመው የአከርካሪ ዲስክ እና እጅ ላይ በመሆኑ መኪና ማሽከርከር እንደማይችል ተጠሪ በኃላፊነት የሚያስተዳድረው ክላኒክ ጭምር በማረጋገጥ ማስረጃ እንደሰጠ ተረጋግጧል። ይህ ከሆነ፣ አመልካች ከሙሉ ደመወዝ ጋር የተሰጠውን የአንድ ወር የህመም ፈቃድ ጨርሶ ከህመሙ አገግሞ ስራ ቦታ መገኘት ካልቻለ፣ ተጠሪ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 85 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ተጨማሪ የህመም ፈቃድ መስጠትና በአንቀፅ 86 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት ግማሽ ደመወዙን በመክፈል ተጠሪ ከህመሙ እንዲያገግም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት ሲገባው፣ የአመልካችንየስራ ውል መሰረዙ አግባብነት ያለውን የሕግ ድንጋጌ መሰረት ያላደረገ ሕገ ወጥ ተግባር ነው።
ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት፣ በስራ ላይ የደረሰበትን አደጋ አሰሪው አውቆ የአንድ ወር የህመም ፈቃድ የሰጠው ሰራተኛ ከህመሙ አገግሞ ስራ ቦታ ላይ ሳይገኝ በሚቀርበት ሁኔታ ተፈፃሚነት ያላቸው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 85 እና አንቀፅ 86 ድንጋጌዎች መሆናቸውን ሳያገናዝብ፣ አመልካችን እንደማናቸውም ጤነኛ ሰራተኛ በመቁጠር፣ የሕመም ፈቃድ ካለቀ በኋላ በተከታታይ ከአምስት ቀን በላይ ስለቀረ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት የደረሰበት መደምደሚያ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ያላደረገና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተጠሪ አመልካችን የስራ ውል ያቋረጠው በሕግ አግባብ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ታህሳስ 4 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ምየሰጠው ውሳኔ ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር ዐ9329 ሐምል 29 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.