No summary available.
ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ርዕሶም እምባፍራሽ ቀረቡ።
ተጠሪ፡- ኢትዮ ቴልኮም ነ/ፈጅ አቶ ፈቃዱ ኃይል ቀረቡ።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይን የሚመለከት ሲሆን፣ ክርክሩም የተጀመረው የስር ከሣሽ የነበሩት የአሁኑ አመልካች በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በተጠሪ ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻነት ነው። የክሱ ፍሬ ነገርም ባጭሩ፡- በተጠሪ ድርጅት ውስጥ ከ27/1/1973 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 30/03/1991 ዓ.ም ስሰራ ከቆየሁኝ በኋላ በስህተት በመሰናበቴ በ5/07/1997 ዓ.ም ወደ ሥራ እንድመለስ ተደርጐ እስከ ሐምል 6 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ በወር ብር 4955 ደመወዝ እየተከፈለኝ ለ24 ዓመታት ከ6 ወር ሳገለግል ከቆየሁ በኋላ ተጠሪ የሥራ ውልን ያለአግባብ ስላቋረጠ ስንብቱ ሕገወጥ ነው ተብሎ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት የተለያዩ ክፍያዎች እንዲፈጸምለት እንዲወሰንለት ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው። ተጠሪም በበኩሉ ቀርቦ ለክሱ በሰጠው መልስ ከ27/1/1973 ዓ.ም እስከ 30/3/1991 ዓ.ም ያለው የሥራ ስንብት ክፍያ በይርጋ የታገደ መሆኑን፤ ይህ መቃወሚያው የሚታለፍ ከሆነም እስከ 30/3/1991 ዓ.ም ያለው የሥራ ስንብት የተከፈላቸው መሆኑን፣ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 16/10/2003 ዓ.ም ያለውን የሥራ ስንብት ክፍያ ደግሞ አመልካች እንዲወስዱ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ስለቀሩ በመሆኑ ጥያቄው ተቀባይነት የልለው መሆኑንና ከሥራ የተሰናበቱትም በሕጉ አግባብ በተፈፀመ ቅነሳ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት ይወሰንልን በማለት ተከራክሯል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ምስክሮች ከሰማ በኋላ ጉዳዩን በመመርመር እስከ 30/3/1991 ዓ.ም ድረስ ያለው የስንብት ክፍያ በይርጋ የሚታገድ መሆኑንና የሥራ ውሉም ላቋረጥ የቻለው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28/1/ ሐ መሰረት በተፈጸመ ቅነሳ ምክንያት መሆኑን ጠቅሶ ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት ከወሰነ በኋላ ከ5/7/1997 ዓ.ም ጀምሮ ያለው የሥራ ስንብቱ ክፍያ ብር 13763.88፣ በሰራተኞች ቅነሳ ጊዜ በአዋጁ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 403 መሰረት ላከፈል የሚገባ ክፍያ ብር 9910፣ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ብር 9910፣ አመልካች ሥራ ሰርቶ ያልተከፈለው የ13 ቀናት ደሞዝ ብር 2147.16 እና የ71 ቀናት የዓመት እረፍት ክፍያ ብር 11726.83 በድምሩ ብር 47457 ተጠሪ ለአመልካች ይክፈል ሲል ወስኗል። በአመልካች ይግባኝ አቤቱታ አቅራቢነት ጉዳዩን የተመለከተው የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በበኩሉ ግራ ቀኙን አስቀርቦ ካከራከረ በኋላ የበታች ፍ/ቤቱን ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 3481 መሰረት በማጽናት ወስኗል።
አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይህንኑ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ውሣኔ በመቃወም ሲሆን፤
አቤቱታውም በሰበር አጣሪ ችሎቱ ተመርምሮ አመልካች የሥራ ውል አላግባብ ተቋርጧል በማለት አቤቱታ ሲያቀርብ ቆይቶ በመጨረሻ ስንብቱ ሕገወጥ መሆኑ ተረጋግጦ በ5/7/1997 ዓ.ም ወደ ቀድሞው ሥራው እንዲመለስ መወሰኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 1643 መሰረት የይርጋውን ጊዜ ማቋረጡ እየታወቀ፤ አመልካች ወደ ሥራ ለመመለስ እየተከራከረ በነበረበት ሁኔታ የስንብት ክፍያ በወቅቱ አልወሰደም ተብሎ ከ1973 1991 ዓ.ም ያለው የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄ በይርጋ ቀሪ ይሆናል የመባሉን አግባብነት ለመመርመር ሲባል መዝገቡ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን፣ ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን፤ እኛም በበኩላችን አቤቱታው ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ብቻ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
በመሰረቱ የሥራ ውል በመቋረጡ ምክንያት በሰራተኛውም ሆነ በአሰሪው የሚቀርብ ማናቸውም የክፍያ ጥያቄ የሥራ ውሉ በተቋረጠ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ካልቀረበ በይርጋ እንደሚታገድ በአዋጅ አንቀጽ 1624 ስር ተደንግጐ ይገኛል። ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስ የአመልካች የሥራ ውል ከ30/03/1991 ዓ.ም ጀምሮ ለ6 ዓመት ከ3 ወር ተቋርጦ የቆየ ስለመሆኑ ግራቀኙን ያላከራከረ ከመሆኑም በላይ በስር ፍ/ቤትም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። የሥራ ውሉም በወቅቱ ላቋረጥ የቻለው በመንግሥት ውሣኔ መነሻነት ነው ከሚባል በቀር በተጠሪ ጥፋት ምክንያት ስለመሆኑ ወይም ያለአግባብ በተጠሪ የተቋረጠ መሆኑን አመልካች አላስረዳም።
የሆነ ሆኖ የሥራ ውሉ ከተቋረጠበት እለት ከ30/3/1991 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 6 ወራት ጊዜ ውስጥ የሥራ ስንብት ክፍያ ጥያቄው ካልቀረበ በይርጋ እንደሚታገድ ግልጽ ነው። በልላ በኩል አመልካቹ በ5/7/1997 ዓ.ም እንደገና በመንግሥት መመሪያ ወደሥራ እንዲመለስ መደረጉም አስቀድሞ በይርጋ የታገደውን የስንብት ክፍያ ጥያቄን ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1991 ዓ.ም ያለውን የስንብት ክፍያ ከአዋጁ አንቀጽ 1643 ድንጋጌ ይዘት አኳያ የይርጋ ጊዜን ላያቋርጥ የሚችል አይደለም። ምክንያቱም እንደድንጋጌው አነጋገር ተጠሪ የአመልካችን መብት በጽሑፍ አውቆለት ወይም በከፊል በራሱ የፈፀመለት ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ አመልካች አላስረዳም።
ይህ ከሆነ ደግሞ ከ30/3/1991 ዓ.ም በፊት ያለው የሥራ ስንብት ክፍያ ጥያቄ በአዋጁ መሰረት በስር ፍ/ቤቶች በይርጋ ይታገዳል መባሉ ተገቢ እና አግባብነት ያላቸው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁን ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያገናዘበ ነው ከሚባል በቀር መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ስላላገኘን ተከታዩን ውሣኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 24120 በ18/6/2005 ዓ.ም ተወስኖ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 132709 በ25/10/05 ዓ.ም እንዲፀና የተደረገበት ፍርድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 3481 መሰረት ፀንቷል።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም ብለናል።
ግራ ቀኙ የሰበር ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.