No summary available.
ሐምል 29 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመስል አመልካች፡- ኢትዮጵያ የርቀት ትምህርት ኮልጅ አልቀረበም ተጠሪ፡- ዶ/ር ደሣለኝ ተመስገን ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ ጉዳይ የተጀመረው በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲሆን አመልካች በሥር ፍ/ቤት ተከሣሽ ሲሆን ተጠሪ ከሣሽ ነበሩ።ከሣሹ(የአሁን ተጠሪ)ባቀረበው ክስ ታህሳስ 19/2005 ባቀረበው ክስ አመልካች ሰኔ 22/2004 በህገ ወጥ መንገድ ከሥራ ያሰናበተኝ በመሆኑ ልዩ ልዩ ክፍያዎችን ይክፈለኝ በማለት ጠይቀዋል።ተከሣሽ (አመልካች)ባቀረበው መልስ የተጠሪ ጥያቄ በ6 ወር የይርጋ ጊዜ የታገደ ነው በማለት ተከራክረዋል። ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የአዋጅ ቁ.377/96 አንቀጽ 162(4) የሥራ ውሉ ለመቋረጡ ምክንያት በሰራተኛውም ሆነ በአሰሪው የሚቀርቡት ማንኛውም የክፍያ ጥያቄ የሥራ ውሉ በተቋረጠ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ካልቀረበ በይርጋ እንደሚታገድ ደንግጓል።
በዚህም መሰረት ተጠሪም ያቀረቡት ክስ የሥራ ውሉ ከተቋረጠበት ሰኔ 22-2004 ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት ድረስ ያለው ጊዜ ሲሰላ 6 ወር ያለፈው መሆኑን መረዳት ይቻላል። የክስ አቤቱታቸው በጊዜ ለማቅረብ ያልቻሉበት ምክንያትም በቂና አሣማኝ አይደለም።በመሆኑም ጥያቄው በይርጋ ይታገዳል በማለት ተወስኗል። ጉዳዩን በይግባኝ ያየው የከፍተኛ ፍ/ቤትም ውል ከተቋረጠ በኋላ የሚቀርቡ ክፍያዎች ከ6ወር በኋላ መቅረብ እንደልለበት ቢደነግግም የፍትሀብሄር ሕጋችን በአንቀጽ 1860(3) ጳጉሜን እንደወር የማትቆጠር በመሆኗ የአመልካች ጥያቄ ከ22-10- 2004 እስከ ታህሳስ 19-2005 በመቅረቡ 6ወር ስላልሞላው በይርጋ ላታገድ አይገባም በመሆኑም የሥር ፍ/ቤት ብይን በመሻር በዋና ጉዳይ፤ በፍሬ ነገሩ አከራክሮ እንዲወስን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህግ ቁ.341(1)መሰረት መልሶታል።
ለሰበር አቤቱታም የቀረበው ይህን ለማረም ነው። አመልካች ባቀረቡት አቤቱታም ተጠሪ ሰኔ 22/2004 የሥራ ውላቸው መቋረጡን ጠቅሰው ታህሳስ 19/2005 ያቀረቡትን የክፍያ ጥያቄ በአዋጅ 377/96 አንቀጽ 162(4)መሰረት 6 ወር ካለፈ በኋላ ነው ብሎውድቅ የተደረገውን ጉዳይ የፍደራሉ የይግባኝ ሰሚ (ከፍተኛው) ፍ/ቤት በፍትሀብሕር ህጋችን ቁጥር 1860(3) ጳጉሜ እንደወር አትቆጠርም በማለት የሰበር ውሣኔን መሻሩ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው፤ላታረም ይገባዋል በማለት ጠይቋል።ይህ ችሎትም የግራ ቀኙ መልስና የመልስ መልስ በፅሑፍ አቅርበው እንዲከራከሩ አድርጓል።
በዚህም መሰረት የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የፍትሐብሕሩን ህግ ቁጥር 1860(3) ጠቅሶ ጳጉሜ እንደወር አትቆጠርም የክሱ ጊዜ 6ወር አልሞላውም ብሎ የመወሰኑን አግባብነት ለማጣራት እንደ ጭብጥ ቀርቧል።
በመሆኑም የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካለው ህግ አኳያ እንደሚከተለው መርምረናል።
የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰው ሲሆን እኛም እንዳየነው አመልካች ባቀረበው አቤቱታ ተጠሪ ያቀረቡት ከውል መቋረጥ ጋር ተያይዞ ያቀረቡት ጥያቄ ጳጉሜ እንደወር ስለማትቆጠር 6ወር አልሞላም ተብሎ የይርጋ መቃወሚያው በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውድቅ መደረጉና በፍሬ ነገሩ እንድንከራከር መደረጉ በአግባቡ አይደለም የሚል ነው።ከመዝገቡ መገንዘብ እንደቻልነው አከራካሪ የሆነው የህግ ጥያቄ በአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 162(4)የሥራ ውል በመቋረጡ ምክንያት በሰራተኛውም ሆነ በአሰሪው የሚቀርብ ማንኛውም የክፍያ ጥያቄ ሥራ ውሉ በተቋረጠ በ6ወር ጊዜ ውስጥ ካልቀረበ በይርጋ ይታገዳል የሚለው ድንጋጌ “ጳጉሜን ያካትታል ወይስ አያካትትም?በሚል ነጥብ ነው።እንግዲህ ይርጋ ማለት የመብት ጥያቄ ጊዜ በማለፋ ቀሪ የሚሆንበት ነው ባንፃሩ መብት ላልነበረው የሚያጐናፅፍ ነው።
ወደያዝነው ጉዳይ ስንመለስ የተጠሪ ጥያቄ በይርጋ አይቋረጥም የተባለበት ምክንያት የፍትሐብሕር ህጋችን አንቀፅ 1860(3)ጳጉሜን እንደወር ስለማይቆጥር እና የአሰሪና ሰራተኛ ህጉም “ወር”ን መሰረት አድርጐ ስለተደነገገ ነው።
ጳጉሜ እንደ አስራ ሦስተኛ ወር የማትቆጠር መሆኑ ከታወቀና የሀገራችን የአንድ አመት ጊዜ 12 ወራቶች ከሆኑ ከዚህ አቆጣጠር ውጭ ያሉት ቀናት በግራ ቀኙ መሀከል መብትም ሆነ ግድታ ላፈጥር አይገባም።ጳጉሜ ተጠሪ ሥራም ላይ ቢሆኑ የሚሰጣቸው ጥቅም ወይም በመብት ደረጃ የሚጠይቁትም ክፍያ የለም።እንግዲህ እንደወር የማይቆጠረው “ጊዜ” ለቀረበው ከውል መቋረጥ ጋር ተያይዞ የሚነሣው የክፍያ ጥያቄ ጳጉሜ ተሰልቶ የተጠሪን መብት ላያጣብብ አይገባውም።
ባጠቃላይ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የመጀመሪያውን ደረጃ ፍ/ቤት ብይን ሽሮ የተጠሪ ጥያቄ የ6ወር ይርጋ ጊዜ አላለፈበትም በማለትወደ ሥር ፍ/ቤት መዝገቡን መመለሱ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት አይደለም ብለናል።በመሆኑም የሚከተለው ውሣኔ ተሰጥቷል።
የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በቀን 4/8/05 በመ.ቁ.07615 የሰጠው ብይን ተሽሯል።
የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በቀን 16/12/2005 በመ.ቁ.133056 የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል።
የግራ ቀኙ በፍሬ ነገር ደረጃ ክርክራቸው ይቀጥሉ ተብሎ በፍ/ብ/ስ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.341(1) መመለሱ በአግባቡ ነው ብለናል።
ግራ ቀኙ ወጭና ኪሣራቸውን ይቻቻሉ።
No topics extracted.