No summary available.
ሐምል 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- በርሄ ሐጎስ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ - ነ/ፈጅ ስዩም ረጋሳ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ገመቹ አዱኛ - የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ ባቀረቡት ክስ ነው።በ30/08/2005 ዓ.ም.አዘጋጅተው ያቀረቡት ክስ ይዘትም ባጭሩ፡-ከሳሽ ከ16/07/2005 ዓ.ም. ጀምሮ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ በጀማሪ ነገረ ፈጅነት የስራ መደብ ላይ ተቀጥረው አንድ ወር ከ15 ቀናት የሰሩ መሆኑን፣የ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ እንዲኖር የተደረገ ስምምነት ሳይኖር ተከሳሽ ድርጅት የስራ አፈጻጸምህ ዝቅተኛ ነው፣ሰዓት አክብረህ ስራ አትገባም የሚል እና መሰል ምክንያቶችን በመዘርዘር የስራ ውላቸውን አላግባብ እንዳቋረጠ የሚገልጽ ሆኖ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ተከሳሽ ድርጅት ከሕገወጥ የስራ ስንብት ጋር የተያያዙ ክፍያዎችን እንዲፈጽምላቸው እና ቅጥሩም ቋሚ ቅጥር ነው ተብሎ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ሲሆን ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ13/10/2005 ዓ.ም. በሰጠው መልስ ከሳሽ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ መሆኑን፣በዚህ የሙከራ ጊዜ ውስጥ በፍ/ቤት ቀጠሮ በጊዜ ሳይቀርቡ ቀርተው መዝገቦች እንዲዘጉ በማድረግ፣በሰዓት ስራ ባለመግባት እና የመሳሰሉ ጥፋቶችን ከመፈጸማቸውም በላይ ማስጠንቀቂያ እና መልሶችን ራሳቸውን ችለው የማዘጋጀት ውስንነት የታየባቸው መሆኑን እና ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳያስፈልግ እንዲሰናበቱ የተደረገውም የሙከራ ጊዜአቸው ባለማጠናቀቁ መሆኑን በመግለጽ ክሱ ውድቅ ላደረግ ይገባል በማለት ተከራክሮአል።
ፍ/ቤቱም የተከሳሽን ምስክሮች ከሰማ እና ከሳሽ ፈርመው ተቀብለዋል በተባለው ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ የተቀጠሩ መሆኑን በሚገልጸው ደብዳቤ ላይ የተመለከተው እና በከሳሽ የተካደው ፊርማ ተመርምሮ ውጤቱ እንዲቀርብለት ካደረገ በኋላ ከሳሽ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ መሆኑን በሚገልጸው ደብዳቤ ላይ የተመለከተው እና በከሳሽ የተካደው ፊርማ የከሳሽ መሆኑ በፎረንሲክ ምርመራ የተረጋገጠ ቢሆንም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 11(3) በተመለከተው መሰረት ግራ ቀኙ በ16/07/2005 ዓ.ም. ባደረጉት የቅጥር ውል ላይ የሙከራ ጊዜ እንዲኖር ስለመስማማታቸው ውሉ የማያመለክት መሆኑን፣ የሙከራ ጊዜ እንዲኖር ግራ ቀኙ ስለመስማማታቸው በውሉ እስካላረጋገጡ ድረስ ቅጥሩ የተፈጸመው ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ ስለመሆኑ የሚገልጸውን ደብዳቤ ከሳሽ ፈርመው መቀበላቸው ብቻውን ከሳሽ በዚህ የውል ሁኔታ ስለመስማማታቸው የሚያረጋግጥ አለመሆኑን፣የሙከራ ጊዜ እንዲኖር ግራ ቀኙ በውሉ ያልተስማሙ መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ ከሳሽ በተከሳሽ የተጠቀሱትን ድክመቶች አሳይተው ቢሆን እንኳ ተከሳሽ የከሳሽን የስራ ውል ማቋረጥ ይገባው የነበረው በማስጠንቀቂያ ሆኖ ሳለ ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጡ ስንብቱ የተከናወነው ከሕግ አግባብ ውጪ እንደሆነ የሚያመለክት መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ ተከሳሽ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ብር 2,500፣የስራ ስንብት ክፍያ ብር 273.97 እና የካሳ ክፍያ ብር 15,000 በድምሩ ብር 17,773.97(አስራ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ ሰባ ሶስት ከዘጠና ሰባት) የገቢ ግብር ቀንሶ ለከሳሽ እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቷል።
አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው ይግባኝ ሰሚው ከ/ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በማጽናቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ የቅጥር ውሉ በተደረገበት በዚያው ቀን ተጠሪ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ ስለመሆኑ የሚገልጸውን ደብዳቤ ፈርመው መቀበላቸው በተረጋገጠበት ሁኔታ ለሙከራ ጊዜ መቀጠራቸው የተገለጸበት ደብዳቤ በአመልካች ብቻ የተዘጋጀ ነው ተብሎ የአመልካች ክርክር በስር ፍ/ቤቶች ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው ለሙከራ ጊዜ የተቀጠረ ሰራተኛ ለስራው ተስማሚ አለመሆኑ ሲረጋገጥ አሰሪው የስራ ስንብት እና የካሳ ክፍያ ለመክፈል ሳይገደድ የሰራተኛውን የስራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ላያቋርጥ የሚችል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 11(5) በግልጽ የተመለከተ ሆኖ እያለ እና ተጠሪውም ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ የተቀጠሩ ስለመሆኑ በቅጥሩ ዕለት በአድራሻቸው የተጻፈውን ደብዳቤ ፈርመው በመቀበል ያረጋገጡ ሆኖ እያለ አሰሪው ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ውሉን ያቋረጠው አላግባብ ስለሆነ ሕገ ወጥ የስራ ስንብት የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች እንዲፈጽም በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ አግባብነት ያላቸውን የአዋጁን ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ አይደለም በማለት መሆኑን ተገንዝበናል።እንደተባለው ተገቢ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ለሙከራ ጊዜ የተቀጠረ ሰራተኛን በሙከራ ጊዜው ውስጥ አሰሪው ያለማስጠንቀቂያ ማሰናበት የሚችል ስለመሆኑ አዋጁ የሚደነግግ ቢሆንም የአዋጁ አንቀጽ 11(5) ድንጋጌ ተፈጻሚ ከመደረጉ አስቀድሞ ግን ተዋዋዮቹ የሙከራ ጊዜ እንዲኖር በቅጥር ውላቸው የተስማሙ መሆኑ በቅድሚያ መረጋገጥ እንዳለበት የአዋጁ አንቀጽ 11(3) በግልጽ ያመለክታል።በተያዘው ጉዳይ የቅጥር ውሉ የተደረገውም ሆነ ተጠሪው የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ ስለመሆኑ አመልካች ለተጠሪው በደብዳቤ የገለጸው በተመሳሳይ ቀን ነው።ተጠሪ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ የመሆን አለመሆኑ ጉዳይ ደግሞ መረጋገጥ ያለበት በአዋጁ አንቀጽ 11(3) መሰረት በቅጥር ውሉ እንጂ አመልካች በተናጠል ለተጠሪው በሚሰጠው ማስታወቂያ ባለመሆኑ ተጠሪው የሙከራ ጊዜውን የቅጥር ሁኔታ በውሉ ላይ በግልጽ የተቀበሉ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ በአመልካች የተጻፈላቸውን የቅጥር ደብዳቤ ፈርመው የተቀበሉ መሆኑ መረጋገጡ ብቻ የሙከራ ጊዜውን የቅጥር ሁኔታ ተስማምተው ተቀብለዋል ከሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችል አይደለም። በመሆኑም ተጠሪ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ በመሆኑ እና የተሰናበቱትም በስራ ላይ የተለያዩ ድክመቶችን በማሳየታቸው በመሆኑ ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት አመልካች የሚያቀርበው ክርክር ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።
ሲጠቃለል የስራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑን በማረጋገጥ አመልካች ለተጠሪው ተገቢ ክፍያዎችን እንዲፈጽም በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
348(1) መሰረት ፀንቷል።
የውሳኔው ቅጂ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 86397 የተያዘው አፈጻጸም ታግዶ እንዲቆይ በዚህ መዝገብ በ10/07/2006 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ ተነስቷል።ይጻፍ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ሰለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.