No summary available.
ሐምል 29 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- አቶ ምህረት አለነ ገረመው - ቀረቡ።
ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅት - ነ/ፈጅ ፈለቀ ካሣሁን ቀረቡ።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት የቀረበውን የአካሉ ጉዳት ካሳ ይከፈለኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡,-አመልካች በተጠሪ ድርጅት ውስጥ በጋራዥ ኃላፊነት የስራ መደብ ላይ ተቀጥረው በወር ብር 3,460.00(ሶስት ሺህ አራት መቶ ስልሳ ብር) እየተከፈላቸው ሲሰሩ የኮድ ቁጥሩ 3-08573 በሆነው የተጠሪ ድርጅት ተሽከርካሪ ለስራ እየተጓዙ ሚያዚያ 05 ቀን 2003 ዓ/ም በደረሰው የመኪና አደጋ በአካላቸው ላይ ጉዳት መድረሱንና በሕክምናም በአካላቸው ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን የተረጋገጠ መሆኑን፣በደረሰው የአካል ጉዳት መጠን መሰረት ላከፈላቸው የሚገባው ብር 171,600.00 (አንድ መቶ ሰባ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ብር) ሁኖ እያለ ተጠሪ ድርጅት ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር ባለው የኢንሹራንስ ውል መሰረት ከፍተኛው የመድን ሽፋን ብር 120,000.00 (አንድ መቶ ሃያ ሺህ ብር) መሰረት ተደርጎና ከጉዳት መጠኑ ጋር ተሰልቶ ብር 36,000.00 (ሰላሳ ስድስት ሺህ ብር) ከሕግና ከድርጅቱ ህብረት ስምምነት ውጪ ከፍሎ ቀሪውን ያልከፈላቸው መሆኑን ጠቅሰው ብር 171,600.00 እንዲከፍላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጠው መልስም፡- አመልካች የድርጅቱ ሰራተኛ በስራ ላይ እያሉ በአካላቸው ላይ ጉዳት መድረሱን ሳይክድ የአካል ጉዳት ካሳ ለአመልካች የተከፈለው ድርጅቱ ባለው የመድን ሽፋን መሆኑን፤ የመድን ሸፋን ላላቸው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሰራተኞች በስራ ላይ ለሚደርስባቸው ጉዳት ካሳ የሚከፈለው በመድን ፖላሲው ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 109(1) ድንጋጌ መጠቀሱን ገልጾ አመልካች በዚሁ አግባብ ብር 36,000.00 የተከፈላቸው በመሆኑ ቀሪ የሚከፈላቸው የአካል ጉዳት ካሳ ክፍያ የለም ሲል ተከራክሯል።የፍድራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከተጠሪ ድርጅት ጋር ያለውን የመድን ፖላሲውን እንዲያቀርብለት አድርጎ ከተመለከተ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ብር 36,000.00 የተከፈላቸው በመድን ፖላሲው መሰረት በመሆኑና በዚህ አግባብ የአካል ጉዳት ካሳ የተከፈለው ሰራተኛ ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 109(1) መሰረት አሰሪውን ላጠይቅ የሚችልበት አግባብ የለም በሚል ድምዳሜ የአመልካችን ቀሪ የአካል ጉዳት ካሳ ክፍያ ጥያቄን ውድቅ አድርጎ ወስኖታል።በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።
የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- በአመልካች ላይ በስራ ላይ ለደረሰው የ30% ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት በአዋጁ ላከፍል የሚገባው የካሳ መጠን ብር 62,280.00(ስልሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰማንያ ብር) ሁኖ እያለ አመልካች ተጠሪ ብር 36,000.00 በመድን ፖላሲው መሰረት ተከፍሐል በማለት ቀሪውን ብር 26,280.00 ላከፍል አይገባም ተብሎ መወሰኑ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 109(3(ሀ)) እና ስራ ላይ ያለውን የድርጅቱን የህብረት ስምምነት አንቀጽ 25(2) ድንጋጌ ያላገናዘበ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮ ለሰበር ችሎቱ ላቀርብ ይገባል ተብሎ በመታዘዙ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት የድርጅቱ ነገረ ፈጅ ቀርበው በጹሑፍ መልሳቸውን ሰጥተዋል።በመልሳቸው ላይም ለአመልካች የአካል ጉዳት ካሳ የተከፈለው በሕጉ አግባብ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።አመልካችም የሰበር አቤቱታቸውን አጠናክረው ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምረናል።እንደመረመርነውም አመልካች በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ምክንያት የተከፈለው ካሳ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 109(3(ሀ)) መሰረት የተሰላ አይደለም በማለት ያቀረበው ክስ የስር ፍርድ ቤቶች ከኢንሹራንስ የጉዳት ካሳ አከፋፈል አንጻር ብቻ በማየት ውድቅ የማድረጋቸውን አግባብነት በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል።
ከክርከሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው በአመልካች ላይ የአካል ጉዳቱ በስራ ላይ መድረሱና የጉዳቱ መጠንም 30% ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት መሆኑን ግራ ቀኙን ያላከራከረ ነጥብ መሆኑን፣ግራ ቀኙን የሚያከራክረው የካሳው መጠን መሆኑን ነው።
በመሰረቱ አመልካች በአካላቸው የደረሰውን የጉዳት መጠን መሰረት በማድረግ ካሳ እንዲከፈላቸው ዳኝነት የጠየቁትና የካሳውን መጠን ለማስላት መሰረት ያደረጉት በአካላቸው ደረሰ የተባለውን 30% ጉዳት መጠን መሆኑን ተገንዝበናል።በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 96(1) መሰረት በስራ ቦታ ላይ ለሚደርስ የአካል ጉዳት የካሳ መጠን የሚሰላበት አግባብን ሕጉ በአንቀፅ 109(3) ደንግጎ እናገኛለን።በዚህም መሰረት በሰራተኛው ላይ የደረሰው ጉዳት ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ከሆነ የሰራተኛው የአመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው ውጤት እንዲሁም ሰራተኛው ላይ የደረሰው ጉዳት ከዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት መጠን በታች ከሆነ ከአካል ጉዳት ደረጃው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ እንደሚከፈለው የተጠቀሰው ድንጋጌ ይገልፃል።በአመልካች ላይ የደረሰው የአካል ጉዳት ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት መሆኑን (30%) የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
በአንድ ሰራተኛ ላይ የሚደርሱት የጉዳት መጠን ደረጃዎች፡-ጊዜያዊ የአካል ጉዳት፣ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት፣ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት እና ሞት መሆናቸው በሕጉ ተለይተው ተቀምጠዋል።
ይህን ደረጃ በመመሪያ በጉዳት መወሰኛ ሰንጠረዥ የሚያወጣው የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር መሆኑና ደረጃውን የሚያወጣውም ለዘላቂ ከፊል እና ሙሉ የአካል ጉዳት ብቻ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 102(1) ስር ተመለክቷል። በጊዜያዊ የአካል ጉዳት ሰራተኛው ቀድሞ የነበረውን የመሥራት ችሎታ መልሶ ስለሚያገኝ፤ ሞትም ቢሆን የጉዳቱ መጠን በራሱ የተገለጠ በመሆኑ ሚኒስትሩ ለእነዚህ ጉዳቶች ደረጃን የማይወሰን መሆኑን የሕጉ ይዘትና መንፈስ ያሳያል።ሚኒስትሩ ደረጃቸውን ለሚወስንላቸው ዘላቂ ሙሉ ወይም ከፊል ጉዳቶች ግን የጉዳቶቹ መጠን ደረጃ ከመወሰኑ በፊት ጉዳቱ በደረሰ በአስራ ሁለት ወራት ውስጥ በተቻለ መጠን የጉዳቱን መጠን መወሰን ከሚኖርበት የህክምና ቦርድ ማስረጃ ማግኘት እንደሚያስፈልግ የአዋጁ አንቀጽ 102 (2) ድንጋጌ ይዘት ያሳያል።ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መረዳት የሚቻለውም አንድ ሰራተኛ በስራ ላይ ጉዳት ሲደርስበትና ጉዳቱ ዘላቂ ሁኖ ጉዳቱ ያስከተለው የመስራት ኃይል ቅነሳ በተገቢው ባለሙያ ተረጋግጦ በደረሰው የጉዳት መጠን ሰራተኛው እንዲካስ ማድረግ የሕጉ ፍላጎት መሆኑን ነው።የአዋጁ አንቀጽ 109(3(ሀ) ድንጋጌ ሲታይም ከስራ ላይ ለሚመጣ ጉዳት ምክንያት ዘላቂና ሙሉ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰራተኛ ላያገኘው የሚችለው ከፍተኛው ክፍያ የሰራተኛው የአመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው የብር መጠን መሆኑን ያስገነዝባል።ይሁን እንጂ የደረሰው ጉዳት ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት ከሆነ ሰራተኛው ላያገኝ የሚገባው የካሳ ክፍያ መጠን በሰራተኛው አካል ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን ደረጃ መሰረት አድርጎ የሚሰላ መሆኑን የድንጋጌው ይዘትና መንፈስ ያስገነዝባል።
ሕጉ የካሳ መጠኑ የሚሰላበትን አግባብ ከመደንገጉም በተጨማሪም ሰራተኛው የአካል ጉዳት ክፍያ ተከፋይ የማይሆንባቸው አጋጣሚዎችም እንዳሉ ያሳያል።ይኼውም፡ አንድ ሰራተኛ ሲሰራ የነበረው በመንግስት የልማት ድርጅት ሁኖ በመንግስት የጡረታ ሕግ የታቀፈ ከሆነ ወይም አሰሪው በገባለት የመድህን ዋስትና ተጠቃሚ ከሆነ በዘላቂ የአካል ጉዳት ክፍያ እንደማያገኝ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 109(1) ስር የደነገገ ሲሆን የዚህ የድንጋጌው መሰረታዊ አላማም ሰራተኛው በደረሰበት ከባድ የአካልጉዳት ምክንያት ከጡረታ ከወጣ ወዲያውኑ በመንግስት የጡረታ ክፍያ ስርዓት የሚታቀፍ በመሆኑ ከአንድ ምንጭ ሁለት ጊዜ የመካስ ሁኔታ እንዳይኖር ለመከላከል ነው ተብሎ ይታሰባል።እንዲሁም አንድ አሰሪ ለሰራተኞቹ በስራ ላይ ለሚደርስ አደጋ ዋስትና ገብቶላቸው የነበረ መሆኑና በፖላሲው መሰረት ስለደረሰበት ጉዳት ሰራተኛው የኢንሹራንስ ሽፋን ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ አሰሪው የጉዳት ካሳ ለመክፈል የሚገደድበት አግባብ የልለ መሆኑን የሕጉ ይዘትና መንፈስ ያስረዳል።ይሁን እንጂ ይህ የህጉ መሰረታዊ ይዘትና መንፈስ ሲታይ ሰራተኛው ተገቢውን ካሳ በደረሰው የአካል ጉዳት መጠን አንፃር እየታዬ ላያገኝ የሚገባ መሆኑን ነው።
ስለሆነም ቀጥሎ መታየት ያለበት ቁልፍ ጥያቄ ሰራተኛው በሕጉ የተጠበቀለትን የካሳ መጠን አሰሪው በመድን ፖላሲው ሙሉ በሙሉ ሳይሸፈን እንዲቀር አድርጎ ቢገኝ የመድን ፖላሲው መኖሩ ብቻውን ሰራተኛው በመድን ፖላሲው ስልት መሰረት ተሰልቶ የሚመጣውን ካሳ ብቻ ተከፍሎ እንዲሄድ ያስገድደዋል? ወይስ አያስገድደውም? የሚለው ነው።በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 109(1) ስር የሰፈረው ድንጋጌ ሙሉ ይዘት ሲታይም "በሕብረት ስምምነት በልላ አኳኋን ካልተወሰነ በስተቀር፣ በዚህ አዋጅ ለሚሸፈኑ የመንግስት ድርጅቶች ሰራተኞች የሚሰጠው የጉዳት ካሳ አሰሪው በገባበት የመድህ ዋስትና ወይም በመንግስት የጡረታ ሕግ መሰረት ይሆናል።ድርጅቱ መድህን ያልገባ ከሆነ በመንግስት የጡረታ ሕግ ለሚሸፈኑ ሰራተኞች የመንግስት የጡረታ ሕግ ተፈጻሚ ይሆናል።"በሚል የተቀመጠ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።ከዚህ ድንጋጌ ይዘት መረዳት የሚቻለው አንድ ሰራተኛ በመንግስት የጡረታ ሕግ የታቀፈ ከሆነ ወይም አሰሪው በገባለት የመድህን ዋስትና ተጠቃሚ ከሆነ የጉዳት ካሳውን አሰሪው እንዲከፍል የማይገደድ መሆኑን ነው።ይህ ድምዳሜ የሚያዘው ግን በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 109(3) ስር የተመለከተውን የካሳ ስልት መሰረት አድርጎ የኢንሹራንስ ሽፋኑ ለሰራተኛው ካሳውን ለመክፈል የሚያስችል ሁኖ ሲገኝ ነው።ይህ ካልሆነ ሰራተኛው በስራው ላይ ለደረሰበት ካሳ ተገቢውንና በሕጉ የተቀመጠለትን ካሳ አግኝቷል ለማለት የሚቻል አይሆንም።ከዚህ ውጪ አሰሪው የገባው የኢንሹራንስ ሽፋን ሰራተኛው በሕጉ በተመለከተው ስልት መሰረት የሚያገኘውን የአካል ጉዳት ካሳ የሚቀንስ መሆኑ ቢረጋገጥም አሰሪው የመድን ሽፋን በመግባቱ ብቻ የጉዳት ካሳውን እንዲከፍል አይጠበቅበትም ላባል የሚችልበት የሕግ አግባብ የልለ ሁኖ አግኝተናል።በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 109(1) መሰረት የመንግስት የልማት ድርጅት ለሰራተኞቹ የገባው የአካል ጉዳት ዋስትና ሽፋን መኖሩ ድርጅቱን ተጠያቂ የማያደርገው ድርጅቱ ሰራተኛው በአዋጁ አንቀጽ 109(3) በተመለከተው ስልት መሰረት ላያገኝ የሚገባውን የአካል ጉዳት ለማስገኘት የሚያስችል የኢንሹራንስ ሽፋን ያለው መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ እንጂ በሕጉ ጥበቃ ከተደረገው የካሳ መጠን ያነሰ የሚያስገኝ የመድን ሽፋን ገብቶ በተገኘ ጊዜም ጭምር አይደለም።ድርጅቱ በሕጉ ከተመለከተው የካሳ መጠን ያነሰ የኢንሹራንስ ሽፋን ገብቶ ሲገኝ ለቀሪው የጉዳት ካሳ ኃላፊነቱን የማይወስድበት ምክንያት የለም።ግራ ቀኙ ለክርክራቸው መሰረት ያደረጉት የድርጅቱ የሕብረት ስምምነት አንቀጽ 25(2) ሲታይም በድርጅቱ ስራ ምክንያት አደጋ ለደረሰበት ሰራተኛ ድርጅቱ በገባው የኢንሹራንስ ፖላሲ መሰረት ያሳክማል፣ደመወዙንም ይከፍላል፣ሆኖም መስራት የማይችል ከሆነ ስራው ላይ ባለው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ስለዚህ ጉዳይ የተደነገጉትን እና በጡረታ አዋጅ መሰረት መብቱ ይጠበቅለታል በሚል የሚያስቀምጥ ከመሆኑ ውጪ በስራ ላይ ለደረሰ የአካል ጉዳት ካሳ የሚከፍልበትን ስልትና የአሰሪውን ከኃላፊነት ነጻ የሚሆንበትን አግባብ የማያስቀምጥ ሁኖ አግኝተናል።ከሁሉም በላይ የሕጉ የጉዳት ካሳና ኃላፊነት ድንጋጌዎች የዝቅተኛ የስራ ሁኔታዎች (minimum labour conditions) አካል ናቸው ተብሎ የሚታሰቡ በመሆኑና ሕጉም የሚያስቀምጠው ዝቅተኛውን ጥበቃ ሁኖ በሕጉ ከተቀመጠው ሁኔታ በላይ ግን በህብረት ስምምነት ወይም በውል ላወሰኑ የሚችሉ መብትና ጥቅሞች ላኖሩ እንደሚችሉ የሚታመኑ ሁኖ ሕጉ ካስቀመጠው ዝቅተኛው ሁኔታ በሕብረት ስምምነት መቀነስ የማይቻል መሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 134(1) በግልጽ የተቀመጠ ከመሆኑ ጋር ሁሉ ተዳምሮ ሲታይ ተጠሪ የሕብረት ስምምነቱን መሰረት አድርጎ የሚያቀርበው ክርክር ተቀባይነት የሚያገኝበትን ህጋዊ አግባብ አላገኘንም።
ከላይ ከተመለከቱት የሕግ ማእቀፎች አንፃር የአመልካችን ጥያቄ ስንመለከተው አመልካች 30% ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ተጠሪም ማስተባበያ ክርክር ያቀረበበት ጉዳይ አይደለም።እንዲህ ከሆነ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 109(3(ሀ)) በአመልካች ላይ ለደረሰው የአካል ጉዳት ላከፍል የሚገባው ካሳ የወር ደመወዛቸው × በአስራ ሁለት ወራት × አምስት አመታት × የመስራት ኃይል ቅነሳ ተባዝቶ የሚመጣው የገንዘብ መጠን ነው።በዚህ የሕጉ ስልት መሰረት ለአመልካች ላከፍል የሚገባው የአካል ጉዳት ካሳ መጠን፡ 3460.00×12×5×30%×=62,280.00 ሁኖ አግኝተናል።ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ተጠሪ ድርጅት በገባው የመድን ሽፋን መሰረት ብር 36,000.00 በመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 109(1) መሰረት ተጠሪ ለአመልካች ላከፍል የማይገደድበት ሁኖ ቀሪውን ብር 26,280.00 (ሃያ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሰማንያ ብር) ግን ከሕጉ ስልት ማስቀረት የሚችልበት ምክንያት ስላልተገኘ ለአመልካች ላከፍል የሚገባው ሁኖ አግኝተናል።
ሲጠቃለልም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካችን የቀሪ የአካል ጉዳት ካሳ ክፍያ ጥያቄን ውድቅ ያደረጉት ተጠሪ በሕጉ አግባብ ሙሉ በሙሉ የመድን ሽፋን የገባላቸው መሆኑን የመድን ድርጅቱም በስልት መሰረት የከፈላቸው መሆኑን ሳያረጋገጡ በመሆኑ በውሳኔው ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል።በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ውሣኔ
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ሐምል 24 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ታህሳስ 11 ቀን 2006 ዓ/ም በትእዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
በአመልካች ላይ ለደረሰው የአካል ጉዳት በሕጉ ስልት መሰረት የሚከፈላቸው የካሳ መጠን በኢንሹራንስ ሽፋን ሙሉ በሙሉ ያልተከፈላቸው በመሆኑ ቀሪውን ብር 26,280.00 (ሃያ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሰማንያ ብር) ለአመልካች ተጠሪ እንዲከፍል በማለት ወስነናል።
ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻቻሉ ብለናል።
No topics extracted.